ላለፉት 21 አመታት የምኒሊክ ቤተ መንግስት
ለአንድና ለሁለት ቀን ግፋ ሲልም ለአንድ ሳምንት ካልሆነ ጌታውን አጥቷቸው አያውቅም፡፡
አቶ መለስ
በግንቦት
ወር በቡድን ስምንት ጉባኤ ከተካፈሉ በኋላ ግን ማንንም አምነው የማይርቁትን
ቤተመንግስት በህመም ምክንያት
ትተው ብራስልስ ከረሙ፡፡ ህመማቸው እና
አማልክቱ ጨክነውም ዳግም ወደ ምኒሊክ ቤተ መንግስት
በቁማቸው ሳይመለሱ ቀሩ፡፡ እናም ቤተመንግስቱ
ላለፉት ሦስት
ወራት ኦና
ሆኗል፡፡ ሀገሪቱን ማን የት ተቀምጦ እንደሚመራት ብዙም ግልጽ ባይሆንም፣
ኃለማርያም ደሳለኝ በተጠባባቂነት
ሀገሪቱን እየመሩ እንደሆነ ሲገለፅ ሰንብቷል፡፡
ይህ በእንዲህ
እያለ ባለፈው አርብ መስከረም 4 ተጀምሮ ቅዳሜ መስከረም
5 ቀን 2005 ዓ.ም የተጠናቀቀው የገዢው አብዮታዊ ፓርቲ ምክር ቤት ስብሰባ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በሟቹ ሊቀመንበሩ ምትክ ቢያስቀምጥም፣ ሰውየው እስከወሩ ማገባደጃ
ቃለ መሀላ
ፈፅመው ወደ
ቤተመንግስት አይገቡም፡፡ ሁኔታው ኢህአዴግ ኃይለማርያምን
ቤተመንግስት ከማስካባቱ በፊት ማጠናቀቅ የፈለገው
ስራ እንዳለ አመላካች
ነው፡፡ ኢህአዴግ ከ21 አመት በኋላ ከህወሓት ውጪ የሆነን ግለሰብ ለፓርቲው
ሊቀመንበርነት በመሾሙ በፓርቲው የውስጥ ፖለቲካዊ የኃይል አሰላለፍ ላይ ለውጥ መጥቷል ለማለት ያስችላል?
የአቶ ኃይለማርያም ፖለቲካዊ
ተክለ ስብዕናስ እንደ መሪ ውሳኔዎችን
ለመስጠት የሚያስች ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች
ቀጣዩ ፅሁፍ ምላሽ ይሰጣል፡፡
የኢህአዴግ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ አሳይቶ ይሆን?
ኢህአዴግ ላለፉት አመታት ከህወሓት ተፅእኖ ስር ተለይቶ አያውቅም፡፡ የአራት ፓርቲዎች ስብስብነቱም አፋዊ ከመሆን ያለፈ አልነበረም፡፡ ህወሓት ያቀደው፣ ህውሓት ያቦካውና የጋገረውን ተቀብሎ ከማስተጋባት ውጪ ህወሓትን የሚገዳደር አንድም አባል ድርጅት ያልነበረው ኢህአዴግ፣ ለህወሓት አንደኛ፣ ለብአዴን ሁለተኛ፣ ለኦህዴድ ሦስተኛ እንዲሁም ለደኢህዴን የአራተኛነት ደረጃ የሰጠ ውስጣዊ የኃይል አሰላለፍ ነበረው፡፡
የህወሓትም ሆነ የኢህአዴግ ጭንቅላት ተደርገው የሚወሰዱት መለስ ዜናዊ ከሞቱ በኋላ ግን የኢህአዴግ ውስጣዊ የኃይል አሰላለፍ እንዲቀያየር የሚያስገድድ ሁኔታ ተከስቷል፡፡ ለፓርቲው ቅርብ የሆኑ ወገኖች እንደሚገልፁት ህወሓት በአቶ መለስ ላይ ከተገቢው በላይ በመተማመመን ተተኪ ሰው ባለማዘጋጀቱ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረውን ተፅእኖ በቀላሉ ለማጣት ተገዷል፡፡ በብአዴን ውስጥ አዳዲስ ፊቶች በፊት እንዲመጡ ባይደረግም ቅሉ ፓርቲው ከአቶ መለስ በኋላ አለቅነቱ ለኔ ይገባኛል የሚል የተሳካ እንቅስቃሴ ማድረጉንም እነዚሁ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡ ኦህዴዶች በስልጣን ሽኩቻ ላይ ብዙም አልተሳተፉም፤ ከብአዴን ጋር የነበራቸውን ዘመን ያስቆጠረ የመቀናቀን አዝማሚያ ላለማድረግ የተገደዱ ይመስላል፡፡ አሁን ከሞላ ጐደል ኢህአዴግ ውስጥ ብአዴን ጠንከር ያለ ባይሆንም መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል የበላይነት ይዟል፡፡