Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday 14 April 2013

ከቤንሻንጉል የተፈናቅለው የነበሩት አማርኛ ተናጋሪዎች ለደረሰብን ጉዳት ተጠያቂው ብአዴን ነው አሉ

IMG0065A
ከሚኖሩበት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው በፍኖተሠላም ሰፍረው የነበሩት አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች “እንድፈናቀል ያደረገንና ለደረሰብን ጉዳት ተጠያቂው የአማራ ክልላዊ መንግስት ገዢው ፓርቲ ብአዴን ነው፡፡” ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን አስታወቁ፡፡

ተፋናቃዮቹ እንደሚሉት “ስንፈናቀል ስድብ፣ዛቻ ድብደባ፣እስራትና ዝርፊያ የደረሰባቸው አሉ፡፡ የስነ ልቦና ጉዳት ደርሶብናል፡፡ ሀብትና ንብረታችን ጥለን በ24 ሰዓት ከአካባቢው እንድንወጣ ተደርገናል፡፡ ለዚህ ሁሉ ድርጊት ግንባር ቀደም ተጠያቂው ብአዴን ነው” በማለት ፓርቲውን ወቅሰዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ለዝግጅት ክፍላችን እንደሚያስረዱት “በሠላም ሠርተን በምንኖርበት ቦታ ልዩ ኃይል (ፌዴራል ፖሊስ) አዝምቶ ያስደበደበንና ከሥራና ከመኖሪያ ቦታችን ያስወጣን የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ናቸው፡፡

ምን አጠፋን? ምን በድለናችሁ ነው? እንዲህ የምታሰቃዩን ብለን ስንጠይቅ ፤ የክልላችሁ መንግስት የማዳበሪያ ገንዘብ ዕዳ አለባቸው ፤ነፍስ ገዳዮች አሉበት፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሽፍታ ማጠራቀሚያ ሆኗል፡፡ ህዝቤን መልሱልኝ ብሎ ስጠየቀን ነው፡፡ ብለውናል፡፡ ይህ ሁሉ ድብደባና ዝርፊያ ሲፈፀምብን ብአዴን ዝም ብሎ ይመለከታል፡፡ ስለዚህ ለደረሰብን ጉዳት ሁሉ ግንባር ቀደም ተጠያቂው ብአዴን ነው፡፡ ” ሲሉ በስፍራው ለተገኙት የፍኖተ ነፃነት ጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

ቁጥራቸው በግምት ከ 3ሺ በላይ የሆኑ እንዚህ ተፈናቃዮች በጊዜያዊነት ሰፍረው በነበረበት ፍኖተ ሰላ ከተማ ተገኝተው ለነበሩት የፍኖተ ነፃነት ጋዜጠኞች እንዳስረዱት “ቤት ንብረታችንን እንዳለ ጥለን እንድንወጣ ተደርገናል፡፡
ያመረትነውን ሰብል አልሰበሰብንም፡፡ የእርሻ በሬዎቻችንን ሜዳ ላይ ጥለን እንድንወጣ ተደርገናል፡፡ ተደብድበናል፤ ፖሊስ ጣቢያ ታስረን ለእያንዳንዳችን ለትራንስፖር ብር 350 እየከፈልን ከአካባቢው እንድንወጣ ተደርገናል፡፡ ፍኖተሠላም ከመጣን በኃላ ከእኛ መካከል የማዳበሪያ ዕዳ ያለበት ማነው? ነፍስ ገድሎ የተሸሸገስ ማነው ብለን ብንጠይቅ የብአዴን ተወካዮች እኛ እንዲህ አላልንም እያሉን ነው፡፡ እናንተ እንዲህ ካላችሁ ይህ ሁሉ ድርጊት ሲፈፀምብን ለምን ዝምታን መረጣችሁ? ብለን ስንጠይቅ መልስ አይሰጡንም ” በማለት በፍፁም ምሬት ተናግረዋል፡፡
በቀን ሁለት ጊዜ በ4 ሰዓትና በ11 ሰዓት መንግስት ምግብ ያቀርብላቸው እንደነበር የሚናገሩትት እነዚህ ተፈናቃዮች ፍኖተሠላም ለበሽታ አጋላጭ በሆነ ስፍራ(ቄራ) ላይ ያለመጠለያ ሜዳ ላይ እንዲያድሩ በደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ ከ1995 ዓ/ም ጀምሮ በአካባቢው እንደኖሩ የሚናገሩት እነዚሁ ተፈናቃዮች “ከነበርንበት ቦታ ከወጣን በኃላ የነበርንበት አካባቢ ባለሥልጣናት የዘረኝነትና የጥላቻ ቅስቀሳ ፈጽመውብናል” በማለት ወደቤንሻንጉል ከተመለሱ በኋላ አደጋ እንዳጋጥማቸው መስጋታቸውን ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡
fnotenetsanet.com

No comments:

Post a Comment