Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Monday 22 July 2013

አዲስ አበባ ላይ የተንሰራፋው ሙስና ለብዙዎች አሳሳቢ ሆኗል

መንግሥት ሙስናን እየተዋጋ የሚያስመስሉ ምልክቶች ቢስተዋሉም፣ የፀረ ሙስና ትግሉን ለመቀልበስ ያደፈጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መኖራቸው ሥጋት ፈጥሯል፡፡

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሙሰኞችን በተመለከተ ሲናገሩ፣ ‹‹ወይ እነሱ ያሸንፋሉ ወይ እኛ እናሸንፋለን፤›› ብለው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን መንግሥት ሙስናን ለመታገል ደፋ ቀና የሚለውን ያህል በመንግሥት ጉያ ሥር ተሸጉጠው የሙስና ትግሉን በመቀልበስና የሚገኘውን አይስክሬም ለመላስ የቆረጡ እንዳሉ እየታየ መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡ 

በሁለቱ አካላት መካከል የሚደረገው ሽኩቻ ወይም ትግል በማን አሸናፊነት እንደሚቋጭ ባይታወቅም አሸናፊና ተሸናፊ የግድ እንደሚያስፈልግ ይታመናል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እየጨሰ ከሚገኘው የፀረ ሙስና ትግል ባሻገር፣ በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ጉዳዮችን ጥቂት ዓመታት ወደኋላ መለስ ተብሎ ቢመረመርና አሁን ካለበት ደረጃ ጋር ቢመዘን የጉዳዩን አሳሳቢነት መረዳት ያስችላል በማለት የሚገልጹ አሉ፡፡

የቀድሞወ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ አስተዳደር ሥልጣኑን ከእሳት አጥፊው ባለአደራ አስተዳደር ሲረከቡ ወደ ከተማው ይዘው ከመጧቸው ቁም ነገሮች መካከል መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ሙስናን መታገልና መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ተግባራዊ ማድረግ ይገኙበታል፡፡ 

በተለይ ከገቢ አሰባሰብና ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ በርካታ የሙስና ተግባሮች እንደነበሩ በመታመኑ፣ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ጠንከር ያለ ግምገማ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ በእነዚህ ግምገማዎች በርካታ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች በሙስና መዘፈቃቸውና በርካታ ገንዘብ መመዝበሩ በተካሄደው ድርጅታዊና መንግሥታዊ ግምገማ ተረጋግጧል፡፡ 

የግምገማው ውጤት ለፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተመራ ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ በደረሰው መረጃ ላይ ተመሥርቶ ምርመራ በጀመረበት ወቅት ግን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለፀረ ሙስና ኮሚሽን በጻፈው ደብደቤ የተፈጠረው ችግር የከተማው ነው በሚል ምክንያት ኮሚሽኑ ምርመራውን እንዲያቆም ጠይቋል፡፡ 

ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የአስተዳደሩና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለሙያዎች ሁኔታውን አሳፋሪ ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ምክንያቱም ያጠፋ መጠየቅ አለበት፡፡ የተመዘበረ የመንግሥት ገንዘብም ሊመለስ ይገባዋል ሲሉ እነዚህ ባለሙያዎች ምክንያታቸውን ገልጸው፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከእንግዲህ ደብዳቤ መጻፍ እንደሌለበትና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ምርመራውን ሊያቆም እንደማይገባ አስረግጠው መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡
 
በግምገማ ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠባቸውና ማጥፋታቸውን በግልጽ ያመኑ የሙስና ተጠርጣሪዎች  ግን ክስ አልተመሠረተባቸውም፡፡ ተመዝብሯል የተባለውም የመንግሥት ሀብት ተመላሽ አልተደረገም፡፡ በዚህ ምክንያት የተበደሉ ነዋሪዎችም እንዲካሱ አለመደረጉ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ 

ብዙዎችን የሚያስገርመውና እያስገረመ የሚገኘው እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ተጠያቂ አለመሆናቸው ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑም በአዳዲስ ሹመቶች መንበሽበሻቸው ነው፡፡ 

ከአሥሩም ክፍላተ ከተሞች በሙስና ተግባር ውስጥ ተሰማርተዋል ተብሎ ነጥብ የተያዘባቸው ሹማምንት ከነበሩበት ክፍለ ከተማው ወደሌላ ክፍለ ከተማ ተቀይረው ተሹመዋል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በክፍላተ ከተሞች በሚገኙ የገቢ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ‹‹ሙሰኞች›› እንዳሉ ይነገራል፡፡ 

እነዚህ ‹‹ሙሰኞች›› ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ፍሬ ግብር በመቀነስ ሊከፈል የሚገባውን የመንግሥት ግብር የሚያሳንሱ፣ ማሳነስ ብቻም ሳይሆን ጭራሹኑ ሊገባ ይገባው የነበረ ገንዘብ ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት እንዳይገባ ዘብ የቆሙ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ 

እነዚህን ያጋለጡ ሠራተኞች ግን በየጊዜው ተፅዕኖ እየተደረገባቸው ጭራሹኑ በፍርኃት ካባ ተሸፍነው እንዲኖሩ እየተደረገ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ ይህንን ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ባላቸው ጠንካራ ኔትወርክ ምክንያት ለአዳዲስ ሹመቶች ሲታጩና ሲሾሙ ይስተዋላል፡፡ 

በሌላ በኩልም ከአንድ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማዕከል ደረጃ በተካሄደው ግምገማ ከአሥር በላይ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሙስናና በኔትወርክ ተገምግመው ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ሐሳብ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ከዛሬ ነገ ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ ባለሥልጣናቱ ባሉበት ፀንተዋል፤ ወይም አዲስ ሹመት አግኝተዋል፡፡ በወቅቱ እነዚህ ባለሥልጣናት ሲገመገሙ በሙስና መዘፈቃቸውና በቡድንተኝነት (ኔትወርክ) ያልተገቡ ተግባራትን ይፈጽማሉ በሚል ምክንያት እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል፡፡ 

አስገራሚው ጉዳይ በአዲስ አበባ አዲስ ምርጫ ተካሄዶ አዲሱ ካቢኔ ሥልጣኑን ይይዛል ቢባልም፣ ወደከተማው የመጡት ከንቲባው ብቻ ናቸው፡፡ አዲሱ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ነባሩን ካቢኔ ይዘው ማዝገማቸውን ቀጥለዋል፡፡ 

የቀድሞው የከተማው አስተዳደር በሚፈለገው ስፋትና ጥልቀት ባይሆንም የልማት ሥራዎችን መሥራቱ እርግጥ መሆኑን ብዙዎችን ያስማማል፡፡ በመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ በቤቶች ልማት፣ በመንገድ ልማት ዘርፎች የሚጨበጥ ሥራ ሠርቷል፡፡ ነገር ግን መልካም አስተዳደርን በማስፈንና ሙስናን በመዋጋት አገልጋይ ሲቪል ሰርቪስ ከመፍጠር አኳያ ብዙ እንደሚቀረው ብዙዎች ያምናሉ፡፡ 

የቀድሞው አስተዳደር መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና አገልጋይ ሲቪል ሰርቪስ በመፍጠር በኩል ፍላጎቱ ነበረው ቢባልም በአቅም ውሱንነት ባያሳካውም፣ ሙስናን በመታገል በኩል ግን የተነሳሽነት ችግር እንዳለበት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአስተዳደሩ ነባር ሠራተኞች ይናገራሉ፡፡

ኅብረተሰቡ ይህንን ችግር በመፍታት በኩል ኢሕአዴግ ቆራጥ መሆኑን በተደጋጋሚ በመግለጹ ምክንያት በአዲሱ አስተዳደር ላይ ተስፋ ቢጥሉም፣ አዲሱ አስተዳደር ከከንቲባው በስተቀር ነባሩን ካቢኔ ይዞ መቀጠሉ በተጣለው ተስፋ ላይ ደመና አጥልቷል፡፡ ምክንያቱም የሠራተኞችና የነዋሪዎች እንቀፋት የሆኑ ባለሥልጣናት ላይ ዕርምጃ ተወስዶ ሥርዓት የሰፈነበት ቢሮክራሲ ይኖራል የሚል እምነት ተጥሎ የነበረ በመሆኑ ነው፡፡ 

በአሁኑ ወቅት ሁሉም ነገር ተዳፍኖ ምንም እንዳልተፈጠረ ተደርጎ ጉዞ ቢቀጥልም፣ ጉዳዩ ብዙዎችን ያስከፋ በመሆኑ መንግሥት የጽሞና ጊዜ ወስዶ ራሱን ሊፈትሽ እንደሚገባ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ያስጠነቅቃሉ፡፡ 

No comments:

Post a Comment