Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday 5 December 2012

ጫጭር የሀገር ቤት ምናብ-አከል ዜናዎች – ቁጥር 3

ከይነጋል በላቸው፣ አዲስ አበባ
አዲሱ ሹመት የጭቡ መሆኑን ዜጎች ገለጹ
Ethiopian news from Addis Ababa“የሰሞኑ የወያኔዎች የቁጭ በሉ ሹመት የልጅነት ጊዜ የዕቃ ዕቃ ጨዋታን ያስታውሰኛል፡፡ እልም ያለ ዐይን ያወጣ የጭቡ ሥራ ነው፡፡ ማንን ሊያታልሉ ይሆን እንዲህ እንሻቸው የሚጥሱትን የራሳቸውን ሕገ መንግሥት ተብዬ ሳይቀር ሽረው ይህን የመሰለ ከማሳቅ ባለፈ የማንንም ቀልብ የማይስብ የአራድነት አይሉት የቂልነት ሥራ የሚሠሩት?” በማለት የገለጡት አንድ የመንደር አዛውንት እንደዚህ ዓይነት ለአንዲት ድሃ ሀገር ለታይታዊው የማስመሰል ቲያትር ሲባል ብቻ ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን በመደርደር የብሔሮችን የሥልጣን እኩልነት ለማሳየት መሞከራቸው ሕዝቡን የመሳደብ በንቀት ልምጭም የመማታት ያህል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የተቀረው ዓለም ሀገሪቱን ቀጥቅጦና አንቀጥቅጦ እየገዛት ያለው ከየትኛው ዘውግ የወጣ የአሰለጦች ቡድን መሆኑን በግልጽ እያወቁት ይህን ድርጊት መፈጸማቸው እነዚህ በሕዝብ ላይ እንደመዥገር ተጣብቀው ሀኪም ይንቀለን ያሉት የመለስ የጡት ልጆች ሀፍረት የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው መሆናቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጠፈር ምርምርና የመንኮራኩር ማምጠቅ ዋና ክፍል ዳይሬክቶሬት የሆኑት ዶክተር ሐጎስ ገመቹ ደስታ እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል፡- “ እኔ በውነቱ እንዲህ ያለ የማጭበርበር ሥራ አይቼም ሆነ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ሕዝብን መናቅ ነው፡፡ ዓለምን መናቅ ነው፡፡ የሰውን ልጅ የንቃተ ኅሊና የዕድገት ደረጃ መናቅ ነው፡፡ ለነገሩ በቅርጽ ካልሆነ ከጥንትም ቢሆን በይዘታቸው ሰዎች ስላይደሉ እንጂ ራሳቸውንም ግምት ውስጥ የሚከት ሥራ ነው የሠሩት፡፡ እስኪ በሞቴ ይሄ ነገር የነሱን የውስጥ ችግር ወይም ሞኛሞኝ የሥልጣን ጥማትና ሽሚያ  በተወሰነ ደረጃ ጋብ ያደርግ እንደሆነ እንጂ የትኛውን የሕዝብ ክፍል ሊያስደስት ወይም ሊማርክ ይችላል? ጡት ያልጣልን ሕጻናት መሰልናቸው ይሆን? ይሁን እንበልና ከተሾሙት ሁለቱ ማለትም አማራንና ኦሮሞን ይወክላሉ የተባሉት ሰዎች ሥልጣናቸውን በትክክል እንደሚጠቀሙበት አምነን እንቀበልላቸው፡፡


 በአፍሪካ ሊያውም ከሰሃራ በታች በምትገኝ የድሆች ሀገር ውስጥ ለአንድ ቦታ ሦስት ሰው መድቦ ከማተራመስ አንድ ከየትኛውም ጎሣ በ‹ሜሪት›(በብቃቱ) ተመርጦ ሌሎቹ ሌላ ቦታ ላይ ቢመደቡ ምን ነበረበት? ደግሞስ ሁለትና ከሁለት በላይ የቢሮ ኃላፊነቶችን ደርበውና ደራርበው የያዙት – ለምሳሌ እንደከድርና ደብረጽዮን – ሌላ ሰው ጠፍቶ ነው? በዚህ መልክስ ቀሪው ሰማንያው ብሔር/ብሔረሰብ ቢያኮርፍ በሀገሪቱ ጎሣዎች ልክ – 80 ጠቅላይ ሚኒስትር፣ 80 ም/ጠቅላይ ሚኒስትር፣ 80 የጦር አዛዥ፣ 80 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ 80 የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር፣ 80 የጅምሩክ ኃላፊ፣ 80 የባንክና ኢንሹራንስ ኃላፊ፣ 80 … 80… 80… ከየዘውጉና ከየነገዱ ሊሾም ነው? እስኪ የነዚህን ሰዎች ሞኝነት ለአፍታ እንቃኘው፡፡

ምን ዓይነት ቂልነት ነው! ሁሉንም ሥልጣንም ሆነ የሀብት ምንጭ ካላንዳች የረባ ተቀናቃኝ ለብቻው ጨምድዶ የያዘውና ማንም ወደነዚያ ሥፍራዎች ዝር እንዳይልበት በአብዛኛው ከራሱ ጎሣ በተመለመለ የማይማን የጦር አለቃና የዕውቀት አድማሱ የምግብ ሰዓቶችን ጠብቆ ከመመገብ በማያልፍ ምንዝር ወታደር ሌት ተቀን በጥብቅ የሚያስጠብቀው ቡድን የማይታወቅ መስሏቸው ይሆን? ደኅንነቱንና አጠቃላዩን የፀጥታውን መዋቅር ከነሀገሪቱ የገቢ ምንጮች – አየሩንም፣ ውኃውንም፣ ፀሐዩዋንም፣ ምድሩንም፣  ወንዞቹንም፣ተራሮቹንም፣ ዛፎቹንም፣ በጥቅሉ የዜጎችን ነፍስና ሥጋ ሳይቀር ሁሉንም በቅርብ ርቀት እየተቆጣጠረ ዜጎች ሕይወታቸውን በሰቀቀን እንዲገፉ እያደረገ ያለው ማን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ታዲያ ይህን የማስመሰል የሥልጣን ዕደላ ምን አመጣው? …” በማለት በመረረ ስሜት አብራርተዋል – ዶክተር ሐጎስ ገመቹ ደስታ፡፡

በተያያዘ ዜና ‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት ሰጡ› እየተባለ የሚወራው ትክክል አለመሆኑን ጥቂት የማይባሉ ዜጎች አባባሉ እንዲስተካከል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአንድ መ/ቤት ሠራተኛ “ለመሆኑ እንኳንስ ለሌላ ሰው ትልቅ ሹመት ሊሰጡ ይቅርና ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው የሚባሉት ሰውዬስ እውነተኛው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት አላቸው እንዴ? በመለስ የሙት መንፈስ የሚመራው የገዢው ቡድን ርዝራዥ በህቡዕ እየተሰበሰበ የሚወስነውን ውሳኔ በመመሪያ መልክ እየተቀበሉ ተውነው ላይተውኑት በሚዲያ ያስተላልፉ እንደሆነ እንጂ ትክክለኛ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ቀርቶ የቤተ መንግሥት የጥበቃ ኃላፊን ያህል መብትና ሥልጣን የላቸውም ፤ ስለዚህ ‹ሹመት ሰጡ› ሳይሆን መባል ያለበት ‹ድብቁ የወያኔ መንግሥት ሹመት መስጠቱን ቃል አቀባዩ ጠቅላይ የቢሮ ጠባቂ አስታወቁ› ነው፡፡

የምን ቀልድ ነው? ሰውዬው መብቴን ልጠቀም ቢሉ ከኋላቸው ማን እንዳለ ማወቅ ይገባል፡፡ በጠመንጃ ኃይልና በጥቅም ለማሠር በሚደረግ ሙከራ አንዳች ነገር እንዲያከናውን ጥረት ይደረግ የነበረው ለወትሮው በእሥር ቤት የሚገኝን ምሥኪን ዜጋ ነበር – በዚህ የወራዳ ተግባርም አንድም ምርጫዎቹ ይጠቡበትና ከእሥር ለመውጣት ሲል የሚባለውን ያደርጋል አንድም በዓላማው እስከመጨረሻው ፀንቶ  ለጥቅም ሳይንበረከክ የሚመጣበትን ሁሉ በፀጋ ይቀበላል – እንደነእስክንድር ነጋ፡፡ አሁን ደግሞ ዘመን ተገለባብጦ  በእውን ይቅርና በህልሙ ያላሰበውን ትልቁን የሀገር ሥልጣን ለአንድ ምሥኪን ወገን በማስጨበጥ የሃይማኖት ቀኖናንም በማስረሳት ‹ነጻ› ሊሆን የሚችልንና የሚገባውንም ሰው የጥቅም እሥረኛ (a hostage to fortune) በማድረግ  የራስን ተልእኮ በሌላ ሰው በተዛዋሪ ማሣካት ኢትዮጵያ ውስጥ በአዲስ ታሪክነት እየተመዘገበ ነው፡፡ ይህ እንግዳ ክስተት በ‹Ghinus Buk of Rikerds› ይመዝገብልን፡፡…” በማለት ገልጠዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ ዘመን ትግሬ ተጠቃሚ ነው የሚባለውን በአንዳንዶች ዘንድ ጠርዝ የለቀቀ አስተያየት በሚመለከት አንድ ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ ተከታታያችን እንዲህ ብለዋል፡- “ይሄ ነገር በጣም ልንነጋገርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ወያኔዎች እርግጥ ነው በትግሬዎች ተጠቃሚነት የሚያምኑና ሌላውም ሕዝብ በዚህ ሃሳብ እንዲያምን የሚጥሩ በውጤቱም መከፋፈሉ ጠንክሮ እንዲቀጥል የሚፈልጉ በሕዝብና ሕዝብ መሀል ሽብልቅ የሚቀበቅቡ መጥፎ ሰዎች ናቸው፡፡ የወያኔዎች ዓይነተኛ የአገዛዝ ዘይቤ ሕዝብን በተለያዩ ነገሮች መከፋፈል ነውና ሕዝብ ሲስማማ አይወዱም፤ ደማቸው ይንተከተካል፡፡ እናም ‹በዚህ ሥርዓት ትግሬ ተጠቅሟል› የሚባለውን ነገር ማጤን አለብን፡፡ የተጠቀመ አለ፤ ያልተጠቀመና እንዲያውም የተጎዳም አለ ብቻ ሳይሆን እጅግ ብዙ ነው፡፡ አማራና ሌላም ሆኖ በዚህ ሥርዓት የተጠቀመ ወገኖቹንም የጠቀመ ሞልቷል – ለከርሱ ያደረ፡፡ እርግጥ ነው የሥልጣን ቦታዎች በአብዛኛው በታማኝ ትግሬዎች መሞላቱ አይካድም፡፡

በዚያ ላይ ማይምት ጥቁር መጋጃውን ባጠላበት የኛን በመሰለ ማኅበረሰብ ውስጥ ‹ዘር ከልጓም ይስባል› ወይም ‹የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ›ና ‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል› የሚሉት አባባሎች የተወሰነ አንድምታ እንደሚኖራቸው መረዳት ተገቢ ነው፡፡  ከዚህ አኳያ በወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ እየተታለሉ በስመ ትግሬነት የማይነጋ መስሏቸው አንድ አምሳል አንድ አካል የሆነውን ሌላውን ወገናቸውን የሚበድሉ በብዛት ስላሉ እነዚህኞቹን ትግሬዎች መለየትና አንቅሮ መትፋት ይገባል እንጂ አሁንም በስመ ትግሬ እሰሊጥ ውስጥ የተገኘሽ መጭ አብረሽ ተወቀጭ ዓይነት ሁሉም በጅምላ መወቀስና መጠላት የለበትም፡፡

እንደሌላው ወገኑ በርሀብ የሚገረፈው በስደት በየዐረቡ ዓለም በግርድና የሚንከራተተው ሕዝባችን በጎሣና በነገድ ተከፋፍሎ ሳይሆን ትግሬውም ኦሮሞውም ከምባታና ሃዲያውም እስላሙም ክርስቲያኑም ፐሮቴሰታንቱም ሁሉም ዜጋ ኢትዮጵያዊነቱ ባመጠባት የዘመን ወረርሽኝ ተጠቅቶ በገዛ ሀገሩ የበይ ተመልካች በመሆኑ ነው፡፡ ሁሉም ትግሬ ተጠቃሚ ቢሆን አንድም የትግሬ ስደተኛ ባልተገኘ ነበር፤ አንድም የትግሬ የዐረብ ሀገር ገረድ ባልኖረ፡፡ አንድም አምባሻ ሻጭና ሊያውም መቀሌ ላይ ሳዋ(ጠላ) ቸርቻሪ ባልታዬ ነበር፡፡ ችግራችን ውስብስብ ያለ ነው ጎበዝ፡፡ ይህ ነገር እነዲያውም የዕዝ ነገር እንጂ የሌላ አይመስልም፡፡ መለስን የመሰሉ የ20 እና የ19 ዓመት ዕድሜ እምቦቀቅላዎች በረሃ ወርደው ይህን ያህል ሀገራዊ ትርምስና ይህን ያህል የታላቅ ታሪካዊት ሀገር ውድመትና ጥፋት ያመጣሉ ብሎ ያሰበ ቀርቶ ያለመ ማን ነበር? ስለዚህ ዕዝ ነው – ዕዝ ነው ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ግን ለባሰ አደጋ እንደሚያጋልጥ ሁሉም መገንዘብ አለበት፡፡ በዚሁ ይማረን ብሎ መለመንና የበኩልን የትግል ድርሻ መወጣት ነው ዋናው፡፡

እናም እንደሕዝብ ትግሬውም ከአማራውና ሌላው ሕዝብ ባልተናነሰ ሁኔታ በዚህ ሥርዓት ተጎድቷልና ይህን እውነት አንርሳ፡፡ ከሥርዓቱ አቀንቃኞች በአንጻራዊነት ጥቂት ሊባሉ ከሚችሉ ግን በምልዓታቸው መላዋን ኢትዮጵያን ከወረሩ የጠላት ምንደኞች በስተቀር በሚሊዮን የሚገመተው ትግሬ እንደሌላው ሕዝብ እንዲያውም ከሌላውም ሕዝብ በተለዬና በከፋ ሁኔታ እንደታፈነና በኢኮኖሚውም እንደተጎሳቆለ መረዳት  ይቻላል – የትግራይ መብለጭለጭ ለጭቁኑ ትግራዋይ የፈየደለት አንዳም ነገር የለም፤ የሚኖረው ያው የጥንቱን የድህነት ኑሮ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ የትግሬ ለማኝ የለም? መጥረጊያና ቁራሌ ይዞ የሚዞረው ሁሉ ከሥነ ልቦናዊ ሆድ የማይሞላ እርካታ ውጪ በውነቱ ምን አገኘ? ሰሞኑን ቤት ከፈረሰባቸው ዜጎች መካከል ትግሬዎች የሉም? ትግሬነታቸው ቀርቶ መመለክ የደረሰውን የመለስን ፎቶ ይዘው መውጣታቸው ከበረንዳ አዳሪነት አላዳናቸውም፡፡

እናስ ወገኖቻችንን ባልተጠቀሙበት ነገር ለምን ከሁለት ያጣ ጎመን እንዳርጋቸዋለን? ማንን ይመኑ? በተቃዋሚዎች ቲቪ ሲናገሩ ከሚደመጡ ከአንደበታቸው ትግርኛ ተናጋሪ መሆናቸው ከሚታወቅ አስተያየት ሰጪ ወገኖች እንደምንሰማው ትግራይ ውስጥ ያለው ነጻነት ከሌላው አካባቢ በጣም የወረደና የማያፈናፍን እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል – እርግጥ ነው የሥርዓቱ ተጠቃሚ ትግሬዎች የሚናገሩትንም እንሰማለን፡፡ እነሱ በበሉበት እንደሚጮኹት ውሾች የሚቆጠሩ ናቸው፤ ሁሉንም አይወክሉም – ከአማራውም ለምን ጥቅሜ ተነካ ብሎ ጭቃማ ልፋጭ አስተሳሰቡን ሲናገር ማዳመጣችን አልቀረም፤ መብቱ ነው ይናገር፡፡ እንግዲያውስ ታዲያን ለዚህ ሥርዓት ጠብ እርግፍ የሚሉ አማሮችስ ሞልተው የለም? ሆድ መጥፎ ነው – ደግነቱ ከፊት ለፊታችን መሆኑ በጄን፤ ከኋላችን ቢሆን ኖሮ ገፍሮ ገደል ይከተን ነበር፡፡ ስለዚህ አስተውለን መራመዱና ጠላትን ከወዳጅ፣ ጨቋኝን ከተጨቋኝ መለየቱ ከዳግመኛ ስህተት ይሠውረናልና መጠንቀቁ አይከፋም፡፡ … “ በማለት በንዴት እየቶንቶገቶጉ ገልጸዋል፡፡ ለወደፊቱ በተለዬ ቃለ መጠይቅ እንደምናገኛቸው ተስፋ አለን፡፡

አንድ ሌላ ግለሰብ ደግሞ እንዲህ ብለዋል፡- “ እኛ ኢትዮጵያን አንዳንዴ ጠላታችንንና ወዳጃችንን እመለየቱ ላይ ችግር ቢጤ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ‹ዐይጥ በበላ ዳዋ ተመታ› ይባላል፡፡ እኛም ዐይጢትን ያገኘን እየመሰለን አጠገባችን የሚገኝን እንደኛው ጭቁን ትግሬ ብንሸረድደውና በነገር ካልቾ ብንጎንፈው ዋናውን ጠላት ያገኘን መስሎን በደስታ እንዳንፈነዳ አደራ፡፡ ዐይጢቷን ላናገኝ ዳዋውን ብንመታው ከሁለት ያጣን ሆነን እንቀራለን – በዚያም ምክንያት ከጠላት ሠፈር እያመለጠና ወደኅሊናው እየተመለሰ ትግላችንን ሊቀላቀል የሚፈልገውን ወገን በዚያው ባለበት የወያኔን ሽንንነት ችሎ እንዲኖር እንገፋፋዋለን፡፡ ለዚህ መድኃኒቱ እንደስከዛሬው ጌታውን እዬፈሩ ገበር ገበሩን በነገር ጦር ከመደሰቅ ይልቅ ልብ ያለው ዋናው የጠላት ሠፈር ገብቶ በጨበጣ መተጋተግ ነው፡፡ ትግርኛ ቋንቋንና ትግርኛ ዘፈንን ስንሰማ የሚያንዘረዝረን ወገኖች ጠበል መሄድና ራሳችንን በአዲስ የፍቅር ዜማ ማደስ ይኖርብናል፡፡ ስንፋቀርና ስንዋደድ ችግራችንን እንረዳዳለን፤ ስንጣላና ስንቆራቆስ ወያኔን እናስደስታለን – እኛም እንደተለያየን እንኖራለን፡፡ምሥጢሩ እዚህ ላይ ነው ወገኖቼ፤ እስከዛሬ ተበልጠናል፡፡ ግዴላችሁም ወደየኅሊናችን እንመለስ፡፡ የተሳሳተን እንምከር፡፡ የኛንም አጠቃላይ አካሄድና አስተሳሰብ እንፈትሽ፤ በጊዜም እናርቀው፤ የእስካሁኑ በጭራሽ አልጠቀመንም – ይበልጥ አፈራቀቀን እንጂ፡፡ እምቢ የሚለንን  አውግዘን ከማኅበራችን እንናስወጣውና እንደፈሳ(ች) ዝንጀሮ ብቻውን በማስቀመጥና ለጠጠት በመዳረግ እናስተምረው፤ ሰው እኮ ሊማርና ከስህተተኛ መንገድም ሊወጣ የሚችል ፍጡር ነው፡፡ ዕድሉን ግን መስጠት ይገባል – ለኛም ለሌላውም፡፡” የዚህን ሰው መሬት ጠብ የማይል አስተያየት ብንሰማ ለአብሮነት የጋራ ሕይወታችን መሠረት የሚጥልና ተስፋን የሚያለመልም ደግ ምክር መሆኑን ዘጋቢያችን በአንክሮ ጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም የመሪዎቹን ስብዕና በተመለከተ አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ አስተያየት ሰጪ እንደተናገሩት ከሆነ ኢትዮጵያን እየገዙ ያሉት ሰዎች ቀደም ባለ ወቅት ሕዝባዊ እርግማን በወላጆቻቸው ላይ ያረፈባቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌም – እንደሰውዬው ገለጻ ከሆነ – ለምሳሌም መለስንና ባለቤቱን ብንወስድ ሁለቱም የርግማን ውጤቶች በመሆናቸው ኢትዮጵያን የማጥፋት ትልማቸው በአብዛኛው እንደተሳካላቸው መረዳት ይቻላል፡፡ በዘር ስብጥርም ቢሆን የመለስ አያት ከጎጃም የሚወለዱ አማራ እንደነበሩና አዜብም ከጎንደር አማሮች የምትወለድ በተጋቦትና በጠናላት ትዳሯ ሳቢያ ግን ትግሬ መሆንን የመረጠች የዮዲት ጉዲት ገነት ዘውዴ የሥጋም ባይሆን የመንፈስ አክስት መሆኗ ተዘግቧል፡፡ ከአማራነት ወደትግሬነት መለወጥ ደግሞ ‹ጥጃ ጠባ እሆድ ገባ› እንደማለት እንጂ ጦር የሚያማዝዝ የዜግነት ለውጥ አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በመሠረቱ ሰውን በሰውነቱ እንጂ በቋንቋውና በዘር ሐረጉ መተልተል ወያኔያዊ ባሕርይ ስለሆነ የወያኔ ዘመነ መንሱት ሲያልፍ ይሄ የምናየው ግራአጋቢ ነገር ሁሉ ታሪክ ሆኖ ይቀራል፡፡

ይህ  የነአዜብ ዓይነቱ የወገን ለወገን ጥቃት ደግሞ “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ፤ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽም አልወጣ” የሚለውን ባህላዊ ሥነ ቃል የሚያስታውስ እንደሆነ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው አንድ ሰው ጠቁመዋል፡፡  የመለስ አያት የጣሊያን አሽከርና ወገንን የበደሉ ነበሩ፤ ባህላዊ የሥልጣን ማዕረጋቸውም ከጣሊያን የተሰጣቸው ነበር፡፡ የዚሁ የተረገመ ሰውዬ ባለቤትም እንዲሁ ወንድ አያቷ ደጃች ጎላ የጣሊያን ባንዳ የነበሩና ማዕረጉም ከጣሊያን የተሰጣቸው እንደነበረ በታሪክ ተመዝግቦ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለቱ እርጉማን በአንድ ጣሪያ ውስጥ በትዳር ተጣምረው ሀገሪቱን መቀመቅ ከተቱ፡፡ የነሱም ልጆች እየተነባበረ ለሄደ እርግማን የተጋለጡ በመሆናቸው ከአሁኑ እርባና ቢስ ሆነው እዚህ ግባ የሚባል ደረጃ ላይ እንደማይገኙ ሀገር የሚያውቀው ነው፡፡ ይህ የእርግማን ሂደት ግን ሀገርንና ትውልድን መቅኖ እያሳጣ በመሄዱ ከአሁን ወዲያ ሀገራዊና ብሔራዊ እርቅ ወርዶ ሰላም መስፈን የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት የሚያምኑ ዜጎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ምክንያታቸውም እየተረጋገሙ የመኖር ጦስ ዘር እንዳይወጣልን በማድረጉ ነው፡፡ ስለዚህ ጥፋተኛን ከመርገም መመረቅ እንደሚሻል ሊሰመርበት ይገባል ብለዋል – ጥቂት የማይባሉ ዜጎች፡፡

ወያኔ ተለጣፊን በማፍራት የሚስተካከለው እንደሌለ አንድ ታዋቂ የፖለቲካ ተንታኝ ገለጹ

ማፊያው የወያኔ መንግሥት አንድን የፖለቲካም ሆነ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋም ለማዳከም ወይም ጨርሶ ለማጥፋት ሲፈልግ ከጎኑ ወይም ከመሀሉ ተለጣፊን በመፍጠርና ለሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሥፍራዎች በመሰነጣጠቅ የሚስተካከለው እንደሌለ አንድ የፖለቲካ ምሁር ለዜና ማዕከላችን በሰጡት ቃለ መጠይቅ አስታወቁ፡፡ በዚህ መሰል ተግባሩ ሕዝብ ሳይፈልገው ለዚህን ያህል ጊዜ ሥልጣን ላይ እንደተጣበቀ መኖሩንም በቃለ መጠይቃቸው ገልጸዋል፡፡ ወያኔ በል ካለው የድርጅት ቀርቶ የቤት ሠራተኛና የትዳር አጋር ተለጣፊ እንደሚያበጅ የታወቀ ነው፡፡ ዘጋቢያችን የቃለ መጠይቁን አንኳር ጭብጦች እንደሚከተለው አቀናብሮታል፡፡

ጥሪያችንን አክብረው ቢሯችን ድረስ በመምጣት ይህን ቃለ መጠይቅ ሊሰጡን ፈቃደኛ በመሆንዎ በእምዬ ኢትዮጵያ ስም ላመሰግንዎ እወዳለሁ፡፡
እንዴ! ምን ማለትህ ነው? እንዲህማ አትበል፡፡ የጋራ ጉዳያችን አይደለም እንዴ?
አይ፣ ደንብ ስለሆነም በዚያም ላይ በሚዲያ ረገድ እኛ እንደዚህ በድፍረትና በግልጽ ወያኔ ራቁቱን እያስቀረን ስንታገል ቃለ መጠይቅ እንዲሰጡን፣ የሕይወት ተሞክሯቸውን በተለይ ለከርታታው ኢትዮጵያዊ ወጣት እንዲያካፍሉና ከተዘፈቅንባቸው አጠቃላይ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ወፖለቲካዊ ችግሮች መውጫ መንገዶችን እንዲያሳዩ ስንጠይቃቸው የሚኖሩት የሸለምጥማጥና የፍልፈል ተዋራጅና ድብቅ ሕይወትም ኑሮ ተብሎ እምቢ የሚሉ ‹ምሁራን› ስላሉ እርስዎ በድፍረት ቢሯችን ድረስ …

አሃ! እንደሱ ከሆነስ ልክ ነህ ልጄ፡፡ ጉዳዩ እንዲያ ከሆነ በል ጥያቄህን ጀምር፡፡ እውነትህን ነው የእናት ሆድ ዥንጉርጉር አይደል እሚባል? የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ አሉ! ሲጠየቁና አስተያየት ሲሰጡ ድምጻቸው እንደተቀደደ ከበሮ የሚነፋነፈው ለካንስ የድምጽ ጥራት ጉደለት ሳይሆን በትራስና በጨርቅ ግርዶሽ ስለሚናገሩ ኖሯል? መች ገባኝና፡፡ ምን ይደረግ! ግዴለም፤ ይህም ያልፋል ልጄ፡፡ እስኪያልፍ ማልፋቱ ጎዳን እንጂ፡፡

መልካም ክቡር ፕሮፌስር፤ ኢሕአዴግ በሚል የማስመሰያ ካባ የሚጠራው አሰለጡ የትግራይ ዳግማይ ወያኔ በጠላትነት የሚፈርጃቸውን ወገኖች ለማጥፋት ተለጣፊ እንደሚያበጅላቸው የታወቀ ነው፤ እርስዎ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዳለዎ ይነገራል፡፡ ባጭሩ እስኪ ያስረዱን፡፡

ከየትኛው ልጀምርልህ?ከራስጌ ወይንስ ከግርጌ?

ከፈለጉት ይጀምሩ ግዴለም፤ ነገር ግን አንባቢዎቻችንና ተመልካቾቻችን የለውጥ ፍላጎት በወቅቱ እውን ያለመሆን የፈጠሯቸው የአይሞቄ-አይበርዴ የግዴለሽነትና የባዶነት ስሜቶችን ጨምሮ በኑሮ ፈተናና በአንጎል መሰረቅ እንዲሁም በብዙ ነገር የተወጠሩ በመሆናቸው ብዙ ጊዜና ትኩረት እያጡ መጥተዋልና አጠር አጠር ቢያደርጉልኝ ደስ ይለኛል፡፡

ጥሩ፤ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁልህ ወያኔ ተለጣፊን በማምረትና ሁነኛ የሕዝብ አለኝታ የሆኑ የሲቪክና የፖለቲካ ተቋማትን በመፈረካከስ በኩል ከዚች ከምንኖርባት ዓለም ቀርቶ ከዩኒቨርስም የሚስተካከለው እንደሌለ ወጥቼ ወርጄ ያከማቸኋቸው መረጃዎቼ ይመሰክራሉ፡፡ በጣም ብዙናቸው፡፡ አሁን የምነግርህ በቃል የማስታውሳቸውን ነው፡፡ ለዝርዝሩ ብትፈልግ አንዱን ጥራዜን መጥተን መዋስ ትችለህ፡፡ ከራስጌ ልጅምርልህ፡፡ እንዴ ወያኔ እኮ ….

ባለፈው 34 የጦር ጄኔራሎች አልተሾሙም? አዎ፣ ተሹመዋል፡፡ ሊያውም መለስ ከሞተ ወዲህ ነው፡፡ ምን አስፈለገ? የሟች ሬሣ ብራሰልስ ላይ ተጋድሞ የቀባሪ ያለህ እያለ እቤት ውስጥ ሰሜነኛ ማይም የጦር መኮንኖችን የማዕረግ ማሳያ ቁርጥራጭ ብረቶች በከዚህ መለስ ማስጌጥ ልዩ ዓላማ ከሌለው በስተቀር ምን ያደርጋል? ዓላማው በጦሩ ውስጥ ክፍፍልን ለመፍጠርና የገዢው ጡንቻ እንደበፊቱ ቅድመ-መለስ ዘመን እንደሚቀጥል ለወዳጅ ለጠላት ለማሳየት ነው፡፡ አንድ ወዳጄ በቅርቡ በሰጠው ቃል ያ ማን ነው የምትሉት የእንጨት ሽበት ሰውዬ አዎ፣ ስብሃት ነጋ የሚሉት ዕድሜ የማያቃናው ሙግድ አፍ መደዴ ሰውዬ ተናገረው የተባለው አማራንና ኦርቶዶክስን ከመንግሥት ሥልጣን ፎሪ አወጣናቸው ያለውም በሕዝቦች … ኖ… ኖ…ኖ ወያኔ ወገንን ከወገን ለመከፋፈል በሚጠቀምበት ‹ሕዝቦች› በሚለው ፀያፍ ቃልማ መጠቀም የለብኝም በማኅበረሰቦች መካከል ቅሬታንና ግጭትን ለመፍጠር መሆኑ ተገምቷል፡፡

በመሠረቱ ወያኔዎች እንኳንስ ለአንደበታቸው ለድርጊታቸውም አንዳችም ለከት የላቸውም፡፡ ሀገርን ገምድለው ሲሠጡ ያላፈሩ ሰውን ወይም አንድን የሕዝብ/የሃይማኖት ክፍል ሲዘረጥጡና ሲሳደቡ ያፍራሉ ማለት ደግሞ ዘበት ነው፡፡ በአንድ ቤተ መንግሥት ውስጥ ተለጣፊ ጠቅላይ ሚኒስትርና ተለጣፊ ቀዳማዊት እመቤት በመፍጠር ወያኔ በዓለም የመጀመሪያውን ሪከርድ ይዟል፡፡ የዚህን አስቂኝ ድራማ እኛ ቀርተን የናይጄሪያ ኮሜዲያን ሳይቀሩ ያፌዙበት በመሆኑ ሁሉም ያውቀዋልና በጥልቀት አንገባበትም፤ ችግሩ ግን ተለጣፊዎቹ አንዳች ስሜት ተሰምቷቸው ‹በሕዝብ ይሁንታ ተመርጠን ገብተንበት የኛ ባልሆነ ቤተ መንግሥት ውስጥ እንዲህ እየተሳቀቅንና እየተፌዘብን – ከሃይማኖታችንም ከሕዝባችንም ከወዳጅ ዘመዶቻችንም በተለይ በተለይ ከክርስቶስ ቃልም ሳንሆን – የሰው መዘባበቻና የወያኔ መጫወቻ ሆነን ከሚሳቅብን የተማርን ነን፣ ለምን የትም ሄደን በነጻነት ሠርተን ጆቻችንን አናሳድግም?› ብለው በራሳቸው ጊዜ ወይም ጊዜው ራሱ ገፍቷቸው ከዚያ የተረገመ ሥፍራ እስኪወጡ ይህ አስቂኝ ድራማ ይቀጥላል፡፡

እንዲያው በደፈናው ጥቂት ተለጣፊዎችንና ወያኔያዊ የክፍፍል ሸፍጦችን በከዚህም ከዚያም ለመጥቀስ ያህል – አንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርን ለማፈራረስ ሌላ የወያኔ ተለጣፊ ኢመማ ተመሥርቷል፤ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ጉባኤ፣ መኢአድ በብኣዴን፣ ኦነግ በኦህዲድ፣ የጉራጌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ በጉሕዲግ፣ ራሱ ወያኔ በህንፍሽፍሹ ዘመን በተቸካይና በተሃድሶ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት በሀገር ቤትና ውጪ ባለው ‹ቅዱስ› ሲኖዶሶች (‹ቅዱስ› የሚለውን ቃል መጠቀም ስለምንችል ብቻ ብንጠቀም ኃጢኣትነቱ ለጊዜው ባይገለጥልንም እግዚአብሔርን ማታለል ይሆናል፤ በዚህች ምድር በተለይ በዚህ የተመሰቃቀለ የጉድለት ዘመን ቅዱስ ሊባል የሚገባው አንዳችም ነገር የሚገኝ አይመስልምና የቃላት አጠቃቀማችንን ደግመን ደጋግመን መቃኘቱ ደግ ይመስለኛል፤ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በትክክል የማይፈጽም ወገን ቅዱ ለመባል የሚቀረው አለና በቃላት አጠቃቀማችን ዙሪያ ጥናትና ምርምር ማድረግ አለብን፡፡ የግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭነትና ዓለማዊ ድርጊቶችን ያለገደብ ማከናወኛ ሥፍራዎችና ተቋማት ‹ቅዱስ› ማለት ከተቻለ በዩኤስ አሜሪካ እንደልባቸው በሰይጣን ቤተ አምልኮቶች የሚያመልኩ ውሉደ አጋንንትን ምን ልንላቸው ነው?ጫፍ ላይ ለደረሰ ዘመን ግዴላችሁም እውነትን ለመናገር አትፍሩ! ከዚህች ከበከተች ዓለም ምን ሲቀርባችሁ? ሃይማኖትን እኮ እንደሸቀጥ …)

ይቅርታ ፕሮፌሰር፤ ጊዜ ለመቆጠብ ወደዋናው ጉዳይ – ወደገደለው – ቢገቡልኝ፤ በዚያ ላይ እርስዎ በዓለማዊ ትምህርት እንጂ በቴዎሎጂ አይመስለኝም ዲግሪዎችዎን የሠሩትና…

አሃ! መንገድ ሳትሁ? ይቅርታ፡፡ ዋና ጉዳይን ወደ ገደለው አላችሁት? አይ የዛሬ ልጆች የማታመጡት የለ፤ እናልህ ወያኔ ያልከፋፈለው ቡድንና ድርጅት የለም፡፡ ችግሩ የሚከፋፈሉት ወገኖች መድሓኒት መቀመም አቅቷው ይሄ ጠንቀኛ የሰይጣን ፈረስ ወያኔ እየተጫወተባቸው አሁን ድረስ ዘልቋል፤ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አፅመ-ርስት የሚነዳው ቦጅባጃው ወያኔ እስከመቼ እንዲህ እያታለለ እንደሚቆይ የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው፡፡ የተለጣፊ ድርጅት ፍብረካው በድርጅቶች ብቻ ተወስኖ የቀረ አይደለም፡፡ ተለጣፊ ሚስትና ተለጣፊ ባልም እስከመሥራት ይሄዳል፡፡ የዘር ፖለቲካው በተሟሟቀባቸው በተለይ ከ80ዎቹ አጋማሽ እስከ 90ዎቹ እኩሌታ ድረስ ይታዩ የነበሩ ዘረኝነትን መሠረት ያደረጉ የትዳር አለመረጋጋቶችንና ብተናዎችን ትተን በቅርብ ጊዜ የተከሰተን አንድ ኹነት ብናይ የወያኔ ሥራ ምን ያህል ዘግናኝ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በነገራችን ላይ የዶክተር መኮንን ቢሻውን ትዳርም እዚህ ላይ ብናስታውሰው ሀገር የሚያውቀው ስለሆነ ችግር የለውም፡፡ ዶክተር አዳነችና ዶክተር መኮንን የተለያዩት በፖለቲካው ጦስ እንደሆነ ይነገር ነበር፡፡

የቅርብ ጊዜው ኹነት ግን ይህን ይመስላል፤ የአንዱን ሰው ሚስት በጠንቀኛው የ97 ምርጫ ሰበብ ያስሯታል፡፡ በመሀሉ ባል ያጣች ወያኔ ሰውዬውን ትይዛለች፤ ቤት ንብረቱንም ትቆጣጠራለች፡፡ ትንሽ ቆየት ሲልም ያቺ ምሥኪን ኢትዮጵያዊት ያለፍርድ በድብደባ ስቃይ እሥር ቤት እንዳለች ትገደላለች፡፡ በስሟ ይጠራ የነበረው የንግድ ቤት ሁሉ  አሁን በሌላ ስም ተቀይሮ እርሷ ባለማችው ቤት ውስጥ ወያኔዋ ትዘባነን ይዛለች፤ ጠቆም ለማድረግ ብዬ እንጂ በታሪክ ተመዝግቦ ተቀምጧል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው ወያኔ ተለጣፊን ለማዘጋጀት ከግለሰብ እስከ ትልቅ ፓርቲና ድርጅት ድረስ የማይሳነው መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በረሃ ሳለ ጀምሮ የተካነበት ነው፡፡ ግንቦት   20/83ዓ.ም አዲስ አበባ ሲገቡ ከሃያ የማያንሱ ማስመሰያ ተለጣፊዎችን ከምርኮኛ ወታደሩም ከሲቪሉም ከስደተኛውም ከእሥር ቤት ካመለጡም አውሸልሽሎ በማምረት ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተብዬውን ሲያጭበረብርበት ነበር፤ ለነገሩ ለዚህ ሁሉ የማጭበርበር ሥራው የኃያላኑ መንግሥታት የደኅንነት ተቋማት የቴክኒክና የማቴሪያል የገንዘብም እገዛና ምክር ያለበት ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ኢትዮጵያን ለምን እንደሚፈሯት አላውቅም ፤ ግን ይህችን ሀገርና ይህን ምሥኪን የእግዜር ፍጡር ሕዝብ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ቀና ደፋ የማይል የዓለም ሀገር የለም፡፡

ይሁንና ከሞላ ጎደል ሁሉም የሥራውን እያገኘ ነው፡- ሱዳንን ውሰድ – ተሰነጠቀች፡፡ ሦርያን ውሰድ ተፍረከረከች፡፡ ኢራቅን   ተመልከት – አበሳዋን እያየች ናት፡፡ ሊቢያን ውሰድ – እንደምታውቀው ነው፡፡ ስንቱን ጠቅሼልህ – የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ይህችን ሀገር የነኩ ያስነኩ ያነካኩ አንዳቸውም ሰላም አያገኙም፡፡ ከጭንቅላቴ ፀጉር ይነቀል ለወደፊቱ ለማየት ያብቃህ…፡፡ በዚህ ጥናት ዙሪያ ዕድሜየን ብቻ ሳይሆን ፀጉሬንም ፈጅቼ መላጣ የሆንኩበት ስለሆነ ኢትዮጵያን ያበሳቆለች እያንዳንዷ ሀገርና ግለሰብ ምሷን ሳትቀምስ አትቀርም፡፡ አሄሄ… አንድዬ የት ሄዶ? የእናቱ ሀገር – የአሥራት በኩራት ሀገር እኮ ናት፡፡

አመሰግናለሁ ፕሮፌሰር፤ እንዲያው ቀረ የሚሉት ነገር ካለ ዕድሉን ብሰጥዎት፤

ምን ማለትህ ነው? ይህን ሁሉ ስዘበዝብ ውዬ እንደገና ምን ቀረህ ትለኛለህ? እኔው ጋ አልነበርክም ማለት ነው? አስቀባጥራችሁ፣ አስለፍልፋችሁ ስታበቁ ‹የቀረዎ ካለ› ማለት የምን ፈሊጥ ነው?

አይ፣ ይህም ያስቆጣዎታል እንዴ ፕሮፌሰር? ምናልባት የዘነጉት ነገር ቢኖርና ያ ቢጠቀስ ደግሞ ሕዝብን ያሳውቃል፣ ያነቃል፣ ያስተምራል የሚሉት ሃሳብ ካለዎት ብዬ እንጂ ለነገር እንኳን አልነበረም ፕሮፌሰር፤ ደግሞም የተለመደ ነገር ነው፡፡ እንዲያው ሳይጠቀስ ቢያልፍ…

አሃ! እንደሱ ከሆነ ትክክል ብለሃል፡፡ ለማንኛውም ወያኔ መከፋፈሉንና ተለጣፊ ማበጀቱን እንደማያቆም ሁሉም በተለይም የዚህ ዕኩይ ተግባሩ ቀጥተኛ ሰለባ የሆነው የፖለቲካው ተቃዋሚ ኃይል መረዳት አለበት፡፡ ይህን የወያኔ የተበላ ዕቁብ ለማክሸፍም እንደ እስከዛሬው በጎሣና በጎጥ ሳይከፋፈል በአንድነት የጋራ ትግል ማድረግ ይኖርበታል እላለሁ፡፡ ወያኔ ሥልጣን ላይ የቆየውና የሚቆየው በጥበቡና በጉልበቱ ሳይሆን ብዙዎች እንደምንስማማበትና ዘወትር እንደሚጠቀሰው – ሰሚ የለም እንጂ – በኛው በተበዮች አለመስማማት ብቻ ነው፡፡

 እኛ መከፋፈላችንን በተውን ማግሥት የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ወደሕዝባችን ይመለሳል፡፡ ያኔ በሃይማኖት ሰበብ መጋጨት አይኖርም፤ ያኔ አንዱ ምርጥ ሌላው ምራጭ ዜጋ አይሆንም፤ ያኔ አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሳዳጅ አይሆንም፤ ያኔ አንዱ በዘሩ የሚኮራ ሌላው የሚያፍር አይሆንም፤ ያኔ አንዱ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት የሆነውን መሬት ሠላሳ ቦታ በሕግ ሽፋን እየዘረፈ የሚሸጥና የሚለውጥ በዚያም ምክንያት በአንድ አዳር የናጠጠ ቱጃር የሚሆንበት ሌላው በሕግም አለሕግም የቀለሳት የወፍ ጎጆ የምታህል ደሳሳ ቤት በፌደራል ጦር እየተደበደበና አለርህራሄ እየተገደለ በገዛ ሀገሩ መጻተኛ የሚሆንበት ሸውራራ አሠራ አይኖርም፤ ያኔ አሁን አንገታችንን የሚያስደፋን የሕጻናት ሽያጭ፣ የዜጎች የገፍ ስደትና የባርነት ሕይወት፣ የምሁራን ፍልሰት፣ የከፋ ድህነት፣ ስም የለሽ አምባገነንነት፣ ዘረኝነትና መድልዖ፣ በገዛ ሀገር የበይ ተመልካችነት፣ ያልተመጣጠነ የሀብት ክፍፍል፣ ሥራ እዬሠሩ በኑሮ ውድነት ምክንያት ግን መኖር አለመቻል፣መፈጠርን መራገም፣… እነዚህና ሌሎችም ችግሮች ሁሉ ቀስ በቀስ ግን በርግጠኝነት ይጠፋሉ፡፡ ያኔ ቅርስን የሚሸጡና የሚያፍርሱ የሀገርና የሃይማኖት መሪዎች አይኖሩም፡፡ ያኔ ሁሉም አንገቱን ቀና አድርጎ የሚሄድባት የጋራ ኢትዮጵያ ትመሠረታለች… እንድልህ ፈልገህ ነው?
አዎ ፕሮፌሰር፣ ለሰጡኝ ቃለ መጠይቅ በንጋት የዜና ማዕከልና በአድማጭቢዎቻችን ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
እኔም አመሰግናለሁ፤ ይህ ዕድል የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ እንደማይሆንም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
(የአንባቢን ጊዜ በቁጠባ ለመጠቀም ለዛሬ እነዚህ ይበቁናል)

No comments:

Post a Comment