Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Tuesday, 29 May 2012

ወ/ሮ አዜብ መስፍን መሬት መውሰዳቸውን ያጋለጠው ሠራተኛ ታሰረ


በቅርቡ በቡራዩ ከተማ በከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በተመራው ሙሰኞችን የማጋለጥ ስብሰባ ላይ “ወ/ሮ አዜብ መስፍን ያለ አግባብ በወንድማቸው ስም መሬት ወስደዋል” ብሎ ያጋለጠው የማዘጋጃ ቤቱ ሠራተኛ መታሰር በከተማው መነጋገሪያ መሆኑን በአካባቢው ያነጋገርናቸው የከተማው ነዋሪዎች ለሪፖርተራችን ገለፁ፡፡ ነዋሪዎች እንደሚሉት “መድረኩ የተዘጋጀው በቡራዩ አካባቢ የመሬት ቅርምት ተፈጽሟል፤ በመንግስትና በህዝብ መሬት ግለሰቦች አላግባብ በልጽገዋል፤ ከፍተኛ ሙስና ተፈጽሟል ተብሎ ነበር” ይላሉ፡፡ ሆኖም ግን ይላሉ ምንጮቻችን “የመድረክ አመራሩ ተሰብስበው በአካባቢው ኃላፊዎችና ከቁጥር በማይገቡ ሙሰኞች ላይ ብቻ ጣቱን እንዲቀስር እንዲያጋልጥ ግፊት ይደረግ ነበር፡፡ ይህንን የተገነዘበው አቶ ኃይሉ ንጉሴ የተባለው የማዘጋጃ ቤቱ የፋይናንስ ሠራተኛ ተነስቶ ትኩረቱን ለምን በትንንሾቹ ብቻ ታደርጋላችሁ፡፡ ሙስናን በቁርጠኝነት የምትታገሉ ከሆነ ወደ ላይም አትመለከቱም፡፡ በዚህ በከተማችን ወ/ሮ አዜብ መስፍን በወንድማቸው ስም መሬት ወስደዋል፡፡ ለምን አይጣራም? ለምን እሳቸውም አይጠየቁም” ብሎ ተናግሯል፡፡ በወቅቱ ስብሰባውን የሚመሩት ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ “ጥቆማው አንድና አንድ ነው፡፡ ጥቆማው በማስረጃ መረጋገጥ አለበት፡፡ ዝም ብሎ መጠቆም አይደለም፡፡” እያሉ ጥቆማውን ለማጣጣልና ለማንቋሸሽም ሞክረዋል፡፡ ይህ ሲገርመን በቅርቡ ጠቋሚውን በሙስና ትፈለጋለህ ተብሎ ታስሯል፡ ፡ መንግስት በተለይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሙስናን ለመዋጋት ያለውን ቁርጠኝነትና ጥያቄ ውስጥ የሚከት ከመሆኑም በላይ በመንግስት ላይ ያለን እምነት እየተሸረሸረ ነው፡፡” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ አቶ ኃይሉ ንጉሴ በገፈርሳ ቡራዩ ውስጥ ሊቀመንበር ሆኖ ያገለገለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በቡራዩ ማዘጋጃ ቤት የፋይናንስ ሠራተኛ ነበር ወ/ሮ አዜብ መስፍን በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ያለአግባብ ከፍተኛ ሀብት አፍርተዋል ተብሎ ከሚታሙት ግለሰቦች ውስጥ አንዷ መሆናቸው
ይታወቃል፡፡

ጥቅምት 23፣ መስከረም 2 እና ግንቦት 20


 
ኢትዮጵያ ሀገር ሆና ኖራለች፡፡ ለዚህ ምስክርነት የሚሰጡ ትርጉም ያላቸው ምሁራን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከውጭዎቹ ሄኔሪ ክሲንገር፣ ሳሙኤል ሀቲንግተን፣ ዶናልድ ሌቪን፣ ሀሮልድ ማልከስ፣ ጆን አቤኒክ፣ ዶናልድ ክሩ ሜይ፣ ሴፋሩድ ፓውስዋንግን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከሀገር ውስጦቹ ምሁራን ተክለፃድቅ መኩሪ፣ ታደሰ ታምራት፣ መርዕድ ወልደ አረጋይ፣ ባህሩ ዘውዴንና ሽፈራው በቀለን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህና ሌሎች ያልተዘረዘሩ ብዙ ምሁራን ኢትዮጵያውያን በመንግሥት ስር የመተዳደር
ልምዳቸው መንግሥት እንኳ ባይኖር ያለመታወክ የሚቆዩ ስርዓት ያዳበሩ ህዝቦች እንዳደረጋቸው ያወሳሉ፡፡ በተጨማሪም በነዚህ ሁሉ ሺህ ዓመታት ኢትዮጵያውያን እንደ ህዝብ ለቁጥር የሚያታክቱ መንግሥታትን እያሳለፉ ኖረዋል፡፡ በህዝብ አዕምሮም በታሪክ ማህደርም ቦታ የሌላቸው ብዙ መንግስታትና መሪዎችም በዚህ መሃል አልፈዋል፡፡ መንግሥታት እና መሪዎቻቸው እንደወራጅ ውሃ ሲያልፉ ‹የማያልፈው› ህዝብ ተመልክቷቸዋል፡፡ እነዚህ የሚያልፍ መሪዎች የሚያልፍ ሃሳቡን
ሲጭንባት ተመልክቷል፡፡ ባብዛኛውም መሪዎቹ እነዚህን ሃሳብ ህዝባዊ በማድረጉ አልተሳካላቸውም፡፡ እስቲ የቅርቦቹን ሁለት እና የአሁኑን መንግሥታት ሁኔታ እናንሳ፡- አፄ ኃይለ ሥላሴ “የተወለድኩበትን ሐምሌ 19 አክብሩ” አሉን፤ አከበርንላቸውም` ፡፡ “ዘውድ የጫንኩበትን ጥቅም 23ንም አክብሩ” አሉን፡፡ ደግመንም አከበረንላቸው፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ አለፉ፤ የሐምሌ 19 እና የጥቅም 23 `በዓላትም` አለፉ፤ ተረሱም፡፡ ደግሞ ደርግ መጣ፤ “የፊውዳሉንና የዘውዱን ስርዓት የገረሰስኩበትን መስከረም ሁለትን አክብሩ” አለን፤`አከበርንለትም`፡፡ ቆይቶ ደርግ አለፈ፤ መስከረም ሁለትም አብሮት አለፈ፤ ተረሳም፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ መጣ፤ “ደርግን የገረሰስኩበትን ግንቦት 20 አክብሩ” አለን፤ እነሆ ‹እያከበርንለት› ነው፡፡ ኢህአዴግ ለጊዜው እንደ አፄውና እንደ ደርግ ስርዓት አላለፈም፡፡ ስለዚህ ግንቦት 20ን “እያከበርን” ነው፡፡ ነገር ግን ፍኖተ ነፃነት ከዚህ አዙሪት የመውጫ ቀዳዳው መፈተሸ እንዳለበት ታምናለች፡፡ እስካሁን ያየናቸው በዓላት ለገዥዎች `አከበርንላቸው` እንጂ የኛ አድርገን በኔነት አላከበርንም፡፡ በመሆኑም ዋናው መፍትሄ ገንዘብ እየከፈሉ አሊያም እያስፈራሩ ካሜራ ፊት አቁሞ የማያምኑትን እንዲያወድሱ ከማድረግ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርዓት ገንብቶ መሪዎች ሲያልፉም ሲከበር የሚኖር በዓል መፍጠር ነው፡፡