Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Friday 5 April 2013

! ….. ‘ህወሓት ለህዝብ ሮሮ ጀሮ የለውም’ …!

! ….. ‘ህወሓት ለህዝብ ሮሮ ጀሮ የለውም’ …!

ህወሓቶች በ9ኛው የኢህኣዴግ ጉባኤ ተሸማቀው መመለሳቸው ተሰምተዋል። በሁሉም የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ኣለመተማመንና እርስበርስ መናናቅ ቢስተዋልም ህወሓቶች የለመዱቱን ‘ክብር’ በመነፈጋቸው (የሚያቀርቡት ሓሳብ ሲብጠለጠል በማየታቸው) እጅግ እንዳዘኑና እንዳፈሩ ለማወቅ ተችለዋል።

ድሮም ቢሆን እነዚህ ተራ የህወሓት ኣባላት (የኣሁኑ መሪዎች ማለቴ ነው) ከሌሎች የድርጅት መሪዎች በቀጥታ (የሓሳብ) ክርክር ኣድርገው ኣያውቁም። በመለስ በኩል ነበር የሚገናኙ። መለስ ለየብቻቸው ያሳምናቸው ነበር። ኣሁን ይሄን ሚና የሚጫወት የለም። እናማ ህወሓቶች ተንቀናል (ተሰሚነት ኣጣን) ብለው ኣኮረፉ፣ ኣፈሩ። በትክክል ውርዴት ነው። ኣንድ ተሳታፊ ‘ ቢስቢስ እኮ አሎምና’ (ትግርኛ) ብለዋል።

እንደዉጤቱም ከጉባኤው መልስ በትግራይ በኣብዛኛው የክልል መንግስት መስርያቤት በስብሰባ ተጠምደዋል። ትናንት (ሓሙስ መጋቢት 19, 2005) የመንግስት ሰራተኞች ስራቸው ትተው ስብሰባ ዉለዋል። የመንግስት ስራ ትተው ለፓርቲ ስብሰባ መጥራት ተገቢ ኣልነበረም።

እነሱ ስልጣናቸውን የሚያራዝሙበት ስብሰባ (የህዝብ ጅንጀና) ሲያካሂዱ ህዝቡ (ተገልጋዩ) ግን የፍትሕ ግልጋሎት ኣጥቶ ሲሰቃይ ማየት ያሳዝናል።

የመኾኒ ነዋሪዎች መኖርያ ቤታቸው እንደሚፈርስ ተነግሯቸዋል። በቅርብ ግዜ ወደ 7 ሺ ቤቶች ይፈርሳሉ (ገጠሩ ጨምሮ መሆን ኣለበት እንጂ 7ሺ ቤቶች በመኾኒ ከተማ ይኖራል ብዬ ኣልገምትም)። በመጀመርያ ዙር 1500 ቤተሰብ ይፈናቀላል። ይቀጥላል።

እነዚህ ነዋሪዎች መኖርያ ቤታቸው ሲፈርስ ሌላ ኣማራጭ መጠልያ ስለሌላቸው መንግስት መፍትሔ እንዲያፈላልግላቸው ለወረዳው ኣስተዳዳሪዎች ኣቤት ብለው ነበር። መትፍሔ ኣላገኙም። ችግሩ ያስጨነቃቸው ነዋሪዎች ከ150-200 የሚሆኑ ተወካዮች መርጠው ወደ ክልል መንግስት ቢሮ (መፍትሔ ፍለጋ) ላኩ። 


የክልል መንግስት ሓላፊዎች ወደ ወረዳቸው እንዲመለሱ ያዛሉ። ‘የወረዳ ኣስተዳዳሪዎች ማ መፍትሔ ሊሰጡን ኣልቻሉም፣ ለዚህ ነው ወደ ክልል የመጣነው።’ ተወካዮቹ ይመልሳሉ። የክልሎችም ‘እኛ የምናውቀው ነገር የለም’ በሚል ከኣከባቢው እንዲርቁ ያስገድዷቸዋል።

የነዋሪዎቹ ጥያቄ ምንድነው? “ኣንደኛ ቤታችን የሚፈርሰው ኣለኣግባብ ነው። ሁለተኛ መኖርያችን መንግስት በሃይሉ የሚያፈርሰው ከሆነ ሌላ ኣማራጭ መጠልያ ልያዘጋጅልን ይገባል።” ይላሉ። በተጨማሪም “መንግስት ለውጭ ዜጎች (ለምሳሌ የኤርትራ ስደተኞች) መጠልያ ያስፈልጋቸዋል ብሎ የተለያዩ ነገሮች ሲያዘጋጅላቸው ለኛ (ለዜጎቹ) ግን ያለ ምንም ኣማራጭ መኖርያችን ለማፍረስ እየተዘጋጀ ነው” ብለው ይከሳሉ።

የክልል ባለስልጣናት መፍትሔ ስላልሰጡዋቸው (ባለስልጣናቱ ለግል ወይ ፓርቲ ስብሰባቸው እንጂ) ለህዝብ ፍትሕ ወይ ግልጋሎት ደንታ ስለሌላቸው ተወካዮቹ ወደ ዓረና ትግራይ ፓርቲ መስራቤት በመሄድ ጉዳያቸውን ማስረዳታቸው ሰምቻለሁ። ሰዎቹ ከመኾኒ- መቐለ ለሳምንት ያህል መመላለሳቸው ገልፀውልኛል። የመንግስትም የግልም የሚድያ ሽፋን ኣለማግኘታቸው ያሳዘናቸው ይመስላል። በመጨረሻም ‘ህወሓት ለህዝብ ሮሮ ጀሮ የለውም’ የሚል ኣስተያየት ሰንዝረዋል።

እባካቹ ህወሓቶች ከመንግስት ስራ የፓርቲ ስብሰባ ኣታስቀድሙ። የመንግስት መስራቤትም ለፓርቲ ስራ ማዋል ሙስና ነው። የፓርቲና የመንግስት ስራ የተለያዩ ናቸው። ቅድምያ ለህዝብ ስጡ። ያለ ህዝብ ስልጣን የለም፣ ሃብት የለም፣ ‘መከበር’ የለም። ሁሉም ነገር የሚያደረው ህዝብ ነው።

ለህዝብ ቅድምያ እንስጥ።

No comments:

Post a Comment