Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Saturday, 14 July 2012

የመለስ ህመም፣ ታክቲክ እና መፃኢ እጣ ፈንታ......ተመስገን ደሳለኝ


ሰሞኑን አዲስ አበባ በወሬ መጋኛ ተመታለች። ወሬው በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በተለይም በአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደ ጉድ እየተራገበ ነው- የ57 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጠና መታመም። ህመማቸውንም ተከትሎ ቤልጂየም ለህክምና መሄዳቸው እና ከፍተኛ ሊባል የሚችል ክብደት የመቀነሳቸውም ወሬ እንዲሁ የመጋኛ ያህል ነው።
በእርግጥ የጉብዝናውን ወራት የዱር ፍሬ እየበላ በረሃ የታገለ ቀርቶ በቤተመንግስት ያደገ ‹‹ልዑል››ም ቢሆን የዚህን ያህል አመት በስልጣን መቆየቱ (ሌላ ምክንያት እንኳ ባይኖር) በጤናው ላይ አንዳች ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ችግርም ይህ ነው። ሌላ አይደለም። በበርካታ አምባገነን መሪዎች ላይ የታየ ማለቴ ነው፡፡
ምናልባትም የጠቅላይ ሚንስትሩን መታመም ተከትሎ በሀገሪቱ ውጥረት የነገሰበት ምክንያት የስርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ያለመሆንም ነው። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ በሆኑ ሀገራት የፕሬዚዳንቱ ወይም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት አደጋ ላይ ከወደቀ እያንዳንዱ የህክምና ሁኔታ እና ሰውዬው ያለበት ደረጃ ለሁሉም ሚዲያዎች ይፋ ስለሚሆን ለአሉባልታ የሚጋለጥበት ክፍተት አይኖርም። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታመሙ ጀምሮ ‹‹ከፍተኛ የጤና መታወክ ገጠማቸው››፣ ‹‹ሕይወታቸው አልፏል››፣ ‹‹ሙሉ በሙሉ ተሽሏቸዋል›› የሚሉ እርስ በእርስ የሚጣረሱ ወሬዎችን እየሰማን ያለነው። ይህ ሁኔታ ወደታች ብቻ ሳይሆን ወደላይም ላሉት ግልፅ አይደለም። ለስርዓቱ ቅርብ የሆኑ ሰው ‹‹ከዚህ በኋላ ወደ ስራቸው አይመለሱም፡፡ ጉዳቱ ከፍተኛ ስለሆነ ሀኪም ለረጅም ጊዜ ከስራ ካልተገለሉ ለህይወታቸው አስጊ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ነግሮአቸዋል›› ሲሉኝ፤ ሌላኛው የፍትህ ምንጭ ደግሞ የዚህን ተቃራኒ ይናገራሉ። የእኚህ መረጃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ በሙሉ ማገገማቸውን የሚያረጋግጥ እና በመኖሪያ ቤታቸው ስብሰባም እያካሄዱ እንደሆነ የሚገልፅ ነው። ‹‹ይህ የሆነው›› ይላሉ ምንጫችን ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩን በደንብ ካለማወቅ ነው። ምክንያቱም የህወሓት አመራሮች አብዛኛውን ጊዜ ይታመማሉ። ህመም የማያጠቃቸው አቶ መለስ እና አቶ ስዬን ብቻ ነው። ሆኖም እነዚህ ሰዎች ሲታመሙ ጉዳታቸው ‹ሞቶ የመነሳት› ያህል ነው። የአቶ መለስም የሰሞኑ ሁኔታ የዚሁ አይነት ሲሆን፣ ሰውዬው ወደ ስራቸው ለመመለስ እየተዘጋጁ ነው። የሰውነታቸው መጎዳትም የህመሙ ብርታት ሳይሆን የህክምናው ባህሪ (Treatment) የሚፈጥረው ተጽዕኖ ነው›› ሲሉ ወሬውን አጣጥለውታል።
የሆነ ሆኖ መለስ ከወትሮ በተለየ መልኩ ከፍተኛ ሊባል የሚችል የጤና መታወክ እንደደረሰባቸው እርግጥ ነው። በዚህም ቤተሰቦቻቸው ተጨንቀዋል፤ የፓርቲያቸው አመራርም ከሚገባው በላይ አሳስቦታል፤ ከስር ያለው ካድሬም የተረጋገጠ መረጃ ባይኖረውም በደፈናው መደናገጡ የሚጠበቅ ነው፡፡ ‹‹ሌሎች›› ኢትዮጵያውያን (ይህ አገላለፅ ከ1983 ዓ.ም በኋላ የመጣ ነው) ደግሞ እንደ ልብ አንጠልጣይ ሲኒማ ክስተቱን በተመልካችነት እየተሳተፉበት ነው፡፡ ሁኔታው የአፄ ምንሊክን የመጨረሻ ዘመን ያስታውሳል፡፡ (ሰውየው ሀገሪቱን ለሁለት አስርት ዓመታት ቀጥቅጠው የገዙ ቢሆንም ‹‹እግዜር ይማሮት›› ማለት ባህላዊ ወጋችን ይመስለኛል፡፡ ለማንኛው እግዜር ይማራቸው) ጉዳዩ ግን ይህ አይደለም። ጉዳዩ የጤንነታቸው ሁኔታ እየተባባሰ ከሄደ ወይም የከፋ ከሆነ ‹‹በማን ይተካሉ?›› የሚለው ነው፡፡ ይህ አሳሳቢ ነው፡፡ ምንም እንኳ አብዛኛው ዜጋ ለዓመታት በሀገሩ ጉዳይ ባይተዋር የተደረገ ቢሆንም በእንዲህ አይነት ቀውጢ ጊዜ መጨነቁ አይቀሬ ነው፡፡ እናም ከዚህ ተነስተን ‹‹ቀጣይ የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ›› ምን ሊሆን እንደሚችል ለመወያየት ያህል ሁኔታውን ከአስተዳደር ዘይቤአቸው ጋር እያነፃፀርን እንፈትሽ።
መነሻ አንድ
የፀረ-ደርግ ትግሉን በበላይነት የመራው ህወሓት ከምስረታው ጀምሮ ለሁለት እስከተከፈለበት 1993 ዓ.ም. ድረስ ይመራ የነበረው በ“Collective leadership” (በጋርዮሽ አመራር) እንደነበረ ይታወሳል፡፡ በዛም ዘመን ‹‹ግለሰብን ማምለክ›› ከግምገማም አልፎ በተፃፈ ህግ እስከመቀጣት የሚያደርስ ጥፋት ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን ‹‹ውድብ (ድርጅት) ወስናለች›› የምትለው አገላለፅም የህወሓት ቀኖና ነበር ማለት ይችላል- እስከ 1993 ዓ.ም። በትግሉ ዘመን ሌላው ቀርቶ ከዩኒቨርሲቲ በወጡት ምሁራን እና እርሻቸውን ትተው በረሃ በገቡት አርሶ አደሮች መካከል የሚታይ ልዩነት እንዳይኖር ህወሓት አጥብቆ ይቆጣጠር እንደነበር የኋላ ታሪኩ ይነግረናል። ሆኖም አሁን ያ ዘመን አልፎአል። ያ ህግም የኦሪት ህግ ሆኖአል። ምክንያቱ ደግሞ ዛሬ ግለሰብን ‹‹ማምለክ›› የህወሓት መለያ በመሆኑ ነው።
መነሻ ሁለት
‹‹ህወሓት››ን የመሰለ አክራሪ ብሔርተኛ እና ኮሚኒስት ድርጅት ውስጣዊ አደጋ ሲገጥመው የቆመበት የፖለቲካ ባህልም ሆነ መተዳደሪያ ደንብ መናዱ ከሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ተሞክሮ ስንነሳ የሚጠበቅ ነው። ልዩነቱ የናዳው ጉዳት ላይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያም በ93ቱ ክፍፍል ህወሓት በአደገኛ ሁኔታ የቆሰለ (የተጎዳ) ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ወደ አንድ ሰው መዳፍ ጓዙን ጠቅልሎ የገባው ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነውና። ህወሓትን ለተከታተለም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም እንዲሁ ‹‹ያ አንድ ሰው›› መሆናቸው የሚጠበቅ ነው።
የማይካደው ነገር በ1981 ዓ.ም አቶ መለስ ዜናዊ የድርጅቱ ሊቀመንበር ተደርገው የተመረጡት ከህወሓትም ሆነ ከኢህአዴግ የአመራር አባላት በርዕዮት አለም ትንተና የተሻሉ እና የተራቀቁ በመሆናቸው ነው፡፡ በአናቱም የብልህነትን ፀጋ ተላብሰዋል፡፡ ከአለፉት ስርዓት እና ከኒኮሎ ማኪያቬሊም የገነጠሏቸውን ‹‹ገፆች›› በማሻሻል የራሳቸው ማድረግ ችለዋል። ይህ በወንበሩ ዙሪያ ሊያደፍጡ ይችሉ የነበሩትን ‹‹እሾሆች›› ለመንቀል ጠቃሚ ቢሆንም-ጉዳትም አለው፡፡ በተለይ ‹‹ተተኪ›› እንዳይኖር ከማድረግ አኳያ ማለቴ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹አጼ ኃይለሥላሴ ‹‹ፀሐዩ ንጉስ›› በሚል መወደስ ወደ መለኮታዊነት ለመቀየር ሩብ ሲቀራቸው ነው ድንገት ‹‹የምርጥ መኮንኖች›› የወታደር ‹‹ጫማ›› የደረሰባቸው፡፡ አፄው ‹‹ፀሐዩ ንጉስ›› ሲባሉ ሊመሰጠር የተፈለገው ግልፅ ነው፡፡ ፀሐይ ለአለም ብቸኛዋ የብርሃን ምንጭ እንደሆነችው ሁሉ አፄውም የኢትዮጵያ መተኪያ የሌላቸው እና ተፎካካሪ የማይገጥማቸው የብርሃን ምንጭ ናቸው የሚል የግለሰብ አምልኮ ጣሪያን ማመልከት ነው፡፡
በእርግጥ አፄው ‹‹ፀሐዩ…›› ይባሉ ዘንድ ዙሪያቸው በ‹‹ከዋክብት›› እንዳይከበብ ከሀገርኛው የፖለቲካ ባህል እና ከማኪያቬሊ ስልት ተደባልቆ በተቀመረ ‹‹ፎርሙላ›› የቻሉትን ያህል ጥረዋል። ለዚህም ነው ከጣሊያን መባረር በኋላ መንግስታቸውን፣ ከአርበኛ ይልቅ ለጠላት ባደሩ ግለሰቦች ያዋቀሩት። የዚህ ምክንያት ደግሞ ህዝቡ ‹‹ንጉሱ ከሌሉ እነዚህ ባንዳዎች ሀገሪቱን መልሰው ለጣሊያን አሳልፈው ይሰጧታል›› በሚል ስጋት መዋጡ አይቀሬ በመሆኑ ለንጉሱ ስልጣን ቀናኢ ይሆናል የሚል ነው። ማኪያቬሊም ይህን ይመክራል ‹‹ችግር (ጉድለት) ያለበትን እየመረጥክ ሹም››፤ አፄውም መለስም ይስማሙበታል። (በነገራችን ላይ አጼ ኃይለሥላሴም የኒኮሎ ማኪያቬሊ ቀንደኛ ተከታይ ነበሩ) እናም አፄው ብቸኛው ፀሐይ ይሆኑ ዘንድ ብዙ ፀሐዮችን አጨለሙ። የዚህ ውጤትም ነው የ66ቱ አብዮት ፈንድቶ ‹‹ደርግ›› ፊቱን ወደ ቤተ-መንግስቱ በመለሰ ጊዜ ከልዑላኑም ከሹመኞቹም አማራጭ ‹‹ፀሀይ›› እንዳይገኝ ያደረገው፡፡ በወቅቱ ደርግ አማራጭ በማጣቱ ደራሲ አዲስ አለማየሁን ሳይቀር ‹‹ጠቅላይሚንስትር›› ይሆኑ ዘንድ እስከመጠየቅ የደረሰበት ሁኔታ ነበር፡፡…ይህ ከሆነ ከ38 ዓመት በኋላ ደግሞ ‹‹መለስ ከሌለ ሀገሪቱ ትበታተናለች›› የሚል ስጋት በእያንዳንዳችን ልቦና እንዲያድር መደረጉን ተከትሎ ‹‹የሚተካቸው ሰው›› አሳሳቢ ሆኗል። በእርግጥ በተለይም በግንባሩ የታችኛው ካድሬ ውስጥ ያለው ሁኔታ ፈረንሳይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ከገጠማት ችግር ጋር የሚመሳሰል ነው። በወቅቱ የ1789 ዓ.ም. አብዮትን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጣው Robespierre (ሮብስፒር) እ.ኤ.አ በ1794 ሲገደል፣ ጦረኛው Napoleon Bonaparte ስልጣን ላይ ወጣ። ናፖሊዮንም የፈረንሳይ አጎራባች ሀገራትን በመውረሩ በእንግሊዝ መሪነት የተባበሩት ሀገራት አሸንፈውና ከስልጣን አውርደው በኤልባ ደሴት ባሰሩት ጊዜም ሆነ ህይወቱ ካለፈ በኋላ በርካታ ፈረንሳዊያን ‹‹ናፖሊዮን አይሞትም!›› በሚል ተስፋ ተመልሶ እንደሚመጣ ይጠብቁ ነበር።
በኢህአዴግ ካድሬ ውስጥ ያለውም አስተሳሰብ የዚህ ግልባጭ ይመስላል፡ ፡ ‹‹መለስ አይሞትም!›› እናም ከዚህ አኳያ አንዳች ነገር ቢፈጠር ከአመራሩ ውጭ ያለው ካድሬ ለመቀበል የተዘጋጀ አይመስልም። ይህ ደግሞ ሌላ የዶግ አምድ ሊፈጥር መቻሉ አያጠራጥርም፡፡ (ለዚህም ነው ሁለቱም ተወራራሽ የአገዛዝ ባህሪያት አላቸው እያልኩ ያለሁት)
ሁለቱም ከፊታቸው ሊቆም የሚችል ‹‹ተገዳዳሪ›› በተነሳ ጊዜ በአደባባይ እየተቹ ወይም እያስተቹ ያሸማቅቁታል፡ ፡ አንገቱን እንዲሰብር ያደርጉታል። ለምሳሌ እውቁ የማራቶን ጀግና አበበ ቢቂላ የዚህ አይነቱ ፖለቲካ ሰለባ ነው፡፡ አቤ በሁለት ኦሎምፒክ ማሸነፉን ተከትሎ አለም አቀፍ ዝናን አገኘ። ይህን ጊዜም የምዕራብ ሀገራት ሚዲያ ኢትዮጵያን ሲያነሱ ‹‹የአፄ ኃይለሥላሴ ሀገር…›› የሚሉበትን ተቀጽላ ‹‹የአበበ ቢቂላ ሀገር…›› በሚለው ቀየሩት። በሁኔታው የተከፉት ንጉሱም ሌላ ‹‹ፀሐይ›› እየወጣ እንደሆነ አልተሰወራቸውም፡፡ ስለዚህም አትሌቱን በአደባባይ (በሚዲያ) መተቸቱን አጀንዳ አደረጉት፡፡ እናም ከዕለታት በአንዱ ቀን ‹‹…እጅግም መታበይ ደግ አይደለም። የዚህ ሁሉ ፈቃጅ እግዚአብሔር መሆኑን አስታውስ›› አሉና አጣጣሉት። …በአንድ ወቅት ታጋይ አርከበ እቁባይ የአዲስ አበባ ከንቲባ ነበሩ። በዘመነ ከንቲባነታቸውም ከተማዋን ካንቀላፋችበት ‹‹የሚቀሰቅስ›› የሚመስል ነገር ለማድረግ ሞከሩ። በዚህም የከተማው ዕድገት በሚያሳስበው ነዋሪ ዘንድ የአርከበ ስም ተደጋግሞ ይነሳ ጀመር። ይህ ከአቶ መለስ የሚሰወር አይደለም። ከእነዚህም ‹‹የአርከበ መብቂያ›› ወራት በአንደኛው ቀን አቶ አርከበ የኤች አይ ቪ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ለመቀስቀስ በአርአያነት ራሳቸው ተመረመሩ። ተመርምረው ሲያበቁም ደማቸው ለናሙና ሲወሰድ የሚያሳይ ምስል በትልቅ ቢልቦርድ ተሰርቶ በከተማው እምብርት እንዲሰቀል አደረጉ። ይህ በሆነ ማግስትም የአርከበን ምስል የያዘው ግዙፉ ቢልቦርድ ‹‹መኪና ገጨው›› ተብሎ ወደቀ፡ ፡ ከወደቀም በኋላ እንደፈረሰው የሌኒን ሀውልት ከቦታው ተነስቶ ተወረወረ። ይህ ብቻም አይደለም፣ ራሳቸው አቶ መለስ ምርመራ ማድረጋቸውን አስመልክቶ ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹ተመርምሬአለሁ። ነገር ግን ለገበያ አላቀረብኩትም›› አሉና በዘወርዋራ ለአቶ አርከበ ‹‹ልታይ ልታይ ማለት ደግ አይደለም›› የሚል መልዕክት አስተላለፉ።
ሌላ ተመሳስሎ ልጥቀስ። አፄው በበርካታ ቦታዎች ስልጣን የሚሰጡት (ከባንዳ በተጨማሪም) በጨካኝነታቸው እና በስግብግብነታቸው ለታወቁ መኳንንቶች እንደሆነ ይነገራል። ምክንያታቸው ደግሞ እነዚህ መኳንንቶች በጨካኝ አስተዳደራቸው ህዝቡን ያስለቅሳሉ፣ ያማርራሉ፡፡ ይህ አካሄድ በመጨረሻ ጉዳዩ ወደ እሳቸው ሲደርስ ትንሽ መፍትሄ ለመስጠት እና መጠነኛ ማስተካከያ ለማድረግ እንዲያመቻቸው ነው። ይህን ጊዜም ህዝቡ ‹‹ንጉሡ እኮ ሩህሩህ እና ቅን አባት ናቸው። ጨካኞቹ መኳንንቶቹ ናቸው›› ሲል ቁጣውን ከስርአቱ ወደ አስፈፃሚው ያወርዳል። እንዲሁም ከንጉሱ ውጭ አማራጭ እንደሌለው ያስባል፡፡ የንጉሡም ፍላጐት ይህ ነው፡፡ ምህረት እና መልካም አስተዳደር የሚፈልቀው ከእኔ ብቻ ነው የማለት። የአቶ መለስ የአለፉት የአስራ አንድ ዓመታት ጉዞም ይህንኑ ነው የሚተርክልን፡፡
ሌላ አይደለም፡፡ ይህ አይነቱን ስልት አምባገነን ገዥዎች ብቻ ሳይሆኑ ‹‹ሆሊውድ››ም ይጠቀምበታል። ሆሊውድ በሚያዘጋጃቸው በርካታ ፊልሞች ላይ የመሪ ገፀ-ባህሪዋን ቁንጅና ለማጉላት በመልከ ጥፉ አክተሮች አጅቦ ያሳየናል። አይኖች ሁሉ፣ ጆሮዎች ሁሉ ወደ ዋናዋ አክትር እንዲያተኩር፡፡ ይህ ቴክኒክ ከፊልም ወደ ፖለቲካ ሲገለበጥ ደግሞ ተቀባይነት የሌላቸው እና የአቅም ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ወደ ስልጣን እንዲወጡ የሚደረግበት ስልት ሆኖ እናገኘዋለን። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ‹‹ፀሐይነት›› ይበልጥ ለማድመቅ ማለት ነው፡፡ በአናቱም ባለስልጣናቶቻቸው ከኢትዮጵያውያን ስነ ልቦና በተቃራኒ እንዲቆሙ የሚያደርጉ ጨዋታዎችን አብዝተን እንድንመለከት የተደረግንበት ጊዜ አንድና ሁለት ብቻ ተብሎ የሚቆጠር አይደለም። ለምሳሌ ለተደጋጋሚ ጊዜ ባለስልጣኖች የተሳተፉበት የእግር ኳስ ውድድር ተደርጓል። በውድድሩ ላይ ግን አንድም ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልተሳተፉም። ይህ የሆነው ከፀጥታ ጉዳይ እና ካለመመቸት ጋር ተያይዞ ብቻ አይደለም። ሆን ተብሎ ነው። አቶ መለስ የኢትዮጵያውያንን ስነ ልቦና ያውቁታል። ሀበሻ ሱሪውን አውልቆ ኳስ የሚራግጥ ባለስልጣን ላይ እምነት ጥሎ እንደመሪ እንደማይከተልም ጠንቅቀው ያውቁታል። ለዚህም ነው እነ አቶ አባዱላ ገመዳ እና ሌሎች ባለስልጣናቶች እንዲያ እንዲሆኑ የሚደረገው። ከዚህ በተጨማሪም የስልጣን መሠረታቸው እንዳይናጋ ከብቃት ይልቅ ታማኝነትን እንደ መስፈሪያ ይጠቀሙበታል። ለምሳሌ አጼው ‹‹ጋብቻ››ን ዋና የፖለቲካ መጠበቂያ ያደርጉት ነበር። ይህ አካሄድም ከንጉሡ የዘር ማንዘር ጋር የተጋባ ባለስልጣን ሁሉ ከ‹‹አማቹ›› ውጪ የሚቀርበው ስለማይኖር የንጉሱን ስልጣን መጠበቅ የህልውና ጉዳይ ይሆንበታል። የ‹‹ጋብቻ ፖለቲካ›› አቶ መለስ ጋ ሲደርስ ደግሞ ‹‹በአውራጃ ትስስር›› እና ‹‹በታማኝነት›› ተለውጦ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ አይነት የፖለቲካ ጨዋታ ለዓመታት ታሽቶ ያለፈው የአቶ መለስ መንግስት ከአቶ መለስ ጤንነት ጋር በተያየዘ አደጋ ተጋረጦበታል፡፡ የሰሞኑ ‹‹አራት ኪሎ›› ባልተለመደ የፖለቲካ ትኩሳት መጋልም የዚህ ምክንያት ነው፡ ፡ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ በጥርጣሬ ሲታይ የነበረው የጠቅላይ ሚንስትሩ ‹‹የመተካካት ፖሊስ››ም ከጊዜው በፊት የደረሰ ይመስላል፡፡ በጠና መታመማቸውን ተከትሎ ማለቴ ነው፡፡ በእርግጥ ሀገሪቱ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የታነፀች ብትሆን ኖሮ በእንዲህ አይነት ጊዜ ‹‹ወንበሩን›› ለመያዝ በሚፈልጉ ተፎካካሪዎች መሀከል ውጥረት አይፈጠርም ነበር፡፡ ምክንያቱም ጠቅላይ ሚንስትሩ ህይወታቸው ቢያልፍ ወይም ከባድ የጤና መታወክ
ቢገጥማቸው የሚተካቸው ሰው ማን እንደሆነ አስቀድሞውን ‹‹በሚተገበር›› ህግ በግልፅ ተደንግጓል፡፡ የኢትዮጵያ ግን ከዚህ ይለያል፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ ግልፅ ስናደርገው ከአገልግሎት ዘመናቸው በፊት ጠቅላይ ሚንስትሩ በድንገተኛ ሁኔታ ከስልጣን ቢነሱ እሳቸውን ለመተካት የህግ ድጋፍ ያላቸው ‹‹የምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ሹመት›› በማይተገበር ህግ የታነፀ የፖለቲካ ጫወታ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እናም የወንበሩ ይገባኛል ጥያቄ ከሀገሪቱ ህግ ይልቅ የፖለቲካ ጉልበት በማሰባሰብ ወደ ሚደረግ ‹‹ስልጣን የመነጣጠቅ ትግል›› ያመዝናል ማለት ነው፡፡ ይህ አይነቱ ፉክክሩም ሄዶ ሄዶ አንድ አሸናፊ ሊያወጣ ስለማይችል ‹‹የስልጣን ክፍተት›› (Power Vacuum) መፍጠሩ አይቀርም፡፡ እንዲሁም ከአቶ መለስ ዜናዊ ‹‹የአንድ ሰው አስተዳደር›› ዝቅ ስንል ፓርቲያቸው ከውስጡ ለመነጨ አደጋ ተጋልጦ እናገኘዋለን። ምክንያቱም የተወሰኑ ኢህአዴግ አመራር አባላት ግንባሩ አሁን ባለበት ሁኔታ ደስተኛ አይደሉምና። ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ሰው የነገሩኝ በቀጣዮቹ ወራት ድርጅቱ የመሰንጠቅ አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በቢሮአቸው ያለመገኘት ጋር ተጋምዶ በፖለቲካው ላይ አዲስ ምዕራፍ ሊከፈት የሚችልበት ዕድል መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ከዚህ አንፃርም ጥቂት የቢሆን ስሌቶችን (Scenarios) ብናይ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡
የግንባሩ አባል ፓርቲዎች ፍላጎት
ግንባሩ የአራት ብሄርን ማዕከል ያደረጉ ፓርቲዎች ጥምረት ከመሆኑ አኳያ ከላይ ያየናቸው አደጋዎች በቀረቡት ጊዜ ነጥሮ የሚወጣው በግርግሩ የተናጥል ፓርቲን ተጠቃሚ የማድረግ ፍላጎት ነው። በተለይ ደግሞ አብላጫ ቁጥር ያለውን ብሔር እንወክላለን የሚሉት ኦህዴድ እና ብአዴን በዚህ አይነቱ ‹‹ሽሚያ›› ዕድሜ ጠገብ ቅራኔዎች እና መገፋቶችን እያነሳሱ ዋነኞቹ ተሳታፊዎች ሆነው በአዲስ ‹‹አቁማዳ›› ብቅ ሊሉ ይችላሉ። እዚህ ጋር ምንአልባት የህወሓት ነባር ሰዎች ከሚጠብቃቸው ፉክክር ለማሸነፍ አዲስ ነገር ሊያመጡ ይችላል። እስከዛሬ የነበረውን የብሔር ኮታ ስልጣን የመከፋፈል አሰራርን ‹‹ብቃትን መሀከል ያደረገ›› በሚል ቀይረው ማለቴ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ዞሮ ዞሮ በሚኒስትር ማዕረግ በተመደቡበት ቦታ የተሻለ እየሰሩ ነው ተብሎ የሚታሰቡት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም የህወሓት ቀጣዩ ‹‹ጆከር›› ሊሆኑ ይችላሉ። ረጅም ጊዜ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የሰሩት ብርሃነ ክርስቶስም ሌላኛው ‹‹ጆከር›› ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ ሌላ ደግሞ በቅራኔ ወይም ቁስል በመነካካት ላይ የተመሰረተ ጨዋታን ከጀመሩ አቶ መለስና ጓደኞቻቸው ያስተዋወቁት የብሄር ፖለቲካን በከፍተኛ ግፊት ያጠናክረዋል። የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪው ሌሎች ብሄሮችን ጨቁኗል የሚለው የፖለቲካው አተናተን፣ ይህም በተለየ መልኩ የተነገራቸው በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የኦሮሞ ልሂቃን “በታሪክ የተፈፀሙ” የሚሏቸውን ጭቆናዎች ለማወራረድ ‹‹አሁን ጊዜው የኦሮሞ ነው›› የሚል ባንዲራ ይዘው ወደ ስልጣን መተጋገሉ ሊመጡ ይችላሉ።
እንዲሁም ምንም እንኳን የቀድሞ ጥንካሬው የከዳው ቢሆንም ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል ‹‹የአንበሳውን ድርሻ›› የሚይዘው ህወሓት ‹‹የአቶ መለስ ብቸኛ ወራሽ›› ለመሆን የሚያደርገው ትግልም በቀላል የሚታይ ላይሆን ይችላል።
ከዚህ ባለፈ ብዙም የ‹‹ፖለቲካ ጉልበት›› የሌለው ወይም የ‹‹ፖለቲካውን ሻጥር›› ከህወሓት እና ብአዴን እኩል ሊያዳውረው የማይችለው ‹‹ደኢህዴን››፣ መሪዎቹን እና ወሳኝ ካድሬዎቹን ከጎናቸው ለማሰለፍ ሶስቱም ድርጅቶች ከሚያደርጉት ትንቅንቅ ባለፈ ‹‹በራሱ ለመቆም›› የሚያደርገው ትግል ላይኖር ይችላል። ደኢህዴን በዋናነት በራሱ ሊቆም የማይችልበት ዋናው ምክንያት ፓርቲው በትግሉ ዘመን ያልነበረ መሆኑና፤ አብዛኛው የፓርቲው አመራር በፓርቲው ካድሬ ድጋፍ ሳይሆን በአቶ መለስ ምርጫ ወደ ላይ የወጣ በመሆኑ ነው። ስለዚህም ከአቶ መለስ ‹‹አደገኛ የጤና መታወክ ጀርባ›› የሚኖረው የግንባሩ አሰላለፍ ይህንን ይመስላል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች ደጋግመው የሚነግሩን ደግሞ በግንባር ደረጃ በተለያዩ ፓርቲዎች በተመሰረተ ድርጅት ውስጥ የዚህ አይነቱ ውጥረት ፈንቅሎ ሲወጣ ድርጅቱ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ሙሉ በሙሉ ሊከፋፍል ወይም ሊፈርስ የሚችልበትን ዕድል እንደሚያሰፋው ነው።
የሸዋ ፖለቲካ
አፄ ምንሊክ ከሞቱ በኋላ ስልጣናቸውን ወደራሳቸው ‹‹ሰዎች›› ለመሳብ በሹማምንቱ (በእቴጌ ጣይቱ በንጉስ ሚካኤል አሊ እና በእነ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ) መካከል የሶስትዮሽ ፉክክር እንደነበር ያለፈው ዘመን ትርክት ይናገራል፡፡ የታሪክ ተመራማሪዎች እንዲህ አይነቱን በጥሎ ማለፍ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ጨዋታ በተለምዶ ‹‹የሸዋ ፖለቲካ›› ይሉታል።
በዚህ ዘመንም በስርዓቱ ላይ ‹‹የሸዋ ፖለቲካ›› መከሰቱ አይቀሬ እንደሆነ የሚጠቁሙ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይም አብዛኛው ሚኒስትሮችን፣ እንዲሁም ወሳኝ የብአዴን እና የኦህዴድ ካድሬዎችን ከጎናቸው ሊያሰልፉ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡት አቶ በረከት ስምኦን ከተገዳዳሪዎቹ አንዱ ሊሆኑ ይችላሉ። በረከት ስምዖን (በወሬ ደረጃ እየተነገረ ያለውን) ‹‹ዶ/ር ቴዎድሮስ አደህኖም አቶ መለስን ተክተው እየሰሩ ነው›› የሚለውን ንግርት ላይቀበሉት ይችላሉ። ዶ/ሩ ለግንባሩ የድል አጥቢያ አርበኛ መሆናቸውን ‹‹በማደማመቅ›› በአናቱም የራሳቸውን የትግል ታሪክ በማግነን ‹‹የመስራች ታጋይነት መብቴን አስከብራለሁ›› ሊሉ ይችላሉ፡፡ (ዶ/ሩ የአቶ መለስ ተተኪ እንደማይሆኑ አንድ ለፓርቲው ቅርብ የሆኑ ሰው ነግረውኛል። በዚህ ወቅትም ብዙ ስራዎችን እየሰሩ ያሉት ዶ/ሩ ሳይሆኑ ከመንግሥት ስራ በጡረታ የተገለሉት አቶ አዲሱ ለገሠ እንደሆኑ ይነገራል)
በተለምዶ ‹‹የእነ ተወልደ ቡድን›› የሚባለውም (ከህወሓት በ1993 ዓ.ም. የወጣው አመራር) በዚሁ አጋጣሚ ‹‹አላዛር›› ለመሆን የሚሞክርበት እድል አለ። ይህ ከሁለት አንፃር ነው የሚታየው። የመጀመሪያው በራሳቸው በአቶ መለስ ፍላጐት ‹‹ህወሓትን ለማዳን›› በሚል ጥቅሻ የቀድሞውን ቅያሜ ‹‹ይቅር ለፖለቲካ›› በማለት ህወሓትን ለማዳን በጋራ ሊሰለፉ መቻላቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው ግን ቡድኑ በተናጠል በተለይም ስዬ አብርሃ፣ ገብሩ አስራአት፣ አረጋሽ አዳነ… ከህወሓት ከወጡ በኋላ ከተቃዋሚዎች ጋር አብረው መስራታቸው የተሻለ የተደማጭነት እድል ሊፈጥርላቸው የመቻሉን አጋጣሚ በማስላት ዕድላቸውን መሞከራቸው የሚጠበቅ ነው። ምንአልባት ይህ ቡድን ነባር ታጋዮችን እና ከኢህአዴግ ጋር ባለመግባባት በጡረታ የተገለሉትን አቶ ተፈራ ዋልዋን ሊያካትት ከቻለም የብአዴንን ድጋፍ ከአቶ በረከት ሊነጥቅ የሚችልበትተጨማሪ የዕድል ቁጥር አለው።
አባይ ፀሐዬ፣ ስዩም መስፍን፣ አርከበ ዕቁባይን የመሳሰሉ አንጋፋ አመራሮችም ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ‹‹ልሞክረው›› ሊሉ የሚችሉበት አጋጣሚም ሌላኛው የጫረታው ተሳታፊ ያደርጋቸዋል። እነዚህ የቀድሞ የህወሓት ነፋስ-አባቶች በ1997ቱ ምርጫ ቅንጅትን እናሳንስበታለን በሚል ሊጠቀሙበት የሞከሩትን ‹‹ትግራይን ከሌሎች ጥቃት የማዳን›› መሰል መፈክሮችን ተሸክመው መሰባሰብ ከጀመሩ፣ ወንበሩን ለመያዝ የሚደረገውን ፍትጊያ እጅግ አደገኛ መዘዝ ወደሚያስከትል ‹‹ጫወታ›› ሊቀይሩት የሚችሉበት ዕድል ይሰፋል።
እንግዲህ ከላይ የተጠቀሱት (ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ህወሓት እና ግለሰቦቹ) ‹‹በሸዋ ፖለቲካ›› ስልት ሙሉ በሙሉ ወደ ፉክክር ከገቡ በሀገሪቱ ያለመረጋጋት እና የእርስ በእርስ ግጭት ሊከሰት የሚችልበትን ቀዳዳ ያሰፋዋል። ይህ ትንተና ነው፡፡ ሆኖም አደጋውን ለመከላከል ሁለት አማራጭ የአለ ይመስለኛል።
አማራጭ አንድ
ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ባሉበት ደረጃ ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ እስረኞች እና ስደተኞች ምህረት አድርገው የታሰሩትን መፍታት፣ የተሰደዱትም ወደሃገራቸው እንዲገቡ መፍቀድ፡፡ እናም አንድም ጊዜ ከወቀሳ አምልጦ የማያውቀውን ምርጫ ቦርድ በትነው በቅንነት እና በታማኝነት በሚሰሩ ሰዎች እንደአዲስ ማወቀር። የፓርላማውንም የስራ ዘመን ክረምቱን እንዳይዘጋ በማድረግ ለዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ እንዳይጎለብት ‹‹አፋኝ›› የሆኑትን (የፀረ-ሽብር፣ የመያድ፣ የፕሬስ…) አዋጆች እና ሕጎች እንዲሽሩ በማድረግ፣ የምርጫውን ጊዜ ሳይጠብቁ ሁሉንም ወገን የሚያሳምን ምርጫ እንዲደረግ ማመቻቸት አደጋውን በቀላሉ ከማሰወገዱም አልፎ ገዥውም ተቃዋሚውም፣ ሌላውም ኢትዮጵያዊ የሚወዳትን ሀገር ወደአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ያሸጋግራል። ነገር ግን በአቶ መለስ ቦታ ከላይ የጠቀስኳቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ወይም ዶ/ር ቴውድሮስ አድህኖም ወደ ስልጣን እንዲመጡ ከተደረገ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ከመተካት ውጭ ለውጥ የለውም፡፡ እንዲያውም በግልባጩ ህዝባዊ አመፅ ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡
ምንም እንኳ አቶ መለስ ከወራት በፊት የአረብ ዓለም አብዮትን አስመልክተው ለ“Pan-African magazine” በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ “Ethiopia and much of the Sub-Sharan Africa already had its own African spring back in the 1980’s and the Arabs are latecomers to the game” (ኢትዮጵያ እና አብዛኛው ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ጣጣቸውን የጨረሱት አስቀድመው በ1980ዎቹ ነው። አረቦቹ ግን ለጨዋታው አርፋጆች ናቸው) ሲሉ እኛ ለአብዮት እንግዳ አይደለንም፡ ፡ ከእነርሱ እንቀድማለን የሚል አንድምታ ባለው መልኩ የነገሩት፡፡ ለመጽሔቱ የነገሩት መተማመኛ የሚገለበጥበት እድል እንደሚኖር የተንታኞች ግምት አለ። ምክንያቱ ደግሞ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጐች ከቀን ወደቀን ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑ ነው። እናም እንዲህ አይነት ኩነቶችን ተከትለው የሚመጡ የመንግስት የመዳከም ምክንያቶች ‹‹ለውጥ ፈላጊውን›› የህብረተሰብ ክፍል ወደአደባባይ መግፋታቸው አይቀሬ ነው።
አማራጭ ሁለት-የታንታዊ መንገድ
የግብፅ አብዮትን ተከትሎ ስልጣን በወታደራዊው ጂንታ እንዲገባ ካደረጉት ውስጥ ዋነኛ ሠው ናቸው-Field Marshal Mohamed Hussein Tantawi (ፊልድ ማርሻል መሀመድ ሁሴን ታንታዊ)፡፡ ታንታዊ ግብፃውያን በታህሪር አደባባይ መሰባሰባቸውን ተከትሎ ከሌሎች 18 ወታደራዊ ኦፊሰሮች ጋር በመሆን የወታደራዊውን ከፍተኛ ምክር ቤት (SCAF) መስርተው፤ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክን ለፍርድ በማቅረብ (በፖለቲከኞቹ አነጋገር ‹‹ለአብዮቱ በመሰዋት››) ግብፅን ያረጋጉበት ጥበብ ነው-‹‹የታንታዊ መንገድ››
ምንአልባት ከላይ ባየነው ድንገቴ ፉክክር የተነሳ ሀገሪቱ በፖለቲካ ውጥረት ወደ አልታሰበ ግጭት ብትገባ የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል ሰራዊትም ከታንታዊ መፃሀፍ ‹‹አንድ ገፅ›› ሊገነጥል ከቻለ ለሀገሪቱ መፃኢ ዕድል የተሻለ መደላድል ሊፈጥር ይችላል። በግብፅ የመጣው ለውጥ (ምንም እንኳን አሁንም ወታደራዊው ሀይል በተወሰነ መልኩ ከመጋረጃው ጀርባ ያደፈጠበት ሁኔታ ቢኖርም) ከቀድሞ መንግስት አስተዳደር በእጅጉ የተሻለ ነው። የፖለቲካ ተንታኞች አሁን ያለውን አይነት የታንታዊ መንግስት ጥቂት የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን መልሶ ሌሎቹን መሰረታዊ የፖለቲካና የሲቪል መብቶችን የሚጨፈልቅን መሪ ‹‹Benevolent Dictator›› (ደግ አምባገነን) ሲሉ ይጠሩታል፡፡
ከዚህ ባለፈም የካውንስሉ አባል የሆኑት ሜጀር ጄኔራል መሀመድ ሰዒድ አል-አሰር ባለፈው ሳምንት ለታተመው ‹‹Time›› መጽሔት እሳቸውና ጓደኞቻቸው ለአብዮቱ ስላደረጉት አስተዋጾ ሲናገሩ “We have done the best we can for our country. We saved the revolution” (ለሀገራችን የቻልነውን ያህል የተሻለ አድርገናል። አብዮቱንም ታድገነዋል) ምንአልባት ይሄ ገፅ ከነታንታዊ በአማርኛ ቢገነጠል ሀገር ሊታደግ ይችል ይሆናል፡፡

Wednesday, 11 July 2012

የእለተ ረቡዕ ማስታወሻ

ዳዊት ዋስይሁን

ይህን ዜና ወዳጄ የላከኝ መልእክት ነው እኔ ለአንባብያን እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ !!

·        እለቱ ረቡዕ ከጠዋቱ  3፡30

የህዝበ ሙስሊሙ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እና ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ዘነበወርቅ አካባቢ በሚገኘዉ ፖሊስ ጣቢያ ተይዘዉ መወሰዳቸዉተሰማ:: ዘነበወርቅ አካባቢ መኪናቸዉን ካስቆሙዋቸዉ ቡሀላ ሁለታችሁንም ስለምንፈልጋችሁ ተብለዉ 2 ቁጥር ፒካፕ መኪና ጭነዎቸዉ የወሰዱዋቸዉ ሲሆን እስካሁን ድረስ የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ተገልጿል ::ሙስሊሙ ለምን እንደታሰሩ እስኪጣራ ድረስ በተለመደዉ ትዕግስ እንድንጠባበቅ እናሳስባለን!!!

እንዲሁም ከወደ ደሴ ደግሞ ሼህ መከተ ሙሄ በደሴ ከተማ ከሆቴላቸው ሳሉ ታፍነው ተወሰደው የት እንዳሉ አየይታወቅም !!!

አጭር ማሳሰቢያ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ከመቅስፈት በስፋት የተሰራጨ መልእክት!!



የህዝበ ሙስሊሙ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እና ኡስታዝ አህመዲን ጀበል የእገታ ድራማ በታጋቾች ሲገለጥ

አልሀምዱሊላህ በሰላም ተፈተናል፡፡ ዛሬ ጠዋት 3፡30 ላይ ከሰፈር ከአቡበከር ጋር ሆነን ወደ ኮሚቴው ስብሰባ ስንሄድ ከወይራ ወደ ዘነበወርቅ ሰፈር ልንደርስ ስንቃረብ መንገድ ላይ ፒክአፕ መኪና መንገድ ዘጋችብን፡፡ ዘለው 4 ሰዎች ወረዱ፡፡የመኪናውን በር ለመክፈት ተጣጣሩ፡፡ የሲቪል ልብስ ስለለበሱ ማናችሁ? መታወቂያችሁን አሳዩን ብንል ቆጣ ብለው አሳዩ፡፡ ሁለቱ የፖሊስ መታወቂያ ይዘዋል፡፡ ከፍተን ወረድን፡፡ የአቡበከርን መኪናውን ኮልፌ ቀራንዮ ፖሊስ ጽ/ቤት በራፍ ላይ አቆምዋት፡፡ ፖሊሶቹ እኛን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ 4 ሰዓት ላይ ደረሰን፡፡ ተፈተሽን ሞባይል፣ ላፕቶፕ፣ ብር፣ዶኩሜንት፣ ቁልፍ፣ ፍላሽ ዲስክ፣ ቀበቶ፣ ማንኛውንም ወረቀት ወስደውብን መዝግበውን ወደ እስርቤት አስገቡን፡፡ ለየብቻ ባዶ ክፍል (5 ሜትር በ5 ሜትር፣ ቁመቱ 4 ሜትር ይሆናል) ዉስጥ አስገቡን፡፡ ክፍሉ ባዶና ቀዝቃዛ ነው፡፡ በሩ ተዘጋብን፡፡ እንደገባሁ አዱሃ ሰገድኩና አንድ ስለ ለውጥ የምታወጋ መጽሐፍ አግኝቼ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ 40 ገጽ እንደደረስኩ አንድ ደህንነት(ሀላፊ ይመስላል) በ4 ፖሊስ ታጅቦ በሯን ከፍቶ ገባ፡፡ ማነህ? የት ተወለድክ? እድሜ? ወዘተ ጠየቀ፡፡ መጽሐፍ እያነበብኩ ነበርና ደግሞ ታነባለህ? መጽሐፉን ከየት አመጣህ? ሲል ጠየቀ፡፡ ከዚሁ አገኘሁ ብዬ ቀጠልኩ፡፡ ጥለው ወጡ፡፡ 7 ሰዓት ላይ ፖሊስ መጥቶ ቢሮ ይፈልጉሃል፡፡ ብሎ ፖሊስ ይዞኝ ሄደ፡፡ ፖሊሱ አስገብቶኝ ወጣ፡፡ ገብቼ ጠበቅሁ፡፡ ያ የቅድሙ ደህንነት እና ሌላ አጠር ያለ ደህንነት አብረው መጡ፡፡ ዳግም ትውልድህ የት ነው? ብለው ጠየቁ፡፡ ‹‹ጅማ ከተማ›› ስል መለስኩ፡፡የጅማውን ግጭት የት ሆነህ ነው ያስበጠበጥቀው? ሲሉ ጠየቁ፡፡ በንግግራቸው ሳቅሁ፡፡ ቆጣ ብለው ‹‹የብጥብጡ ጊዜ የት ነበርክ?›› ብለው ጠየቁኝ፡፡ ‹‹እዚሁ አዲስ አበባ››፡፡ የት ተማርክ? የት የት ሀገር ሄደሃል? ወዘተ ጠየቁ አከታትለው፡፡ ከዚያም ‹‹ስማ ከጸረ ሰላም ሃይሎች ጋር የምታደርገውን ሁሉንም እንቅስቃሴ መንግሥት ደርሶበታል፡፡ ዝም ሲልህ መንግስት የፈራህ እንዳይመስልህ፡፡ ከዘሬ ነገ ትታረም ይሆናል ብለን ታግሰን ጠብቀን ነበር፡፡›› ሲሉ ተናገሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ሳቅሁ፡፡ ተቆጡ፡፡ ‹‹እኛ ለስብሰባ አልያም እንድትናገር አይደለም፡፡ የመጨረሻ መስጠንቀቂያ ልንሰጥህ ነው፡፡ በየመስጊዱ በሰደቃ ሽፋን ሕዝቡን የምታነሳሳውን ታቆማለህ፡፡ ሕዝቡ ወክሎኛል ብለህ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ካላቆምክ ዋጋህን ታገኛለህ፡፡›› አሉ፡፡ ይህን ሁሉ ሲናገሩ እግሬን አነባብሬ ነበርና ተቆጡ፡፡ ‹‹እግርህን አውርድ›› አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ጣልቃ ገባሁና ‹‹መረጃ ካላችሁ ፍርድ ቤት ዉሰዱና ክስ መስርቱ፡፡ ምን ታስፈራራላችሁ? እንኳን ማስፈራት ለእምነታችን ሕይወት ለመስጠት ዝግጁ ነኝ፡፡ ማስራጃ ካላችሁ ያሻችሁን አድርጉ፡፡›› አልኩ፡፡ ለምን አልፈራም ብለው ነው መሰል ቆመው ቆጣ ብለው ‹‹ላንተ ፍርድ ቤት በመውሰድ ጊዜ አናባክንም፡፡ ዋጋህን እንሰጥሃለን፡፡ አንዲት ችግር ቢፈጠር የመጀመሪው ጥይት አንተ ላይ ነው የሚያርፈው፡፡ ትሰማ እንደሆን ስማ፡፡ መስጊድ እያደራጀህ ታስበጠብጣለህ፡፡›› ሲሉ ተናገሩ፡፡ ካዋጣችሁ ቀጥሉ-ስል ተናገርኩኝ፡፡ ‹‹መንግሥት አንተን ፈርቶ መሰለህ? አንተ ስለመጅሊስ ምርጫ ምን አገባህ? እንቅስቃሴህን አቁመህ እንደ ዜጋ አርፈህ የማትኖር ከሆነ የምናሳይህን እናሳይሃለን፡፡ ኮሚቴ ምናምን ትላለህ? ህገ ወጥ ናችሁ፡፡ ማን መረጣችሁ? ሕዝቡ መንግሥትን እንጂ እናንተን መች መረጠ? ታርፍ እንደሆን ይህ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ነው!›› ብለው ጨርሰናል፡፡ ዳግም ‹‹ካዋጣችሁ ቀጥሉ›› አልኩ፡፡ ፖሊሶቹን ‹‹ጠሩና እቃውን ስጡትና ይሂድ›› ብለው ወጡ፡፡ እቃዬን ተቀብዬ 7፡30 ላይ ከዚያ ወጣሁ፡፡ ስወጣ አቡበከር ቀድሞኝ ወጥቶ ነበርና ከዚያ ሄድን፡፡ እርሱም እንደኔ ተመሳሳይ ሁኔታ ዉስጥ እንደነበረ ነገረኝ፡፡ የሁለታችንም ሂደት ተመሳሳይ ነበር፡፡ የዋህ ሰዎች! ሕጋዊውንና ሕገ መንግሥዊውን የሕዝበ ሙስሊሙን የመብት ማስከበር ሂደት በተራ ማስፈራት ሊያቆሙ ይሻሉን ? አልሀምዱሊላህ በሰላም ወጣን!

ከወደ ደሴ የተሰማ ዜና፣

ቢስቲማ ላይ የሚካሄደው የአንድነትና የሰዶቃ ፕሮግራም  በመከላከያ ሰራዊት ተከቦ ፕሮግራሙ እየተካሄደ ሲሆን ስርአቱ ሲከናወን የሚያስተባብሩና የሚመሩ ወጣቶች ደግሞ በአካባቢው የደህንነት አካላት ልዩ ክትትል እየተደረገባቸው እንዳለ የአይንእማኞች ገልጸዋል ከታች የሚታየውም ፎቶ ይህንን ያረጋግጣል።


በዚህ ፕሮግራም ላይ ለመካፈል ከተለያየ ቦታ የሙስሊሙ ማህበረሰብ የተመመ ሲሆን የወያኔ ሰራዊትም ይህንን እንቅስቃሴ ለመግታት መንገድ በመዝጋት እንዲሁም ትራንስፖርት በማቋረጥ እንቅስቃሴውን ለማስተጓጎል ሙከራ አድርጓል ነገር ግን ማህብረሰቡ ልቡንና ጉልበቱን በማጠናከር ከአጎራባች አካባቢዎች ሁሉ በእግሩ እያቆራረጠ በመምጣት አይበገሬነቱን አሳይቷል ነገር ግን ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶች ለጥያቄ ተብለው የተወሰዱበት ቦታ እንደማይታወቅ የአይን እማኞች ገልጸዋል በማያያዝም ከቢስቲማ ሃይቅ ወደ ደሴ በመጓዝ ላይ የነበሩ ወጣቶች ሶስት ግዜ በመንገድ ላይ በወያኔ ሰራዊት ታስረው ከቀኑ 10 ከ 30 ከቢስቲማ ሃይቅ ተነስተው ደሴ ከምሽቱ 4 ሰአት 45 ደርሰዋል ይህ ሁሉ የሚከናወነው በፊት አውራሪነት በወያኔ ሰራዊት እየተመራ ነው እንደሆነ ታጋቾቹ ገልጸዋል።

የመለስ ቅዠትና የመጪው እሁድ ሐምሌ 8 ሱናሜ

በመጪው እሁድ ሐምሌ 8 ቀን 2004 ዓ.ም ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት እስከ አሥር ሰዓት ተኩል በአወሊያ መስኪድ ቅጥር ጊቢ በሚካሄደው ህዝባዊ አንድነትና የተቃውሞ ስብሰባ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ሙስሊም ማህበረሰቦችና ክርስቲያን ወንድምና እህቶች እንዲገኙ ጥሪው በሰፊው በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ እየተዳረሰ ሲሆን ይህንንም ታላቅ የአንድነት ስብሰባ ለማስተጓጎን  የኢህአዴግ ካድሬዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተደርሶበታል ፡፡

ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ላይ በግዳጅ የኢህአዴግ ካድሬ ስብስብ የሆነውን መጅሊስ እና የአህባሽን አስተምህሮ ለመጫን እየሞከሩነው ያሉን የኮሚቴ አባል የገጠሩ ማህበረሰብ በሃይማኖታችን መንግሥት ጣልቃ አይግባብን የሚለውን ተቃውሞ እንዳይቀላቀል መንገድ በመዝጋት፣ የመጓጓዣ መኪኖችን በማገት ሊያደናቅፍ ቢሞክርም ሰው በጋማ ከብትና በእግሩ እየተጓዘ በያካባቢው የሚደረገውን የአንድነት ስብሰባ እንዲሳተፍ ጥሪ ተደረጓል፡፡

የህዝበ ሙስሊሙ ኮሚቴ ከታሰሩ ምን መደረግ እንዳለበት የሚገልጽ በማን እንደተዘጋጀ የማይታወቅ መመሪያ በማህበረሰቡ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራጨ ሲሆን ይዘቱም እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡

1.       ሰላማዊ ትግላችንን ያለምንም መደናበር መቀጠል
2.        ኮሚተዎች የሚደርስባቸውን ማስፈራራትና ዛቻ በመረጃ ለህዝቡና ሚዲያዎች ማሳወቅ
3.       ተተኪ አመራሮችን ማዘጋጀት
4.        ለዓለም ዓቀፍ የሰላማዊ መብት ድርጅቶች እየተካሄደ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ማሳወቅ (ህጋዊ ትግላችን አለማቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ )
5.        ከታሰሩብን _አላህ አያድርገውና_ በህብረት ረብሻ ሳንፈጥር ወደ ታሰሩበት ቦታ ሄዶ መሰብሰብና የጉዳዩን ግዝፈት ማንጸባረቅ
6.        እነዚህ እንቅስቃሴዎች አዲስ አበባ ሳይገደቡ በሁሉም ክፍለ ሃገራቶች ማንኛውንም መንገድ ተጠቅሞ የሰላማዊውን ትግል ማጠናከር
7.        በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ላይ እየሰሩ ያሉ ሙስሊሞችና ፍትህ ወዳድ የሆኑ ክርስትያን ወገኖቻችን አድማ መምታት
8.        በመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም በዩንቨርሲቲ ተማሪዎ አድማ ማድረግ
9.        ዲያስፖራ ያሉትም ሰላማዊ ሰልፎችንና የተቃውሞ ደብዳቤዎች መላክ
10.   በፓልቶክ እየተደረገ ያለው ፕሮግራም ሙሉ በሙሉ ወደ ሶሊዳሪቲነት መቀየር
11.   በመጨረሻም ተውበት በማድረግ ወደ አላህ ተጸተን መመለስና ወደሱ ማልቀስ ማልቀስ

ድል ያለመስዋእትነት እንደማይገኝ ስለምናውቅ 34 ሚልየን ሙስሊም በቂ የሆነ እስር ቤት ካለ ካሁኑ አዘጋጁልን። ልትገሉንም ከሆነ 34 ሚልየን ጥይት አዘጋጁ ነጣጥሎ መምታት የማይገኝ የተስፋ ዳቦ መሆኑን ተረድታችሁ መብታችንን ነጻነታችንን ሳይሸራረፍ መልሱልን
ወላሂ ወላሂ ወላሂ ቃላችን ነው የምንለው ከኮሚቴዎቻችን ጋራ አብረን እንቀበራለን ወይ አብረን ታችንን እናስከብራለን !!
ጁላይ 11፣ 2012
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

የፍትህ ዋና አዘጋጅ ደኅንነት አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል

ሐምሌ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በሳምንታዊው ፍትህ የአማርኛ ጋዜጣና በዋና አዘጋጁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የግል እንቅስቃሴ ላይ የደህንነት ኃይሎች የሁለት ቀናት የሃያ አራት ሰዓታት ግልጽ ክትትል ማድረጋቸውን ለጋዜጠኛው ቅርበት ያላቸው ምንጮች አስታወቁ፡፡
በጋዜጣው የኢሜል አድራሻም ከአልሸባብ ለዋና አዘጋጁ የተላከ የሚያስመስል ቁጥር 2 የፈጠራ ደብዳቤ ከሰሞኑ ተልኳል፡፡
ቅዳሜ ሰኔ 30 ቀን እና እሁድ ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም ጋዜጠኛ ተመስጌን ራሳቸውን በግልጽ ባቀረቡ የደህንነት ሰዎች ሙሉ ክትትል ሥር የዋለ ሲሆን ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት ዙሪያ፣ በመመገቢያ ሥፍራው፣ በቢሮው አቅራቢያ፣ በቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት ዙሪያ እና በሚንቀሳቀስበት ሁሉ እየተፈራረቁ በመከታተል አእምሮው እረፍት እንዲያጣና እንዲጨናነቅ ጫና ለመፍጠር ሞከራውል በማለት ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡
መንግሥታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣም በፍትህ ጋዜጣ እና በጋዜጣው ዓምደኞች ላይ የመወንጀያ፣ የማስፈራሪያ እና የማሸማቀቂያ ጽሑፎችን ማስነበቡን ቀጥሏል፡፡
ቅዳሜ ከጠዋቱ 3፡30 ሰዓት ላይ ጋዜጠኛ ተመስጌን ደሳለኝ ከመኖሪያ ቤቱ ሲወጣ የክትትል ቀለበት ውስጥ የከተቱት ወጣት የደህንነት ኃይሎች ሙሉ ቀኑን እንደሚከታተሉት እንዲያውቅ በማድረግ ሲከታተሉት የዋሉ ሲሆን አመሻሽ ላይ ወደ ቤቱ የሚሄድ በመምሰል በአቅራቢያው በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ቤርጎ ይዞ ለማደር ተገዷል።
ጠዋት ሲወጣ ግን ከአደረበት ሆቴል በር ፊት ለፊት ጠብቀው ልክ ከወራት በፊት የፍትህ ባልደረቦችን ሲያስጨንቁበት ወደ ነበረው ግልጽ የክትትል መረብ ሥር ከተውታል ብለውናል፡፡
ወደ ጋዜጣው የኢሜል አድራሻ የተላከው የፈጠራ መወንጀያ ከአልሸባብ ለዋና አዘጋጁ የተላከ የሚያስመስል ቁጥር 2 የፈጠራ ደብዳቤ ሲሆን የመልዕክቱ አዝማሚያ በኢህአዴግ መንግሥት አሸባሪው ተብለው የተፈረጁት አልሽባብ፣ ግንቦት 7 ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የኤርትራውን መንግሥት የሚመራው ሻቢያ በጋራ እንደሚሰሩ እና የፕሮፓጋንዳ ሥራቸውንም በፍትህ ጋዜጣ በክፍያ እንደሚስተናገዱ በማስመሰል የቀረበ ነው ያሉን ምንጫችን የላኪው ሥም ኮሎኔል ተወልደ ሃብቴ ነጋሽ የሚል ነው ብለዋል፡፡
ይህ ደብዳቤ ከቀድሞው የሚለየው ላኪው የሰሜን ኢትዮጵያና የኤርትራ ሰው ሥም የያዘ እና ከግንቦት 7 እና ከሻቢያ ጋር አያይዞ ፍትህ ጋዜጣን እና ዋና አዘጋጁን ለመወንጀል የተዘጋጀ ወጥመድ ነው ያሉን የፍትህ ምንጮች፣ ቋንቋውም ከቀድሞው የተሻለ እና የቀድሞዎቹን የአመክንዮ መጣረሶች ለማስተካከል የሞከረ ነው ብለዋል።
ኢህአዴግ የኢሳት ጋዜጠኞችን አሸባሪ ብሎ ስለከሰሰ ዋና አዘጋጁ ቀደም ሲል ከኢሳት ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ሁሉ እንደመወንጀያ ሊጠቀሙበት ያሰቡ ይመስላሉ ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “የመለስ አምልኮ” መጽሐፍ ሦስተኛ ህትመት በመጠናቀቁ አራተኛው ህትመት በመታተም ላይ መሆኑን አሳታሚው ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
ይህን መጽሐፍ ሲያትም የነበረው የግል ማተሚያ ቤት በመንግሥት የደህንነት ኃይሎችና በፌዴራል ፖሊስ ማስጨነቅና ውክቢያ የደረሰበት ሲሆን ለማተሚያ ቤቱ ባለቤትም መንግሥት አካባቢውን ለልማት ስለሚፈልገው ማተሚያ ቤቱ በቅርቡ ሊፈርስ እንደሚችል በመግለጽ አስፈራርተዋቸዋል። ይህን መጽሐፍና መሰል ሥረታዎችን እንዳያትሙም እንደነገሯቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በዚህ የተነሳም የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የመለስ አምልኮ መጽሐፍ አራተኛ ህትመት በሌላ የግል ማተሚያ ቤት በመታተም ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለአስቸኳይ ልዩ ስብሰባ የተጠራው ፓርላማ የቴሌን ህግ አጸደቀ

ሐምሌ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-99 ነጥብ ስድስት በመቶ በአንድ ድርጅት አባላት የተሞላው ፓርላማ ለአስቸኳይ ልዩ ጉባኤ የተጠራው አዲሱንና አወዛጋቢውን የቴሌ ህግ ለማጽደቅ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል።
ዘጋቢያችን እንዳለው በጥሪው ላይ አስቸኳይና ልዩ የተባለው ፓርላማው ካለፈው ሰኔ ሰላሳ ቀን ጀምሮ እንደተዘጋ በመቆጠሩ ነው። የፓርላማ አባላቱ ፓርላማው እንደተዘጋ የማያውቁ ሲሆን፣ የዛሬው ልዩ ስብሰባ የተጠራው የፓርላማ አባላቱ እረፍት ላይ በሚሆኑበት ጊዜ አፈ ጉባኤው አስኳይ ስብሰባ መጥራት እንደሚችሉ ህጉ ይፈቅድላቸዋል በሚል ምክንያት ነው።
እስከ ዛሬ ድረስ በነበረው የፓርላማ አሰራር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሚቀጥለው አመት በጀት ላይ ጥያቄ ቀርቦላቸው መልስ ከሰጡ በሁዋላ ፓርላማው ለእረፍት ይዘጋል። ይህ አሰራር ላለፉት 18 አመታት የነበረ ሲሆን በዚህ አመት ግን የበጀት ዝርዝሩ ሳይጸድቅ ፣ አቶ መለስም በበጀቱ ላይ አስተያየት ሳይሰጡ እንዲሁም አፈ ጉባኤው ፓርላማው መዘጋቱን ሳያሳውቁ ፓርላማው ተዘግቷል ተብሎአል።
ሰንደቅ ጋዜጣ ፓርላማው ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓም ለምን እንዳልተዘጋ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑትን ወ/ሮ አሰፉ ገ/አምላክን የጠየቀ ሲሆን ፣ ሃላፊዋም ፓርላማው ሰኔ 30 መዘጋቱን በማረጋጋጥ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 58 ንኡስ አንቀጽ 4 ላይ ምክር ቤቱ በእረፍት ላይ በሚሆንበት ወቅት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ስብሰባ ሊጠራ እንደሚችል ስለሚገልፅ በዚሁ መሠረት ቀጣይ ስብሰባዎች እንደሚካሄዱ ገልፀዋል። ቀኑ ለጊዜው ባይታወቅም የ2005ቱ በጀትም ከሰሞኑ ይፀድቃል ብለዋል።
ጋዜጣው ለዶ/ር መረራ ጉዲና እና ለብቸኛው የፓርላማ ተመራጭ አቶ ግርማ ሰይፉ ጥያቄ አቅርቦላቸው ሁለቱም ላቀረበላቸው ጥያቄ በሕገ-መንግስቱ መሠረት ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም መዘጋት ሲገባው መቀጠሉ አነጋጋሪ እና ከተለመደው የፓርላማው አሰራር ውጪ ነው ብለዋል። አቶ ግርማ ያልፀደቁ አዋጆች ስላሉ ፓርላማው እንደሚቀጥል እንደተነገራቸው ገልፀዋል።
ለፓርላማው መዘጋትና ለ2005ቱ በጀት በጊዜ አለመፅደቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት በምክንያትነት ስለመነሳቱ በተመለከተ ዶ/ር መረራ ጉዲና ፤ “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት በከተማው የመንገድ ወሬ ሆኗል፤ ባለፈው ጊዜ በቴሌቪዥን ባየሁዋቸው ጊዜ ፊታቸው የተለወጠ ይመስላል” ሲሉ ለጋዜጣው ገልጠዋል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ የስልጣን ክፍፍል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከገባ ቆይቷል” የሚሉት ዶ/ር መረራ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አለመመቻቸት የመንግስት ስራ መስተጓጎሉ በኢህአዴግ ውስጥ የቡድን አመራር አለመኖሩን ያሳያል ሲሉም አክለዋል።
በዛሬው ስብሰባ እንደ ስካይፒ፣ጎግልቶክ ያሉ የኢንተርኔት አገልግሎቶች ለንግድ እንዳይውሉ የሚደነግገው የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅ ጸድቋል፡፡
አዋጁን ዝርዝር ተመልክቶ ፣የሚመለከታቸውን ወገኖች አወያይቶ የውሳኔ ኀሳብ ይዘው እንዲቀርቡ ረቂቁ የተመራላቸው ሁለት ኮሚቴዎች ባቀረቡት የውሳኔ ኀሳብ አከራካሪ ለነበረው ጉዳይ መጠነኛ ምላሸ አሰገኝተዋል፡፡
ኢንተርኔትን በመጠቀም የድምጽና የፋክስ መልዕክትን ማስተላለፍ ማለትም ስካይፒና ጎግል ቶክን የመሳሰሉትን እና በድምጽ የኢንተርኔት መግባቢያዎች ይከለክል የነበረው በሥራ ላይ የነበረው አዋጅ ቁጥር 281/1994 እንደነበር፤ ይህ አዲሱ አዋጅ ግን ይህንን በመሻር የኦፕሬተር አገልግሎት በሕገወጥ መንገድ ከሚሰጡ በስተቀር ማንኛውም ዜጋ መጠቀም እንዲችሉ ፈቅዶአል ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረት የተከለከለው የቴሌኮም አገልግሎትን በመጠቀም ሌሎችን በማስደወል መንገድ መሆኑን፣ዜጎች ግን በቤታቸው፣በሥራ ቦታቸው አገልግሎቶቹን በግል እንዳይጠቀሙ እንደማይከለክል ግልጽ አድርገዋል፡፡
የመድረከ ተወካይ አቶ ግርም ሰይፉ አዋጁ የቴሌን ሞኖፖሊ በማጠናከር ዜጎች ምንም አማራጭ እንዳይኖራቸው ለማድረግ የታለመ መሆኑን በመጥቀስ የአዋጁን መጽደቅ ተቃውመዋል፡፡

አቶ ጁነዲን ሳዶ ስለ ኮብል ስቶን ያደረጉት ንግግር ተቃውሞ ገጠመው

Wednesday, 11 July 2012 09:45 
የቀድሞው ድምቀቱና ውበቱ በተለየው የዘንድሮ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ በንግግራቸው ስለ ኮብል ስቶን በማንሳታቸው ከፍተኛ የተቃውሞ ጩኸት ገጠማቸው፡፡ አቶ ጁነዲን ባለፈው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግራቸውን ሲጀምሩ በአድናቆት ጭብጨባና በፉጨት ቢታጀቡም፣ ድንገት የንግግራቸውን አቅጣጫ ወደ ኮብል ስቶን በማዞራቸው ነበር ሳይታሰብ ከፍተኛ የተቃውሞ ጩኸት፣ ጉርምርምታና ፉጨት ከተመራቂዎቹ የተሰማው፡፡ ይኼው የተማሪዎች ተቃውሞ አይሎ ቢቀጥልም ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ከመቀጠል አልተገቱም፡፡

ሚኒስትሩ ‹‹ኮብል ስቶን›› የሚለውን ቃል ገና መናገር ሲጀምሩ ተመራቂዎቹ ከአፋቸው ተቀብለው በተቃውሞ እንዲጮኹ ምክንያት የሆናቸው፣ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀረበው የአንድ ባለዲግሪ ወጣት በኮብል ስቶን መሰማራቱን ስላስታወሳቸው እንደሆነ ነው ተመራቂዎቹ የተናገሩት፡፡

ተማሪዎች ስለሚገጥሙዋቸው ችግሮችና በትምህርት ቤት ቆይታ ስለሚታየው ከባድ ሕይወት እያዋዙ በመናገራቸው የሙገሳ ፉጨት ሲቀርብላቸው የነበሩት ሚኒስትር ጁነዲን፣ ንግግራቸውን በተቃውሞ ጩኸት ለማስቆም ተመራቂዎች ያደረጉት ጥረት አልተሳካም፡፡ ተመራቂዎቹ በተቃውሞ እየጮኹ ሊያዳምጡዋቸው በማይችሉበት ሁኔታ እሳቸው ንግግራቸውን ጨርሰው ከመድረክ ወርደዋል፡፡

‹‹ያለቦታውና ያለጊዜው ያደረጉት ንግግር ነው፤›› በማለት በርካታ ተማሪዎች የሚኒስትሩን ንግግር የተቹ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ባለፈው ቅዳሜ ረፋዱ ላይ በማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተናገሩት መሆኑም የተመራቂዎቹን ቅሬታ በእጅጉ እንዳባባሰው ገልጸዋል፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ በኮብል ስቶን ትምህርት ላልሠለጠኑ ተመራቂዎች የኮብል ስቶን ጉዳይን ማንሳት አይገባም ነበር ያሉት ተመራቂዎቹ፣ እሳቸውም ቢሆኑ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴርን የሚመሩ ባለሥልጣን ሆነው፣ ዘርፉም ሆነ የግንባታ ጉዳይ ለማይመለከታቸው ተመራቂዎች ስለ ኮብል ስቶን ማንሳታቸው፣ ለተቃውሞው መነሻ ሰበብ መሆኑን ተመራቂዎቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ሳይጠናቀቅ በርካቶች የስድስት ኪሎ ካምፓስን የልደት አዳራሽ ጥለው ወጥተዋል፡፡ በወቅቱ ተመራቂዎቹ ያሰሙት የነበረውን ጩኸትና ፉጨት ያዳመጡ አንዳንድ መንገደኞች ያልተለመደ ስለሆነባቸው፣ ‹‹የዘንድሮ ተማሪዎች በፉጨት ሆነ እንዴ የሚመረቁት?›› በማለት እንዲቀልዱ አድርጓቸዋል፡፡

Tuesday, 10 July 2012

በኢህአዴግ ውስጥ የጐላ ልዩነት እየተፈጠረ ነው

ስድስት ወራት በላይ የስቆጠረውን ሀገር አቀፍ የሙስሊሞች ተቃውሞና ከዋልድባ ገዳምና የስኳር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ በኢህአዴግ ውስጥ የጐላ ልዩነት እየተፈጠረ መምጣቱን ቅርበት ያላቸው ምንጮች አመለከቱ፡፡ ለገዢው አብዮታዊ ግንባር ኢህአዴግ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን እንዳመለከቱት ኢህአዴግ ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ፓርቲው ከፍተኛ ባለስልጣናቱን በሀይማኖት ዙሪያ በተደጋጋሚ በማወያየት ላይ ይገኛል፡፡ ምንጮቻችን አንድ ተወያይን ጠቅሰው እንደዘገቡት በውይይቱም ሆነ በመወያያ ሰነዱ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት የሰፈረው ነጥብ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አለመግባቱን ተሳታፊዎቹ በቀና ልቡና እንዲረዱ የሚያግባባና የሚማፀን ነው፡፡ውይይቶቹ አስፈላጊ የሆኑት ከዝቅተኛ የፓርቲ አደረጃጀትና መዋቅር ጀምሮ ያሉ አባላት መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ገብቷልየሚል አቋም በመውሰዳቸው ነው፡፡የሚሉት ተሳታፊው ፓርቲው ውይይቱም በተለያዩ ደረጃዎች ማካሄዱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ እንደ ምንጮቻችን ማብራሪያ እነዚህ አይነት ውይይቶች በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ሲሆን ከተወሰኑ የተቃውሞ አስተያየቶች ውጪ አወያዮቹም ሆነ ተሳታፊዎች አንድ አይነት ቋንቋ ተነጋግረው የመውጣት አዝማሚያ አሳይተዋል ፡ ተነጣጥለው ሲወያዩ ግን በሙስሊሞች የወቅቱ ጥያቄና በዋልድባ ገዳም መደፈር ጉዳይ ላይ መንግስት እየተከተለ ያለውን አቋም አምርረው የሚተቹ አባላት መበራከታቸው በፓርቲው ውስጥ የጐላ ልዩነት በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ ምንጮቻችን አመልክተዋል፡፡