Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Monday, 23 July 2012

ለውጥና ማምከኛ የወያኔ ስልት!......ከዳዊት ዋስይሁን


ለውጥ የተፈጥሮ ህግ ነው። ነገሮች በህዋችን ውስጥ በማያቋርጥ አንቅስቃሴ እና ለውጥ ላይ እንዳሉ ሳይንሱ አረጋግጦታል። አገራችን እና ሕዝቦችዋ ለውጥን ከተራቡና ከናፈቁ አመታት ተቆጠሩ። ከዚህ በፊት ህዝቡ ተስፋ ጥሎባቸው ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎባቸው የነበሩ የለውጥ ወቅቶች በኛ እንዝላልነትና በገዢዎቻችን ብልጣብልጥነት ከእጃችን ላይ በቀላሉ ሲነጠቁ አስተውለናል። ገዢዎቻችን በጣም ጥንቁቅና የነቁ ስለሆነ እነሱ እጅ የሚደርስ የመረጃ እና የእንቅስቃሴ ትንሽ የለውም፤ ለደረሳቸው መረጃ አፋጣኝ ምላሽ ሲሰጡ ለሚጀመሩ ማናቸውም አይነት የለውጥ እንቅስቃሴዎች በጭካኔ በትር ያኮላሹታል ድጋሚ እንዳያንሰራራ ለሌሎች ትምህርት ይሰጡበታል።
አሁን ግን የሚጠቀምበት ካለ ለለውጡ በከፍተኛ ደረጃ አስተዋጾ የሚያደርግ ፍንጭና ጅማሬ እየታየ ያለው ከዚህ በፊት በሸሩ፣ በተንኮሉ፡ በከፋፋይነቱ ወደር ከሌለው ከህውሓት መንደር ውስጥ ሲሆን፤ ይህም ከዚህ በፊት ከህዝብ ዘንድ ተነስቶ በቶሎ እንደሚታፈነውና ጭላንጭሉን እንደሚያጠፉት ብልጭታ አልሆነም ይልቅስ ከቀን ወደ ቀን ነገሮች ከቁጥጥር ስር እየወጡባቸው እርስ በራሳቸውም እየተሰላለሉና እየተጠባበቁ እንዳለ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ጥበቡ እንግዲህ እዚህ ላይ ነው በወያኔዎች ሰፈር የተፈጠረው ድንገተኛ ያልተጠበቀ አደጋ ወደሚታይ የእርስ በርስ አለመተማመንና መከፋፈል እንደመራቸው በሌላው ወገን ደግሞ በንሮ ውድነት፤ በፍትህና በመልካም አስተዳደር እጦት፤ በእንግልት እንዲሁም በሁሉም ማህበራዊ ዘርፍ የተቆላና የተጠበሰ ማህበረሰባች አፋጣኝ ለውጥ ናፋቂ ሲኖር፤ እንግዲህ የተቃዋሚ መሪዎቻችን የመምራት ምህንድስና ሚስጥሩ የሚፈተነው እነኝህን ሁለት ያፈጠጡ ዋና ግብአቶች አገናኝቶ ለለውጥ ፈላጊው ህዝባችን ጥያቄው ሲመልሱለት ነው።
በወያኔ መሐል በተፈጠረው ክስተት ካለው እሮሮ ጋር ተዳምሮ በህዝብ ዘንድ የለውጥ ናፍቆቱንና ረሃቡን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጉልቶታል፣ ከዚህም የተነሳ ተስፋ ሰጭ ጭላንጭሎች ከአራቱም ማእዘን እየታዩ ይገኛሉ። ”አሁን ለውጥ” ”ቀጣይ ሂደት” ”የሚፈጠር ክስተት” ህዝቦችዋ በጉጉት እየጠበቁት ያለው ታላቅ ተስፋዎች ሆነዋል። ውነትም ያለውን ሂደትና ተጨባጭ ሁኔታውን ስንፈትሸው ወደ አንድ ደረጃ እየደረሰን እንዳለ ንፋሱ ይናገራል፣ የለውጥ ደመናዎች የመጨረሻ በረከታቸውን ሊለቁ በተጠንቀቅ እንዳሉ ይመስክራሉ።
እንግዲህ የህዝቡን ወቅታዊ ጥያቄና ናፍቆት የትኛውም የተቃዋሚ መሪና የህዝብ ስቃይ ይሰማኛል የሚል የፖለቲካ ስው አፋጣኝና ታሪካዊ ተጨባጭ ምላሽ ሊሰጥ ይገባዋል።
ስለዚህ ምን ይደረግ?
በመጀመሪያ ደረጃ ወያኔ ከዚህ በፊት ይጠቀምባቸው የነበሩ አፍራሽ ስልቶችን ጠንቅቆ ማጥናት ለያንዳንዱ ማምከኛ ማዘጋጀት መቻል፤ ከነዚህም ውስጥ ማናቸውም ከየትኛውም አካባቢ የሚገኙ ወሳኝ መረጃዎችን ያለመናቅ፤ በወያኔም ሆነ በህዝቡ አካባቢ ያሉ ክስተቶችን በትእግስትና በጥሞና እየተከታተሉ መፍትሄ የሚሰጠውን መስጠት፤ ክትትል የሚያሻውን መከታተል፤ ተግባር የሚሻውን መተግበር አንዲሁም ለድርጅት ፍጆታ የሚሆነውን እንደየ ፈርጁ እየለዩ እንደ አስፈላጊነታቸው መጠቀም።
ሌላውና ዋናው ወያኔ ለሚጠነስሳቸውን አፍራሽ ተንኮሎች በጥንቃቄ መፍትሄ ማዘጋጀት ከንኝህም ውስጥ በአሁን ሰአት አገር አቀፋዊ አንቅስቃሴ እየሆነ የመጣውን የኢትዮጵያውያን ምስሊሞችን እንቅስቃሴ ወያኔ ሂደቱን ወደ አልተጠበቀና እርሱ ቁማር ሊቆምርበት ትርፍም ሊያገኝበትና እርስበርስ ሊያፋጀን ወደሚችል አቅጣጫ ለማስያዝ የሚያረገውን ያላሰለሰ የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ተገንዝቦ በማህበረሰባችን ዘንድ አስፈላጊውን የማንቃትና የማደራጀት ስራ መስራት።
በዚህ ላይ ወያኔ የአቶ መልስ ሁኔታን የሚገልጽ ማናቸውም አይነት መረጃ የማህበረሰቡን የልብ ትርታን የሚጨምርና ለለውጥ የሚያዘጋጅና የርሱ ህልውና ማክተሚያ ነው ብሎ ስለሚያምን፣ ከንደዚህ አይነት መረጃዎች ማህበረሰቡን የማገድ ዘመቻ ስለሚጀምር።
እንዲሁም በአሁን ሰአት በህውሓት ማሃል በተፈጠረው ከፍተኛ ድንጋጤ ከዚህ በፊት ያለማቋረጥ ይደሰኮሩ የነበሩ ልማታዊ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎች ለጊዜው ጋብ ያሉ ይመስላል፤ ነገር ግን ይህ ክስተት ቀጣይነት ስላምይኖረው እንደውም በተጠናከረ ሁኔታ የፕሮፖጋንዳው ዘመቻ ሊጀመር ስለሚችል እና በማያያዝ ለተከታታይ ማህበረሰቡ ላይ አሰልቺ የሆነውን ልማታዊ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በመጠነ ሰፊ ከተለቀቀበት ምንም እንዳልተፈጠረና ሁኔታዎች መስመራቸውን እንደያዙ ማህበረሰቡ አመለካከት ላይ ማስረጽ ይቻላል ብሎ ስለሚያምን።
በማያያዝም የአቶ መለስም ጉዳይ ከዋና ጉዳይነት ወርዶ ተራ ይሆናል፤ እንዲሁም በህውሓት መካከል የተፈጠረው ችግርም መፍትሄ ያገኛል ብሎ ቅስቀሳውን በተጠናከረ ሁኔታ ስለሚሰራ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ታች ላለው ማህበረሰብ የሚያስፈልገውን ትክክለኛው መረጃ በየጊዜው እንዲደርሰው ሁኔታዎችን ማመቻቸት።
ማስገንዘቢያ! ወያኔ ቀውስ በተፈጠረ ሰአት ሁሉ ማህበረሰቡን ከተፈጠረው ሁኔታ የሚያርቅበትና ለራሱ ጊዜ የሚገዛበትን ክስተት ይፈልጋል፣ ለምሳሌ አይዶል ሾው፤ እግር ኳስ፤ የቲቪ ድራማ እንዲሁም ሌሎች መዝናኛዎችን ይጠቀማል።
በተለይ ጁላይ 27፣ 2012 የሚከፈተውን የለንደን ኦሎምፒክ እንደ ትልቅ እድል ነው የሚጠቀምበት። ሙሉ ወጪውን በመሸፈን ከፍተኛ የመገናኛ ሽፋን በመስጠት እንዲሁም በየአደባባዩ በትላልቅ እስክሪን በነጻ በማሳየትና በህብረተሰቡ መካከል የመወያያ ርእስ እንዲሆን በማድረግ የማህበረሰቡን አስተሳሰብ መስመር ለማስቀየር ከፍተኛ ዘመቻ እንደሚጀምር ይታመናል ስለዚህ በዚህም አካባቢ ምን መሰራት እንዳለበት መዘጋጀት።
ለማጠቃለያ ወቅቱ ጠንካራና ብልህ አመራርን የሚጠይቅበት ጊዜ ነው፤ ጥያቄው ግልጽና ወሳኝ ነው፤ ሕዝቡም የኛን ጥሪ እየጠበቀ ነው፤ ግን እኛ የት ነው ያለነው???? 
ጁላይ፡ 25፣ 2012
ፀሃፊውን ለማግኘት፦ zoloaba112@yahoo.com         

No comments:

Post a Comment