Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Monday 9 April 2012

ሽራፊ ጨዋታ


ሽራፊ  ጨዋታ

ከፍትህ ጋዜጣ
ተመልካቾቻችን ይህ ጨዋታ የሚተላለፍላችሁ አዲስ አበባ ስታዲየም ከሚገኘው ጊዜያዊ እስቱዲዮአችን ነው፡፡ ለአለፉት ዘመናት፣ እንዲሁም ለመጪው ዘመን ብቸኛ የዜና ምንጫችሁ ሆኖ አብሮአችሁ ከሚቆየው ኢቲቪ እንደሰማችሁት ጨዋታው በእጅጉ በበርካታ ተመልካቾች በጉጉት የተጠበቀ ነው፡፡ ሙሉ ጨዋታውን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በቀጥታ እናስተላልፋለን፡፡ መቼም ኢቲቪ በአለማችን ገዥው ፓርቲ ላይ ‹‹ክፉ የማይወጣው ታታሪ ቴሌቪዥን›› የሚል ሽልማት አሸናፊ እንደሆነ ሁላችሁም የምታውቁት ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይህ ጨዋታ ሊደረግ የነበረው በተወዳጆቹ ባለስልጣኖቻችን እና በዲፕሎማቶች መካከል እንደነበር ማንሳቱ ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ዲፕሎማቶቹ በሻዕቢያ እና በተላላኪዎቹ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሴራ ከጨዋታው ራሳቸውን አግለዋል፡፡ በእውነቱ ይህ የሚያናድድ ነገር ነው፤ የሚያናድደው ግን የገቡትን ቃል አለማክበራቸው እንጂ እኛ አውራ ፓርቲ እንደሆንን ማንም ያውቃል፡፡ እናም እራሳቸውን እንኳን ከጨዋታ ከምርጫም ቢያገሉ መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው፡፡ ከፈለጉምተቃዋሚዎችም አብረዋቸው በሊማሊሞ ያቋርጡ፡፡
አራት ነጥብ ተመልካቾቻችን ከጊዜያዊ እስቱዲዮአችን የምናስተላልፈውን ዘገባ አቋርጠን በእርግማን ላይ እንድንጠመድያደረጉንን አንዳንድ ተቃዋሚዎችን እና የሻዕቢያ ተላላኪዎችን የሚያወግዝ ሰልፍ ጠርተን፣ በዚህ አጋጣሚ ህዝባችን በልማት ጎዳና እየተራመደ እንደሆነ ለመላው አለም በመፈክር ብዛት ስለምናረጋግጥ በተስፋ ጠብቁን፡፡
አሁን ወደ ጨዋታው እንመለሳለን……ባልደረባዬ እንደገለፀላችሁ ዲፕሎማቶቹ በልማታችን ቀንተው፣ አይናቸው ደም ለብሶ ከጨዋታው እራሳቸውን ቢያገሉም፣ ልማታዊ አርቲስቶቻችን ተክተዋቸዋል፡፡ ሪሊ፣ ሪሊ ይኼ በጣም ሀገር ወዳድነት ነው፡፡ ምንአልባትም በቀጣዩ አመት በሚደረገው የአዲስ አበባ ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው እንወዳደርም ቢሉ እንኳ አርቲስቶቻችን ተክተዋቸው እንደሚወዳደሩ የዛሬው ተነሳሽነታቸው ያረጋግጥልናል፡፡ኦያያያሪሊ፣ ሪሊ እስከዛሬ ድረስ ፓርቲዎቹን እሹሩሩ ስንልየከረምነው ሪሊ ለካስ ስህተት ነበር፡፡ ተመልካቾቻችን በአሁኑ ሰዓት የባለስልጣናት ቡድን ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ በዚህ ጨዋታ የክብር እንግዶቹ ለተጫዋቾቹ የትግል አጋር የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩእና የአዲስ አበባ ከንቲባው ናቸው፡፡ ሪሊ፣ ሪሊ ይህ በሀገራችን የመጀመሪያው ነው፡፡ ከፍተኛ ባለስልጣን የክብር እንግዳ  ሲሆን፣ ሪሊ፣ ሪሊ በእስታዲዮም የተገኙ ተመልካቾችም በፉጨት ድጋፋቸውን እየሰጡ ነው፡፡ ኦያያያ ህዳሴ ማለት ይህ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔን ‹‹ሌባ፣ ሌባ…›› ሲሉ የተሳደቡ ተመልካቾች በተገኙበት እስታዲዮም ዛሬ ያውም ብዙ ታምራት ላይኔዎችን ‹‹ሌላ፣ ሌላ…›› እያለ የሚያበረታታ ደጋፊ መገኘቱ በራሱ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጫ ነው፡፡ ሪሊ፣ ሪሊ. ኢንስፔክተርም ከአጠገቤ አሉ፤ በእርግጥ እንደኢንስትራክተር አንድ ኢንስፔክተር ብቻ አይደለም የጋበዝኩት፣ በአጠገቤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢንስፔክተሮች ይገኛሉ፡፡ እንደሚታወቀው ከአፍሪካ በኢንስፔክተር ብዛትም የመጀመሪያው ነን ተመልካቾቻችን አሁን የባለስልጣናት ቡድን ተሰላፊዎችን አስተዋውቃለሁ፡፡ በግብ ጠባቂነት የተሰለፉት የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነሩ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ተጫዋጮች ለግዜው አይታዩኝም፤ ኦያያያሪሊ፣ ሪሊ የተከበሩ አፈ ጉባኤ ለቡድኑ በተከላካይ መስመር የሚጫወቱ መሆኑን አሁን ገና ነው ያወኩት፡ ሪሊ፣ ሪሊ አፈ ጉባኤው ከዚህ ቀድም መከላከያ ሚኒስትር እንደነበሩ ይታወቃል፤ በዚህ ጨዋታ ተከላካይ መሆናቸው ካላቸው ልምድ አኳያ ተገቢ ነው፡፡ ኦያያያ በፊት አጥቂነት የፍትህ ሚኒስትሩ ይገኛሉ፡፡ በጣም ጥሩ አሰላለፍ ነው፡፡ (በተለይ መንግስታችንን በፍትህ በኩል ነው ጥቃት የሚፈፅምብን ለሚሉ አሉባልተኞች በዚህ አጋጣሚ ቢሆንስ! ምን ይጠበስ? ለማለት እፈልጋለሁ) ኦያያያ የባለስልጣናት ቡድን የያዘው ታክቲክ የሚገርም ነው፡፡
ኢንስፔክተር ምን አስተያየት አሎት? በታክቲኩ ላይ ማለቴ ነው፤ ኦያያያ ልክ ኖት ኢንስፔክተር እንዲህ አይነት እቅድ ያወጡ ሰዎች ግድብ ለመገደብ ማቀድ አይሳናቸውም ነው ያሉኝበእውነቱ ልክ ኖት፡፡ አሁን ጨዋታው ተጀምሯል፡፡ (ተመልካቾቻችን የአርቲስቶቹ ቡድን ‹‹የተጋጣሚያችን ቡድን አባላት የታገሉ ስለሆነ ስማችን ከእነሱ እኩል መጠራት የለበትም፡፡ እኛ ገና መች ታገልን፡፡ ፓርቲውንም በቅርቡ ነው የተቀላቀልነው›› ስላሉ አሰላለፋቸውን አንገልፅም፡፡ ሪሊ፣ ሪሊ፣ ይሄ በጣም ጥሩ አስተያየት ነው፡ እንዲህ ለፍተው የታገሉ ሰዎችን ሃያ አመት ‹‹በቃ›› ማለት የሻዕብያ ተላላኪ መሆን ማለት ነው፡፡ ሪሊ፣ ሪሊ ዛሬ አርቲስቶቹ አርዓያ ሆነዋል፡፡) ..የአርቲስቶች ቡድን ኳስ ይዟል፣ ኳስ ይዟል...ኦያያያ... ሆኖም የባለስልጣናት ቡድን ለመጠባባቂ የያዘውን ኳስ ከአሰልጣኙ ተቀብሎ መጫወት ጀምሮአል፡፡ አዎ አሁን ኳሷ ለባለስልጣን ቡድን ግብ ጠባቂ ደርሳለች፤ ግብ ጠባቂው ኳሷን ይዘው ለማን መስጠት እንዳለባቸው መመሪያ ይተላለፍላቸው ዘንድ በመገናኛ ሬዲዮ እየጠየቁ ነው፡፡ አዎ! አሁን መመሪያው የደረሳቸው መሰለኝ፡፡ ኳሷን በአክብሮት ለአፈ ጉባኤው አቀብለዋል፤ አፈ ጉባኤው ኳሷን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው እየገፉ ነው፣ እየገፉ ነው፣ አዎ! አሁንም እየገፉ ነው፤ እሳቸውም ለማን ማቀበል እንዳለባቸው ከጠቅላይ ሚንስትሩ በሬዲዮናቸው እየተነጋገሩ ነው፡፡ አዎ! ጠቅላይ ሚንስትሩ እየተቆጡ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment