Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday 8 April 2012

የእኛስ ጠቅላይ ሚንስትር ማን ነው?


የእኛስ ጠቅላይ ሚንስትር ማን ነው?
ተመስገን ደሳለኝ፣ ከፍትህ ጋዜጣ
የጦር ሃይሎች አዛዥ የኢህአዴግ ሊቀመንበር፣ የህወሓት ዋና ፀሀፊ፤ የአፍሪካ የአየር ንብረት ተደራዳሪ፣ አባይን የደፈሩ፣ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሚሉ በርካታ የሹመት ተቀጥላዎች በኋላ የምናገኛቸው መለስ ዜናዊ ሰሞኑን የአባይ ግድብ የታቀደበትን (የተሰራበትን አይደለም) አንደኛ አመት አስመልክቶ ከሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ካሉ ኢትዮጵያውያኖች ‹‹የተሰበሰበ›› ተብሎ የተለያዩ ጥያቄዎችን (በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አቅራቢነት) ሲመልሱ ተመልክተናል፡፡ ምንም እንኳ አንድ ፕሮጀክት የተጠናቀቀበት እንጂ ‹‹እቅድ የታቀደበት ቀን›› በሚል አመታዊ ክብረ በዓል ሲከበር የህዳሴው ግድብ በአለማችን የመጀመሪያው ቢሆንም፤ ለጥያቄዎቹ መልስ መስጠታቸውም ሆነ ጥያቄዎቹ መቅረባቸው በራሱ ክፋት አለው ብዬ አላስብም፡፡ ክፋቱ ለጠቅላይ ሚንስትሩ መቅረብ የሚገባቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች አለመቅረባቸው ላይ ነው፡፡ እናም መለስ መጠየቅ እና መመለስ የነበረባቸውን ወሳኝ እና ህዝባዊ ጥያቄዎችን (ምንም እንኳ ኢቲቪ አይቶ እንዳላየ ቢያልፋቸውም) እኔ ለማቅረብ መገደዴን በትህትና እገልፃለሁ፡፡ መጀመሪያ ግን ጥቂት ስለኢህአዴግ ‹‹መደበሪያዎች›› ወይም ‹‹ቅምጦች›› ጨርፈን እንመልከት፡፡
የኢህአዴግ ‹‹ቅምጦች››
‹‹የህዳሴው ግድብ መሰረት የተጣለበት አንደኛ አመት›› በሚል በዓል ከማክበር ጋ ፍቅር የወደቀው ኢህአዴግ ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በዓሉን እያከበረ ነው፡ ፡ ለ‹‹በዓሉ ድምቀት››ተብሎ ነገር ግን ከግድቡ ጋር ተያያዥነት የሌላቸው (ኧረ እንዲያውም ጭራሽ የማይገናኙ) የተለያዩ ፕሮግራሞች ተዘጋጅተው አይተን እንደዋዛ ታዝበን አልፈናል፡ ፡ በእርግጥ እንደዋዛ የማናልፈው ዝግጅትንም ተመልክተናል፡፡ ለምሳሌ በዓሉን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ‹‹ከህዝብ ተሰበሰበ›› የተባሉ የተለያዩ (በይዘት ሳይሆን በአቅራቢዎቹ) ጥያቄዎች ቀርቦላቸው ሲመልሱ ያየንበትን ፕሮግራም አይቶ ማለፉ ተገቢ አይመስለኝም፡፡
የሆነ ሆኖ በዚህች አንቀጽ ጨርፈን የምናየው በአምባገነኖቹ ባለስልጣናት እና በካድሬ አርቲስቶቻችን መካከል የተደረገውን የእግር ኳስ ውድድር ነው፡፡ ስለዚህ ውድድር መጀመሪያ ላይ የሰማነው ከአርቲስቶቹ ጋር ሳይሆን ከዲፕሎማቶች ጋር እንደሚካሄድ ነበር፡ ፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ መንግስት (በኢህአዴግ) ባለስልጣናት እና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ባደረጉ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች መካከል ይደረጋል ተብሎ በመንግስት ሚዲያ ስንሰማው የነበረው ይህ የእግር ኳስ ግጥሚያ አልተደረገም፡ ፡ ለምን እንዳልተደረገም ምክንያታዊ ግምቴን አቀርባለሁ፡፡
በቅድሚያ ከመንግስት ‹‹ሰበብ›› እንነሳ፡፡ አዎ! መንግስት ‹‹ዲፕሎማቶቹ መጫወት ያልፈለጉት ስላልተሟሉ ነው›› ብሎናል፡፡ (ለነገሩ ከዚህ ውጭ ምንም ሊል አይችልም ነበር) ሆኖም ይህ ምክንያት ተቀባይ አላገኘም፡፡ ምክንያቱም ለውድድሩ የሚያስፈልገው አስራአንድ ተጨዋች ብቻ መሆኑን አስበን፣ ይህንን ማስተባበያ ከተቀበልን በአዲስ አበባ ያሉ ዲፕሎማቶች ከአስራ አንድ ሰው በታች ናቸው ወደሚል ድምዳሜ እንድንደርስ እንገደዳለንና፡፡ እዚህ ድምዳሜ ላይ ደግሞ ልንደርስ አንችልም፡፡ ለምን? የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ካለ፣ መልሱ ቀላልና አጭር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዲፕሎማቶች በሺህ ቤት የሚቆጠሩ መሆናቸውን ከእኛ ይልቅ ፍቃድ ሰጥቶ ያስገባቸው መንግስት ያውቃል የሚል ማለቴ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በታላቁ ሩጫ እንኳ ምን ያህል ዲፕሎማቶች እንደሚሳተፉ ለአመታት ያየነው ነው፡፡ በአናቱም አዲስ አባባ ከኒዎርክ እና ከቤልጄየም ቀጥላ በአለማችን በርካታ ዲፕሎማቶች የሚገኙባት ከተማ መሆኗን አለም ያውቃል፡፡ እናም ከዚህ አንፃር ስንነሳ ነው እሁድ እለት ሊደርግ በነበረው የባለስልጣናት እና የዲፕሎማቶች ጨዋታ፣ ዲፕሎማቶቹ ሊሟሉ ስላልቻሉ ጨዋታው ከምንጊዜም የገዥው ፓርቲ ‹‹ቅምጥ›› አርቲስቶች ጋር ሆነ የምትለውን እርባና ቢስ ማስተባበያን መቀበል የሚያዳግተን፡፡
ተቀበልነውም አልተቀበልነውም ዲፕሎማቶቹ ከኢህአዴግ ባለስልጣናት ጋር የነበራቸውን የእግር ኳስ ጨዋታ የሰረዙበት ምክንያት ‹‹ጨዋታው የፖለቲካ መጠቀሚያ ነው›› ብለው እንደሆነ ከዲፕሎማቶቹ አካባቢ ሰምተናል፡፡ ነገር ግን ዲፕሎማቶቹም ቢሆኑ በደፈናው ‹‹የፖለቲካ መጠቀሚያ አንሆንም›› አሉ እንጂ፣ ‹‹መጠቀሚያ ሊሆኑ የነበረው›› ለሀገር ውስጥ ይሁን ለውጭ ፖለቲካ ያብራሩት ነገር የለም፡፡ ስለዚህም የሚኖረን መረጃ ሳይሆን፣ መላ-ምት (ምክንያታዊ) ትንተና ይሆናል ማለት ነው፡፡
የመጀመሪያው መላ-ምታችን የሚሆነውም ጨዋታው የተዘጋጀው የህዳሴውን ግድብ አንደኛ አመትን አስመልክቶ መሆኑ እና ግድቡ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ‹‹የኢህአዴግ ማስቀየሻ›› ስልት ተደርጎ መወሰዱን ዲፕሎማቶቹ በበቂ ሁኔታ ስለሚያውቁ የኢህአዴግ ተባባሪ ላለመሆን ነው ከውድድሩ ራሳቸውን ያገለሉት ልንል እንችላለን፡፡ ሁለተኛው መላምት ደግሞ ዲፕሎማቶቹ ‹‹የአባይ ግድብን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ኳስ መጫወቱ፣ ግብፅን ጨምሮ ከአባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር ውዝግብ ውስጥ ይከተናል›› በሚል ይመስለኛል-የሰረዙት፡፡ እንዳልኩት ይህ መላምት ነው፡፡ መረጃ አይደለም፡፡ መረጃው ‹‹ለፖለቲካ መጠቀሚያ አንሆንም›› በሚል ምክንያት ዲፕሎማቶቹ ከጨዋታው እራሳቸውን ማግለላቸው ብቻ ነው፡፡
በእርግጥ ዲፕሎማቶቹ አንጫወትም ቢሉም በሰዓታት ውስጥ አርቲስቶቻችን ለጨዋታው ዝግጁ ሆነው ቀርበዋል፡፡ እስከ ቅዳሜ ግማሽ ቀን (ለጨዋታው አንድ ቀን እስኪቀረው) ድረስ የዲፕሎማቶቹ አለመጫወት አልታወቀም ነበር፡፡ ሆኖም ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ አለመጫወታቸው ሲታወቅ፣ መንግስታችን አርቲስቶቹን (በቅዳሜ ከሰዓት ሊገኙ ከሚችሉባቸው ቦታዎች) አሰባስቦ ዲፕሎማቶቹን ተክተው እንዲጫወቱ ቀጭን ትእዛዝ ሰጣቸው፡ ፡ እነሱም ወደ አስር ሰዓት አካባቢ ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆኑ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ፡፡ በዚህ መልኩም ነው የባለስልጣናትና የአርቲስቶችን ጨዋታ ልናይ የቻልነው፡፡
መቼም የሀገሬ አርቲስቶች ‹‹መፍሰሻ ቦይ›› ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ለእነሱ አዛዡ ኢህአዴግ ይሁን እንጂ፣ ትእዛዙ እውነትም ይሁን ውሸት ግድ አይሰጣቸውም፡ ፡ ስለትራንስፎርሜሽን እንዲያ የባጥ የቆጡን እየለፈልፉ ሲመናቸኩ ቢከርሙም እስከአሁን ድረስ ጠብ ያለ ነገር አላየንም፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹አባይ ተገደበ›› እያሉን ነው፤ እራሱ የፕሮፓጋናዳው ኦፕሬተር ኢህአዴግ እንኳ ‹‹አባይን ልገድብ ነው›› አለ እንጂ ተገደበ አላለም፡፡ እንዲህ ነው ከመምህሩ ደቀ- መዝሙሩ…
የሆነ ሆኖ ‹‹አባይ፣ አባይ…›› ማለት ክፋት የለውም፡፡ የአባይ መገደብም ሀገሪቱ ተጠቃሚ ልትሆን የምትችልባቸውን እድሎች ሊፈጥር እንደሚችል ማንም አይክድም፡፡ (በእድሉ መጠቀም ከተቻለ ማለት ነው) ነገር ግን አባይ በመገደቡ ብቻ ‹‹አለፈላችሁ›› ተራ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ በግድቡ የሚጠራቀመው ውሃ እንጂ ዳቦ እንዳልሆነ የማያወቅ የለምና፡ ፡ ስለዚህም ግድቡ ቢገደብም እንኳ በቀጣይ ተጠቃሚ ለመሆን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እና መልካም አስተዳደርን የግድ ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ አብዛኛዎቹ አረብ ሀገራት እስከ ልጅ ልጆቻቸው ድረስ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ነዳጅ አላቸው፣ ያውም የግድብን ያህል ልፋት የማይጠይቅ፤ ነገር ግን ገዥዎቻቸው አምባገነን ስለሆኑ ከነዳጁ ሽያጭ በሚገኘው ገቢ እንዳሻቸው የሚሆኑት የሀገሪቱ ዜጎች ሳይሆኑ አምባገነን አስተዳዳሪዎቹ እና ቤተሰቦቻቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ኢህአዴግ በዘፈነ ቁጥር ‹‹እስክስታ›› የሚወርዱ ወንድምና እህቶቻችን የማይመቹኝ፡፡ ወይም ስተው የሚያስቱ መስለው የሚታዩኝ፡፡
ሌላው ግልፅ መሆን ያለበት ኢህአዴግን ከሃያ አመት በላይ ዛሬ በተቀመጠበት ወንበር ላይ ተቀምጦ እናውቀዋለን፡፡ እናም ቃል የሚገባው እና የሚተገብረው የሰማይና የምድርን ያህል እርቀት እንዳላቸው ያለፉት ተሞክሮዎች ያሳብቃሉ፡፡ ከዚህ ቀደምም ወደብን ያህል ነገር ‹‹አያስፈልገንም፣ ግመላቸውን ውሃ ያጠጡበት፤ እኛ በምርጥ እቅዶቻችን ያለወደብ በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ እንሰለፋለን›› ሲል የገባውን ቃል እንደአስረጅ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ግድብ ልሰራ ነው›› ስለተባለ ብቻ ይህ ሁሉ ጫጫታ አስፈላጊ አይመስለኝም የምለው፡፡ በተቀረ ገና ምኑም ሳይያዝ ‹‹የግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት አንደኛ አመት›› በሚል ‹‹ያዙኝ ለቀቁኝ›› ማለቱ ሌላው ቀርቶ በወዳጅ ዘመድ ዘንድ እንኳ ግምት ውስጥ ያስጥላል፡ ፡ …መቼም ኢህአዴግ በዚህ አያያዙ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ሁለተኛ፣ ሶስተኛ፣ ሀምሳኛ፣ ስልሳኛ በዓል…እያለ አለመቀጠሉንም እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
አምርረን እንነጋገር ከተባለም ኳስ መራገጡ ለግድቡ ሲሚንቶ ወይም አሸዋ አይሆንም፡፡ አንዳንድ የዋህ አርቲስቶች በግድቡ ስም ኳስ መጫወትን ‹‹የሀገር ጉዳይ ነው›› ሲሉ እሰማለሁ፤ ይህ ግን ከየዋህነት የመነጨ ነው፤ ኢህአዴግ ገና ምኑም ባልተያዘ ዕቅድ ቀርቶ፣ በባድሜ እና ሽራሮ ጉዳይ እንኳ እልፍ አላፍት ወጣቶች ካለቁ በኋላ፣ ያውም በአደባባይ ካስጨፈረን በኋላ ‹‹Give and Take›› ሲል የተሳለቀ ደፋር ድርጅት ነውና፡፡ እናም የግድብ ፖለቲካውን ከሀገር እና ከባንዲራ ጋር አታገናኙት፡፡ ካምቦሎጆ እነ አባዱላ ገመዳ ኳስ መጫወታቸው ለጤናቸው ጠቃሚ ሊሆን ይችል ይሆናል እንጂ ግድብ አይሰራም፤ ቦንድም አይገዛም፤ ባይሆን ለኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ ቀልብ ይገዛ ይሆናል፡፡ …አርቲስቶቻችን ሆይ ከዚህ አንፃር ነው ከጫጫታው ትርቁ ዘንድ ወይም ፍሬውን ከገለባው ትለዩ ዘንድ የምመክራችሁ፡፡ በእርግጥ ለሀገር እድገት ማሰቡ ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ የማይሆነው ‹‹ግድብ እሰራለሁ›› የሚል ዕቅድ በማቀድ ብቻ የትኛውም ሀገር አድጎ አለመገኘቱን አለመስተዋሉ ላይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ግድቡ ተሰራም አልተሰራም፣ ከሁሉም ነገሮች በፊት መሰረታዊ መብቶች ሊከበሩ እንደሚገባ ልብ-ልትሉ ይገባል፡ ፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ፣ የፍትህ ስርዓቱ ልብ-ወለድ ቀመስ መሆኑ፣ የፖለቲካ ምህዳር መጥበቡ፣ ድሆች መፈናቀላቸው፣ የ‹‹መንግስት ሌቦች›› መብዛታቸው… ሊያሳስባችሁ እና ልትታገሉለት ይገባል፡፡ ለዚህም ነው በደፈናው ህዝብና መንግስት ተጣመሩ፣ ተጋቡ፣ ሶስት ለሶስት ወጡ… ከምትሉት ትርኪምርኪ ራቁ እያልኩ ያለሁት፡፡ …እንዳልኳችሁ ዛሬ ሀገር እና ህዝብ ሀዘን ላይ ነው፡፡ እናም ህሊና ካላችሁ ሀዘኑን ተጋሩት፤‹‹የለም! አያገባንም›› ካላችሁም እንዳሻችሁ፣ ነገር ግን የማስታወቂያ ገቢ፣ መሬት፣ ኮንድምንየም ቤት፣ ጂኒ ቁልቋል… ጥቅማ ጥቅሞችን እያሰባችሁ አታምታቱት፡፡ (አሁን ወደ ዋናው እርሰ ጉያችን እንመለስ)
የእኛ ድምጽ
የህዳሴው ግድብ መሰረት የተጣለበትን አንደኛ አመት ምክንያት በማድርግ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከመላው አለም ሰበሰብኩ ያለውን ጥያቄ በ22 እና 23/2004 ዓ.ም. በተላለፈ የምሽት ስርጭቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አቅርቦላቸው ሲመልሱ ሰምተናል፡፡ ሁሉም ጥያቄ ከአባይ መገደብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እንደተለመደውም ሁሉም መልስ ፕሮፓጋንዳ ተኮር ነው፡፡ በእርግጥ በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ቅሬታ የለኝም፡፡ ቅሬታዬ ለመለስ ዜናዊ የሚቀርቡት ጥያቄዎች እነዚህ ብቻ ናቸውን? የሚለው ላይ ነው፡፡ እናም ኢቲቪ ያላቀረበውን ጥያቄ እኔ ለማቅረብ ወደድኩ፤ ፈቅደንም ይሁን ሳንፈቅድ ለእኛ ለጭቁኖችም ቢሆን ጠቅላይ ሚንስትራችን ሌላ አይደሉም፤ ራሳቸው መለስ ዜናዊ ናቸውና፡፡
አዎ! ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያኖች መለስን የምንጠይቃቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉን፡ ፡ ወንድምና እህቶቻችን በሀገራቸው ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራትም እንደሰው የማይታዩበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ መዋረድ ዕጣ ፈንታቸው ሆኗል፡፡ ሌላው ቀርቶ መንግስት አልባ በሆኑ ሀገራት ዜጎች ሳይቀር ኢትዮጵያዊ የተናቀ እና የተገፋ ሆኖአል፡፡ ተቆርቋሪ አልባ ሆኗል፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር ስልጣን ከያዙ 21 አመት ሆኖታል፡፡ ሆኖም ትዝ ይልዎት እንደሆነ፣ ደርግ የወደቀ አካባቢ ‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያዊያን በቀን ሶስቴ የሚበሉበት ደረጃ እንዲደርሱ እናደርጋለን›› ሲሉ በአደባባይ ቃል ገብተው ነበር፡፡ የሆነው ግን በግልባጩ ነው፡፡ የገቡት ቃል እንኳን ሊሳካ ቀርቶ እርስዎ ወደስልጣን ከመምጣትዎ በፊት የነበረንንም እስከማጣት አድርሶናልና፡፡ እርስዎ ግን ዛሬም በስልጣንዎ ላይ ነዎት፤ ነገም በስልጣንዎ መቀጠል ይፈለጋሉ፡፡ እናሳ! ከዚህ የበለጠ አምባገነንነት የት የሚኖር ይመስልዎታል? እንደሀገርስ ቢሆን የዜጐቼን ክብረ አስጠብቂያለሁ ብለው በኩራት ሊናገሩ ይችላሉን? ኧረ በጭራሽ፡፡
መቼም በቅርቡ በሊባኖስ አንዲት ኢትዮጵያዊ (ያውም የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ፊት ለፊት) በአሰሪዋ መንገድ ለመንገድ እየተጎተተች ተሰቃይታ ስታበቃ ሆስፒታል ውስጥ መሞቷን ሰምተዋል፣ ይህስ ምን ስሜት አሳደረብዎት? የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንኳ የሊባኖስ መንግስት ስለልጅቷ አሟሟት አጣርቶ ሪፖርት እንዲያቀርብለት ሰሞኑን እንደጠየቀ ቢቢሲ ዘግቧል፡ ፡ እርስዎ ግን አሁንም ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነትን እየተዋጋው ነው›› በሚል አምባገነኑን ድርጅቶትን በማጠናከር ስራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ስለዚህ አሳዛኝ እና እኩይ ድርጊትም አንዳች ያሉት ነገር የለም፡፡ ታዲያ የዚህች ሴት ቤተሰቦች ስለልጃቸው አሰቃቂ ሞት አንዳች ያልተነፈሱትን ሰው ጠቅላይ ሚንስትራችሁ ናቸው ብንላቸው ምን የሚሉ ይመስልዎታል? በተጨማሪም ይህንን እና የመሳሰለውን አይነት ስቃይ እንደሚደርስባቸው እያወቁ ወደዛው የስቃይ ከተማ ለመሄድ በኢምግሬሽን በር ላይ በየቀኑ ስለሚሰለፉ እህቶቻችንስ አስበው ያውቃሉ?
ክቡር ጠ/ሚኒስትር፡- ስለቦንድ መግዛት እና አለመግዛት እየተጠየቁ ባለበት በአሁኗ ሰዓት እንኳ ከቤንች ማጂ ዞን ‹‹ውጡ! ይህ ሀገራችሁ አይደለም›› ተብለው የተባረሩትን የአማራ ተወላጆችንስ ስቃይ እና እንግልት ሲያዩ ስለምን ሀዘን አልተሰማዎትም? በበኩሌ ይህ አይነቱ ስራ ከሀዘንም አልፎ ቁጣን ይቀሰቅሳል ባይ ነኝ፡ ፡ ሌላው ቀርቶ የተባራሪዎቹ ብሔር ተወካይ ነኝ ብሎ የአማራ ክልልን እየገዛ ያለው ብአዴን እንኳ አንዳች ሊረዳቸው አለመፈለጉን ሲያዩ ‹‹አበጀህ!››፣ ‹‹እሰይ!›› አሉት? ወይስ የብአዲኖችን ጭካኔ እና ደንታቢስነት ታዘበው አለፉት? በግልባጩስ ተቃዋሚ ፓርቲው መኢአድ በጠባብ ጽ/ቤቱ አስጠልሎ ከአውሬ እየጠበቃቸው እንደነበረ ሲሰሙ ከሞራል አኳያ ምን ተሰማዎ? እስቲ ይህን ችግር ከያዙት ስልጣን አኳያ ሳይሆን፣ ለፈጣሪ ብለው እንኳ ቢፈቱት ምን ይጎልቦት ነበር? አንድ መሪስ ለመመራው ህዝብ ጋሻ መከታ መሆን ካልቻለ፣ ለሰላሙ ዋስትና መስጠት ከተሳነው በስልጣኑ ላይ ምን ያደርጋል? ምን ያህል የኦሮሞ ተወላጅችስ በረባ ባረባው ምክንያት እንደበግ እየተጎተቱ በእስር ቤት እንደሚገኙ ያውቃሉ? እነዚህ ታሳሪዎች አባት፣ እናት፣ ልጅ፣ እህት፣ ወንድም እንዳላቸው ሲያስተውሉ ምን ይሰማዎ ይሆን? የዚህ ሁሉ ችግር ምንጭ ደግሞ እርስዎ እና የትግል አጋርዎ ያመጡት ዘውገ ተኮር ፌድራሊዝም ፖለቲካ ነው፡፡ በአጠቃላይ ካድሬዎችንም ሆነ ሰላይዎችን ጠይቁ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያኖች በኑሮ ውድነት፣ በፍትህ እጦት፣ በአጉራ ዘለል ካድሬ ያልተገባ ድርጊት… ታላቅ ሀዘን ላይ ነን፡፡ እርስዎ ግን የሚያስቡት ከቀጣዩ ምርጫ በኋላም በስልጣንዎ እንዴት እንደሚቀጥሉ ነው፡፡
ክቡርነትዎ፡- ወደ ስልጣን ሲመጡ ተቋቁመው ከነበሩት የፕሬስ ውጤቶችስ ዛሬ ምን ያህሉ በህትመት ላይ እንዳሉ አስተውለዋል? ከቶስ ጋዜጠኛ እና አልቃይዳ በአንድ ህግ የሚዳኝበት ሀገር ከኢትዮጵያ ሌላ ወዴት ይኖራል? ምን ያህል ጋዜጠኞች በእርስዎ እስር ቤት ውስጥ አሉ? ምን ያህሉስ ለአስከፊው ስደት ተዳረጉ? የመንግስትን ፖሊስ እና አምባገነንነትን መተቸት ነውር የሆነው እርስዎ በሚመሩት ሀገር ብቻ መሆኖ አላስጨነቀዎትም? ሌላው ቀርቶ ስህተቶቾ ካልተጋለጡ፣ ድክመቶቾ ካልተተቹ በምን መልኩ ነው ሊሻሻሉ የሚችሉት? ተሃድሶ፣ ተሃድሶ ይሉስ የነበረው በባዶ ሜዳ ሲያደናግሩን ነውን? መቼም ለመታደስ መተቸት እና ስህተትን መረዳት አስፈላጊ መሆኑን ከእኔ በላይ እርሶ ያውቃሉ፡፡ …አረ ለመሆኑ ‹‹ዲሞክራሲያችን ለኢሰፓ አባላትም ይተርፋል›› ሲሉ የነበረውስ ሲያሾፉብን ነው እንዴ?
ክቡር ሚኒስትር፡- አመኑም አላመኑም ኢትዮጵያ ምሁራኖች ተሸማቀው የሚኖሩባት፣ አገር ለቀው የሚሰደዱባት፣ ወጣቶች በአንድ ፓርቲ ስር እንዲጠለሉ የሚገደዱባት፣ በስራ አጥነት ለሱስ የሚጋለጡባት፣ ሙስና የተንሰራፋባት፣ ድህነት የሰፈነባት፣ በሽታ እንዳሻው የሚፈነጭባት፣ አምባገነንነት የነገሰባት…ግዙፍ ገሀነመ እሳት ከሆነች ከራርማለች፡፡
ክቡርነትዎ በዚህ የኑሮ ውድነቱ ጣሪያ በነካበት፣ ኢኮኖሚው ህዝቡን በጭራሽ በረሳበት ዘመን እርስዎ ጠቅላይ ሚኒስትር ባይሆኑ እና የደሃ ቤተሰብ አባል ቢሆኑ ኖሮ ስለመንግስት ምን ያስቡ ነበር? መቼም ከዚህ ቀደም ‹‹ልጆቼ ፋኖ ተሰማራ እያሉ እንዲዘምሩ አልፈልግም›› ማለቶትን ይረሱታል ብዬ አላስብም፡፡ እውነቴን ነው የምልዎ ያን ጊዜ ‹‹ልጆቼ…›› ሲሉ እኛንም ጨምሮ መስሎኝ ነበር፤ ግና ምን ዋጋ አለው እርስዎ ለካስ እየነገሩን ያሉት ስለሚመሩት ህዝብ ሳይሆን ከአብራክዎ ስለተገኙት ሶስት ልጆችዎ ብቻ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ይህ በእጅጉ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን በእርስዎ እና በድርጅትዎ ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርግ ነው፡፡ በእርግጥ እመኑኝ የራስዎ ልጆች ሳይቀሩ ከኢትዮጵያ ነፃነት ጎን የሚቆሙበት ጊዜ እሩቅ አይደለም፡፡
የሆነ ሆኖ የዚህ ሁሉ ጣጣ ፈንጣጣ ተጠያቂ እና ሀላፊ እርስዎ መሆንዎን ሲያስቡ ምን ይሰማዎታል? የዚህ የተበላሸ እና አስወቃሽ ታሪክ ሰሪ መባሉንስ እንዴት አዩት?
…ይህንን ፅሁፍ ከመጨረሴ በፊት ከዓመታት በፊት ከታይም መጽሔት ጋር ያደረጉትን አጭር ቃለ-መጠይቅ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ መጽሔቱ ድንገት ከእንቅልፎት የሚያናጥቦት ጉዳይ ምን እንደሆነ ጠይቆት የመለሱለት መልስ ቀልቤን ሳበው፡-
‹‹ It has always been fear-fear that this great nation, which was great 1,000 years ago but then embarked on a downward spiral for 1,000 years, and reached its nadir when millions of people were starving and dying, may be on the verge of total collapse. Now it’s not a fear of collapse. I believe we are beyond that It’s the fear that the light which is beginning to flicker the light of a renewal an Ethiopian renaissance that this light might be dimmed by some bloody mistake by someone, somewhere. This [renaissance] is still fragile, a few shoots [which] may need time to be more robust. At the moment it is fear born out of hope that this new millennium will be as good as the first one and not as bad as the second one.››
(የሁልጊዜም ፍርሃቴ ይህች በመጀመሪያው ሚሊንየም ዓመት ታላቅ የነበረች፣ ነገር ግን በቀጣዩ ሺህ ዓመት ቁልቁለቱን ተጉዛ ህዝቧ በችጋር የሚያልቅበት በመጨረሻም የመፈራረስ ጠረዝ ላይ የቆመች ሀገር መሆኗ ያባንነኝ ነበር፡፡ አሁን ግን የመፈራረስ ስጋቱን ተሻግረነዋል፡፡ እናም የአሁኑ ፍርሃቴ የጀመርነው የህዳሴ ጉዞ በሆነ ሰው /ቡድን/ ይቀለበስ ይሆን? የሚል ነው፡፡ የአሁኑ ስጋቴ መነሻ የሚመነጨው አደጋን ከማሰብ ሳይሆን ይህ ሚሊንየም እንደ መጀመሪያው መልካም ይሆናል ከሚል ተስፋ ነው፡፡) ነበር ያሉት፡፡
ክቡርነትዎ ይህ ህልሞት ቢሳካ ጥቅሙ የሀገሬ ነውና ደስታዬ የበዛ ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን የእርስዎ አምባገነናዊ ስርዓት ያመጣቸው ሀገራዊ መከራዎች የመጀመሪያውን ፍርሃቶትን እውን እንዳያደርገው እሰጋለሁ፡፡ ስርዓቶትን ለማስተካከልም ሆነ ከስልጣን በሰላማዊ መንገድ ለመውረድ አሁንም ጊዜው አልረፈደም፡፡ በይበልጥ ደግሞ ስልጣን መልቀቅዎ እንዴት ቅዱስ አሳብ መሰልዎ! ይበሉ አቶ መለስ

No comments:

Post a Comment