እንደምን አደራችሁ ብስጭት እናስነብባለን በመጀመሪያም አርዕስተ ብስጭት።
በትላንትናው ዕለት ብሄራዊ ቡድናችን ላይ በደረሰበት መጠነ ሰፊ ጥቃት በርካቶች መበሳጨታቸው ተሰማ።
በቅድሚያ፤
ብሄራዊ ቡድናችን፤ በደቡብ አፍሪካ ያለ ኮከብ በሚያበራው የኢትዮጵያ ባንዲራ፤ በባለ አንበሳው ሞአንበሳ ባንዲራ
በባለኮከቡ የፌደራሉ ባንዲራ እንዲሁም በባለ ዋርካው የኦነግ ባንዲራ ምን እርሱ ብቻ በባለ ቀንበጡ የኤርትራ
ባንዲራ ሁሉ ሲደገፍ ተመልክተን እማማ ኢትዮጵያ ብዙ ልጆች እንዳሏት አየን ደስም አለን!
የብስጭቱ ዝርዝር ቀጥሎ ይቀርባል፤
ጨዋታው እንደተጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ቁጭ ብድግ የሚያሰኝ ማራኪ ጨዋታዎችን አድርጎ የነበረው ብሄራዊ
ቡድናችን በሽመልስ አማካይነት የተሞከረችው የጎል አጋጣሚ ለጥቂት በጣም ለጥቂት በግቡ ቋሚ አማካይነት መከነች።
እንዴት ነው ነገሩ የግቡ ቋሚ የቡርኪናፋሶ ረዳት በረኛ ነው እንዴ ብለን በጣም ተበሳጨን! እርርር..ም አልን።
እያለ እያለ አንድ ጎል ገባብን አንድ የቡርኪናፋሶ ተጫዋች ኦፍሳይት ክልል ውስጥ ነበር። ምናልባት እርሱ
አዘናግቷቸው ይሆን…? ብለን አሁንም ተበሳጨን። ትንሽ ቆይቶ አሉን ከምንላቸው ተጨዋቾች ውስጥ አዳነ ግርማ ከአንዱ
የቡርኪናፋሶ ተጫዋች ጋር ተጋጭቶ ሲወድቅ አየነው። ሲገጭ ያየነው እግሩ አካባቢ ነው። አዳነ ግን የያዘው ብሽሽቱን
ነበር። እንዴት ነው ነገሩ ሰዎቹ እግር ገጭተው ብሽሽት የሚያሳምሙት…? የአዴ ስልት ነው… ወይስ ህመም በእግር
“ሜሴጅ” ያደርጋሉ። ብለን እየተጨነቅን ሳለ አዴ ህመሙ በረታበትና ከሜዳ ወጣ። ኤርሚ እንደዘገበልን፤ አዳነ
የታመመው እግሩን ከተገቢው በላይ ከፍ በማድረጉ አማካይነት የሚመጣ የጡንቻ መሳሳብ ነው። ይህ ህመም ለሚቀጥሉት
አስር ቀናት ከሜዳ ያርቃል። ተበሳጨን አይገልፀውም፤ “ኦ…. ብስጭት ሆይ እንዲህ ደጋግመሽ የምትጎበኝን አንቺ
የቤተሰባችን አባል ነሽን!?” አልን።