Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Friday 28 September 2012

የሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሐውልት አሠራ

Wednesday, 26 September 2012 09:34, By Tamirat Getachew
በታምራት ጌታቸው
ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር በሃያ ሺሕ ብር ወጪ ሐውልት አሠራ፡፡
በማኅበሩ የተሠራው ሐውልት ሁለት ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፣ አቶ መለስ የሰላም ምልክት መሆናቸውን ለማመላከት እጃቸውን አንስተው ለሕዝብ ሰላምታ ሲያቀርቡ የሚያሳይ ሐውልት መቀረጹን ማኅበሩ ገልጿል፡፡ ሐውልቱ በሃያ ሺሕ ብር ወጪ መሠራቱን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሥዩም አያሌው  ለሪፖርተር ገልጸው፣ የሐውልቱ ሥራ ሙሉ ወጪ በአንድ ድርጅት አማካይነት መሸፈኑን አስታውቀዋል፡፡ ሐውልቱ  የማኅበሩ አባላት በሆኑ አምስት ቀራፂያን በአንድ ወር ውስጥ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡ ገንዘቡ የዋለው ለግብዓት ግዢ ብቻ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕይወት ሳሉ ለአገራቸው ከሠሩት ታሪክ አኳያ ሐውልቱ በብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ እንዲቆም የማኅበሩ ፍላጎት መሆኑን አቶ ሥዩም ገልጸዋል፡፡

ማኅበሩ ሐውልቱን በሙዚየሙ ውስጥ ለማቆም በመፈለጉ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረባቸውንም አስረድተዋል፡፡ ማኅበሩ ወደፊት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ስም አደባባይ የሚሰየም ከሆነ፣ አምስት ሜትር ከፍታ ያለው ሐውልት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አሁን የተሠራው ሐውልት ሌሎችም በክፍያ እንዲሠሩት ቢደረግ ኖሮ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ያስወጣ ነበር ሲሉ አቶ ሥዩም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

Tuesday 25 September 2012

አቶ መለስ ዜናዊ የግማሽ ሚሊዮን ብር ሃውልት ተሰራለት

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሁለት ሜትር ርዝመት ያለው ሃውልት የተሰራለት መሆኑ ታወቀ። በህይወት በነበረበት ወቅት ከአንድ ሜትር ተኩል ያልበለጠ ቁመት የነበረውን ጠቅላይ ሚንስትር ቁመትን አግዝፎ የሰራው የሰአሊያን ማህበር ሲሆን፤ ጸጉራቸውም በጣም ያልተመለጠ ሰው አድርገው ነው ሃውልቱን የሰሩት። ማህበሩ ግማሽ ሚሊዮን ብር አስወጥቶኛል ያለው ሃውልት በብሄራዊ ሙዚየም እንዲቀመጥለት ጥያቄ አቅርቧል። አስፈላጊ ከሆነ አምስት ሜትር ቁመት ያለው ሌላ ሃውልት ወደፊት ለመስራት እቅድ ያለው መሆኑን ተናግሯል።

ወ/ሮ አዜብ የምኒልክ ቤተ መንግስትን የሚለቁ አይመስልም

(ኢ.ኤም.ኤፍ) በየትኛውም አገር አንድ መንግስት ሲቀየር አዲስ የሚመረጠው አካል፤ ወደ አስተዳደር ቢሮው መግባት ይኖርበታል። በራሺያ የክሬምሊን ቤተ መንግስት ወይም በአሜሪካ ኋይት ሃውስ የመንግስት መቀመጫ ስፍራዎች ናቸው።  ለኢትዮጵያ ደግሞ የመንግስት ስራ ማከናወኛ የአራት ኪሎው ምኒልክ ቤተ መንግስት መሆኑ ይታወቃል። ታዲያ በሌሎች አገራት የመንግስት ለውጥ ሲደረግ፤ ፕሬዘዳንቱም ሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ በጨዋ ደንብ ጨርቅ እና ማቃቸውን ይዘው ይወጣሉ። በኢትዮጵያ ግን ይህ አልሆነም። የቀድሞው እመቤት ቤተ መንግስቱን የሙጥኝ እንዳሉት ነው።

አቶ ኃይለማርያም ምኒልክን ቤተ መንግስት ከሩቅ ከማየት ውጪ ከነቤተሰባቸው ወደ ቅጥር ግቢው አልተዛወሩም። ሌላው ቀርቶ በትላንትናው እለት የሁለቱን ሱዳኖች ልዑካን ተቀብለው ያነጋገሩት፤ ፕሬዘዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በሚገኙበት ኢዮቤልዩ ቤተ መንግስት ውስጥ ነበር። ከዚህ በፊት በመለስ ዜናዊ ይደረጉ የነበሩ የእንግዳ አቀባበል ስርአቶች ይፈጸሙ የነበረው በአራት ኪሎው ምኒልክ ቤተ መንግስት ሲሆን፤ አሁን ግን ሴትዮዋ አልወጣም በማለቷ ምክንያት… አቶ ኃይለማርያም ፕሬዘዳንቱ የሚገኙበትን ቤተመንግስት በጋራ ለመጠቀም ተገደዋል።

በአሁኑ ወቅት ስልጣን ያለምንም ኮሽታ “ከኢህአዴግ ወደ ኢህአዴግ ተሸጋግሯል” ቢባልም፤ አዜብ መስፍንን ጨምሮ በርካታ የህወሃት ባለስልጣናት ደስተኛ አይመስሉም። ሌላው ቀርቶ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር (በፈጣሪ ፋንታ) ለመለስ ዜናዊ ዘላለማዊነትን በተመኙበት ፓርላማ፤ ወ/ሮ አዜብን ጨምሮ ሌሎች የህወሃት አባላት፤ የራሳቸውን ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ ሲያደርጉ ቢቆዩም በፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አልተገኙም ነበር። ይህ ብዙዎችን ቢያሳዝንም፤ ውስጥ ውስጡን ግን የርስ በርሱን ሽኩቻ አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

ሌላው ቀርቶ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚንስትር ተብለው ከመሰየማቸው በፊት፤ ባስቸኳይ ለህወሃት አባላት የጄነራልነት ማዕረግ ማንበሽበሹ በራሱ፤ የርስ በርሱ የስልጣን ሽኩቻ ውጤት ነበር። ህወሃት በትግርኛ ባወጣው መግለጫ ላይ አስፈላጊ ከሆነ፤ እንደገና የትጥቅ ትግል ሊያደርግ እንደሚችል ማስፈራሪያ ቢጤ በመግለጫው ላይ አስፍሯል። ይህ ማስፈራሪያ ለማን እና ለምን እንዳስፈለገ እስካሁን ድረስ ግልጽ አይደለም። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም የአራት ኪሎውን ቤተ መንግስት ከሩቅ ከማየት በቀር፤ በለቅሶ ሰሞን ጎዳና ተዳዳሪ ጭምር ሲንሸራሸርበት ወደነበረው የምኒልክ ቤተመንግስት እንዳይገቡ ተደርገዋል።