ይህ የትርጉም ሥራ መታሰቢያነቱ
በተስፋይቱ ምድር ኢትዮጵያ ከአለፉት አያሌ ዓመታት ጀምሮ ለፍትህ፣ ለአንድነት፣ ለባንዲራ ክብር፣ ለሀገር ሉዓላዊነት፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት መከበር፤ ለዜጎች ሁሉ እኩልነት፤ በጥቅሉ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓትና ለመልካም አስተዳደር እውን መሆን የሕይወት መስዋዕትነትን ለገበሩት፤ በየወህኒ ቤቶችም በግፍ ለማቀቁት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይሁን!!
ተርጓሚ – መስፍን ማሞ ተሰማ
ደራሲ – ጆርጅ ኦርዌል
ሙሃመድ ቡአዚዝ ራሱን በማቃጠል በቱኒዚያ የቀሰቀሰው አብዮት እነሆ ሰደድ እሳት ሆኖ በ17 የዓረብ ሀገራት ተቀጣጥሎ፤ የታችኛውንም የአፍሪካ ክፍል መጎብኘት ጀመረ።በዚህም ወቅት ከ65 ዓመታት በፊት ለንባብ የበቃው የጆርጅ ኦርዌል ‘Animal Farm’ መጽሀፍ በመስፍን ማሞ ‘የእንስሳት አብዮት’ በሚል ወደ አማርኛ ተመልሶ ደረሰኝና አነበብኩት።ብዙዎች በንግግራቸውና በፅሁፎቻቸው የሚጠቅሱት ይህ ዝነኛ መፅሀፍ ዘመን የማይሽረው መሆኑን ዛሬ በአብዮት በሚናጠው የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ክፍል ተወላጆች የሆንን ይበልጥ ይከሰትልናል።