ነሀሴ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኩማ አስተዳደር በተለምዶ ማዘጋጃ ቤት ተብሎ በሚጠራው ቅጥር ግቢ ውስጥ የጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት አስመልክቶ ሁለት ትልልቅ ድንኩዋኖችን በግቢው ውስጥ ተክሎአል። አስተዳደሩ
ከፌዴራል መንግስት በተለየ የከተማዋ ነዋሪዎች ሐዘናቸውን የሚገልጹበት ቦታ ያስፈልጋል በሚል ሁለት ትልልቅ
ድንኩዋን ትላንት የተከለ ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ሐዘናቸውን በለቅሶ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ ከዚሁ ጋር
በተያያዘም በይፋ ባይገለጽም የአቶ መለስ ሞት ከተሰማ በኃላ የአስተዳደሩ ልዩ ልዩ ቢሮዎች ምንም ዓይነት አገልግሎት
መስጠት ያቆሙ ሲሆን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችንም በቢሮአቸው ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖአል፡፡
አንድ አስተያየት
ሰጪ በመንግስት ተቋም ደረጃ ድንኩዋነወ ተክሎ ሕዝብ እንዲያለቅስ ማነሳሳት ተራ የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ ካልሆነ
በስተቀር ፋይዳ የሌለው ተገቢ ያልሆነ ተግባር ነው ሲል ተችቶታል፡፡አስተያየት ሰጪው አያይዞም ሕዝብ በራሱ መንገድ
በየቤተ እምነቱ ሄዶ ሐዘኑን የሚገልጽበት ጸሎትም የሚያደርግበት ሥርዓት ቀድሞም ያለ መሆኑን በማስታወስ እስከ ቀብሩ
ድረስ ከ15 ቀናት በላይ አገር ሐዘን ላይ እንዲቀመጥ ማድረግ ኃላፊነት ከሚሰማው አመራር የሚጠበቅ አይደለም
ብሎአል፡፡