Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Saturday 8 September 2012

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ያረፈበት 300 ካሬ ሜትር የሚሆን ቦታ ታጠረ


Meles Zenawi's photo on Selassei church wall



ስላሴ ቤተ ክርስቲያን “የአቡነ ጳውሎስ ፎቶ ተነስቶ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ በግራም በቀኝም ቦታ በጣም በትልቁ ተሰቅሏል” ደፍሮ የሚያነሳው ጠፍቷል!
 
የጠቅላይ ሚኒስትሩ  ግብዓተ መሬት ከተፈጸመ እነሆ 5 ቀናት አለፉ ፤ አስከሬናቸው ያረፈበት ቦታ ከዚህ በፊት የማንም አስከሬን ያላረፈበት ከቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በስተ ግራ በኩል ይገኛል ፤ በቴሌቪዥን እንደተመለከታችሁት የውስጡ ግድግዳ በሴራሚክ ተነጥፎ ሳጥኑ በክብር አፈር እንዳይበላው ታስቦ አስከሬኑ አርፏል ፤ ሳጥኑ ላይ ወደፊት ሙዚየም እንደሚሰራ ታሳቢ በማድረግ ብዙ ድንጋይ እና አፈር ሊያሸክሟቻ አልወደዱም ፤ ባይሆን ትንሽ ባዞላ ቢጤ ከላይ በማስቀመጥ ክፍተቱን በሲሚንቶ በመሙላት ከላይ የኢትዮጵያ ባንዲራን አልብሰዋቸዋል ፤
 
በቀብር ስነ ስርዓት አንድ ሰው ከሞተ በኋላ የተቀበረበት ቦታ አፈር መመለስ የተለመደ ቢሆንም ይህ ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ላይ አልተደረገም ፤ ስርዓተ ቀብሩ ከተፈጸመበት ቀን አንስቶ በርካታ ፊደራል ፖሊሶች እና የመከላከያ ሃይሎች በቦታው ይገኛሉ ፤ አስከሬናቸው ያረፈበት ቦታ ላይ 2 ሜትር በ 3 ሜትር የሆነ ቤት በአሁኑ ሰዓት ተሰርቶበታል ፤በሩ መግቢያው ላይ የኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ ያለው ባለ 5 ኮከብ አርማ አርፎበታል ፤ ሰዎች አሁንም የተቀበሩበት ቦታ ድረስ እየሄዱ ሲያለቅሱ ተስተውለዋል ፤ ያረፉበትንም ቦታ ለማየት እስከአሁን ድረስ በርከት ያሉ ሰዎች ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲመጡ ተስተውሏል ፤ ቦታው ላይ ምን ለመስራት እንዳሰቡ ባናውቅም መሰረተ ልማት ለመገንባት የሚያስችል ሸክላዎች ፤ ሲሚንቶዎች ፤ በርካታ ትላልቅ ብረቶች ፤ እንጨቶችና የተለያዩ መሳሪያዎች በቦታው ላይ እየተራገፈ ይገኛል ፤ አስከሬናቸው ሙዝየም ውስጥ ከተቀመጠ ለምን ይህን ሁሉ ነገር ይደረጋል? ሲሉ ሰዎች ሲያወሩ ይደመጣሉ ፤ ባሳለፍናቸው 4 ቀናት ውስጥ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ባይኖርም አሁን ግን አስከሬኑ ያረፈበትን  በአማካይ 300 ካሬ የሚሆን ቦታ በላስቲክ የማጠር ስራ እየተሰራ ይገኛል ፤ ሀውልቱን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ነው እንዳይባል አስከሬናቸው ሌላ ቦታ ያርፋል ተብሏል ፤ ታዲያ ለምን ይህን ያህል ቦታ ማጠር አስፈለገ ? 4 ካሬ የማይበልጥ ቦታ ላይ ያረፈን አስከሬን ስራ ለመስራት ይህ ያህል ቦታ ማጠር አስፈላጊነቱ አልታየንም ፤ ወደፊት ይህ ቦታ የታጠረው ላስቲክ ተነስቶ ለቤተክርስትያኒቱ ምዕመናን የቀድሞውን ቅዳሴ የማስቀደሻ ፤ በዓል ማክበሪያ እና መሰል አገልግሎቶችን ይሰጣል ብለን አሁን መናገር አንችልም::
Abune Paulos photo's on Selassei church wall
የአቡነ ጳውሎስ ፎቶ ያለበት ሸራ የቀብራቸው እለት በቤተክርስትያኑ በስተግራ በኩል መሰቀሉ ይታወሳል ፤ ከሁለት ቀን በኋላ ግን የአቡነ ጳውሎስ ፎቶ ተነስቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ በግራም በቀኝም ቦታ በጣም በትልቁ ተሰቅሏል ፤ መጀመሪያ እኛ የአቡነ ጳውሎስን ፎቶ ሰቅለን ባናሳያቸው ኖሮ እነርሱም ፎቷውን ለመስቀል ጥያቄ ባላቀረቡ ነበር  ፤ መሰቀሉን ለምን? እያልን ሳይሆን የተሰቀለበት ቦታ ግን አግባብ ነው የሚል ሀሳብ የለንም ፤ ፎቶው ዛሬ ከተሰቀለ 7 ቀን ሞልቶታል እስከመቼ እንደሚቆይ አይታወቅም ፤ የጥላሁን ገሰሰ ፎቶ የሞተ ሰሞን በእጁ ማይኩን ይዞ በትልቁ በግቢው ውስጥ መሰቀሉ የዛሬ 3 ዓመት ትውስታችን ነው ፤ የጥላሁንን ፎቶ ማይክ ይዞ በግቢው ውስጥ የተመለከቱ ጥቂት ሰዎች በሁኔታው ደስተኛ አለመሆናቸው በጊዜው ሲገልጡ ነበር ፤ ለምን ? ብለው ቢጠይቁም መልስ የሚመልስ ሰው አይገኝም ፤ ቤተክርስትያን ውስጥ በትልቁ እንዲህ አይነት ፎቶ መመልከት ለአማኙ ምን አይነት መንፈስ ውስጥ እንደሚያስገባው ማወቅ አይከብድም ፤ በጊዜው ጥቂት ወጣቶች “ኮንሰርት ያለበት ነው የሚመስው” እያሉም ሲቀልዱ ተስተውሏል ፤ ስለዚህ የቤተክርስትያንን ግቢ እኛው መደረግ ያለበትንና የሌለበትን ለይተን ማወቅ መቻል አለብን ፡፡
 
5ኪሎ ቅድስት ማርያም በሩ ላይ ቆመው ሲሳለሙ ከፊት ለፊት ያለው የአቡነ ጳውሎስ ፎቶ ይመለከታሉ ፤ አሁን ደግሞ ቅድስት ሥላሴ ሄደው እጅዎትን ወደላይ አንስተው ለማማተብ ሲሉ ከፊት የሚታይዎት ሌላ ነገር ነው ፤እነዚህ ነገሮች ከጊዜ ወዲህ የመጡ ተለጣፊ ነገሮችን እየለመድናቸው መጥተን ወደፊት ሌላ ነገር እንዳይፈጥሩ ፍራቻ አለን ፤ ከዓመታት በፊት የአቡነ ጳውሎስ በየቤተክርስትያኑ የተሰቀሉት ፎቶዎች ቅዱስ ሲኖዶስ ይነሱ ብሎ መወሰኑ የሚታወቅ ነው ፤ ማንሳት ሲያቅተን ለአእምሯችን ተገቢ ነው ብለን ነግረነው ካበቃን በኋላ አሁን ብናያቸውም ባናያቸውም ምንም ላይመስለን ይችላል ፤ ነገር ግን አግባብ አለመሆኑን ግን ማወቅ አለብን ፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ፎቶም ቢሰቀል አግባብ የሚሆነው አስከሬናቸው ያረፈበት ቦታ ቢሆን መልካም ነው ፤ እንደ አሁኑ ተደርጎ መሰቀሉ ግን አግባብ ነው አንልም(ከተሳሳትን እንታረማለን)፡፡
ቸር ሰንብቱ
No related posts.

No comments:

Post a Comment