Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Saturday 4 August 2012

የአቶ መለስ ዜናዊ መጨረሻ አሁንም የኢትዮጵያውያን ያልተመለሰ ጥያቄ ሆኗል

ሐምሌ ፳፰ (ሀያ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እጅግ ውስብስብ የሆኑ ሚስጢሮችን በማውጣት የሚታወቁት አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን የአቶ መለስን የደህንነት ሁኔታ ለማወቅ አለመቻላቸው ብዙዎችን አነጋግሯል። አንዳንድ ወገኖች የምእራባዊያን የመገናኛ ብዙሀን ከአሜሪካ ወይም ከአውሮፓ መንግስታት የ”ይለፍ መብራት” ካልበራላቸው፣ ዜናዎችን ለማውጣት ፈቃደኛ አይሆኑም በማለት ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵያ የምእራባዊያን የመገናኛ ብዙሀን የምትስብ አገር ባለመሆኑዋ የመገናኛ ብዙሀኑ ትኩረት እንደነፈጉዋት ይገልጣሉ።
በመሀሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ድረገጾች በመግባት ዜናዎችን በእየለቱ ይቃርማሉ። አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣን ቦታ መራቅ ለኢትዮጵያ አዲስ ተስፋን ይዞ ሊመጣ ይችላል ሲሉ፣ ሌሎች ወገኖች ደግሞ፣ በፍትህ ጋዜጣ ላይ የደረሰውን በመፍራት ከእስካሁኑም የባሰ አፋኝ መንግስት እንዳይመጣ ይሰጋሉ።

በየክልሉ ያሉ የኢሳት ወኪሎች ባሰባሰቡት የናሙና መረጃ ከ51 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ አቶ መለስ አርፈዋል ብሎ የሚያምን ሲሆን፣ 49 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ደግሞ አቶ መለስ አላረፉም ነገር ግን ስራ ለማስራት በማይችሉበት የህመም ደረጃ ላይ ይገኛሉ ብሎ ያስባል። ኢሳት በቅርቡ በአለማቀፍ ግጭት ተንታኝ ቡድን ውስጥ የሚሰሩ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ አቶ መለስ ዜናዊ ማረፋቸውን የሚያመላክት ዜና ካስተላለፈ በሁዋላ አቶ መለስ አርፈዋል ብሎ የሚያምነው ህዝብ ቁጥር ጨምሮአል። በሌላ በኩል ግን አቶ መለስ እንደምንም ብለው ለህዝብ በቴሌቪዥን ቢታዩ ኢሳት ላለፉት ሁለት አመታት የገነባውን ታአማኒት ያጣ ይሆናል በማለት የሚጨነቁ ወገኖች መኖራቸውንም ዘጋቢዎቻችን ገልጠዋል።
ገዢው ፓርቲ የኢሳትን ዘገባ በመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ በአቶ በረከት ስምኦን በኩል ለማስተባበል ቢሞክርም፣ አቶ መለስን በመገናኛ ብዙሀን አቅርቦ ለማሳየትና ለማሳመን እስከ ዛሬ ሳይችል ቀርቷል። የኢሳት የኢዲቶሪያል ቦርድም አቶ መለስ ለህዝብ ቀርበው እንዲታዩ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።
ዛሬ አዲስ አድማስ ባወጣው ዘገባ አቶ መለስ ሰሞኑን ለህዝብ ቀርበው ለመታየት ፈልገው የነበረ ቢሆንም ሳይችሉ ቀርተዋል ብሎአል። አዲስ አድማስ  እንዳለው ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት በጽህፈት ቤታቸው አጠር ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጡ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ከጤናቸው ጋር በተያያዘ እንዲሰረዝ ተደርጓል።”
አድማስ ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ከአራት ባለስልጣናት ጋር ብቻ በመነጋገር እየሰሩ ናቸው” በማለት አንድ ባለስልጣንን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። አቶ መለስ ከሳምንት በፊት አዲስ አበባ እንደገቡ ፣ በሁለት ኢትዮጵያውያን ዶክተሮች ክትትል እየተደረገላቸው ነው ሲል ጋዜጣው አቶ መለስን በህይወት መኖር አጠናክሮ ዘግቧል።
አቶ መለስ ያለፉትን 45 ቀናት ያሳለፉት ታመው መሆኑን መንግስት ለማመን የተገደደው የኢሳት በሬ ወለደ ዜና እያለ ሲያጣጥል ከቆየ በሁዋላ ነው።
የገዢው ፓርቲ ድምጽ የሆነው ሬዲዮ ፋና ስለተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ውይይት መክፈቱ አቶ መለስ ሞቱም አልሞቱም ወደ ስልጣን አይመለሱም የሚለውን ግምት አጠናክሮታል።
የአንድ አገር ህዝብ ስለመሪው የጤና ሁኔታ እንዲያውቅ አለመደረጉ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አፈና የሚያመለክት ነው በማለት የተለያዩ ጸሀፊዎች  ይገልጣሉ።

No comments:

Post a Comment