Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday 29 July 2012

አቶ መለስ የማን ናቸው?.........ከዳዊት ዋስይሁን




አቶ መለስ ከዚህ በፊት የራሳቸው እንዳልሆኑ በምርጫ 2010 ወቅት ነግረውናል። እንዲህ አሉን ”ድርጅቴ ቀጥል ካለኝ አሉ ”ታዲያ ይህ ድርጅት የትኛው ነው ብትሉኝ? ያልገባቸው ኢሕአድግ ይላሉ መች ሆነና እሳቸውማ የዚህ ድርጅት ሊሆኑ አይችሉም፣ በመጀመሪያ ኢሕአዲግ የሚባል ድርጅት የለም እሳቸውም ያውቁታል። 

በዚህ ስም የሚጠራ ግን ተለጣፊ ቡድን ኢትዮጵያን ለማከሰስና ለመቦጥቦጥ እንዲያመቸው ህውሓት የፈለፈላቸው ተምቾች ጥርቅም መሆኑን መገንዘብ አለብን። በምንም ቀመርና ቅመማ ብትመረምሩት ኢሕአዲግ ከሕውሓት ውጭ ህልውና እንደሌለው እርግጠኞች ልንሆን ያስፈልጋል፣ እንደውም እነኛ ፓርላማ ተሰብስበው የህውሓትን ግጥምና ድርስት በጭብጨባ ከሚያቆለጳጵሱ እቁባቶች በላይ ይህ እውቀት የተገለጠለት ማንም ያለ አይመስለኝም፣ ነገር ግን ለምንድን ነው የህውሃት ጭሰኛ ሆነው የሚቀጥሉት ብትሉኝ መልስ የለኝም? ሆዳምና ለጊዜያዊ ጥቅም ስብእናቸውን የሸጡ ባሮች ከማለት ውጭ። 

ታድያ እሳቸው የኢሕአዲግ ካልሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ናቸው ማለት ነው? በፍጹም ሊሆን አይችልም ይህንን እሳቸውም ስለሚያውቋት ለንዲህ አይነቱ ፌዝ ዶሮን ሲያታለሏት ብለው እንደሚመልሱ አልጠራጠርም። ታድያ የማን ናቸው? የህውሓት፣ ትክክል የዚህ ድርጅት የግል ንብረቱ ናቸው ነገር ግን ሕውሓትም ቢሆን ብዙዎች የትግራይ ልጆች የሚወዱትና የሚያፈቅሩት ለአላማው የተሰውለት እውነተኛው ህውሃት ሳይሆን ሰውየው ለራሳቸው በሚመች ሁኔታ ጠፍጥፈው የፈጠሩት የቤተመንግስቱ አዲሱ የዘራፊዎች ቡድን ድርጅት ማለት ነው። 

በአለፈው ሳምንት አንድ አሳዛኝ ታሪክ ተፈጸመ እርሱም የዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ጋና ፕሬዚዳንት ጆን አታ ሚልስ በድንገት ማረፋቸው በአለም መገናኛ ተነገረን እኛም ምነው ብለን ደነገጥን በአንዴ ሁለት መሪ አፍሪካ ማጣቷ ያስደነግጣል፣ ያው የኛውም ከመድረክ ስለጠፉ እንደው እንዳረፉ\እረፍቱ ከስራም ይሆናል\ ልቁጠር ብዬ ነው። 

ከዚህ ክስተት ግን አንድ ነገር ተረዳን እርሱም የጋናው ፕሬዚዳንት ጆን አታ ሚልስ የህዝብ ንብረት ስለነበሩ ህዝቡ አለቀሰላቸው አዘነላቸው ከዛም አልፎ ጋና አዘነች፣  አፍሪካም አለምም ሃዘናቸውንና ለጋና ህዝብም ያላቸውን አጋርነትና ፍቅር ገለጡ። ዜናውም በሁለት ቀን ከመገናኝኛ ብዙሃን ጠፋ ጋናም በህገመንግስቱ መሰረት ግልጽ በሆነ መንገድ መሪዋን ሾመች ጉዞው ቀጠለ። ጋና የአፍሪካ ብርሃን! 

የኛ ጉዳይ እንቆቅልሽ እንደሆነ ይኸው 40 ቀናችንን ደፈንን ኧረ አስገባሪያችንን ያየ ይንገረን? የሁሉም ጥያቄ ሆኖአል። የህውሕቱ መሃንዲስ አቦይ ስብሃት ”እመኑኝ 100% እርግጠኛ ሆኜ ነው የምነግራችሁ ቢበዛ ከ10 ቀን በኻላ ወደስራ ይመለሳል” ብለውን ተመስገን ብለን ሳንጨርስ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ተነስተው ሲቃ እየተናነቃቸውና ድምጻጨውን በብርጭቆ ውሃ እያጠቡ እናንተን 21 አመት በመግዛት ስራ ስለደከመ ዶ\ር እረፍት እድርገህ ድጋሚ እርገጥ ብሎታል ብለውን ቁጭ፤ የት አሉ የሚለው ጥያቄ አሁንም የባለ ንብረቱ መረጃ ብቻ ስለሆነ ለኛ ምንም እንደማያስፈልግ ነግረውን ቁጭ አሉ። ደሞስ ምን ሆንን እና ነው እንዲህ አይነት መረጃ የሚሰጠን።

ማወናበዱ በዚህ ብቻ አልተገታም በአገር ቤትም ድርጅት አደር ጋዜጦችም እንዲሁ አምታተውን ቁጭ አንዱ አርብ ማታ አዲስ አበባ ገቡ ሲለን አንዱ ደሞ አሜሪካ በመዝናናት ላይ ሳይሆኑ አይቀሩም አለን።

ጥያቄው እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ለምን ይህን ያህል ህዝብን ማወናበድ አስፈለገ የአቶ በረከት ስሞንስ ቢሮው ስራው ምንድነው ለህብረተሰቡ ትክክለኛውን መረጃ መስጠት ከተሳነው ቢሮውን ዘግቶ ለምን ጥቃቅንና አነስተኛ ንግድላይ ወይም የኮብልስቶን ተከላ ላይ አይሰማራም። የሚኒስቴር ቢሮን እንደው በማስፈረስ ልምድ እንዳላቸው ከቀድሞውና ከፈረሰው ማስታወቂያ ሚኒስቴር ትምህርት ወስደናል። እዚህ ላይ እንዲተኮርልኝ የምፈልገው ከዚህ በፊትም ትክክል መነጃ ይህ ቢሮ ይሰጣል የሚል እምነት የለኝም። 

ነገሩማ የእሳቸው ንብረትነት ለህውሃት ስልሆነ ንብረቱ ላልሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መረጃ መስጠት አያስፈልግም የሚል አቋም እንዳላቸው መች ዘነጋን። ከዚህ በፊት ህዝብ ሆብሎ በቅተህናል የኛ የሆነ ለኛ የሚያገለገል ንብረታችን ንብረቱ የሆንን መሪ እንፈልጋለን ባለበት ሰአት ቀጥተው ዝም እንዳሰኙት የቅርብ ግዜ ትውስታ ነው። እንዲሁም በ2010 ምርጫ 99.9% በማግኘት ገዚዎቻችን እንዴት ተደርጎ እንደሆን እነሱ በሚጋባቸው መንገድ ባቻ አሸነፍን ሲሉ አቶ መለስ እንዲህ በነቂስ ወጥቶ መረጠኝ፣ ለሚሉት ህዝብ መስቀል አደባባይ ምስጋና ሲያቀርቡ በወታደር ተከበው እንዲሁም ጥይት በማይበሳው ሳጥን ውስጥ ታሽገው መሆኑንስ መች ዘነጋን።

ስለዚህ ለቅሶም ሲከርም ይጠነዛል ብዙ ከቆየንም የመሪያችን ናፍቆት ይገለናል በመሆኑም ቁርጡን ንገሩን እኛም ምንም ቢሆን 21 አመት በእግር ብረት አስረው የገዙንን አስመራሪያችንን ባናለቅስ እንኳን ሲቀበሩ አይተን አፎይ እንበልና ለቀጣይ ትግል እንነሳ።
አቶ መለስ ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ ቁልፍ እንደሆኑ ወዳጆቻቸው ደረታቸውን ነፍተው ያከናወኑትን ተግባር በመደርደር ይከራከሩላቸዋል ይዘፍኑላቸዋል ያዘፍኑላቸዋል። ተክለ ሰውነታቸውን በአንድዬ ምትክ ያስተክሉላቸዋል እንዲሁም የመልኳቸዋል እንድናመልካቸውም ይሰብኩናል።   

ታዲያ በዚህ የልብ ወዳጆቻቸው ከጎናቸው መለየት በሌለበት ሰአት፣ ምነው እንዲህ ከሚያፈቅሯቸውና ከሚወዷቸው ወዳጆቻቸው መለየት? የኛስ ጉዳይ ለይቶለት የሳቸው ህዝብም ብንሆንም በጠላት ስለተፈረጅን ምንም አይነት መረጃ ላይደርሰን ይችላል ግን ለምን ለድርጅት አጋሮቻቸውና ጓዶቻቸው እንኳን ይህ መረጃ ተነፈገ። የአገርን ደህንነት የሚያናጋ ነው ማለት፣ አቶ መለስ ማለት አገር ናቸው እንዴ? ተነገረን እኮ፤ እኛም ሰማን ”…..ፋጢማም ብትሞት” ተባልን ታዲያ ምን ይህን ያህል የሳቸውን ጉዳይ አስገዘፈው።

ስለዚህ እኔም ዛሬ የሚመለከተውን አካል ካለ? ለዚህ ህዝብ ትክክለኛውን መረጃ ይስጥ፣ አገሪቷንም በአሁን ሰአት ማን እየመራ እንዳለ ማብራሪያና ገለጻ ያድርግ።

በተጨማራም አገራችንን ከፊቷ የተደቀነውን ከፍተኛ አደጋ በጋራ በመግባባት፤ በመተባበርና በርብርብ አስወግደን፣ ጠንካራና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ያገባኛል የችግሩ መፍትሄ አካል እሆናለሁ የሚሉ ማንኛውም አካላትን ሁሉ ያሳተፈ ሂደት እና ጅማሮ በአፋጣኝ እንዲተገበር ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ባለቤት በሌለው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ
ጸሓፊውን ለማግኘት፦ zoloaba112@yahoo.com
  

  

No comments:

Post a Comment