(Reporter) - ባለፈው ዓርብና ቅዳሜ በዝግ የተካሄደው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ የግንባሩን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር በሙሉ ድምፅ በመምረጥ ተጠናቀቀ፡፡
ከአራቱ አባል ድርጅቶች የተውጣጡ 180 አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ምክር ቤት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በሊቀመንበርነት ሲመርጥ፣ አቶ ደመቀ መኮንን ደግሞ ለምክትል ሊቀመንበርነት ተመርጠዋል፡፡ በድርጅቱ ልምድ መሠረት ሊቀመንበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ምክር ቤቱ ሲስማማ፣ ምክትል ሊቀመንበሩም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ መወሰኑ ታውቋል፡፡
ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የግንባሩን ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊን እንዲተኩ በኢሕአዴግ ሕገ ደንብ መሠረት በምክር ቤቱ አባላት የተመረጡት አቶ ኃይለ ማርያም፣ የደኢሕዴን ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡ ለግንባሩ ምክትል ሊቀመንበርነት የተመረጡት አቶ ደመቀ የብአዴን ሊቀመንበርና የትምህርት ሚኒስትር ናቸው፡፡