Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday 2 January 2013

የውጭ ምንዛሪ እጥረት የፈጠረው ሙስና ጥያቄ እያስነሳ ነው


ethiopian reporter
የውጭ ምንዛሪ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ በመባባሱ ከንግዱ ማኅበረሰብና ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥያቄ እየቀረበ በመሆኑ ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጉዳዩን ለመመርመር መረጃ መሰብሰቡን ምንጮች ገለጹ፡፡
በእጥረቱ ምክንያት የተፈጠረው ሙስና ጥያቄ አስነስቷል፡፡ 


መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የለም ቢልም፣ ባንኮች የሚቀርቡላቸውን የሌተር ኦፍ ክሬዲት (ኤልሲ) ጥያቄዎች ማስተናገድ አልቻሉም፡፡ ሌተር ኦፍ ክሬዲት ለመክፈት ጥያቄ አቅርበው ከሦስት ወራት በላይ መስተናገድ ያልቻሉ ነጋዴዎችም ምሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ 


“መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እጥረት የለም ይላል፤ 500 ሺሕ ዶላር ለማግኘት ያቀረብኩት ጥያቄ ከሁለት ወር በላይ ሆኖታል፤” ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የጨርቃ ጨርቅ ነጋዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ “የውጭ ምንዛሪ አለ ከተባለ ለምን አይቀርብልንም?” ሲሉ ጉዳዩ ግራ እንዳጋባቸው እኚሁ ነጋዴ ይጠይቃሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ባንኮች አካባቢ ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጋር የተፈጠረው ሙስና እንደሚያሳስባቸው ይገልጻሉ፡፡ 


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሁለት ወራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዳለው ይናገራል፡፡ ይህ ክምችት ባንኩ በዕቅድ ዘመኔ ማሟላት አለብኝ በሚለው ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ የነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ግን በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ እንዳልተቻለ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡  


የባንክ ባለሙያዎችም የውጭ ምንዛሪ ችግር መኖሩን ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ብዙዎች የውጭ ምንዛሪ ሲፈልጉ ለበርካታ ባንኮች ፕሮፎርማ ስለሚያቀርቡ ችግሩን እያባባሰው ነው ይላሉ፡፡ ለአንድ ባንክ ታማኝ በመሆን ኢንሹራንስ አሠርተው ከማቅረብ ይልቅ አሥር ባንኮች ዘንድ እየሄዱ ፕሮፎርማ ስለሚያቀርቡ ሠልፉን ያስረዝሙታል በማለት ይገልጻሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሰው ሠራሽ መሆን አለመሆኑን ለማጥናት ሲል መረጃ ሊሰበሰብ ይችላል ሲሉ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡ 


የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች ለአንድ ባንክ ፕሮፎርማ ሲያቀርቡ ለኢንሹራንስ የከፈሉበትን፣ የውጭ ምንዛሪ ማመልከቻ ፎርም፣ እንደ ዕቃው ዓይነት ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት አስፈላጊ ሰነዶችንና ማረጋገጫዎችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል የሚሉት የባንክ ባለሙያዎች፣ እነዚህን የማይጠይቁ ባንኮች ስለሚኖሩ ብሔራዊ ባንክ ይኼንንም ማጣራት ይፈልጋል ብለዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ማሰባሰቡ የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎችን ጫና ከመቀነሱም በላይ፣ ለተፈጠረው ችግር እንደ መፍትሔ ሊያገለግል ይችላል ይላሉ፡፡ 


በሌላ በኩል አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ባንኮች አካባቢ ከውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በርካታ ሐሜቶች እንዳለ የሚናገሩት የባንክ ባለሙያዎች፣ ብሔራዊ ባንክ በተለይ በውጭ ምንዛሪ ግዥና ሽያጭ ሙስና መኖሩንም ሊያጣራ ይችላል በማለት ይገልጻሉ፡፡ በባንኮች አካባቢ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ኮሚሽን ይከፈላል የሚል መረጃ እየተሰማ በመሆኑ፣ ምናልባት የብሔራዊ ባንክ ምርመራ ይኼንንም ሊያካትት ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ 


የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦት እየተመጣጠነ ባለመሆኑ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘትና ለመስጠት ሙስና እየተዘወተረ መምጣቱን ሌሎች ባለሙያዎችም ይገልጻሉ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት መፈጠሩ ይታወሳል፡፡ በዚያን ወቅት በብሔራዊ ባንክ ካዝና የአንድ ወር ብቻ ክምችት እንደነበር ሲታወስ፣ የፍላጎቱ መባባስ የሙስና ክስተቶችን ፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ 


የዘርፉ ታዛቢዎች እንደሚሉት በዚያ ወቅት ለአንድ ዶላር አንድ ብር ይጠየቅ ነበር፡፡ አሁን በተከሰተው የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን ምክንያት ለአንድ ዶላር ከአንድ ብር ከ20 ሳንቲም በላይ ኮሚሽን በጉቦ መልክ እየተጠየቀ መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የተሰከሰውን እጥረት ብሔራዊ ባንክ ሰው ሠራሽ ፍላጎት ነው ቢለውም፣ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው በሚል የተለያዩ ጥያቄዎችን ሰብስቦ ወደማጣራት መምጣቱ ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ችግሩ ተጠንቶ ለብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ቀርቦ በጠረጴዛቸው ላይ እንደሚገኝ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ 


መንግሥት አሁንም በይፋ እንደሚለው ለመሠረታዊ የመንግሥት ግዥዎች የውጭ ምንዛሪ እጥረት የለም፡፡ ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ አቅርቦትና ለካፒታል ፕሮጀክቶች የውጭ ምንዛሪ ክምችት መኖሩን የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ በቅርቡ ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ መንግሥት በጣም አንገብጋቢ ለሚባሉ ገቢ ምርቶችም የውጭ ምንዛሪ ያለምንም ወረፋ እንዲሰጥ ማድረጉም ይታወቃል፡፡ 

No comments:

Post a Comment