0
አንዳንዴ ወሬ በባዶ ሜዳ ይናፈሳል። ብዙ ጊዜ ትንሽ ጫፍ ይዞ ይናፈሳል። የህወሓት መንግስትን በተመለከተ አያደርጉም የምለው ነገር ስለሌለ ለመጠራጠሬ ገደብ አብጂቸ ነው የምጠራጠረው። ብዙ ጊዜ ግን ስለነሱ የሚወራውን አልጠራጠርም። ያደርጉታል።
ሰሞኑንን (ምናልባት ሌሎቻችሁ ከሰማችሁ ቆይታችሁ ይሆናል!) የህወሓት መንግስት የአመስት መቶ ብር ኖት የማዘጋጀት ሃሳብ እንዳለው እና በገንዘቡ ላይ የ “ባለ ራዕዮ መሪ” ምስል እንደሚያርፍበት ሰማሁ። የታላላቅ መሪዎችን ምስል በምንዛሬ ላይ ማስቀመጥ አዲስ ነገር አይደለም። ጥያቄው ግን ታላቅ ማነው? ታላቅነቱ እንዴት ነው? በየትኛውም ማህበረሰብ የበቀሉ የፖለቲካ መሪዎች የራሳቸው የሆኑ ተቃዋሚዎች እንደሚኖራቸው እሙን ነው። ነገር ግን ከሚከተሉት ፖሊሲ በመነሳት ዜግነታቸው ጭምር ጥያቄ ውስጥ የገባ እና በእኛ ሃገር ዘይቤ በባንዳነት ሂሳብ የተያዙ የሌሎች ሃገር መሪዎች ያሉ አይመስለኝም። ያውም ምስላቸው ምንዛሬ ላይ የሚወጣ?! ፈጽሞ አይመስለኝም። የቻይናው ማኦ የጠባብ ብሔርተኛ የፖለቲካ መሪ አልነበረም። የዘር ትምክህት አባዜ አልነበረውም። የኢንዶኔዢያው ሱካርኖ እንደዚያው። የፓኪስታኑ መሃመድ አሊ ጂና እንደዚያው። ብዙ የ”ሶስተኛውን ዓለም” ሃገሮች መሪዎች ለአብነት ማንሳት ይቻላል።