Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Saturday 16 June 2012

ፍትሕና መልካም አስተዳደርን ያየህ ወዲህ በለኝ

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያችን የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ በየዕለቱ እያነጋገረንና እየጮኽንበት ያለው ዋናው ጉዳይ የኑሮ ውድነት ችግር ነው፡፡
ነገር ግን በፍትሕና በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት እየደረሰ ያለው ችግርም በእጅጉ ከፍተኛ ነው፡፡ መርሕና ሕጋዊ መብት መሆኑ ቀርቶና ተረስቶ ፍትሕና መልካም አስተዳደር ገጠመኝ ሆኗል፡፡ ‹‹ፍትሕና መልካም አስተዳደርን ያየህ ወዲህ በለኝ›› ያልነውም ለዚህ ነው፡፡

በቂ ማስረጃ ተይዞና በቂ ምስክር ቀርቦ በፍርድ ቤት ፍትሕ የማይገኝበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ለምን? በርካታ ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ ጥቂቶቹን ብቻ እንጠቃቅስ፡፡

የፍትሕ አካላት ራሳቸው ፍትሕ ያጡ ናቸው፡፡ በቴሌፎንና በአካል ያልሆነ ትዕዛዝና ጫና ይደርስባቸዋል፡፡ ነፃ ሆነው መሥራት የሚቸገሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ፍትሕ ያላገኘ ዳኛም ፍትሕ መስጠት አይችልም፡፡

ሙስና የፍትሕ ሥርዓቱን እያበላሸ ነው፤ እያጨማለቀ ነው፡፡ ጉዳዮች ችሎት ውስጥ ከመጠናቀቅ ይልቅ ከችሎት ውጭ የሚያልቁበት ሁኔታ የዘወትር ትዕይንት ሆኗል፡፡ አንቀጾችና ንዑስ አንቀጾች ይጠቀሱበታል የሚባለው የፍትሕ ሥርዓት፣ ቼክና ማቴሪያሎች አንቀጾቹንና ንዑስ አንቀጾቹን የሚገዙበት የፍትሕ ሥርዓት ሆኗል፡፡ ገንዘብ በሕገ መንግሥት ላይ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ላይ፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ላይ፣ በሰነዶች ላይና በምስክሮች ላይ የበላይነት የያዘበት የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ  ነን፡፡

አቅም ማነስ የፍትሕ ሥርዓቱን እያዳከመው ነው፡፡ የልምድና የብቃት ማነስ በዳኞችም፣ በአቃቢያነ ሕግም፣ በፖሊሶችም በጠበቆችም ጭምር እየታየ ነው፡፡ የሚታየውንና የሚሰማውን ማመን የሚያቅትበት ሁኔታ አለ፡፡ የሥነ ምግባር ችግር በሌለበት የሚታይ የአቅም ችግር አሳሳቢ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እየታየ ያለው ሁኔታ በእጅጉ ችግር እያስከተለ ነው፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ ሊሸከም ከሚችለው በላይ ጉዳዮች ወደ ፍትሕ ሥርዓቱ ይጎርፋሉ፡፡ ጉዳዩ ብዙ ዳኛው ጥቂት ይሆናል፡፡ መቼ ተጀምሮ መቼ ያልቃል ሲባል አይታወቅም፡፡ ፍትሕ ለማግኘት ተሂዶ ለዓመታት መንገላታትና ምነው ባልከሰስኩ፣ ምነው በእርቅ በጨረስኩ የሚያሰኝ ሁኔታ እየተስተዋለ ነው፡፡

የችሎት መቀያየር፣ የዳኛ መቀያየርና የዓቃቤ ሕግ መቀያየር ራሱ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ጉዳዩን ያወቀውና የለመደው እየሄደ አዲስ ለመጣው ጉዳዩን ለማሳወቅና ለማለማመድ የሚጠፋው ጊዜም ብዙ ነው፡፡ አካሄዱና መንፈሱ ተለውጦ እንዴት ነው ነገሩም የሚያሰኝ ነው፡፡

እንደዚህ ዓይነት ችግር ከታችኛው ፍርድ ቤት እስከ ላይኛውና የመጨረሻው ፍርድ ቤት ሲታይና የተለመደ ሲሆን እንዴት ነው ነገሩ? መንግሥት ለምን አያስተካክለውም? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፤ ይጎርፋል፡፡ መልስ የለም፡፡

እየታየ ያለው ችግር ግን በፍርድ ቤቶች ብቻ አይደለም፡፡ በሁሉም የመንግሥት መሥርያ ቤቶችም ከፍተኛ ችግሮች ይታያሉ፡፡ በወረዳና በክፍላተ ከተሞች ችግሮች አሉ፡፡ በዋናዎቹ ማዘጋጃ ቤቶችም ችግር አለ፡፡ በሚኒስቴር መሥርያ ቤቶችም ችግር አለ፡፡ ኤጀንሲ ይባሉ ኮሚሽን፣ ባለሥልጣንም ይባሉ እንደዚሁ፡፡ በተቀመጠላቸው ኃላፊነትና ግዴታ ሕዝብን እያገለገሉ አይደሉም፡፡

የመንግሥት መሥርያ ቤቶችም ጉቦ እያጨማለቃቸው ነው፡፡ ገንዘብ የበላይነት እየያዘ ነው፡፡ ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› የሚባሉ የሚያሽከረክሩዋቸው እየሆኑ ናቸው፡፡

ለስንትና ስንት ዓመታት አቤት የሚል አድማጭ አጥቶ ተመሳሳይ፣ ያነሰና ሕጋዊ ያልሆነ ጉዳይ የያዙ በደቂቃዎች የፈለጉትን ሲፈጸምላቸው ግልጽና ግልጽ በሆነ ማስረጃ የሚታይ ነው፡፡ ሕዝብን ለማገልገል የተቀመጡ ሹመኞችና ሠራተኞች ሕዝብን ረስተውና ክደው የግለሰቦች ተላላኪና አስፈጻሚ ሲሆኑ እየተስተዋሉ ናቸው፡፡

የብቃት ማነስም በመንግሥት መሥርያ ቤቶች በእጅጉ እየታየ ነው፡፡ በጉቦ ሳይገዙ ንፁህ ሆነው መሥራት እየፈለጉ አቅም አጥተው የሚያጠፉና የሚያበላሹ በርካቶች ናቸው፡፡ መንግሥት ምን አይቶ በምን መዝኖ እዚያ ቦታ ላይ እንዳስቀመጣቸው ግራ የሚያጋባና የሚያሳዝን ነው፡፡ ሕዝብን የሚጎዱትን ያህል ደግሞ መንግሥትን ይጎዳሉ፡፡ አባልነትና ደጋፊነት መመዘኛ ከሆነም የተሻለ አባልና ደጋፊ አጥተው ነው ወይ? ያሰኛል፡፡

ፋይል ጠፋ፣ ጉዳዩ ገና አልታየም የሚል መልስ በብዛት ይሰጣል፡፡ ለወራት ከተቀመጠ በኋላ ሌላ መሥርያ ቤት ሂዱ የሚባሉ ቅሬታ አቅራቢዎች በርካታ ናቸው፡፡ ‹‹ቅሬታ ሰሚ›› አካል በዋነኛነት ‹‹ቅሬታ የሚቀርብበት›› አካል እየሆነ ነው፡፡

በራችን ክፍት ነው የሚለው ሁሉ በሩ ዝግ ነው፡፡ በሩ ክፍት ከሆነም ሹመኛው ቢሮ አይገባም፡፡ ከሚወስኑ አካላት ጋር ለመገናኘትና ለመወያየት ተስፋ ተደርጎ በመጨረሻው የተለመደው ከጸሐፊዎች ጋር ጭቅጭቅ ነው፡፡

ራዕይና ዓላማ ቀልድ ሆነዋል፡፡ ሐሳብ መስጫ ሳጥን ፌዝ ነው፡፡ አቀራረቡ ራሱ ሲታይ ዜጎች አቤት ለማለት መብታቸው መሆኑንና ኃላፊዎች የሕዝብን ቅሬታ ማስተናገድ ግዴታቸው እንደሆነ ተዘንግቷል፡፡ ዜጎች ይሸማቀቃሉ፡፡ ሹመኞች ይቀልዳሉ፡፡

ሕዝብ፣ ባለጉዳይ፣ ዜጋ ጉዳዩን ለማስፈጸም ወደ መንግሥት መሥርያ ቤት ለመሄድ እየተሸማቀቀ ነው፡፡ የሚሰማኝ አገኛለሁ ብሎ አያምንም፡፡ ጉዳዬ ይገባቸዋል ብሎ አይተማመንም፡፡ ፍትሐዊ ውሳኔ አገኛለሁ የሚል አስተሳሰቡ ጨለምተኛ ነው፡፡ ካለ ጉቦ ያልቅልኛል የሚል ተስፋው የመነመነ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ተጠቃሎ ሲታይ መንግሥትን ሊያደናግጠውና ሊያሳስበው ይገባል፡፡ በቃል፣ በራዕይ፣ በፖስተር፣ በቢልቦርድ ስለፍትሕና መልካም አስተዳደር ብዙ ቢነገርና ቢለፈፍም በተግባር ግን አይታይም፡፡

እንዲያውም እንዲያውም አሁን አስደንጋጭ እየሆነ ያለው የመንግሥት አካላት ሥራቸውን በሚገባ አለመሥራታቸውና ሕዝብን አለማገልገላቸው ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥት አካላትን የሚያንቀሳቅሱና የሚያሽከረክሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ የግል ማፍያዎች መኖራቸው ነው፡፡

ሕዝብን ለማገልገል ቀና ደፋ የማይሉ ለሠርግና ለድግስ ግን ጎንበስ ቀና ሲሉ የሚታዩ በርክተዋል፡፡ ልማትን የሚያደናቅፉ ሲያዩ አፋቸው መከፈት የሚያቅተው ሹመኞች ሀቀኞችን ለማደናቀፍ ግን ሲጮሁና ሲያወግዙ ይሰማሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ከመንግሥት ውጭ ሌላ መንግሥት አለ ወይ የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡ ከስጋት ጋር፡፡

አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነን፡፡ የግል ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት ሌቦችም አሉ ሲባል እንጂ፣ በመንግሥት ሌቦች ላይ ግምገማ ሲካሄድና ዕርምጃም ሲወሰድ ግን አይታይም፡፡ ይህም ለምን የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡

ሕዝብ እየጠበቀ ያለው ተግባር ነው፡፡ መግለጫ በቃ፣ ዕቅድ በቃ፣ ቃለ መጠይቅ በቃ፡፡ የናፈቀን ተግባር ነው፡፡ ፍትሕና መልካም አስተዳደርን እውን የሚያደርግ ተግባር፡፡

ገጠመኝ ሳይሆን መርህ! መፈክር ሳይሆን ተግባር! ነገ ሳይሆን ዛሬ! ኢትዮጵያ በፍትሕና በመልካም አስተዳደር ‹‹ድርቅ›› እየተጠቃች ናትና፡፡

No comments:

Post a Comment