Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Monday 23 July 2012

‹‹አንድ ፊሊፒን ለሚቀጥር ኢትዮጵያዊ ይመረቃል››

Sunday, 22 July 2012 00:00
By Miheret Aschalew

ልማት ባንክ ፊት ለፊት ቆማ ወደ ተክለሃይማኖት የሚወስደው መንገድ የትኛው እንደሆነ ትጠይቃለች፡፡ ዕድሜዋ ከአሥራ አምስት አልያም ከአሥራ ስድስት እንደማይበልጥ ማንም አይቷት መገመት ይችላል፡፡
ተክለሃይማኖት ድረስ በእግሯ ለመሄድ ማሰቧን ስትገልጽልን ታክሲ እንደምናሳፍራት ገልጸንላት ከእኛ ጋር ታክሲ ተራ ድረስ እንድትሄድ አደረግን፡፡ መኪያ ትባላለች፡፡ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ወደ ዓረብ አገር ለመሄድ ነው፡፡ ተወልዳ ያደገችው ወሎ ውስጥ በአንድ የገጠር አካባቢ ነው፡፡ ሁለት እህቶቿ ሳውዲ መሆናቸውን ነገር ግን አንደኛዋ ከአሠሪዎቿ ቤት ጠፍታ ድምጿን ከሰሙ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆነ ነገረችን፡፡ ‹‹ወንድሞቼም መንገድ ላይ ናቸው›› ስትለን ተገርመን ወዴት እየሄዱ እንደሆነ ጠየቅናት፡፡ ሁለቱም  ሳውዲ ለመግባት አንደኛው የመን አንደኛው ጅቡቲ ላይ መሆናቸውን ስትገልጽልን እህትና ወንድሞቿ እንዲህ ችግር ላይ ሆነው፣ ወደ ዓረብ አገሮች በቤት ሠራተኝነት የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይም የተለያየ ችግር ደርሶ እየታየ ባለበት ሁኔታ ወደዚያ መሄድ እንዴት እንደማያስፈራት ጠየቅናት፤ ‹‹ኧረ እኔ አልፈራም፡፡ ዕድሌን ያቅናው ነው የምለው›› የሚል አጭር መልስ ሰጠችን፡፡ ልጅቷ ተግባቢ ናት፡፡ እግረ መንገዳችንን እያደረግን ባለነው ውይይትም ፍጹም ነፃነት እንደተሰማት እርግጠኛ ስለሆንን ጨዋታችንን ቀጠልን፡፡

ለመሄድ ያነሳሳት የመጀመሪያው ነገር የጓደኞቿ በሙሉ መሄድ መሆኑን ከንግግሯ በመረዳታችን ይህ ለመሄድ በቂ ምክንያት እንደማይሆን ገለጽንላት፡፡ ‹‹እንዴ ቀዬው ላይ የቀረው እኮ ባልቴት ብቻ ነው፡፡ ታዲያ እኔ ምን ላደርግ ነው የምቀመጠው፡፡ የምሄደው ጓደኞቼ ስለሄዱ ብቻም አይደል፣ እኔም እንድሠራና እንድለወጥ ነው›› በማለት እንዴት ለምን ትሄጃለሽ ትላላችሁ በሚል አስተያየት ቀና ብላ አየችን፡፡ ሁለት ሦስት ሕፃናት ልጆቻቸውን በትነው የሄዱ የአካባቢዋ ሴቶች እንዳሉ፤ ስለዚህም የእሷ መሄድ ምንም የሚገርም እንዳልሆነ ልታስረዳን ሞከረች፡፡

ከቤት የቀረችው የአሥራ ሁለት ዓመት ትንሽ እህቷ ነች፡፡ እዚህ ያረፈችው መርካቶ ወይራ ምንጭ እንደሆነ፣ የመጣችውም ከደላላ ጋር መሆኑን ነገረችን፡፡ እኛ ያገኛናት ወደ ሳውዲ ለመሄድ የሚያስችላትን የሕክምና ምርመራ ለማድረግ ካዛንችስ ከሚገኘው ጋምካ (የባሕረ ሰላጤው አገሮች የመረጧቸው የጤና ተቋማት ስብስብ ጽሕፈት ቤት) ወረቀት ለመውሰድ በመጣችበት ወቅት ነበር፡፡ ፈጣንና ቀልጣፋ ብትሆንም ሁለመናዋ ልጅነቷን ያጋልጣል፡፡ ዕድሜዋ ስንት እንደሆነ ስንጠይቃት አሥራ ስድስት መሆኑን ነገረችን፡፡ እንዴት ፓስፖርት አወጣሽ? ‹‹ሃያ ሦስት ተደርጎልኝ ነው ፓስፖርት ያወጣሁት፡፡ ሰባት የጨመረልኝ የወረዳው ሊቀመንበር ነው፤›› አለችን፡፡

በቤት ሠራተኝነት ወደ ተለያዩ ዓረብ አገሮች የሚሄዱ ኢትዮጵያውያት ላይ ከፍተኛ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ በግልጽ እየታየ፣ ሠርተን እንለወጣለን ለቤተሰቦቻችንም እንተርፋለን ያሉ ሴቶችም ሕይወታቸውን እያጡ ባሉበት ሁኔታ የሚሄደው ሴት ቁጥር ዕለት በዕለት እየጨመረ የተጓዦቹ ቁጥር ከቁጥጥር ውጭ ስለመሆኑ ካዛንችስ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አቅራቢያ፣ እንዲሁም ወደ ዓረብ አገሮች ለሚሄዱ የሕክምና አገልግሎት በሚሰጡ የጤና ተቋማት በቅርቡ ታይቶ የነበረው ከፍተኛ ትርምስ ምስክር ነው፡፡ ተጓዦቹ ወረፋ ለማግኘት ሜዳ ላይ አድረዋል ሰልፍም በገንዘብ ገዝተዋል፡፡
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ወላጆች በሬ እየሸጡ ልጆቻቸውን ወደ ዓረብ አገር እየላኩ ነው፡፡ ዕድሜያቸው ለሥራ ያልደረሱ ልጆችም በመሄድ ላይ መሆናቸው በተለያዩ መደረኮች እየተገለፀ ነው፡፡ ወደ አረብ አገሮች በቤት ሠራተኝነት የሚሄዱ ኢትዮጵያውያት በሚያጋጥሙ ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦች ዙሪያ የሚያጠነጥን ጥናት ሐሙስ ዕለት በሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተዘጋጅቶ ቀርቦ ነበር፡፡

ጥናቱ የተደረገው በዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ሰባቱም ስቴቶች ላይ ሲሆን፣ ሁለት ወር በፈጀው ጥናት ስድሳ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያት መካተታቸውን የጥናቱ አቅራቢና በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የሆምኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት ኃላፊ የሆኑት አቶ መስፍን ተክሉ ገልጸውልናል፡፡ በጥናቱ ኤጀንሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶችም ተካትተዋል፡፡ አቶ መስፍን ለ14 ዓመታት ዱባይ በመኖራቸው፤ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተባባሪ ሆነው በማገልገላቸውም ችግሩን በደንብ ያውቁታል፡፡

ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ በሰባቱ የዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ግዛቶች ኢትዮጵያውያቱ ለሚያጋጥሟቸው አስከፊ ችግሮች፣ ለሚደርስባቸው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣና የጉልበት ብዝበዛ መነሻ የሴቶቹ የአገሩን ባህልና አኗኗር ዘይቤ አለማወቅና ለሥራቸው የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠና አለማግኘት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ተሟልተው ሴቶቹ እንዲሄዱ ባለመደረጉ እንደ ልብስ ማጠቢያ ወይም ምግብ ማብሰያ ባሉ ማሽኖች ሴቶቹ ግራ ይጋባሉ፡፡ ስለሚቀጠሩበት ቤት ሁኔታ፣ የቤተሰብ ብዛት ሌላም ሌላም አንድም የሚያውቁት ነገር ሳይኖር ከአገር ይወጣሉ፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሚታየው ወደ አረብ አገሮች በመሔድ ላይ ያሉት ለአዲስ አበባ እንኳ እንግዳ የሆኑ ከገጠር አካባቢ የሚመጡ ሴቶች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያውያቱ በአሠሪዎቻቸውም ይደፈራሉ፡፡ ደሞዛቸውን ይከለከላሉ፡፡ በአሰሪዎቻቸው ብቻም ሳይሆን በኤጀንሲዎች ግፍ ይፈጸምባቸዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ስቃይ ለመውጣት ከአሠሪዎቻቸው በማምለጥ ወደ ሴተኛ አዳሪነት የሚገቡበት እድል ሰፊ መሆኑን አጥኚዎቹ ዱባይ ውስጥ በሚገኙ ስምንት፣ ኦማን ውስጥ በሚገኙ ሦስት የምሽት ክበቦች ተገኝተው አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህ አገር በሚልኳቸውና እዚያ በሚቀበሏቸው ኤጀንሲዎች መካከል ከፍተኛ የአሠራር ክፍተት መኖሩን፤ በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ኤጀንሲዎች የሚልኳት አንዲት ሴት ምን አይነትና ስንት ቤተሰብ ያለበት ቤት እንደምትገባ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ጥናቱ ያሳያል፡፡ ችግሩ በዚህ ብቻም ሳይበቃ ዱባይ ከደረሱ በኋላ ወደ አፍጋኒስታንና ኢራን ለቤት ሠራተኝነት የሚጓዙ ኢትዮጵያውያትም አሉ፡፡ ዱባይ አየር መንገድ ደርሰው የሚቀበላቸው ሰው ባለማግኘት አየር ማረፊያው አካባቢ ሜዳ ላይ ለመዋልና ለማደር፣ ለምኖ ለመብላትም የተገደዱ በርካቶች መሆናቸው በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

ጥናቱ በዱባይ ኢትዮጵያውያንና የፊሊፒንስ ዜጋ የቤት ሠራተኞችን ሁኔታ ለማነፃፀር ሞክሯል፡፡ ፊሊፒኑ በዱባይ የሚገኘው ኤምባሲያቸው ጉዟቸውን ሳያፀድቅ አገራቸውን ለቀው አይወጡም፡፡ የአገራቸው መንግሥትም ማንኛውም የቤት ሠራተኛ ሆኖ የሚሄድ ዜጋው ከ450 ዶላር በታች ተከፋይ ሆኖ እንዳይጓዝ በሕግ ደንግጓል፡፡ ችሎታና የትምህርት ደረጃቸውን በሚመለከት የሚሞሉት የቅጥር ፎርም ትክክለኛና እውነተኛ ነው፡፡ በተቃራኒው ለሥራ የሚሄዱ ዜጎችን በሚመለከት በኢትዮጵያና በዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ መካከል ምንም ዓይነት መንግሥታዊ ስምምነት የለም፡፡ ቢሆንም 365 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በቀን ለሥራ የዱባይ ኤርፖርትን ይረግጣሉ፡፡ በሌላ በኩል የሚቀጥራቸው እንዲገኝ ሲባል የኢትዮጵያውያኑ የቅጥር ፎርም ችሎታቸው ምንም ይሁን ምን ሁሉንም ዘመናዊ የቤት ውስጥ መገልገያ ማሽን መጠቀም እንደሚችሉ፤ ማንኛውንም ሥራ ለመሥራትም ብቃት እንዳላቸው ተደርጎ ይሞላል፡፡ ይህን ከፍተኛ ቁጥር የተመለከቱ ዱባይ ውስጥ የሚገኙ ህንድና ፓኪስታናዊ ደላሎች አማርኛ ለምደው ሥራቸውን እያቀላጠፉ የሚገኙበት ሁኔታ መኖሩን አጥኝዎቹ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ በወር የሚከፈላቸው 135 ዶላር ሲሆን፣ ኤጀንሲዎች አንዲት ኢትዮጵያዊትን በማስቀጠር የሚያገኙት 500 አልያም 550 ዶላር ነው፡፡ በተቃራኒው አንዲት ፈሊፒን የቤት ሠራተኛን በማስቀጠር ኤጀንሲዎች ከ2700 ዶላር በላይ ያገኛሉ፡፡ ‹‹አንዲት ፊሊፒን ለሚቀጥር ኢትዮጵያዊ ይመረቅለታል›› የሚሉ ማስታወቂያዎች በተለያዩ የሥራ ማስታወቂያ ጋዜጦችና ድረ ገጾች ላይ መመልከትም እንግዳ ነገር እንዳልሆነ አቶ መስፍን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አገሪቱ እየታየ ባለው ቁጥር የሰው ኃይል ወደ ውጭ አገር ልካ የማሠራት ልምድ እንደሌላት፤ አሁን ግን ወደ ዓረብ አገሮች በቤት ሠራተኝነት የሚሄዱ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆን ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለቁጥጥር አስቸጋሪ መሆኑን ፍትሕ ሚኒስቴርን በመወከል በውይይቱ ላይ የተገኙት አቶ ዮሴፍ ኪሮስ ገልጸዋል፡፡ ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የሆኑ ሴት ልጆች እየሄዱ መሆኑን፣ እሳቸው ብቻም ሳይሆኑ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ቡድን አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ መሰለች አሰፋን ጨምሮ ሌሎችም ጠቁመዋል፡፡ መኪያም ከእነዚህ ልጆች አንዷ ናት፡፡

ጥናቱን በማድረጉ ወ/ሮ መሰለች ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን ቢያመሰግኑም ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ላይ ብቻ በማተኮሩ የጥናቱን ውስንነት ሳይገልጹ አላለፉም፣ መንግሥት የዜጎች ወደ ውጭ አገር መሄድን እንደማያበረታታ ነገር ግን ችግሩ ሁሉም አገሮች እየተጋፈጡት ያሉት የግሎባላይዜሽን ገጽታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንደገለጹትና በጥናቱ ላይ የተቀመጡት ችግሮች ያጋጠሟቸው በሕገወጥ መንገድ ወደ ዱባይ የሄዱትን ሴቶች ነው፡፡ በአምስት ሕጋዊ ኤጀንሲዎች አማካይነት ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ አውቆ ባለፉት ሦስት ዓመታት ወደ ዩናይትድ ዓረብ ኤሜሬትስ የሄዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ 1400 ገደማ ብቻ ነው፡፡ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ግን ወደ ዱባይ ለቤት ሠራተኝነት የሚደረግ ጉዞ መቆሙን መግለጫ መሰጠቱንም አስታውሰዋል፡፡ በአገሮቹ መሀል ምንም አይነት ስምምነት በሌለበት ሁኔታ እስከ ዛሬስ በሠራተኛና ማኅበራ ጉዳይ በኩል ለቤት ሠራተኝነት የሄዱት ኢትዮጵያውያት በሕጋዊ መንገድ ነው የሄዱት ለማለት ያስደፍራል?

በመጀመርያ ደረጃ ጉዳዩ የሚመለከተው ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይን ቢሆንም ወደ ዓረብ አገሮች በቤት ሠራተኝነት የሚሄዱ ኢትዮጵያውያንን ለሚያጋጥሙ በርካታ ችግሮች የቀበሌ መታወቂያ በተሳሳተ ዕድሜ ከሚሰጥ የመንግሥት አካል ጀምሮ እስከ ኢሚግሬሽን ድረስ የተለያዩ አካላት ተጠያቂ መሆናቸው በጥናቱና ጥናቱ ላይ በተደረገ ውይይት ተመልክቷል፡፡

በተዋረድ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ማወያየትና ጉዳዩን ለመፍትሔ ክፍት ማድረግ፣ አብዛኞቹ ችግሮች የተከሰቱት በተጓዦቹ ኢትዮጵያውያን ግንዛቤ አለመኖርና ስልጠና አለማግኘት በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጥና የሥነ ልቦናን ጨምሮ ሁለንተናዊ ሥልጠና መስጠት ጥናቱ እንደ መፍትሔ ሐሳብ ካስቀመጣቸው መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት አቶ አብነት ግርማይ ደግሞ ጉዳዩ የፖለቲካ ውሳኔ የሚጠይቅ እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment