Tue, 06/19/2012 - 08:16
ዓለማየሁ ገላጋይ
ሮማዊው የታሪክ ሰው Tranquillus suetonius (75-150)ዓ.ም “Lives of the twelve Caesars” የሚል መጽሐፍ አለው። የአሥራ ሁለት ቄሳሮችን ስንክሳር ያካተተበት ሥራው ነው። ከእነዚህ ቄሳሮች መካከል ‹‹እብዱ›› በሚል ተቀጥላ የሚጠራው ካሊጉላን (Caligula) ነው። በእርግጥም አንዳንድ የቄሳሩ ተግባሮች ጤነኞች የሚያከናውኗቸው አይደሉም። ለምሳሌ መኳንንቱና ሹማምንቱ እንዲሁም መሳፍንቱ በተገኙበት አዳራሽ ውስጥ ሚስቱ ቄሶኒያ (Caesonia) እርቃነ-ሥጋዋን እንድትመጣ ያዝዛታል። ልብሷን ጥላ እራቁቷን ስትመጣ የአዳራሹን ሁናቴ ይቃኛል። ከዚህ የሚያገኘውን ትርፍ እራሱ ካሊጉላ ይወቀው። ሌላም የእብድ መዝናኛ አለው። በመኳንንቱ ፊት መኳንንቱ እርስ በእርስ ትግል እንዲገጥሙ ማዘዝ። አንዱ ይጥላል፣ ሌላው ይወድቃል። ካሊጉላ ይስቃል። ቄሳሩ ከሳቀ የተቀረው መኳንንት አያኮርፍም- አብሮ ያውካካል። ከዚህ ትዕይንት ካሊጉላ የሚያተርፈው መዝናናትን ብቻ አልነበረም። ፖለቲካዊ ረብጣም አለው። የወደቀው መኳንንት በጣለው መኳንንት ላይ ያቄማል፤ ጠላትነትም ያበቅላል። እርስ በእርስ ተፈላላጊ ይሆናሉ።
ወደኛ አገር እንምጣ… …ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማሪያም ‹‹ኦቶባዮግራፊ (የህይወቴ ታሪክ)›› የተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ የሚያስተዋውቁን ልጅ ኢያሱም የካሊጉላ ከፊል መንፈስ ያረፈባቸው ናቸው። የተከበሩትን መኳንንቶች ለእረኝነት እንደወጣ ኩታራ ትግል ያጋጥሟቸዋል። ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹… ታዲያ ልጅ ኢያሱ ቀኛዝማች ወልደአማኑኤልንና ቀኛዝማች ፋሪስን አታገሏቸው። ቀኛዝማች ወልደአማኑኤል በንቀት አስተያየት እያየ ተጋጠመ። (ቀኛዝማች ወልደአማኑኤል በራስ መኮንን ቤት ጉልበታምነቱ የታወቀ ነው።) ቀኛዝማች ፋሪስ ጣለ፣ ልጅ ኢያሱ እያጨበጨቡ ደስታቸውን ገለጡ። እኛ ግን ዐፈርን። ቀኛዝማች ወልደአማኑኤል ተገረመና እንደገና ታገሉ። ቀኛዝማች ወልደአማኑኤል ጣለ።››
በፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ግምጋሜ ልጅ ኢያሱ ለመቦረቅ ያመጡት የልጅነት ፍላጐት እንጂ የመኳንንቱን ትግል መግጠም በፖለቲካ ትርፍነት አይተውት አልነበረም። ይሁንና ለታዛቢዎቹ ለእነፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ትግሉ ከግለሰቦች አልፎ ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ሆኖ ተተርጉሞላቸዋል። በቅንፍ ውስጥ ይሄንን ትርጓሜ ጣል ያደርጋሉ። ‹‹በልባችን ውስጥ የሚታገሉት ወልደአማኑኤልና ፋሪስ አይደሉም ሸዋና ወሎ፣ ክርስቲያንና እስላም ናቸው (አልን)›› ይላሉ። የዚያ ወቅት ፖለቲካ ይሄው ነበር። ከሸዋ ወገን እነደጃዝማች ተፈሪ (ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ)፣ ከወሎ እነራስ አሊ (ንጉስ ሚካኤል) የተፋጠጡበት። ትውልዳቸውንና ሃይማኖታቸውን የወከሉት ቀኛዝማቾች በግጥሚያው አንድ ለአንድ ባይወጡ ምን አይነት ቂም ውስጣቸው ይፈጠር ነበር? በእንዴት አይነት ሁኔታስ ወደበቀል ይለወጥ ነበር?
አብዛኛው መንግሥት የራሱን ፖለቲካዊ ሁኔታና ሥልጣን የሚያስጠብቀው ትኩረት የሰጠባቸውን ‹‹ቀኛዝማች ወልደአማኑኤል እና ቀኛዝማች ፋሪስ›› በጠላትነት አኳኩኖ በማታገል ነው። ለምሳሌ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የነበሩ ትግል ገጣሚዎች ‹‹በተወላጅነት›› እና ‹‹በትምህርት›› ሥልጣን የያዙ ሁለት ቡድኖች ነበሩ። የእነዚህ ቡድኖች ጠላትነት በአፄ ኃይለሥላሴ የሥልጣን ማስጠበቅ ፖለቲካዊ ፍላጐት የተፈበረከ ቢሆንም ደርግ እስኪመጣ ድረስ እንደተናነቁ ሥራ መሥራት ተስኗቸው ቆይተዋል። አንዴ አንዱ ሲጥል አፄ ኃይለሥላሴ እንደልጅ እያሱ ያለ ግን ስውር ጭብጨባ በማካሄድ ደስታቸውን ሲገልጡ፤ ሌላ ጊዜ ሌላው ሲጥል እንዲሁ ሲደረግ በመካከል ዋነኛው የንጉሱ ሥልጣን ከመካከላቸው የሚማትረው ሳይኖር ለረጅም ጊዜ ቆይቷል። ስለዚህ ጉዳይ ባህሩ ዘውዴ እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹የአብዛኛዎቹ ሚኒስትሮች የመደብ ጀርባም በንጉሰ ነገሥቱ ፊት ነፃ አቋም ለመውሰድ የሚያደፋፍር አልነበረም። ብዙዎቹ የመሣፍንት ወገን ባለመሆናቸውና ሹመቱና ክብሩንም በቀጥታ ከንጉሠ ነገሥቱ ያገኙ በመሆናቸው ታማኝነታቸው የተረጋገጠ ነበር። በዚህም አኳኋን ንጉሠ-ነገሥቱ ሚኒስትሮቹን የመሣፍንቱን ኃይል ለመቋቋም አይነተኛ መሣሪያው አድርጓቸው ነበር። የድህረ 1933 የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዱ ገፅታ ይህ በመኳንንቱና በመሣፍንቱ መካከል ይካሄድ የነበረው ስውር ትግል ነበር ማለት ይቻላል።›› (‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ…›› ገፅ 213)
በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን በጠላትነት ትግሉን የገጠሙት ከመኳንንቱ ወገን ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ሲሆኑ ከሚኒስትሮች ወገን ደግሞ የእርሻ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የሆኑት መኮንን ኃብተወልድ ናቸው። ሁለቱም በሥራቸው የስለላ ቡድን በማቋቋም አንዱ የሌላውን ድክመት ሲያነፈንፍ ይውልና ያድር ነበር።
በደርግ ዘመን ‹‹ቀኛዝማች ወልደአማኑኤልም ሆነ ቀኛዝማች ፋሪስ›› እራሱ ደርግ ነበር። ለጠላት ሌላ ጠላት ፈጥሮ ከማታገል ይልቅ አድሀሪ፣ በዝባዥ፣ ከላሽ፣ ቀልባሽ፣ ገንጣይ፣ አስገንጣይ… የሚለውን እራሱ እጅጌውን ሰብስቦ ይገጥማል። ከጣለ በኋላ በአዋጅ ይፎክራል። የሚወረሰውን እራሱ ይወርሳል፣ የሚገደለውን እራሱ ይገድላል፣ የሚሾመውን እራሱ ይሾማል…። በሽኩቻ ጠላት በጠላት እስኪጣፋ አይጠብቅም፣ ትዕግሥት የለውም። ዘው ብሎ እራሱ አጣጥሞ ቁልጭ ለማለት ይፈጥናል።
ወደዚህ ዘመን እንምጣ…
…ከሁሉም ዘመን እጅግ የከፋው የዚህ ወቅት ሽኩቻ ነው። ያለማጋነን ህዝቡ እንዳለ ‹‹ቀኛዝማች ወልደአማኑኤሎችንና፣ ቀኛዝማች ፋሪሶችን›› እንዲሆን ተጥሯል። በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በክልል አስተዳደር፣ በፖለቲካ… እየተናነቀ ሙሉ ትኩረቱን አጠገቡ ያለ ወገኑ ላይ እንዲያደርግ እየተሴረ ነው። በገዢዎች የተመደበለትን ተጋጣሚ የመጣል ባዕድ ትልም ግቡ አድርጐ እንዲቀርና ወደላይ እንዳያማትር በዕለት ተዕለት ሽኩቻ እርስ በእርሱ እንዲጠላለፍ ተደርጓል። ከበድ ያሉትን አገር አቀፍ ጉዳዮች ትተን በህግ፣ በፖሊሲና በደንብ እየታከኩ የሚጠሩትን የእርስ-በርስ ጠላትነቶች እንመልከት።
የልማት ተነሺ በመሆናችን ስንት የቀበሌ ነገሥታት እያጣደፉና እያክፋፉ እንድንጠላቸው አደረጉን? መኖሪያችንን በላያችን ላይ ለማፍረስ ሲቋምጥና ሲቁነጠነጥ በማየት ስንት አፍራሽ ግብረኃይል ላይ ቂም ያዝን? ስለመፈናቀሉ
በመደስኮር በቁስላችን እንጨት እየሰደደ ስንቱ ጠላታችን ሆነ? በቤት ግምት ወሽመጣችንን ከቆረጠ ስንት ባለስልጣን ጋር ተቂያቂያምን? ያልተገባ፣ የተጋነነ የቤት ግምት የወሰደ ስንት ጐረቤት ታዘብን?...
….ደግሞ በተከራይ አከራይ ያልተብላላ ደንብ ስንቱ ተባላ? ስንቱስ ስንት የዘለአለም ባላጋራ አፈራ? ምን ያህሉስ ለመጋደል ተፈላለገ? እኔ እንኳን ሦስት አሰቃቂ የተከራይ አከራዮች ጭፍጭፍ አጋጥሞኛል። ሃያ ሁለት አካባቢ ገብርኤል ሆስፒታል መስመር፣ አትክልት ተራ እና ካሳንቺስ። ካልወረስክ መንግሥት ይወርሰዋል የተባለ ተከራይ ምርጫ በማጣት ከአከራዩ ጋር ጥርስ ከተናከሰ በኋላ እንደገና መልስለት በሚል የመንግሥት ትዕዛዝ ነው እንደጐሣ ወረራ በገጀራ ሲጨፋጨፉ የታዩት።
….እናስ? ልጅ ኢያሱ ያታገሏቸውን ቀኛዝማች ወልደአማኑኤልንና ቀኛዝማች ፋሪስን አልሆንም? ያታገለንን ትተን የታገለንን አልጠላንም? ከመታገላችን የሚያተርፈውን ‹‹የፖለቲካ ቁማርተኛ›› አልፈን የኛ ብጤ ሰለባውን ጠላት አላደረግንም? ለመሆኑ ጠላታችን ማነው?

No comments:
Post a Comment