ይህ ፎቶግራፍ የተወሰደው “የበፍቄ አለም” ከተባለው ከወዳጃችን በፍቃዱ ብሎግ ነው። ፍቄ ምስጋናህን እንካ…!
ታድያስ አቶ መለስ ዛሬ እንኳ ልፅፍልዎ አላሰብኩም ነበር። አንድ የሚያበሳጭ ዜና አንብቤ እርሱን ልነግርዎ፣ እግረ መንገዴንም እግዜር ይማርዎ ልበልዎ ብዬ ነው፤
ሰሞኑን ባለፈው በምርጫ ዘጠና ሰባት ግዜ የታየብዎ አይነት ህመም ድጋሚ አገርሽቶብዎ ቤልጄም ብራሰልስ ሊታከሙ እንደሄዱ ሰማሁ። በልቤም እግዜር ይማራቸው ስል አሰብኩ። ነገር ግን በአገሬ መሬት በእርስዎ ቆራጥ አመራር እና በድርጅታችን ፈፃሚነት የሚከናወነውን ነገር ሳይ፤ እግዜር ይማራቸው ማለቴን እግዜሩ ቢሰማ “ተው… በስራዬ አትግባብኝ” ብሎ የሚገስፀኝ መሰለኝ! እንዴት ካሉኝ ለዚህ የሚሆን አንድ ማሳያ ከወደ ስር አቀርባለሁ። ከቸኮሉም ሌላውን ዘለው የመጨረሻውን አንቀፅ ማንበብ ይችላሉ። (ግን የት ይሄዳሉ… ለራስዎ በእግዜር እጅ ተይዘው!)
የህመምዎ ነገር ድሮም የተፈራ ነው። እንኳንስ በአበበ ገላው ላይ ያደረው መንፈስ እንደዛ ቀልቦን ገፎት ይቅርና እንዲሁም በየ ግምገማው በሚደረግ እሰጣ ገባ በተለይ ህውሃት ለሁለት ከመሰንጠቋ በፊት በነበሩት ከበድ ከበድ ያሉ ግምገማዎች እነ አቶ ስዬ እና አቶ ገብሩ እንዲሁም ሌሎች ዛሬ ከድርጅቱ የወጡ ግለሰቦች በሚያደርሱብዎ ግምገማ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ነፍስዎን ስተው ነበር እየተባለ ሲወራ ሰምቻለሁ። በርግጥ እውነት መሆኑን ምሎ ያረጋገጠልኝ ባይኖርም “እሳት ሳይኖር ጭስ አይፈጠርም” በሚለው አባባል መሰረት ነገሩ እውነት ሊሆን እንደሚችል ጠርጥሪያለሁ።
ያኔ በዘጠና ሰባቱም ምርጫም አቶ በረከት ስምዖንን ጨምሮ በርካታ አመራሮች ለአደገኛ የእራስ መቃወስ ህመም ተዳርጋችሁ እንደነበር ውስጥ አዋቂዎች ተናገረዋል። እንደውም የዛን ጊዜ ሁሉም በየጎጆው “አነዚህ ሰዎች አመራራቸው የተቃወሰው ለካስ ወደው አይደለም” ብሎ ከንፈሩን መጧል። የአቶ በረከትን በሚመለከት በቅርቡ መፅሀፋቸው የተመረቀ ጊዜ ሼክ ማህመድ አላሙዲን “እያንጠለጠልኩ ወስጄ አሳክመው ነበር” ብለው ነግረውናል። እንግዲህ የእርስዎ መፅሀፍ ደግሞ ሲታተም ማን እያንጠለጠለ ወስዶ ሲያሳክምዎ እንደነበር እንሰማ ይሆናል።
እኔ የምልዎ የአቶ በረከት ስምዖንን መፅሀፍ አይተው እርማት እንደሰጡ ሲነገር ሰምቼ ነበር… እውነት እርሶ አይተውት ነው ያሁሉ የሚያስተዛዝብ ነገር የተገኘበት…? እውነትም ሁላችሁም ታማችኋል ማለት ነው። እና እግዜር ይማራችሁ ብዬ እመርቃለሁ…! ግን አይመስለኝም። ለምን አይመስለኝም…?
ለምሳሌ ዛሬ እንዴት ያለ ኮሚክ ዜና ሰማሁኝ መሰልዎ…! “ዘ ዲክታተርስ” የሚለው የፈረንጅ ፊንም በኢትዮጵያ ሲኒማ ቤቶች እንዳይታይ ታገደ የሚል።
እውነቴን ነው የምልዎ ይሄ በጣም አሳዛኝ ዜና ነው።
ወይ ካድሬዎችዎ መንግስታችንን በጣም እያስፎገሩት ነው። ወይም ደግሞ እርስዎ ራስዎ ለይቶልዎታል።  እስቲ አሁን “ዘ ዲክታተር” ፊልምን ማገድ ማለት ምን ማለት ነው? እርግጥ ነው ሌላ ሰው ፊልሙን ከእርስዎ እና ከመንግስታችን ጋር ማመሳሰል ከጀመረ ቆይቷል። ነገር ግን እራሳችን በራሳችን “ፊልሙ እኛን የሚነካ ነው” ብለን ማገዳችን በእውነቱ ምህረት የማያሰጥ ወንጀል ነው። እንዲህ ስልዎ ለፊልም ተመልካቹ ተቆርቁሬ አይደለም። ከፈለጉ ልማልልዎ! ለድርጅታችን ተጨንቄ ነው። ይህ ፊልም እንዲታገድ ሲደረግ ትዕዛዝ ያስተላለፈው ግለሰብ “ድርጅታችንን እና እርስዎ መሪያችንን ሙልጭ አድርጎ ሰድቧል በድሏልም።” ብዬ ልናገር ነበር፤ ነገር ግን በአገሪቷ ካለ እርስዎ ቀጭን ትዕዛዝ የሚከናወን ነገር እንደሌለ ትዝ ሲለኝ እንደሚከተለው አሰብኩ፤
የተሰዉ ታጋዮች “አምባገነንነትን ለማጥፋት ነው የተሰዉት!” እያልን ለበርካቶች እንዳላስተማርን ዛሬ “ይህ ፊልም እኛን ይመለከታል” በሚል ስናግድ ራሳችንን በራሳችን “አምባ ገነነን ነን!” ብሎ የማወጅ ያህል ነው።  እኔ ግን የምልዎ እሺ ድርጅቷን ተዋት፣ ታጋዮቹንም እርሷቸው ግን የተሰዉ ታጋዮች አምላክ፤ የላይኛው እግዜር  ያን ሁሉ መስዋትነት ውሃ ሲያስበሉት አይቶ ምህረት የሚያደርግልዎ ይመስልዎታል…? እኔ ግን አይመስለኝም። ለማንኛውም እግዜር ይማርዎ!