Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Saturday, 7 July 2012

መንግስት የጠላው ህዝብ

ከዳዊት ዋስይሁን, ጁላይ 02\2012

ይህ የምትመለከቱት ፎቶ እየጸለዩ ለመሆኑ ምንም ማብራሪያ አያስፈልገውም፣ ታዩታላችሁና ነው፣ ነገሩ ግን እየጸለዩ ያለው የእምነት ተቋም ውስጥ ነው ብላችሁ እንዳትደመድሙ፣ ወይም የተመቻቸ ቦታ ላይ ሆነውም አይደለም፣ አንድ አይነት እምነትም የላቸውም፣ ክርስቲያን ሙስሊም ሌላም ሌላም ሆነው ነው የሚታዩት፣ ጸሉታቸውን የሚመራ የሃይማኖትም አባት የላቸውም ሁሉም ባንድነት ሆኖ ያነባል፣ ይቃትታል፣ ያለቅሳል ወደፈጣሪ።

እነኝህ ከሞት መንጋጋ የተረፉ ኢትዮጵያውያን ለነሱና ከጎናቸው ስለተለዩአቸው 43 ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ያለቅሳሉ ለኢትዮጵያም መከራና ስቃይ ኡኡኡ ይላሉ ቀይ መስቀል ለጊዜው እንዲጠለሉበት ከሰጣቸው አዳራሽ ውስጥ ሆነው!!!!!!

በአለፈው ወራቶች ውስጥ ከሰማናቸው አስከፊ የወገኖቻችን ሰቆቃዎች መሃል

·        በሰኔ 20፣ 2012, 60 ኢትዮጵያውያን በሌክ ማላዊ ውስጥ ሰምጠው መሞታቸው፣

·        ንጹኃን እህቶቻችን በመካከለኛው ምስራቅ ለአስከፊ እንግልትና ውርደት መጋለጣቸው፣

·        1700 በላይ የሚሆኑ የአገራችን ዜጎች በሳውዲ አረቢያ እስር ቤት በመማቀቅ ላይ መሆናቸው፣

·        43 ወገኖቻችን ወደታንዛኒያ በኮንቴይነር ተጭነው ሲጓዙ በአየር ማጣት ታፍነው በስቃይ ህይወታቸው ማለፉን፣

·        ይህ አልበቃ ብሎን ከ50000 በላይ እህቶቻችን አሁንም ለባርነት በመንግስት ይሁንታ ባለፈው ሁለት ወር ብቻ ወደ መካከለኛው ምስራቅ መላካቸው፣

ይህ እንግዲህ የታየውንና የተሰማውን በጥቂቱ ለመጥቀስ በማሰብ ብቻ ነው ጉዳዩ ግን ከምንገምተው በላይ ከመሆኑ የተነሳ ዛሬ ወገኖቻችን በየትኛውም የአለማችን ክፍል በተበተኑበት ቦታ ሁሉ የመጀመሪያው የስደት መከራ ቀማሽ እየሆኑ ይገኛሉ።

ዛሬ የአለም አቀፍ ድርጅቶች መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያውያን አገራቸውን እየለቀቁ በመሰደድ ግንባር ቀደም እየሆኑ መጥተዋል፣ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት በዛች አገር ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እድገትና ለውጥ ማስገንዘቡን ህዝቡ ከመብላት አልፎ ሃብት በሃብት መሆኑን በኢትዮጵያ የሚመረቱ ቁጥሮች ያሳዩናል።

የኢትዮጵያ መንግስት ቁጥርን በማምረት የሚወዳደረው የለም በሁሉም ዘርፍ ቁጥሩ ትልልቅ ነው እውነቱ ግን የተገላቢጦሽ ነው። ከሰሞኑ አንድ የወያኔ ጽንፈኛ አቀንቃኝ  ’’ለምን ቁጥር ይነግሩናል መለስ ዜናዊን አታለውታል ውነታው መርካቶ ሄዶ የጤፍና የቅቤ ዋጋ መጠየቅ ነው ለምን መለስ ወረድ ብሎ ዞር ዞር ብሎ አይጠይቅም’’ በማለት በተስፋ መቁረጥ ሲብከነከን ተስምቷል፣ እንግዲህ እውነቱን ራሳቸውም አልካዱት።

አንድ የሚጣረስ ነገር ይታየኛል ይህ ምናምን ፐርሰንት እየተባለ የሚነገረን ለማን ነው እድገቱ ለህዝቡ ከሆነስ፣ ለየትኛው? ለምንስ ይሰደዳል? ወይስ ለአቶ መለስ ቡድንና ኃገሪቷን እየተቆራመቷት ላሉ ህንዶች፣ ቻይናዎችና አረቦች። ህዝቡማ በየቦታው ከቀየው እየተፈናቀለ ጭሰኛ እና ስደተኛ እየሆነ በየደረሰበት ህይወቱን እያጣ ያለበት እውነታ ነው የሚታየው።

ለምን አቶ መለስ አንዴ ረጋና ሰከን ብለው አያስቡም የዛች አገር ችግሯ ከቀን ወደቀን እየከፋና ሁኔታዎች እየተወሳሰቡ እየሄዱ እንዳለ የፖለቲካ ተንታኝ መሆን አያስፈልግም እዚህም እዚያም የመመረርና የአመጽ ምልክቶች ሲታዩ በመደብደብ፣ በማሰር እንዲሁም በመግደል ለማፈን እየተሞከረ ነው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ በኦጋዴን በሌሎችም የየለት ክስተት ከሆኑ ሰንበትበት ብሏል፣ ግን እኮ ይህ ሕዝብ የማን ነው ለምንስ እንዲህ ሊጠላ ተፈለገ? ያላሰቡበትና ያልተዘጋጁበት አደጋ ግን ሁሉም በአንዴ በቃኝ ያለለት ውጤቱ የከፋ ይሆናል ለዚህም ነው ታላቁ መጽሃፍ ክፉ የሚባሉ ቀኖች ሳይመጡ ….. ይላል፣

አሁን አልመሸም አብዮቱ ጎረቤት አገሮችን እያንኳኳ ነው ሰለዚህ ህዝብ ይደመጥ፣ ይከበር እንዲሁም ይወደድ፣ በኢንቬስትመንት ስም ህዝብ አይፈናቀል፣ የትውልድ ቅርስ የሆነው የእምነት ቦታ አይነካ፣ የኃይማኖት ተቋማት ውስጥ የገቡ እጆች ይውጡ፣ በየስር ቤት የታጎሩ ንጹሃን ዜጎች ይፈቱ፣ እርሶም በቃዎት ስልጣን ይልቀቁና ለህዝብ ያስረክቡ፣ በመቀጠልም መጽሃፍዎን ያንብቡ ካለበለዛ ይህ እድልም ሊያመልጥዎ ይችላል ያስቡ ለዚህ ያልታደሉ አብዮቱ የበላቸው መሪዎች አሉና!!!

የሚገርመውና የሚያሳዝነው የተገለጠው እውነት የህዝቡ ድህነት፣ የመጎሳቆሉ መጠን እንዲሁም ነጻነት የማጣቱ ጉዳይ ሲሆን፣ ነገር ግን ሁሌ ተቃራኒው ይነገረዋል። ምንያህል እንደተንበሸበሸና እንደተትረፈረፈ፣ እንደፈለገ መሪዎቹን መምረጥ እንደሚችል፣ ኑሮው እንዴት እንደተቀየረ 24 ሰአት በኢቲቪ አላፊነት የጎደለው ፕሮፖጋንዳ ይጋታል ስለዚህ በኢትዮጵያ ቴሌቪዢን ያለችው የበለጸገችውንና የተነገረላትን ኢትዮጵያ ፍለጋ ይሰደዳል።

መንግስት እንደመንግስት ህዝቡን የመጠበቅና የማስተዳደር አላፊነት ተጥሎበታል በዚህ መስፈርት የአቶ መለስ መንግስት በተቋም ደረጃ የራሱን ህዝብ የሚጠላ፣ የሚዋሽ፣ የሚያስር፣ የሚገል እንዲሁም የሚያሰድድ ለመሆኑ ማጣቀሻ መስጠት አያስፈልግም ዜጎቹ በገፍ ሲሰደዱ ምክንያቱ አጥንቶ ለዜጎቹ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በመንግስት እቅድ ተይዞ ዜጎች አገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ይገፋፋል፣ ያበረታታል፣ ዜጎች በተሰደዱበት ቦታ መከራና ስቃይ ሲበዛባቸው ቀድሞ ከመድርስና መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ተጠያቂነቱን ወደስደተኛው ወርውሮ አላስፈላጊ ስም ሲሰጥ ይታያል፣ ዜጎች በየትም ቦታ አደጋ ቢደርስባቸው \ነፍስ ማጣትንም ያጠቃልላል\ የሚያስፈልገው መስዋእትነት ተከፍሎ ላገራቸው ምድር እንዲበቁ ሲደረግ አይታይም ይልቁንም የፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ ያደርጉታል፣ ታዲያ የአቶ መለስ መንግስት ለማን ነው የቆመው ወይስ ’’ሁሉም እኩል ናቸው እንዳንዶች ከእኩሎች በላይ ናቸው’’ ነው ጉዳዩ?። 

ጽሁፌን ሳጠናቅቅ በመላው አለም በግፍና በታላቅ ስቃይ ላይ ያሉ ስደተኛ ወገኖቼ የመጽናኛችንን ግዜ እግዚያብሄር አቅርቦ ሁላችንም በአገራችን የሰላም አየር የምንተነፍስበትን ግዜ በመመኝት ሲሆን በሌክ ማላዊ፣ በአረብ አገራት አንዲሁም በታንዛኒያ የተከበረ ህይወታቸውን ላጡ በገኖቼ የህሊና ጸሎት በማድረግ ጭምርም ነው።

በተለይ በታንዛኒያ ህይወታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ያለፈው 43 ወገኖቻችን የቀብር ስነስርአት ከሚናፍቋትና ከሚወዷት አገራቸው ውጪ፣ 22ቱ በሞርጎጎ ቀሪዎቹ በዶዶማ ተከናውኗል በስነስርአቱም ወቅት ከአደጋው የተረፉ ወገኖቻችን የመረረ ሃዘናቸውን በቁጭትና በለቅሶ ገልጸዋል፣ በዚህ በተጠቀሱ አደጋዎች ሁሉ የአቶ መለስ መንግስት ዜጎቹን ለመታደግም ሆነ አደጋው ከደረሰ በኋላ አስፈላጊውን እርዳታ ከማድረግና ፈጥኖ ከመድረስ ይልቅ እንዳልሰማና እንዳላየ የዜጎቹን ጉጋይ ከመጤፍ ሳይቆጥር ዝምታንና ማሰደድን ስራዬ ብሎ ይዞታል።



ጸሃፊውን ለመገናኘት፦zoloaba112@yahoo.com

Friday, 6 July 2012

የአእምሮ ክስረት፣ ሁሉም ነገር ሽብርተኛነት!

በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ በፓኪስታን፣ በየመን፣ በአንዳንድ የሰሜን-ምዕራብ የአፍሪካ አገሮች፣ አሁን በቅርቡ ደግሞ በናይጂርያ፣ አልፎ አልፎም በትልልቆቹ የምዕራባውያን አገሮች፣ አልፎ አልፎም በምሥራቅ አፍሪካ በአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ የደረሰው ዓይነት የሽብርተኛነት አደጋ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ላይ እስካሁን ድረስ አልደረሰም ለማለት ይቻላል፤ ሰላም በራቃት ሶማልያም እንኳን ከላይ በተጠቀሱት አገሮች ውስጥ የሚታየው ዓይነት ሽብርተኛነት የለም ለማለት ይቻላል፤ ጦርነትን ከሽብርተኝነት የማንለየው ከሆነ ግንዛቤያችን የተለየ ይሆናል፤ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ሶማልያውያን ቡድኖች የሚያሳዩት የባሕር-ላይ ሽብርተኛነት ፈጽሞ በባሕርዩ የተለየ ነው፤ ለዘረፋና ለገንዘብ መሰብሰቢያ እንጂ ሰዎችን ለመግደል ወይም ለመጉዳት አይመስልም።
ሽብርተኛነት ከዲያብሎስ ፋብሪካ የወጣ፣ የጠራ ክፋት ነው፤ በኢትዮጵያ ባሕርይ ውስጥ ፈጽሞ የለም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የስዒረ-መንግሥት ሙከራዎች ሁሉ የሚከሽፉት ይህ የጠራ ክፋት ስለሌለብን ነው፤ በእርግጥ ሻዕቢያና ወያኔ በሽብርተኛነት አልተጠቀሙም ለማለት አይቻልም፤ ግን እነሱም ቢሆኑ ኢትዮጵያዊ ባሕርያቸው ልጓም ሆኖባቸው የነበረ ይመስላልና በዓይነቱም ሆነ በመጠኑ በጣም አነስተኛ ነበር፤ ምናልባትም አሁን በአዋጅና በተለያዩ ማስፈራሪያዎች የሚሰማው ኡኡታና መሸበር ከራሳቸው ልምድ የተገኘ ይሆናል እንጂ ኢትዮጵያውያን የሽብርተኛነት ጥፋት ያደርሳሉ ተብሎ በመስጋት አይመስለኝም፤ ሽብርተኛነት የሚለፈፈው የፖለቲካ ትርፍ ይገኝበታል ተብሎ ከሆነ ከስሕተት ካለመማር የመነጨ መሆን አለበት።
በ1998 እነሽመልስ ከማል የዓቃቤ ሕጉን ወንበር በአቋራጭ ይዘውት በነበረ ጊዜ ክሱን ለማሳመር የወንጀል ዓይነት እንዳይቀርባቸው ብለው በመጀመሪያ በዘር ማጥፋት፣ ይህ መሳቂያ ሲሆንባቸው ደግሞ ወደዘር ማጥፋት ሙከራ ለውጠውት ነበር፤ በመጨረሻም ይህንኑ ክስ ሁለቱ ዳኞች ከውስጥ ባልወጣ መንፈሳዊ ወኔ ውድቅ አደረጉት፤ በአሁኑ ጊዜ የሽብርተኛነት ሕግና ዛቻ፣ ማስፈራሪያ ሁሉ ምንጩ ያው የዱሮው የወንጀል ፋብሪካ ሳይሆን አይቀርም፤ ማንም ጤናማ ኢትዮጵያዊ ምንም ያህል የፖለቲካ ጥላቻ ቢኖረውና የፖለቲካ ትግሉ የተዳፈነበት መስሎ ቢታየውም፣ ልጆቹ ከትምህርት ቤት ሲወጡ፣ ሚስቱ ከሥራዋ ወይም ከገበያ ስትመጣ፣ ቤተሰቡ በቤተ ክርስቲያን ወይም በቤተ መስጊድ ሄደው ፈጣሪያቸውን ሲማፀኑ በድንገት በቦምብ እንዲቃጠሉ ወይም በጥይት እንዲጠበሱ -- ማንም ጤናማ ኢትዮጵያዊ ይህንን አይመኝም።
ለፖሊቲካ ትርፍ ከሆነ የዘር ማጥፋት ወንጀል መለጠፉ በመጨረሻ አሳፋሪ እንደሆነ ሁሉ የሽብርተኛነት ወንጀልም ከአሁኑ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም- አቀፍ ደረጃም መሳቂያ እየሆነ ነው፤ በአገር ላይ፣ በማኅበረሰብ ላይ የሚቃጣ ወንጀል ሁላችንንም የሚያስቆጣን እንጂ የሚያስቀን ወይም ለፌዝ የሚጋብዘን ሊሆን አይገባም፤ ሽብርተኝነትን ሁላችንም አምርረን ስለምንጠላው ልናፌዝበት አይገባም፤ ነገር ግን አንዱ የኢትዮጵያዊ ባሕርይ የማይመስለው ነገር ከላይ ከባለሥልጣኖቹ ሲወረወርበት ማፌዝ ነው፤ በደርግ ዘመን ዜና ማሰራጫዎቹ ስለሻቢያና ስለወያኔ እስቲሰለች የሚያወሩት የማይጥመው ሁሉ ሻቢያና ወያኔ የሚሉትን ቃላት መቀለጃ አድርጎ ‹‹አንተ ሻቢያ… አንተ ወያኔ›› ይባባል ነበር፤ አሁንም ‹‹አንተ ሽብርተኛ›› መባባል እየተጀመረ ነው፤ እንዲህ ሲሆን ሽብርተኛነት የሁላችንም ፍርሃትና ስጋት መሆኑ ቀርቶ የነጌቶች ብቻ ይሆናል።
የማሰብ ችሎታ እንደቆመ የሚያመለክተው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ድርጅትም፣ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ድርጅትም፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ ጋዜጠኞችም፣ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖችም… ሁሉም በሽብርተኛነት እየተፈረጁ የሚከሰሱ ከሆነ የኢትዮጵያን ችግር ሁሉ አንድ ከረጢት ውስጥ በመክተት ለማቅለል መሞከሩ የችግሩን ውስብስብነትና ከባድነት አይለውጠውም፤ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ቡሽን የጡንቻ አስተሳሰብ ለመከተል ቢፈለግም ብዙ ነገሮች ይጎድሉናል!
ለተመስገን ከአል ሸባብ የተላከ አስመስሎ መልእክት የሚልክለት ምን ዓይነት አንጎል በአንገቱ ላይ የተሸከመ ነው? ለፍትሕ ጋዜጠኞችስ በተለያዩ መንገዶች ማስፈራሪያ የሚልከው ምን ያህል የማሰብ ችሎታው የተዳፈነበት ነው? ይህንን የሚፈጽሙት የሽብርተኛነት ጥንስሶች ናቸው።
ከዚህ በፊት ብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ነበሩ፤ ዛሬ የሉም፤ ግን ሌሎች ቦታቸውን ይዘው ሀሳባቸውን እያሰራጩ ናቸው፤ ገንዘብ እንደልባቸው እያገኙና የፈለጉትን ባለሙያ የመቅጠር ችሎታ እያላቸው፣ ማንኛውም ዓይነት የጋዜጠኛነት መሣሪያ በእጃቸው እያለ፣ የሕዝብ የመገናኛ ብዙኃኑን በሙሉ እየተቆጣጠሩ፣ የሌሎችን ጭልጭል የሚሉ ሀሳቦች በጉልበት ለማዳፈን የሚፈልጉ ወይም ፍርሃታቸው ከመጠን እያለፈ እንቅልፍ ነሥቶአቸዋል፤ ወይም ያልነበረ የአእምሮ ኃይላቸው እየተሟጠጠ አልቆ ጡንቻ ብቻ ሆኖባቸዋል፤ ስለዚህም ሀሳብን በሀሳብ ለመቋቋም አቅም የላቸውም፤ ለዚህ ተጨባጭ ማስረጃ የሚሆነው በብዙ የቴሌቪዥንና የራዲዮ ጣቢያዎች፣ በብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ከኢትዮጵያ አልፈው በእስያ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ሀሳብ ካላቸው በየቀኑ ማሰራጨት የሚችሉ አገልጋዮች አሉአቸው፤ ይህ ሁሉ የኢሕአዴግ ኃይል በአገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ በአጠቃላይ በሳምንት ከሃምሳ ሺህ የማይበልጥ ጋዜጣን በሀሳብ ማሸነፍ ሲያቅተውና በጡንቻው ወደመተማመኑ ሲመለስ ምን ሊባል ነው? ይህ ድካም የአእምሮ ድካም ብቻ አይደለም፤ ውሎ አድሮ የፖለቲካ ድካምም ይሆናል፤ የፖለቲካ ድካም በጊዜው ካልታረመ የውስጥ ችግሮችን መፈለፈሉ ብቻ ሳይሆን ወደውጭም እንደሚዛመት መረዳት አለብን፤ ዛሬ በአእምሮ ስንፍና አንድመልክ እንዲመስልልን በሽብርተኛነት ቀለም የለቀለቅናቸው ሁሉ ሌላ እየሆኑ ሲወጡ መፍትሔ ብለን ያወጣነው የጡንቻና የስንፍና ዘዴ ለጡንቻ የማይበገር ያፈጠጠና ያገጠጠ ችግርን ይወልዳል።
አካባቢያችን በሽተኛ ነውና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሽብርተኛነት ለማዳን አስፈላጊም ተገቢም ነው፤ ዘዴው የኢትዮጵያን ሕዝብ በመከፋፈል፣ በማጋጨት፣ በማስጨነቅና በጠላትነት በመፈረጅ አይደለም፤ ይህ ኮረኮንች መንገድ እያንገላታ የሚያመራው ወደገደል ነው!
ለተመስገን ደሳለኝ አል ሸባብ ደብዳቤ ጻፈለት ብሎ የሚያምን ኢትዮጵያዊ የለም፤ አል ሸባብ ምናልባት ዱሮም ሆነ ዛሬ የሚተዋወቃቸው ኢትዮጵያውያን ይኖሩ ይሆናል፤ እነዚያን ማፈላለግ ያስፈልግ ይሆናል፤ የአል ሸባብንም ሆነ የአል ቃይዳን ወዳጆች በፍትሕ ጋዜጣ አካባቢ ይገኛሉ ብሎ መጠርጠር ደኅንነቱ ወደ እውነቱ እንዳያተኩር ለማደናገር የተፈጠረ የጠላት ዘዴ ነው፤ በበኩሌ የኢትዮጵያን ሕዝብ ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል የውጭ ኃይል ከየትም መጣ ከየት እቃወማለሁ፤ አይቼ አላልፈውም፤ ኢትዮጵያ የእነዚህ የአእምሮ አቅመ-ቢሶች፣ ሰነፎችና እበላ- ባዮች አገር ብቻ አይደለችምና እኛም ለደኅንነቷ ስለምንጨነቅ የሚሰነዝሩትን ማስፈራሪያም ይሁን ማደናገሪያ አውቀንባችኋል እንላቸዋለን።
የምንታገለው ለኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና እኩልነት፣ ለፍትሐዊ አስተዳደር፣ ለልማትና ለብልጽግና መሆኑ የማይገባቸው እስቲገባቸው ድረስ እንቀጥላለን፤ እነሱ እየተማሩ ወደኛ ይመጣሉ እንጂ እኛ ወደነሱ አንሄድም።

Wednesday, 4 July 2012

ዲግሪ ያላቸው ዜጐች የጐዳና ተዳዳሪዎች ሆነዋል

ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የማስተርስና የመጀመርያ ዲግሪ ያላቸው ዜጐች አዲስ አበባ ውስጥ የጐዳና ላይ ተዳዳሪዎች ሆነው መገኘታቸው ተጠቆመ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ትናንትና በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጸው፣ በከተማው ያሉትን የጐዳና ላይ ተዳዳሪዎች ወደ መልካም ሕይወት ለመመለስ፣ አስተዳደሩ በማድረግ ላይ ባለው እንቅስቃሴ መምህር፣  ነርሶችና በተለያዩ ሙያዎች የተመረቁ ዜጐች የጐዳና ላይ ተዳዳሪ ሆነው መገኘታቸውን አረጋግጧል፡፡

እነዚህ የተማሩ ዜጐች ለጐዳና ሕይወት የዳረጋቸውን ምክንያት በማጣራትና አስፈላጊውን የማስተካከያ ውሳኔ በማስተላለፍ ቀድሞ ወደ ነበሩበት ሥራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን፣ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ካህሣይ ገብረ መድኀን ገልጸዋል፡፡

አስተዳደሩ በጐዳና ላይ የሚኖሩትን ዜጐች ለማቋቋምና ሥራ በመፍጠር ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ፣ በአራት ዙር ከሰባት ሺሕ በላይ የጐዳና ተዳዳሪዎችን በተለያዩ የሥራ መስኮች ማለትም በኮብል ስቶን ሥራ፣ በጥቃቅንና አነስተኛና በመሳሰሉት ለማሰማራት ባደረገው ጥረት አስደሳችና አሳዛኝ ገጠመኝ እንዳለው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለጊዜው ቁጥራቸውን በውል አላውቀውም ቢልም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ጎዳና ላይ ይኖራሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ ገበታቸው የተፈናቀሉ፣ በተለያዩ ሱሶች የተለከፉና በሕመም ምክንያት ሥራቸውን ማከናወን ያልቻሉ የመጀመርያና የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች መኖሪያቸውን ጎዳና ላይ አድርገዋል፡፡ ቢሮው በሥሩ በተዋቀረው የማኅበራዊ ችግሮች፣ መንስኤዎች መከላከልና ተሃድሶ ዋና የሥራ ሒደት በከተማው ውስጥ ያሉ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በተመለከተ ያደረገው ጥናት ቢጠናቀቅም፣ ምን ያህል ምሩቃን ጎዳና ላይ እንዳሉ ውጤቱን ይፋ አለማድረጉ ታውቋል፡፡

ሕፃናትን በመምከር ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ በማድረግ፣ ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች ዕርዳታ በመስጠት አስተዳደሩ ዜጐች ወደ ተሻለ ሕይወት እንዲያመሩ ቢያደርግም፣ በጐዳና ላይ ቆይታቸው በተለያዩ ሱሶች የተጠመዱና ያለ  ሥራ እየለመኑ መኖር የወደዱ፣ ተመልሰው ወደ ጐዳና ሕይወት መግባታቸውን አቶ ካህሣይ ገልጸዋል፡፡ በቀን አራት መቶ ብርና ከዚያም በላይ እያገኙና እየቆጠቡ ብዙ ወጣቶች ሕይወታቸውን ሲለውጡ፣ የራሳቸውን ሥራ በመሥራት መለወጥ የማይፈልጉ ደግሞ ጐዳና ላይ  እንዳሉም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

አስተዳደሩ የካ ትንሳኤ መንደርና ቦሌ ህዳሴ መንደር በማለት ባቋቋማቸው የማሠልጠኛ ቦታዎች ለሁለት ወራት እየሠለጠኑ ወደተለያዩ ሥራዎች (ኮብል ስቶን፣ ኮንዶሚኒየም ግንባታና ሌሎችም) እየተሰማሩ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ካህሳይ፣ ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ዜጐች አዲስ አበባ  የሚያርፉ በመሆኑ የጐዳና ተዳዳሪዎችን ብዛት ለመቀነስ አለመቻሉን አውስተዋል፡፡

ከየክልሉ በመልካም አስተዳደር እጦት በተለይ በቀበሌ ሹማምንት መሬታቸውን እየተነጠቁና የተለያዩ በደሎች እየደረሱባቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የጐዳና ላይ ተዳዳሪ የሆኑትን ሳይቀር፣ አስተዳደሩ ወደ መጡበት ለማጓጓዝ ወይም ለመርዳት የበጀት እጥረት እንዳለበት የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ ክልሎች የየራሳቸውን ሰዎች የሚያቋቁሙበት ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ቡድን ተቋቁሞ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በየቀበሌ ማኅበሩ የሚደርስባቸው ወከባና ጫና ቀርቶላቸው ሕይወታቸውን በመልካም ሁኔታ እንዲመሩ ለማድረግ እንዲሠሩና ወደየቀያቸው ለሚመለሱትም የሦስት ወራት ቀለብ ለመርዳት ስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል፡፡

ዜጐችን ለማጓጓዝ እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ ሆነው በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩትን ለመርዳት፣ ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ በተደረገ ቴሌቶን ብራይት ሆፕ የሚባል በጐ አድራጐት ድርጅት ለእያንዳንዳቸው የጐዳና ተዳዳሪዎች 120 ዶላር የሚገመት ጫማና ለቀለብ የሚሆናቸው ሩዝ ለመርዳት በድምሩ ስምንት ሚሊዮን ብር ሲለግስ፣ በአጠቃላይ ከቴሌቶኑ ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ አስተዳደሩ ግን 15 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ተጠቁሟል፡፡

በሥራ አጦችና በጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ ለመምከር የአስተዳደሩ ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ በየክልሉ የሚገኙ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዎች ባህር ዳር ላይ ስብሰባ መቀመጣቸውን አቶ ካህሳይ አስረድተዋል፡፡ 

በሊባኖስ መሬት ለመሬት የተጎተተችው ኢትዮጵያዊት አስከሬን አዲስ አበባ ገባ

-    የቀብር ሥርዓቷ ዛሬ በትውልድ ሥፍራዋ ይፈጸማል

በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ደጃፍ አጠገብ በአሠሪዋ መሬት ለመሬት ስትጐተትና ስትደበደብ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የታየችው፣ በኋላም አወዛጋቢ በሆነ ሁኔታ ራሷን አጠፋች የተባለችው የ33 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ዓለም ደቻሳ አስከሬን ትናንትና አዲስ አበባ ገባ፡፡
ሕይወቷ ካለፈ አራት ወራት ሊሞላ ቀናት ብቻ የቀሩት የዓለም ደቻሳን አስከሬን፣ ትናንትና ሰኔ 26 ቀን 2004 ዓ.ም. አባቷና ወንድሞቿ ከቦሌ ጉምሩክ የተረከቡ ሲሆን እንደተፋቱ የሚነገርለት የልጆቿ አባት ደግሞ ከአጥር ውጭ ሆኖ ሲጠብቅ ታይቷል፡፡

የሟች ዓለም ደቻሳ ታናሽ ወንድም አቶ ለታ ደቻሳ አስከሬኑን በተረከቡበት ወቅት “የኛን ሐዘን ያየ ወደ ዓረብ አገር ሄዶ ለመሥራት አይነሳሳም፡፡ ዓለም ለእናትና ለአባቷ ረዳት ነበረች፡፡ እዚሁ ያለንን ተካፍለን ብንኖር ይሻል ነበር፤” በማለት እንባ እየተናነቃቸው ተናግረዋል፡፡

አባቷና ወንድሞቿ በተገኙበት ከቦሌ አስከሬኗ ጉምሩክ ወጥቶ ከአዲስ አበባ  180 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ምዕራብ ሸዋ አቡና ግንደበረት ተጓጉዟል፡፡
አቶ ለታ እንዳሉት፣ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ዛሬ ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ሟች በምትከተለው የፕሮቴስታንት እምነት መሠረት በግንደበረት ይፈጸማል፡፡

የዓለም አስከሬን ከጉምሩክ ሲወጣ ሌላ አንድ አስከሬን አብሮት ነበር፡፡ የአስከሬኑን ተቀባዮች ለማነጋገር ቢሞከርም፣ ተረካቢዎቹ “ከዓረብ አገር በሰው ተልኮልን ነው፤” ከማለት ውጭ ተጨማሪ መረጃ ሊሰጡ አልፈቀዱም፡፡

“በሊባኖስ በሞተችው ኢትዮጵያዊት አሠሪ ላይ ክስ ተመሠረተ” በሚል ርዕስ እሑድ መጋቢት 9 ቀን 2004 ዓ.ም.፣ በሊባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ኃላፊ የሆኑትን አቶ አሳምነው ደበሌ ቦንሳን ጠቅሰን እንደዘገብነው፣ በሊባኖስ በኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች ላይ የሚታየው ችግር አስከፊ ገጽታ አለው፡፡ እረፍት አይሰጣቸውም፤ ምግብ ይከለከላሉ፤ ሌላው ቀርቶ የሠሩበት ደመወዝ እንኳን በአግባቡ አይሰጣቸውም ከዚህም በላይ ዱላና ግድያ ይፈጸምባቸዋል፡፡

አሁንም ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች በሕገወጥ መንገድ ወደ ሊባኖስ መግባታቸው አልቀረም፡፡ በቤይሩት ሕጋዊ የቤት ሠራተኛ የለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም የዜጐችን መብት የሚያስጠብቅ የጋራ የሥራ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ኢትዮጵያውያን ወደ ቤይሩት እንዳይሄዱ እገዳ ከጣለ ከሦስት ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡

በሕገወጥ መንገድ ሊባኖስ የገባችውና ለሦስት ወራት ያህል በቤት ሠራተኝነት ያገለገለችው ዓለም ደቻሳ፤ ከአስከሬኗ ጋር የተላከው መረጃ  የአሟሟቷ ሁኔታ ራሷን በማነቅ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በወቅቱ ስለአሟሟቷ ሁኔታ ተጠይቀው የነበሩት አቶ አሳምነው በዓለም ድንገተኛ ሞት ጥርጣሬ እንዳላቸው መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ የሊባኖስ መንግሥት በተደጋጋሚ በሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች አሟሟቷን እንዲያጣራና ውጤቱን እንዲገልጽ ቢጎተጎትም፣ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል፡፡

ሟች ዓለም ደቻሳ የሁለት ልጆች እናት ነበረች፡፡

Tuesday, 3 July 2012

ሀገር በምን ይፈርሳል? 2 .... Temesegen Desalrgn

ከዚህ ቀደም ‹‹ሀገር በምን ይፈርሳል?›› በሚል ርዕስ የዚህን ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ፅፌ ነበር። በዚያ ፅሁፍ ላይ ያነሣሁት አንጓ ዘውግ ተኮር የሆነው ፌደራሊዝም ከዕለታት አንድ ቀን ሀገር ማፍረሱ አይቀሬ መሆኑ ላይ ነው። ለዚህም እንደ ‹‹ሠርቶ ማሳያ›› የጉራፈርዳ፣ የጋምቤላ እና የሲዳማ ችግሮች ሊወሰዱ እንደሚችሉ ተነጋግረንባቸዋል። በዚህ ፅሁፍ ደግሞ ከዘውግ ተኮር ፌዴራሊዝሙ በተጨማሪም ዜጎች ‹‹ሀገሬ›› ብለው በሀገራቸው ላይ መተማመን ካልቻሉ ‹‹ሀገር ሊፈርስ›› እንደሚችል እንነጋገራለን። በእርግጥ ይህን ርዕሰ ጉዳይ ደግሜ ለማንሳት ሌላኛው ምክንያቴ ከስርዓቱ የሃሳብ ‹‹ቀሳውስቶች›› ዋነኛው የሆኑት አቦይ ስብሃት ነጋ ሰኔ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ከ‹‹አዲስ ጉዳይ›› መፅሔት ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ነው፡፡
ከአጀንዳችን በፊት…
ባለፈው ሳምንት በወጣችው ፍትህ ላይ ‹‹አልሸባብ›› ከሚባል የሽብር ድርጅት ጋር ጋዜጣዋን ለማቆራኘት ስለተደረገው ከንቱ ሙከራ አንድ ፅሁፍ ፅፌ እንደነበር ይታወሳል። በፅሁፉ ላይም የዚህ እኩይ ምግባር ‹‹ፊታውራሪ›› አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደሆነ የራሱን (የአዲስ ዘመን) ህትመት ጠቅሼ ነበር። ይህንንም ተከትሎ በማግስቱ ቅዳሜ (ሰኔ 16/2004 ዓ.ም.) በወጣው አዲስ ዘመን ላይ አዘጋጁ ቁጣቸውን ሲገልፁ እንደ ከዚህ ቀደሙ በብዕር ስም ወይም በገደምዳሜ ለማድረግ እንኳ ጥቂት አልተጨነቁም። በግልፅ እና በድፍረት ነው ሀገር ጥዬ መጥፋት እንዳለብኝ የነገሩኝ። ይህ ማስጠንቀቂያቸውም የታተመው በገፅ 11፣ የፖለቲካ አምድ ላይ ሲሆን አስፈራሪውም የገፁ ም/ዋና አዘጋጅ ሠይፈ ደርቤ ናቸው። ርዕሱ ‹‹ለሀገር ጥፋት ከመኖር…›› ይላል፡፡ በውስጡ ደግሞ እንዲህ የሚል ትዕዛዝና ማስጠንቀቂያ ይዟል፡- ‹‹ምንም እንኳን ፍትህ ሽብር፣ ሽብር፣ አልሸባብ፣ አልሸባብ ብትልም፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የአንጋፋነት ስያሜ እየሰጠች ‹ይችን ሀገር ለቀን አንወጣም› የሚል ሀሳብ በየጊዜው ብታንፀባርቅም ሀገር ከጠፋ በኋላ መቀመጫ እንደሌላት አለመጠርጠሩ ያስፈግጋል።… መሰደድና እንደገና የልማት ‹ሀሁ…› ውስጥ መግባት አንፈልግም። ከአዲስ መጀመርን አንሻም፤ በእምነት ሽፋን በየጊዜው የውዥንብር አጀንዳ በመቅረፅ ወሬ መፍጠር፣ የተፈጠረውን ወሬ ዜና ማድረግ፣ ሲሻ በእምነት ሽፋን፣ ካልሆነ በጦር ኃይል፣ አልሆን ሲል በመምህራን ጉዳይ፣ እንዲያ ሳይሆን በግንቦት ሰባት፣ እምቢ ሲል ‹… ጊዜ ለኩሉ› እያሉ መወትወት ብዕረኛም ጋዜጠኛም አያሰኝም። ሀገር መውደድና ለሀገር መኖር እንዲያ አይደለም። ይልቅ ለሀገር ጥፋት ከመኖር ከሀገር መጥፋት ይሻላል።›› (ሠረዝ የእኔ)
የተሠመረበትን አንቀጽ ስናየው ይህ አቋም የመንግሥት ጋዜጣ አዘጋጅ አቋም ይሆናል ማለት ሊከብድ ይችላል። አሳዛኙ ነገር ግን አዘጋጁ በስማቸው ስለሆነ የፃፉት ሳንወድ በግድ ከመቀበል ውጭ የሚኖረን አማራጭ አለመኖሩ ላይ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ የተለያዩ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም፡ ፡ ለምሳሌ ለሀገር ጥፋት ከመኖር ከሀገር መጥፋት ይሻላል ምን ማለት ነው? የምንጠፋውስ ወዴት ሀገር ነው? የሚሉትን ልናነሳ እንችላለን፡፡ (በነገራችን ላይ ይህ ማስጠንቀቂያ ‹‹አልሸባብ ላከው›› ከተባለው ማስፈራሪያ የተለየ አይደለም። ምን አልባት ልዩነት አለው ከተባለ እንኳ የአዲስ ዘመኑ ‹‹ሀገር ለቆ መጥፋት›› የሚል አማራጭ ሲኖረው፤ የአልሸባቡ ‹‹ህይወት እናጠፋለን›› የሚል አማራጭ ማስቀመጡ ብቻ ነው)
የሆነ ሆኖ በፍትህ ላይም ሆነ በእኛ በአዘጋጆቹ ላይ ለሚደርስ አንዳች ‹‹ክፋት›› እኚህ የጋዜጣው አዘጋጅም ሆኑ ማስጠንቀቂያውን በሚያዘጋጁት የፖለቲካ አምድ በኩል እንዲያደርሱ የላኳቸው ‹‹ሰዎች›› አስቀድመው ሀላፊነቱን ወስደዋል፡፡ መቼም ከዚህ የበለጠ መንግስታዊ የሽብር ድርጊት የትም ተሠምቶ እንደማያውቅ እርግጠኛ ነኝ፡፡ አልቃይዳ እና አልሸባብ እንኳ አደጋ ሲጥሉ እንዲህ ግልፅ ማስጠንቀቂያ ሠጥተው የሚያወቁ አይመስለኝም፡፡ እንግዲህ የሚሆነውን እናያለን፡፡ አሁን ወደ አጀንዳችን እንመለስ።
ሀገር በምን ይፈርሣል?
በእርግጥ ይህ ጥያቄ አይደለም። በተግባር እየታየ ያለና ሊሆን የሚችል አደጋ ነው። የሀገሪቱን የፖለቲካ ስልጣን ከጨበጠ ሃያ አንድ ዓመት የሞላው ኢህአዴግ ከፖለቲካው ባሻገር ኢኮኖሚውንም ሆነ ፕሮፓጋንዳውን ‹‹ጉልተ-ርስት›› አድርጎታል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ይልቁንም እንዲህ በጉልበት ያከማቸውን ‹‹ኃይል›› እና ‹‹ገንዘብ›› መልሶ ወደ ህዝብ ሲያመጣው ጉዳይ መፈፀሚያ ወይም ድጋፍ ማሰባሰቢያ እያደረገው ነው፡ ፡ ለዚህም ነው ግንባሩ የእኔ ከሚለው ርዕዮተ-ዓለም የተለየ አመለካከት ያለው ከመንግስት የስራ ‹‹ዕድል ፈንታው››ን እንዳያገኝ የሚያደርገው፡፡ ይህ ሰው ተበድሎ ቢከስ ወይም በሀሰት ቢከሰስም አይረታም። በአጠቃላይ ለህዝባዊ አገልግሎት የተቋቋሙ መንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችም እንዲሁ መስፈርታቸው ከ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› ይልቅ ‹‹ኢህአዴጋዊነት›› የሚል ከሆነ ውሎ አድሯል። ልክ ኢህአዴግ የሚባል ዳር ድንበሩ የተከበረ ሀገር ያለ ይመስል።
በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ ተራራና ወንዞቹ ሳይቀሩ ‹‹የግንቦት ሃያ ፍሬ ናቸው›› ወደ ማለት አዘንብሏል። ይህም ዕውን ይሆን ዘንድ ማደራጀት፣ ማደራጀት… አሁንም ማደራጀት። አባላትን ማብዛት፣ ማብዛት፣ ማብዛት… አሁንም ማብዛት የሚል ፍልስፍናን እንደዋነኛ አጀንዳ የያዘው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከኢህአዴግ ጥቅምም ሆነ ከፖሊሲው ጋር አንዳች ግንኙነት የሌለው ለእስረኞች የሚሰጠውን ‹‹አመክሮ›› ያልተደራጀ እንደናፈቀው ይቀራል የማለት አዝማሚያዎችን እየሰማን ነው። ይህ አይነቱ ‹‹ጥርነፋ›› ደርግ ለመጨረሻ ጊዜ የተፍጨረጨረበትን፣ ነገር ግን ግብአተ መሬቱ ከመፈፀም ያልታደገውን ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር›› መፈክርን ያስታውሰኛል። …ሁሉም ነገር የኢህአዴግ ነው። ‹‹ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አይኑርህ›› ምድራዊው ትርጓሜ ይህ ነው፤ ሌላ አይደለም፡፡ ከኢህአዴግ በቀር…
ከዚህ ቀደም ፕሮፌሠር መስፍን ወልደ ማርያም በፍትሕ ጋዜጣ ‹‹መሬት መሬት አንድ›› ሲሉ በፃፉት አርቲክል ላይ መሬቱ በሙሉ ለባለሀብት ተሸጦ ካለቀ፤ ቀሪው ኢትዮጵያዊ መሬቱ ቢወረር ለማን መሬት ብሎ አጥንትና ደሙን ይከሰክሳል? የሚል ይዘት ያለው የነገ ስጋታቸውን ገልፀው ነበር። በእርግጥ ፕሮፍ ልክ ናቸው። የጋምቤላን መሬት የተቀራመቱት ህንድና ሳውዲአረቢያም ሆኑ ዋና ዋና የከተሞቻችን እምብርት እየገዛ ያለው መሀመድ አላሙዲ ‹‹ሀገሪቱን በጥቂቶች የመጠቅለል›› ኢህአዴጋዊ ፍልስፍናን ከዳር እያደረሱት ይመስለኛል። የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤትም ነው ሀገር የሚያፈርሰው። …ሀገር ህልውናዋ የሚረጋገጠው ዜጎች ‹‹ሀገሬ›› ሲሉ እንጂ የጥቂት ጉልበተኞች ‹‹ማረሻና ማጭድ›› ስትሆን አይደለም። አሁን እየሆነ ያለው ግን በግልባጩ ነው። ከዚህም በመነሳት ነው ‹‹አይበለውና!›› እንደቀድሞዎቹ ቀውጢ ጊዜያት የሀገሪቱ ሉአላዊነት ቢደፈር ማን ይሆን ‹‹ሀገሬን ዳር ድንበሬን›› ብሎ የሚሞተው? በሚል ስጋት የተዋጥነው፡፡ መቼም አላሙዲ እና የካራቺ ሩዝ አምራች ገበሬዎች ‹‹ኢትዮጵያ የእኛ መመኪያ…›› እያሉ ሊዘምቱ እንደማይችሉ ግልፅ ነው።
በ ጋ ም ቤ ላ - ፓ ኪ ስ ታ ና ዊ ያ ን ፤ በኡጋዴን-ቻይናውያን የተገደሉት ምክንያትም ምልክቶች ሊሰጠን ይችላል፡፡
እናም መሬትን ያህል ነገር ቀርቶ ጥቃቅን የዜግነት ጥቅሞቹን በጠየቀ ቁጥር ‹‹የፓርቲ አባል ነህ? ወይስ አይደለህም?›› በሚል ማንፈሻ የሚንገዋለለው ኢትዮጵያዊ እንደከዚህ ቀደሙ ባንዲራ ለብሶ ሊዘምት ይችላል ማለቱ ገራገርነት ነው። ጥላሁን ብርሃን ስላሴ ቤተ ‹‹የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ-ክፍል አንድ›› በሚል ርዕስ በፃፉት መፅሕፍ ላይ በ1928ቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ ከቤልጅግ ሀገር ተገዝቶ የመጣው የጦር መሣሪያ ለወታደሮች ሊከፋፈል ሲል ራስ ካሣ ወታደሮቹ መሳሪያውን ይዘው ወደጦር ሜዳ ላይሄዱ ይችላሉ ብለው በመስጋት እንዳይታደላቸው ተቃውመው እንደነበረ ይገልፃሉ።
‹‹ሃሳባቸው ወታደር መሣሪያውን ይዞ ተፈሪን ይከዳል ብለው በመጠርጠር ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ወታደሩ በወር የሚከፈለው ሦስት ማርትሬዛ ብር (ጠገራ ብር) ስለኾነና ቅሬታ ስለነበረው ነው። ወታደሮቹም፡-
‹እንደራበኝና እንደሞረሞረኝ
ከጠገበው ጋራ ልሞት ነው መሰለኝ›
ብለው ዘመቱ ይባላል›› ሲሉ ጽፈዋል። እኔም ይህን ነው እያልኩ ያለሁት። ‹‹ከመንግስት ቤት›› እስከ ‹‹መንግስት ስራ›› ማግኘት የዜግነት ሳይሆን የፓርቲ መብት ከሆነ፤ የመከላከያም ሆነ የፌዴራል ሠራዊቱን ከሚተማመንበት ይልቅ የሚፈራው ከበረከተ፣ የስለላ መዋቅሩ ከፓርቲ መዋቅር ካልተለየ፣ የፍትሕ ስርዓቱ የድርጅት ግምገማን ከመሠለ… አባቶቻችን በደም- በአጥንታቸው ያቆዩልንን የምንወዳት ሀገራችንን ሊያፈራርስ ጉልበት ካለው ማዕበል አንዳች ኃይል አያቆመውም፡ ፡ የአቶ በረከት ስሞዖን ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› መፅሀፍም ቢሆን እንኳ-አይቻለውም። (ይህን ያልኩበት ምክንያት በረከት፣ ፓርቲያቸውን በጉልበቱ ከተሰቀለበት የስልጣን ማማ ሊያወርደው ጥቂት ቀርቶት የነበረውን ሱናሚ ምርጫ 97 ‹‹ናዳ›› ሲሉ ከገለፁ በኋላ፣ የጎዳና ላይ ግድያውን፣ የጋዜጠኞችና የፖለቲከኞችን ጅምላ እስር ጨምሮ ሲቪል ተቃውሞን ደምስሰው ‹‹አውራ ፓርቲ›› የተሆነበትን ቀመር በዚሁ መፅሃፍ ‹‹ናዳን የገታ ሩጫ›› ሲሉ በማንቆለጳጰሳቸው ነው)
በእርግጥ ሀገር የመታደጉ ጊዜው የረፈደ ቢመስልም ጥቂት ወራት ወይም አመታት ይቀሩታል። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ‹‹ኢህአዴጋዊነት››ን በማስቀደም አይደለም። ወይም ‹‹ታግዬ ጥዬአለሁና ሀገር ምድሩ የግል ርስቴ ነው›› በሚል ፍልስፍናም አይደለም። ይህ የተሳሳተ ፍልስፍና መሆኑ ያልገባው ካለ ምናልባት ከአፄ ምኒልክ አስተዳደር መማር ይቻላል። መማር ለፈለገ ማለቴ ነው። ከዛው ‹‹የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ- ክፍል አንድ›› መጽሐፍ ላይም እንዲህ የሚል ምርጥ የአስተዳደር ምሳሌ ልናገኝ እንችላለን፡-
‹‹አፄ ምኒልክ የግል መሬት እንዲይዙ ተብለው ሲመከሩ ‹መላው ኢትዮጵያ የማን ኾነና እኔ በግሌ መሬት እይዛለሁ?› ብለው በመመለሳቸው በምኒሊክ ስም የተያዘ አንድም መሬት አልነበረም። የእናታቸውን የዘር ርስት ወራሽ ቢሆኑም ገበሬው እያረሰ ሲሆን፣ በግብር ምክንያት ከምስለኔው ጋር ተጋጭተው ጉዳዩ አፄ ምኒልክ ዘንድ ሲቀርብ ‹ፈጣሪዬ የመላ ኢትዮጵያ አባት ስላደረገኝ እሡም ከልጆቼ አንዱ ስለሆነ በስሙ ሊገበር ይችላል› ብለው መረቁለት፡ ፡›› በእርግጥ ይህ ድንቅ የአስተዳደር ዘይቤ ቢሆንም ከዚህ በተቃራኒው የሚቆም ታሪክም አለን፡፡
የዚህ ታሪክ ባለቤት በታሪካችን ከተጠቀሱት ገብጋባ ንጉሶች አንዱ ነው፡ ፡ ንግስናውም በአክሱም ዘመን ሲሆን ስሙም ዞስካለስ ይባላል፡፡ እንደታሪካችን ትርክት ዞስካለስ ለሀገራችን የመጀመሪያው ወይም ‹‹Known›› ንጉስ ነው፡፡ ‹‹THE PERIPLUS OF ERYTHREAN SEA›› በሚል ርዕስ በዘሙኑ የተፃፈ መፃሀፍ ይህንን ንጉስ ‹‹Greedy Merchant›› (ገብጋባው ነጋዴ) ሲል ይገልፀዋል፡፡ ይህ ንጉስ የነበረው ከክርስቶስ ልደት በኋላ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ነው፡ ፡ ከዚህ አንፃር ነው ወደኋላ 2ሺህ አመት ተጉዘን ከዞስካለስ ከመማር በህይወት ካለፉ በቅጡ መቶ አመት እንኳን ካልሞላቸው ምንሊክ መማሩ የተሻለ ነው የምለው፡፡ …ለእኔ መንግስት ማለት እንደ ምንሊክ ያለ አስተዋይ እንጂ እንደ ጥንቱ ዞስካለስ ያየው የሚያምረው ‹‹ቆንቋና›› ነጋዴ አይደለምና። ስለዚህም ይህ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ምንሊክ ካደረጉት የተለየ ትርጉም ሊኖረው አይገባም። እንደዕድል ሆኖ ግን በመሬት ያለው የዚህ ተቃራኒ ነው። እናም በህዝብ ሀብት የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) ገንብቶ ሲያበቃ እንደ ስስታም ነጋዴ አትርፎ መሸጥ በየትኛውም መንገድ ‹‹ልማታዊ›› ሊያስብል አይችልም፡፡ አርባ አመት ግብር ሲከፍል የቆየ ነጋዴን ከቦታው እንዲነቀል ተደርጎ ሲያበቃ ‹‹ለመንግስት ቤት ምትክ አንሰጥም›› ማለቱም ማጅራት ከመምታት በምን ሊለይ እንደሚችል ግልፅ አይደለም፡ ፡ የፖለቲካ ስርዓቱ የወለደው የድርጅትም ሆነ የግለሰብ ነጋዴ፣ ከለፍቶ አዳሪው ነጋዴ በተለየ ሁኔታ ከታየ መቼም ቢሆን እንደአስተዳደር አምኖ መቀበሉ ድንገት ሀገር ሊያፈርስ የሚችልበት አጋጣሚ ለመብዛቱ ጥርጥር የለውም። ነጋድረስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› በሚለው መጽሐፋቸው ይህንን ሃሳብ እንዲህ ሲሉ ያጠናክሩታል።
‹‹በያንዳንዱም መንግሥት የሚያድሩ ብዙ ልዩ ልዩ ነገዶች ይኖሩ ይሆናል። ስለሆነም መንግሥት አንዱን ነገድ አጥቅቶ ሌላውን ነገድ ለመጥቀም ሥራው አይደለም። አስተካክለን ካሰብን ዘንድ መንግስት መቆሙ ለሕዝቡ ሁሉ ጥቅም ነው። መንግስት ህዝቡን ሁሉ በትክክል ለመጥቀም ካላሰበ መንግሥት በዙፋኑ ሊቆም አይችልም። ላንዱ ነገድ ወይም ለጥቂት ሰዎች ብቻ ማድላት ለመንግሥት የሚገባ ሥራው አይደለም።››
እኔም ይህንን ነው እያልኩ ያለሁት ‹‹ለጥቂት ሠዎች ብቻ ማድላት ለመንግሥት የሚገባ ሥራው አይደለም።››እኔም ይህንን ነው እያልኩ ያለሁት ‹‹ለጥቂት ሠዎች ብቻ ማድላት ለመንግሥት የሚገባ ሥራው አይደለም።›› የነጋድራስን ምክር አስተውለን በዚህ ዘመን መንፈስ እንፈክረው ካልን ደግሞ ‹‹ይህ አይነቱ አድልኦ አልፎ ተርፎም እንዲህ የምትሟሟቱበትን ዙፋን በህዝባዊ አብዮት ወደታሪክነት ይቀይረዋል›› የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ከዚህም ባለፈ ለስርዓቱ ዕድሜ መራዘም ሲባል የረዥም ዘመን ታሪክ ተጋሪ በሆኑ ዜጎች መካከል ‹‹መናፍቃዊ›› ስርዓት ማንበሩ ሀገር ከማፍረስ ውጭ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ይህ አንድ እውነት ቢሆንም በግሌ ‹‹የሀገራችን አንድነት የፀናው የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል በመከበሩ ነው›› የሚለው የአቦይ ስብሓት ትንተና ውሃ የሚቋጥር ሆኖ አይሰማኝም። ነገር ግን አቦይ ከላይ በጠቀስኩት ቀን በወጣችው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ‹‹ሀገር ማለት ለእርስዎ ምንድነው?›› በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ‹‹ሀገር ማለት ህዝቡ ነው። የህዝቡ ታሪክ ነው። ትናንት የነበረበት አሁን ያለበት፣ ወደፊት የት እንደሚደርስ ማሰብ ነው›› ካሉት ማብራሪያ ጋር ችግር የለብኝም። ሆኖም ‹‹ሀገሪቱ ልትፈርስ መሆኑ ነው ይህን አንቀጽ (39) የወለደው?›› ለሚለው የመፅሔቱ ጥያቄ ‹‹አይደለም፡፡ እኛም የታገልንበት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሁኔታ ያንፀባርቃል። ነገር ግን ከገመትነው በላይ ሀገር ፈርሳ አገኘናት። ወዲያው የመገንጠል ፍላጐት ከገመትነው በላይ ነው የሆነው። ኢትዮጵያ በምትባል ሀገር መቆየት የማይፈልጉ ብዙ ድርጅቶች ነበሩ። ‹እስከ መገንጠል› የሚለው ነገር ሀገሪቱን አቆይቶልናል። ባለፉት መንግስታት በተሰራበት ግፍ አሁንም ህዝቡ ያለው ምሬት ቀላል አይደለም…›› ያሏት ደንገርጋራ ሃሳብ ብዙም አትመችም። ባይሆን ከዚሁ ጋር አያይዘው የተናገሯት ቁም ነገር ከብዙሃኑ አተያይ ጋር የሚያሰልፋቸው ከመሆኑም ሌላ ጥቂት ተጨማሪ ነገሮች ቢደመሩበት ኖሮ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሰሱት ያለውን አትኩሮት በተሻለ ሁኔታ ይስብላቸው ነበር።
አቦይ እንዲህ ነው ያሉት ‹‹አሁንም ቢሆን በዴሞክራሲያዊ ስርዓቱና ልማቱ ካልተፋጠነ ችግር ውስጥ መግባታችን አይቀርም›› እኒህ አንጋፋ ታጋይ አንዳንዴ በጣም ግልፅ ናቸው፡፡ ከማንም በተሻለ ስለዲሞክራሲ እና ልማት የሚወራው ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ያውቃሉ፡ ፡ ጠንቅቀው ስለሚያውቁም ነው ችግር መከሰቱ አይቀሬ እንደሆነ በዘወርዋራ የነገሩን። (ዳሩስ! ዳገት ወቶ፣ ቁልቁለት ወርዶ ካነበረው ስርዓት እየተገፋ ያለ ሰው ከዚህ የበለጠ ምን ሊል ይችላል? መቼም በግልፅ ልማት የለም እንዲሉን ከጠበቅን ፖለቲካ አልገባንም ማለት ነው)
በእርግጥ አቦይ የረሱት ነጥብ የተፋጠነ ልማት ቢኖር እንኳ ተጠቃሚው ‹‹ጥቂቶች›› ከሆኑ የፈሩት ችግር መድረሱን አለማመላከታቸው ላይ ነው፡፡ ጥቂት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የአጋር ፓርቲ ወሳኝ ሰዎች እና ብልጣ ብልጥ ነጋዴዎች ቁመናው ያማረ፣ ዛላው የተንዥረገደ፣ በመስታወት ያበደ ሕንፃ ባለቤት መሆናቸው በሀገሪቱ ልማት አለ የሚያስብል አይደለምና፡፡ በተቀረ አቦይ ከህወሓት የአመራር አባልነት ጡረታ ከወጡ ወዲህ ከበርካታ ‹‹እንጀራ ፈላጊ›› ምሁራኖች የተሻለ ድፍረት እና ሕዝባዊ አቋም እየያዙ መጥተዋል (ለመጽሔቱ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ውስጥ በሌላ ጊዜ የምመለስበት ሊፍታቱ የሚችሉ ጥቆማዎች እንዳሉ አልክድም)
በነገራችን ላይ አቦይ በቃለ- መጠይቁ ወቅት የሳቱት ግዙፍ ነጥብ (ግንቦት ሃያ በድል አዲስ አበባ ሲገቡ) ‹‹ከገመትነው በላይ ሀገር ፈርስ አገኘናት›› የምትለዋ ነች። እውነት ለመናገር ይህን መቀበል ያዳግታል፡፡ ምክንያቱም ደርግ ሁሉንም ችግር፤ በጦር መሳሪያ የሚፈታ ሕግ የማይገዛው መንግሥት መሆኑ አያከራክርም። በዚህ ግልባጭ ደግሞ ደርግ 17 ዓመት ሙሉ አንድም ስልጣኑን እንዳያጣ፤ ሁለትም ሀገሪቷ እንዳትፈርስ ሙሉ በሙሉ ወደ ጦርነት ሊገባ መቻሉን ልናነሳ እንችላለን። ይህ ሁኔታ ሲብራራ ከኢህአፓ፣ ከህወሓት፣ ከኦነግ እና ከመሳሰሉት ጋር የነበረው ጦርነት የስልጣን ጥያቄ ሲሆን፤ በኤርትራ ምድር ከሻዕቢያ ጋር የነበረውን ግን ሀገር ለማዳንና ለመገንጠል የተደረገ ሆኖ እናገኘዋለንና። ለዚህም ነው የአቦይ ‹‹ሀገር ፈርሳ አገኘናት›› ምላሽ በጲላጦሳዊ ብልጠት የተለበደ የሆነብኝ፡፡
ሌላው ቀርቶ አቦይ የሚኩራሩበት የመገንጠል መብት የሚፈቅደው አንቀፅ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሰራ አይደለም፡ ፡ ለምሳሌ ደቡብን ብንወስድ በርካታ ብሄሮች በዞን ተካፋፍለው በአንድ ክልል ታስረው እናገኛለን፡፡ ሲዳማ ዞን፣ ስልጤ ዞን፣ ወላይታ ዞን፣ ጉራጌ ዞን… የመሳሰሉትን፡፡ እናም በሕገ-መንግስቱ መሰረት መገንጠል የሚሉት የተከለለ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ያላቸው ብሔር፣ ብሔረሰቦች አልያም ህዝቦች ናቸው። የደቡብ ብሔር ብሔረሰብ ክልል ከአንድ ወጥ ብሄር አልያም ብሔረሰብ አለመዋቀሩ እንደ ክልል ‹‹ልገንጠል›› ቢል እንኳ የማይቻለው ነው። እንደ ብዙ ፀሐፊዎች ትችትም የዚህን አንቀፅ መኖር ተማምነው ጥያቄያቸውን ለመግፋት የሚሞክሩትን ‹‹በጠባብነት›› እየከሰሰ ራሱን ሀገር አረጋጊ አድርጎ ከማቅረብ በዘለለ ዕውናዊ ፋይዳውም ብዙ አይደለም።
ምክንያቱም ከእነዚህ ብሄሮች አንዳቸው ‹‹ልገንጠል›› የሚል ጥያቄ ቢያነሱ ህገ-መንግስቱ ራሱ ይደፈጥጠዋል፡፡ ህገ-መንግስቱ የመገንጠል ጥያቄን የሚፈቅደው በክልል ምክር ቤት የሁለት ሶስተኛውን የድጋፍ ድምፅ ሲያገኝ ነውና፡፡ ይህ ሁኔታ ነው አንቀፅ 39ን በራሱ ኢ-ፍታሃዊ የሚያደርገው፡፡ መቼም ከዚህ ከተነሳን ‹‹የብሄር ብሄረሰቦች መብት እስከመገንጠል›› ምፀት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
የሆነ ሆኖ በሀገራችን ‹‹የእኔነት›› ስሜት የሚሰማን ጎጣችን ተጠቅሶ በታደለን የቀበሌ መታወቂያ አይደለም። ከዚህም በላይ ከሀገራችን ሃብት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም የማንም ስጦታ ሳይሆን መብታችን መሆኑ በአፋዊ ሳይሆን በተግባር ሊረጋገጥ ይገባዋል፡፡ የኢህአዴግን ርዕዮተ- አለም ሳንከተል፣ በየትኛውም መዋቅር ሳንደራጅ ቤት፣ ንብረት፣ ስራ፣ ብድር እና የመሳሰሉት ወሣኝ ነገሮች የግድ እንዲመቻቹልን መጠየቅም እንችላለን። ይህንን ጥያቄ መጠየቅም ሆነ፣ ማስተዳደር አልቻላችሁምና ‹‹ስልጣን ልቀቁ›› ማለቱም ተፈጥሮአዊ እና ህገ-መንግስታዊ መብታችን ነው። ጥያቄውን ይዞ አደባባይ መውጣቱም እንዲሁ መብታችን ነው፡፡ …እነዚህ እነዚህ መብቶችን መደፍጠጡ ወይም ለመደፍጠጥ መሞከሩ ደግሞ አመንም አላመንም ሃገር ማፍረሱ አይቀሬ ነው፡፡
ሌላው ሀገር ሊያፈርስ የሚችለው ‹‹ካምሱር›› በአገር ጉዳይ ተቀራርቦ የመነጋገር ፍላጎትን ለመገደብ የሚደረገው ሙከራ ነው፡፡ ዜጎች ይህንን ልማድ እንዲያዳብሩ አስትዋፅኦ ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቅ ግዴታ ነው። ይህን ማድረጉም ሀገርን ካልታሰበ አደጋ ይጋርዳል። በተቀረ አሁን ኢህአዴግ እያደረገ ያለውን ሌሎች አምባገነኖችም አድርገውት ከሽፎባቸዋል። የሚያሳዝነው ነገር ግን ሙከራቸው አለመስራቱን ያረጋገጡት የማይታረም ስህተት ከሠሩ በኋላ መሆኑነው። … ወደተረት-ተረት ከተቀየሩ በኋላ… በሀገራችንም አፄ ኃይለስላሴ ተማሪዎችን ለማፈን ሞክረዋል። አፄው በሀገር ጉዳይ እርስ በእርስ መነጋገርን ለማፈን የቻሉትን ያህል ቢያደርጉም ከ66ቱ አብዮት ሰይፍ ሊያመልጡ አልቻሉም። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም እንዲሁ በተመሣሣይ ሞክረው ከሽፎባቸዋል። ለዚህም ነው ኢህአዴግ በሰላዮች ብዛት እና በቻይና ቴክኖሎጂ የተሻልኩ ‹‹አፋኝ›› እሆናለሁ የሚለው ምኞቱ ቀቢፀ-ተስፋ ነው እያልኩ ያለሁት። እንዲያውም ጋዜጠኞችን ከአሸባሪ ጋር ደምሮ ማሰሩን እና የድረ-ገፅ አፈናውን በፍጥነት ካላቆመ ‹‹መጪው ጊዜ ብሩህ ነው›› የሚለው የዝነኛ መፈክሩ ፋይዳ ከተፃፈበት ጨርቅ አያልፍም። ይህ ሁኔታም ነው ሀገር የሚያፈርሰው።
በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባትም ሀገርን በፍቃደኝነት እንደማፍረስ የሚቆጠር ተግባር ነው። በእርግጥ ኢህአዴግ በነቢብ በሃይማኖት ጣልቃ አልገባም ሲል ደጋግሞ ተናግሯል፤ ጽፎአልም፡፡ እንዳሻው በሚያዝበት የመንግስት ሚዲያም እናምነው ዘንድ ብዙ ወትውቷል። አልፎ ተርፎም ወደ ኋላ ተጉዞ በዚሁ ወር በታተመው የንድፈ ሃሳብ መጽሔቱ (አዲስ ራዕይ የግንቦት-ሰኔ 2004 ዓ.ም ዕትም) ላይም የቀድሞ መሪዎች በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን ‹‹ውግዝ ከመ አሪዎስ›› ሲል አውግዟል። ‹‹በየዘመኑ የነበሩ ነገስታት እና የበላይ መሪዎች አንዱን ሃይማኖት ከሌላው በሚበላለጥ ሕገ-መንግስታዊ እውቅናና ጥበቃ የነበረው ግፍ ሲፈፅሙ ኖረዋል። መንግሥታዊ ሃይማኖቶች እንዲኖሩ በሕገ-መንግስት በመደንገግ፣ ሃይማኖትና ትምህርትን በማዋሃድና መሪዎቹ የሚፈልጉት ሃይማኖት የህግ ልዕልና እንዲያገኝ በማድረግ የሌሎች እምነቶች ተከታዮች የሚሸማቀቁበትን ስርዓት በመፍጠር ለበርካታ ዘመናት ሕገ-መንግስታዊ የተደረገለትና እውቅና የነበረው መድሎ አስፍነው ቆይተዋል›› ይላል-ኢህአዴግ።
ይህ እውነት ነው። በተለይም አፄ ኃይለሥላሴ ከመንበራቸው እስኪወርዱ ድረስ ሀይማኖት እና መንግሥት የተለያዩ አልነበሩም። ‹‹መንግሥታዊ›› የሚባል ሃይማኖት ነበርና።
ሆኖም ‹‹ጉድ በል ጎንደር!›› የሚያስብለን ግን ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት እንዲነጣጠሉ ተደርጓል። መንግስት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ አይገባም። ሕገ- መንግስታችን ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ እንደሆኑ በመደንገጉ ዜጎች የትኛውንም ሃይማኖት ወይም ሴክት መከተል እንዳለባቸው እና በምን መንገድ መከተል እንዳለባቸው መንግሥት መወሰንና አቅጣጫ ማስቀመጥ አይችልም። …በምንም መልኩ ግን መንግስት ሃይማኖት ሊያስተምር አይችልም። ይህን ተከተሉ ያንን አትከተሉ ማለት አይቻልም። እስከአሁን ባለው ተግባሩም ሆነ ከታገለለት መርህ አንፃር ኢህአዴግም ሆነ በእሱ የሚመራው መንግሥት ይህን ሊያደርጉ አይችሉም። ይህ የሆነበት ሁኔታም የለም።›› የሚለውን የኢህአዴግን ‹‹ቃል›› በንድፈ ሀሳብ መጽሔት ላይ ስናነብ ነው። ምክንያቱም በዚህ ወቅት እንኳ ቢያንስ ሕዝበ ሙስሊሙ ‹‹መንግሥት ጣልቃ ገባብን››፣ ‹‹የአህባሽን ወይም የወሀቢያ ሴክትን ለመከተል መንግሥት አይመርጥልንም››… የመሣሠሉትን ተቃውሞ ማሰማቱ በግልፅ ጣልቃ መግባትን የሚያሳዩ ናቸውና።
በአጠቃላይ እ.ኤ.አ¸በ2007 ዓ.ም የወጣው የጋሉብ ጥናት ውጤትም የዜጎች በሀገሪቱ ተቋማት ያላቸውን ዕምነት በአስፈሪ ደረጃ እንደወረደ ይናገራል። እንደ ዓለም አቀፋዊው የጥናት ተቋም ዘገባ፣ በፍርድ ቤቶች፣ በምርጫ ፖለቲካ፣ በወታደራዊው ሃይልም ሆነ በእምነት ተቋሞቻቸው ላይ የሚተማመኑ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሰሃራ በታች ካሉት ሀገራት እጅግ ዝቅ ያለ መሆኑ ሁኔታውን አደገኛ ያደርገዋል። ሁላችንም እንደምናውቀው ደግሞ ዜጎች በሀገራቸው ተቋማት ላይ እምነት ሲያጡ፣ ከዋነኛው የፖለቲካ ተዋፅኦ በመራቅ፣ ነፃነታችንን ነፍገውናል ብለው የሚያስቧቸውን ዓለማዊ ተቋማት ወደ ማፍረስ ይሄዳሉ። እንግዲህ ኢህአዴግ በራሱ አምባገነንነት የተነሳ ሁኔታዎችን ወደዚህ እየገፋ፤ ዜጎች ደግሞ ይህን ለማረም ሌላ መንገድ ሲታያቸው አሸባሪ፣ ሀገር ገንጣይ… እያለ በጡንቻ ለመደፍጠጥ እየሞከረ ነው።
በአናቱም የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውን ዜጎች ‹‹በኮብል እስቶን›› ስራ ማሳተፍን እንደ ምርጥ ‹‹ሞዴል›› በመውሰድ ከተኩራራን፣ የፍትህ ስርዓቱ የፓርቲው አፈ-ቀላጤ ከሆነ፣ የሀገሪቱ አንጡራ ሃብት ከዜጎች ይልቅ የስርዓቱ ቁንጮዎች እና የምንደኞቻቸው ከሆነ፣ ሠራዊቱ ከሀገር ይልቅ ፓርቲውን ካስቀደመ… እውነት እውነት እላችኋለሁ ሀገር በመፍረስ ጠርዝ ላይ ቆመች ማለት ነው፡፡ መቼም አቦይ ስብሃት ነጋ ግንቦት ሃያ ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሶስት ‹‹ፈርሳ አገኘናት›› ያሏት ሀገር ዛሬ ካለችብት በእጅጉ የምታስመርጥ ነች፡ ፡ ለዚህ ደግሞ ቀላል ማሳያ ማንሳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በደርግ ጊዜ የነበረችው ኢትዮጵያ ቀይ ባህር ዳር ድንበሯ ነው፡፡ ለአንድ ሃገር ወሳኝ ከሚባሉት ውስጥ ቀዳሚው ወደብ ነው፡፡ ያንጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ የሁለት ወደብ ባለቤት ነበረች፡፡ በአናቱም ከጎሳ ይልቅ ኢትዮጵያዊነት የሚቀድምበት ደጉ ዘመን ነበር፡፡ እናም የሀገር ትፈርሳለች ፍርሃታችን ነፍሳችንን ወጥሮ ቢይዘንም የታሪክ ምሁሩ ፕሮፈሰር ባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ያዘጋጅ በነበረው ‹‹ርዕይ 2020›› ላይ ‹‹ኢትዮጵያ በአክሱም ዘመነ መንግስት ውድቀት ማግስት፣ በዘመነ መሳፍንት ወቅት፣ በ1966ቱ አብዮትና በ1983ቱ የሽግግር ዘመን ትፈራርሳለች ተብሎ ብንሳቀቅም እነዚህን ጊዜያቶች ተሻግራለች፡፡ እነዚህ የመከራ ጊዜያትን እንድትሻገር ያስቻላት ጥልቅ የዜጎቿ ማህበራዊ ትስስር ይመስለኛል›› በማለት የተናገሩት ቢያንስ ነገን ‹‹ሀገሬ ትፈርሳለች›› በሚል ፍርሃት እንዳንወጠር ያደርገን ይሆናል፡ ፡ አሊያም ‹‹When dictatorship is a fact Popular uprising is a right›› የሚለውን የፈረንጆች አባባል ከሙሴ አስርቱ ትዕዛዛት የቀጠለ 11ኛው ትዕዛዝ አድርገን በፍፁም ልባችን መቀበላችን አይቀሬ ሊሆን ነው፡፡

Sunday, 1 July 2012

ሰበር ዜና - የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም በፌዴራል ፖሊስ ተከቧል



·        አራት መነኰሳት በፖሊስ ተይዘው ተወስደዋል፤ ሌሎቹ መነኰሳት እየተደበደቡ ተበታትነዋል።
·        የገዳሙ የሱባኤ ወቅት በፖሊስ የኀይል ርምጃ እየታወከ ነው።
·        በዛሬማ ወንዝ ላይ የሚገነባውን የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ግድብ የሚሠራው ሱር ኮንስትራክሽን  ለቆ መውጣቱ እየተነገረ ነው፤ በምትኩ የቻይና ተቋራጭ የገባ ቢኾንም በእርሱም ላይ ተቃውሞው መቀጠሉ ተሰምቷል።
( READ THIS NEWS IN PDF)፦ በሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ዓዲ አርቃይ ወረዳ የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም ከማይ ፀብሪና ዓዲ አርቃይ ወረዳዎች በአምስት መኪና ተጭነው በመጡ የፌዴራል ፖሊስ ኀይሎች ሥምሪት ውስጥ እንደሚገኝ የስፍራው ምንጮች ለደጀ ሰላም ገለጹ፡፡

ትናንት፣ ሰኔ 23 ቀን 2004 ዓ.ም፣ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ገዳሙን በተቆጣጠረው የፖሊስ ኀይል አራት የገዳሙ መነኰሳት ተይዘው ወደ ወረዳው ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱ ሲኾን ሌሎቹ መነኰሳት ደግሞ ለሱባኤ (ሕርመት) ከተሰበሰቡበት በቆመጥ እየተደበደቡ መበታተናቸው ተጠቁሟል፡፡
ከአራቱ መነኰሳት መካከል ሦስቱ፣ አባ ኀይለ ኢየሱስ፣ አባ ግርማይ፣ አባ ገብረ እግዚአብሔር እንደሚባሉ ተረጋግጧል፤ የአራተኛውን መነኰስ ስም ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ማኅበረ መነኰሳቱን የማሳደዱ ተግባር ከገዳሙ ውጭም የቀጠለ ሲኾን ፖሊስ አባ ገብረ ሕይወት የተባሉ ሌላ የገዳሙ መነኮስን ለመያዝ በደባርቅ ከተማ አሠሣ እያደረገ መኾኑ ተገልጧል፡፡ የአሠሣው እና ስምሪቱ መጠናከር ምክንያት፣ ከግንቦት 22 ቀን አንሥቶ የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም ሴት መነኰሳዪያት፣ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት በገዳሙ ላይ የሚያደርሰውን አካባቢያዊና ማኅበራዊ ጉዳት በመቃወም “ኑና ገዳሙን ተረከቡ፤ እኛ መሰደዳችን ነው” በሚል ለሕዝቡ ጥሪ ካስተላለፉ በኋላ በተለይም በዛሬማ ቀበሌና በእንዳባጉና ወረዳ ዲማ ቀበሌ እየተጠናከረ የመጣው የተቃውሞ እንቅስቃሴ መኾኑ ተመልክቷል፡፡  
በዋልድባ አብረንታንት ገዳም፣ በዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም እና በዋልድባ ዳልሽሐ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም በየዓመቱ ከሰኔ 21 - ኅዳር 8 ቀን የሱባኤ ወቅት ነው፡፡ ገዳሙ ዓመት እስከ ዓመት ሱባኤ የሚያዝበት፣ አባቶች ያለማቋረጥ ከእግዚአብሔር የሚገናኙበት የሰማይ በር ቢኾንም፣ ይህ ወቅት ግን ከሌላው ጊዜ ተለይቶ ማንም አቋርጦ ለመውጣት የማይፈቀድበት ነው፡፡ በአንድነትና በፍቅር ተሰብስበው የሚኖሩት ማኅበረ መነኰሳት ጭው ካለው በርሓ ገብተው በቋጥኝና በዋሻ እንደሚኖሩት ግሑሳን ባሕታውያን ከሰው ተለይተው በአንድ ቦታ ተወስነው በጾም፣ በጸሎትና በስግደት መንፈሳዊ ተጋድሏቸውን የሚያጠናክሩበት ወቅት ነው፡፡
ዋልድባን በአራቱም ማእዝናት የከበቡት የእንሰያ (ምሥራቅ)፣ ዛሬማ (ምዕራብ)፣ ተከዜ (ሰሜን)፣ ዛሬማና ወይባ (ደቡብ) የተሰኙት ታላላቅ ወንዞችም በሰኔ የሞሉ እስከ ኅዳር አይጎድሉም፡፡ ከሱባኤው ፍጻሜ በኋላ፣ ኅዳር ስምንት ቀን የአርባእቱ እንስሳ ክብረ በዓል ቀን፣ ወንዞቹን ተሻግረው በምሥራቅ - ፀለምትና በምዕራብ - ወልቃይት በሚገኙ የገዳሙ እርሻ ቦታዎች ከተዘጋጀው ድግስ የሚቀምሱ አሉ፡፡ ለዚህም በተለይም ማይ ለበጣ ታላቁ የማኅበሩ መገናኛ ቦታ ነው፡፡
የዘንድሮው የገዳሙ የሱባኤ ወቅት ግን ይህን ለዘመናት የቆየ የአበው ሥርዐትና ትውፊት የሚደግምበትን የጥሞና ጊዜ የታደለ አይመስልም፡፡ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት በገዳሙ ህልውናና ክብር ላይ በጋረጠው ስጋት ሳቢያ የሰቋር ኪዳነ ምሕረት ማኅበረ መነኰሳት በተለይም ከግንቦት 22 ቀን ጀምሮ “ኑ ፣ ታቦቱን፣ ቅርሱን ተረከቡ፤ እኛ እንፈልሳለን (ወደ በርሓ እንሰወራለን)” በሚል ለምእመኑ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ከስድስት ያላነሱ የዓዲ አርቃይ ወረዳ ቀበሌዎች (ሳንቅ፣ ዛሬማ፣ ያሊ፣ የጥራይና፣ ጅሮሰ፣ ነብራና ፍድቃ) አርሶ አደሮች ከግንቦት 23 እና 24 ቀን አንሥቶ ዛሬማና ሰቋር ላይ በመሰብሰብ ተቃውሟቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ተነግሯል፡፡
የአማራ ብ/ክ/መ ፖሊስ ኮማንደርና የሰሜን ጎንደር ዞን ብአዴን ጽ/ቤት ሓላፊ ግንቦት 27 እና 28 ቀን ዛሬማ ቀበሌ ላይ የወረዳ አመራሮችንና ምእመኑን በአንድነት ጠርተው ስለ ፕሮጀክቱ ለማሳመን ስብሰባዎችን አካሂደዋል፡፡ ይኹንና በዚያው ዛሬማ ቀበሌ የመድኃኔዓለም ታቦት ማረፊያ ዋርካ ሥር በመገናኘት ስብሰባው አሳታፊ አለመኾኑንና በስብሰባው ላይ ተገኝተው አቋማቸውን እንዳይገልጹ መከልከላቸው አግባብ አለመኾኑን በመቃወም እስከ 50 ያህል ወጣቶችን ለእስር ከመዳረግና በጭከና ከመደብደብ በቀር ውጤት እንዳላስገኘላቸው ነው የተዘገበው፡፡ ግንቦት 29 ቀን ከታሰሩት ኀምሳዎቹ ወጣቶች መካከል “ወጣቱን ለስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ቀስቅሰዋል፤ ከተቃዋሚዎች ጋራ በመገናኘት እንቅስቃሴውን አስተባብረዋል፤” በሚል ስምንት ወጣቶች ተለይተው ከዛሬማ ቀበሌ 40 ኪ.ሜ ወደሚርቀው የወረዳው ከተማ (ዓዲ አርቃይ ፖሊስ ጣቢያ) ሲወሰዱ ሌሎቹ በዋስና በገንዘብ ቅጣት ደረጃ በደረጃ መለቀቃቸው ተገልጧል፡፡
ይህ ሁሉ ሲኾን የዋልድባ ገዳም የሚገኝባቸው ሦስቱ አህጉረ ስብከት ይኹን ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ድምፃቸውን ባለማሰማታቸው ምእመኑ ከዘንድሮው ዓመት ጀምሮ “የነፍስ ዐሥራት በኵራት” ሲል የሚጠራውን መባዕና የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦ እንደማይከፍል ለወረዳ ቤተ ክህነት በጻፈው ደብዳቤ ማስታወቁ ተመልክቷል፡፡ የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱ ጉዳዩን ለአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች ያስታወቁ ቢኾንም ምን ምላሽ እንደተሰጠ ለማወቅ አልተቻለም፡፡
የተቃውሞው ከዕለት ወደ ዕለት መጠናከር ያሳሰበው የክልሉ (የአማራ ብ/ክ/መ) አስተዳደር፣ ፕሬዝዳንቱን አቶ አያሌው ጎበዜን፣ የክልልና ዞን ጸጥታ ሓላፊዎች እንዲሁም የብአዴን ጽ/ቤት ሓላፊዎች በተገኙበት ሰኔ ሰባት ቀን 2004 ዓ.ም ዓዲ አርቃይ ላይ ስብሰባ ጠርቶ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ከዋልድባ አብረንታንት ቤተ ጣዕማና ቤተ ሚናስ፣ የሰቋር ኪዳነ ምሕረትና ዳልሽሓ ኪዳነ ምሕረት ገዳማት ከእያንዳንዳቸው ዐሥር፣ ዐሥር መነኰሳት፤ 28 የቀበሌ አመራሮችና “የልማት አርበኛ” የተሰኙ አርሶ አደሮች እንዲሳተፉ ጥሪ ተደርጎላቸው ነበር፡፡
የክልል፣ የዞንና ወረዳዎች (ደባርቅ፣ ፀለምት - ማይ ፀብሪ፣ ዓዲ አርቃይና ጎንደር) አመራሮች የታደሙበት ይኸው ስብሰባ ልጆቻቸው በታሰሩባቸው ወላጆች ጥያቄ ከዓዲ አርቃይ ወደ ዛሬማ እንዲዞር የተደረገ ቢኾንም በስብሰባው ከተሳተፉት ብዙኀኑ “ከጎንደር እስከ ማይ ፀብሪ ያሉ የኢሕአዴግ ደጋፊዎችና የተለየ ሐሳብ የማያነሡ ናቸው” ብለዋል ታዛቢዎች፡፡ ከዋልድባ አብረንታንት ዘቤተ ጣዕማ ስድስት መነኰሳት ቢገኙም ከዋልድባ አብረንታንት ዘቤተ ሚናስ ማኅበር የታየ አልነበረም፡፡ ከሰቋር እና ዳልሽሓ የተገኙትም የተወሰኑት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በጸሎት ሲያሳርጉ ከመሰብሰቢያው ወጥተው ሄደዋል፤ የቀሩትም ባሉበት በመቀመጥ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፤ መስቀላቸውንም ለመሳለም ፈቃደኛ አልኾኑም፡፡
በዚሁ ስብሰባ እንደ ማይ ፀብሪው አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ መረሳ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት፡- “ሃይማኖትን ሽፋን እያደረጋችኹ የፖለቲካ ዘመቻ ታደርጋላችኹ፤ የፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰለባ ኾናችኋል፤ የእነርሱን ድምፅ ነው የምታስተጋቡ” በማለት ግልጽ ዘለፋ ማሰማታቸው ተገልጧል፡፡ “ብትስማሙና ልማት ቢለማ ምናለበት?” የሚሉ ልመናዎችም ተደምጠዋል፡፡ መነኰሳቱ በበኩላቸው “በልቅሶ ነው ያለነው፤ ዐፅም ወጥቶ ውኃ አይቆምም፤ ቤተ ክርስቲያን እየፈረሰ በሚለማ ልማት አንስማማም፤ ዋልድባ ቅንጣት ያህል አትነካም›፤ ይህ የሃይማኖት ጉዳይ እንጂ ፖለቲካ አይደለም” በሚል ቁርጡን ማስታወቃቸው ተነግሯል፡፡
በዚሁ ስብሰባ ዋዜማ፣ ሰኔ ስድስት ቀን 2004 ዓ.ም፣ በዓዲ አርቃይ ከተማ አስጋሪት ማርያም በተሰኘችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተገናኙ የከተማው ወጣቶች ስብሰባው ወደሚካሄድበት ዛሬማ ቀበሌ በመሄድ ድምፃቸውን ለማሰማት እየተመካከሩ በነበረበት ወቅት የወረዳው ፖሊስ ደርሶ በሽመል በመደብደብ እንዲበተኑ ማድረጉን የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት በምትገኘው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰብሰበው የነበሩት ቁጥራቸው ከ30 የማያንሱ ወጣቶች ከተበታተኑ በኋላ ፖሊስ በየቤቱ በመዞር ወላጆች ልጆቻቸውን ይህን ዐይነቱ የተቃውሞ ምክክር ከማድረግ እንዲቆጠቡ የማይመክር ከኾነ ጥብቅ ርምጃ እንደሚወስድባቸው ሲያሳስብ መዋሉ ታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ንድፉ በትግራይ ውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ተሠርቶ በትግራይ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ግንባታው የተጀመረውን የዛሬማ ወንዝ ግድብ ሥራ ተረክቦ ሲመራ የቆየው ሱር ኮንስትራክሽን ሥራውን አቋርጦ መውጣቱ ተሰምቷል፤ ምክንያቱ ቁፋሮው የሚካሄድበት ቦታ ከመሬት በሚፈልቅ ውኃ እየተሞላ ማስቸገሩና የምእመኑ ተቃውሞ ያሳደረው ግፊት ነው ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስሙ ያልተገለጸ አንድ የቻይና ተቋራጭ የግድቡን ሥራ ለመቀጠል የተተካ ቢኾንም በተመሳሳይ አስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡ የሱር ኮንስትራክሽን መውጣት ከተጠቀሰው ምክንያት ጋራ መያያዙን የሚጠራጠሩ ሌሎች ምንጮች በበኩላቸው፣ በግድቡ ዲዛይን (የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ውኃ አጠቃቀም) ላይ መሠረታዊ ለውጥ በማድረግ ሥራውን ለመቀጠል ሳይታሰብ እንዳልቀረ ያላቸውን ሐሳብ ገልጸዋል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን።