Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Saturday 16 June 2012

ዓረና ፓርቲ የሑመራ ጽሕፈት ቤቱ መዘረፉን አስታወቀ

Sunday, 17 June 2012 00:00
በትግራይ ክልል ቃፍታ ሑመራ ወረዳ የተከፈተው የዓረና ትግራይ ሉዓላዊነት ለዲሞክራሲ ፓርቲ አዲስ ጽሕፈት ቤት መዘረፉን ፓርቲው አስታወቀ፡፡ በተጠቀሰው አካባቢ ልዩ ስሙ ማይካድራ በተባለው ሥፍራ የሚገኙ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በራስ ተነሳሽነት ከፈቱት የተባለው አዲሱ ጽሕፈት ቤት፣  የቢሮ መሣርያዎች ተሟልተውለት ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ሳለ መዘረፉን ነው ፓርቲው ያሳወቀው፡፡

በወረዳ  የዓረና ፓርቲ ኮሚቴ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ገብረ ዋህድ ሮምሐ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዛሬው ቀን የፓርቲው አመራር አባላትና ደጋፊዎች በተገኙበት ጽሕፈት ቤቱን በይፋ ሊከፈት በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ የአካባቢው ሹሞች ጽሕፈት ቤቱ በተዘረፈበት  ዋዜማ ሲያስፈራሩዋቸውና ሲዝቱባቸው መዋላቸውን አቶ ገብረ ዋህድ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ጽሕፈት ቤቱን ለፓርቲው ያከራዩ ግለሰብ ‹‹ቤትህን ለጠላቶች አከራይተሃል›› በሚል ኃላፊዎቹ ሲዝቱባቸው መሰንበታቸውን ገልጸው፣ ለፓርቲው ያከራዩትን ቤት መልሰው እንዲረከቡ የቀረበላቸውን ጥያቄ አለመቀበላቸውን  አክለው አስረድተዋል፡፡

ወንበርና ጠረጴዛን ጨምሮ በቢሮው ውስጥ የነበሩ የጽሕፈት መሣርያዎችና  የፓርቲው ሰነዶች መወሰዳቸውን ዓረና ፓርቲ አስታውቋል፡፡

በትግራይ ክልል ለመጀመርያ ጊዜ ከአራት ዓመት በፊት ተቃዋሚ ሆኖ ብቅ ያለውና  ከሕወሓት በአንጃነት በወጡ አመራሮች ዋና አስተባባሪነት የተመሠረተው ዓረና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ስብሰባ አባል ነው፡፡ ፓርቲው በመቐለ የሚገኘው ዋናው ጽሕፈት ቤቱን ጨምሮ በማይጨው፣ በአድዋና በአላማጣ ቢሮዎች መክፈቱ ሲታወስ፣ የአድዋው በምርጫ 2002 ተዘርፎ መዘጋቱንና፣ የአላማጣው ደግሞ ፓርቲው በራሱ ችግር መዝጋቱን ገልጿል፡፡

የሑመራ ጽሕፈት ቤቱን ዝርፊያ በተመለከተ የአስተዳደርና የፀጥታ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ ያልተሳካ ሲሆን፣ የወረዳው ፖሊስ ጉዳዩን በማጣራት ላይ መሆኑን ከምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡

No comments:

Post a Comment