Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Saturday, 8 September 2012

የጌታቸውን ስድብ የተሞሉ በቀቀኖች






ከዳዊት ዋስይሁን

 እንደተለመደው ሁሌም ጠዋት ከምሰራቸው ስራዎች አንዱ የማህበራዊ ገጽ ጓደኞቼን እንኳን አደራችሁ ማለት እና ባንዳንድ ጉዳዮች ላይ ኦንላይን መጻጻፍ ነው። በተለይ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ መልእክቶች በሰፊው ከማውቃቸውም ከማላውቃቸውም ሰዎች ይደርሱኛል ባብዛኛው ገንቢና ትግላችንን አጠናክረን ለውጡን ማፍጠን እንዳለበት የሚያሳስቡኝ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ግን መረን የለቀቀ ከባህላችን ውጭ በሆነ መንገድ በሚያንቋሸሹና በጥላቻ የተሞሉ መልእክቶችን የያዙ ናቸው ይህም ከመገረም አልፌ ተደምሜባቸዋለሁ፣ በተለይ ከሰሞኑ የጻፍኳት መለስን የማልወድበት ምክንያት የምትል ጽሁፌን ያነበቡ ጥቂት /ይህንን ቃል ተውሼ ነው/ የመለስ ደጋፊዎች በመቅበጥበጣቸው አቋሜ በግልጽ እንዲያውቁ ይህንን ደግሜ ጽፌያሁ።

ጥያቄው ለምን በአሁን ሰአት ስድቡና ማንቋሸሹ እንዴት እንዲህ ሊበዛ ቻለ የሚለው ነው። አንድ መምህሬ ባንድ ወቅት ሲያስተምሩኝ ሰዎች በራሳቸው መተማመን ሲያቅታቸው እና ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሲሆኑባቸው የውስጣቸውን መሸነፍ፣ መረበሽ እና መታመስ ያሸነፉ ስለሚመስላቸው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከመሳደብና እራሳቸውን ከማዋረድ ወደኋላ አይሉም ምክንያቱም በምክንያታዊነት ከማሳመንና ከማሸነፍ ይልቅ ሌሎች ላይ በሚሰነዝሩት አስጸያፊ ቃል ሰዎች ተንቀጥቅጠው የሚገዙላቸው ስለሚመስላቸው ነው ያሉት ትዝ ያለኝም ወቅት ነው።


የገረመኝ ምነው ይህ ሁሉ ስድብ መለስ ከሞተ በኋላ እንዳሸን ፈለቀ እንደውም የስድብ አምራቹ ጌታቸው ሃያ አንድ አመት ያመረተውን ፌዝ፣ ቧልት እና ስድብ ይዞት ወደ አፈር የገባ መስሎኝ ነበር ነገር ግን በተገላቢጦሹ ከመቃብር የስድብ ውርጂብኝ በሪኮማንዴ እንደላከላቸው ሁሉ ከላይ ጀምረው እስከታች ሰዎችን በመስደብ በማዋረድ ተጠምደዋል፣ በዚህ ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ከግብ በላይ እንዳከናወኑ አልጠራጠርም።

እኔ የምለውና የማይገባኝ ነገር እኔ እንደ ዜጋ እና እንደ ግለሰብ የፈለግሁትን ማለት፣ ማሰብ፣ መጻፍ የለብኝም፤ ለሁሉም ነገር አስገባሪዎቼን ማስፈቀድ አለብኝ እንዴ? እኔ መለስ ጀግና አይደለም ማለት አልችልም? እስቲ እንቀምር መለስ ዜናዊን ከሽብሬ ምን ለየው? መልሱ ምንም፤ ምክንያቱም ሁለቱም የሰው ልጆች ስልሆኑ።

እርግጥ ነው ከእሳቸው የታዳጊዋን ሽብሬ ደም የሚከብረው በመለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትእዛዝ ከተገደሉት አእላፋት ንጹሃን ዜጎች አንዷ በመሆኗ ነው፤ ነገር ግን ልክ እንደሳቸው በቅስቀሳና በገንዘብ ድለላ ጀግና ሳትባል የብዙዎችን ልብ የገዛች ለዘመናት የምትዘከር ጀግና ስለሆነች ነው። እርግጥ ነው አቶ በረከት ስምኦን እንደ መለስ አሁን በአገር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ህዝብ ለሽብሬ ወይም ባለፉት ሃያ አንድ አመታት ለተጨፈጨፉት ሰማእታት እንዲያዝን በየአካባቢው እንዲደራጅና ጥቁር ለብሶ እንዲያለቅስ መመሪያ አልሰጡም። 

ነገር ግን ከተነገረለት፣ ከተቀሰቀሰለትና ሃዘን ከታወጀለት መለስ ይልቅ የሰማእታት ደም የኢትዮጵያውያንን ልብ ይገዛል፣ የእነሱም እውነተኛ ጀግንነት በየትኛውም ትውልድ እየተዘከረ ይኖራል፤ የአቶ መለስ ጀግንነት ግን ጀምበር እስኪጠልቅ የሚቆይ የአድርባዮች ሁካታና ስካር ነው ይህንን ደግሞ የሚደግፏቸውም ከልብ ያውቁታል፣ ግዜ ደጉ ያሳየናል፣ ሁሉም ይሰክናል ተዛ ዛሬ በጡሩንባና በገንዘብ ያስለቀሱት ህዝብ ነገ ለምን ምክንያት እንዳለቀሰ ደውሉ ሲደወል አስለቃሾች በደንብ ይረዱታል፣ ኧረ እንደውም ሰው እኮ ደስ ሲለውም ያለቅሳል አትሌቶቻችን ሜዳልያ ሲሸለሙ አልቅሰው የለ።

ወዳጄ አንድ ከወደ አሜሪካ የተፈጸመ ታሪክ አጫወተኝ፣ ታሪኩ እንዲህ ነው፣ በአንድ ወቅት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በብዙዎች አሜሪካውያን ዘንድ እንደ ለውጥ መሪ የሚታዩት በተገደሉበት ወቅት በመሞታቸው አሜሪካና መላው አለም ሲያለቅስ፣ የጥቁር መብት ተከራካሪው ማልኮሜክስ ስለ ፕሬዚዳንቱ ሞት ሲያስረዳ ”The chicken goes to roast” አለ፤ እንግዲህ በግርድፉ ሲተረጎም ዶሮዋ ገሃነም ወረደች ማለት ነው፤ በድፍረት የፕሬዚዳንቱ መሞት ለሱ እረፍቱ መሆኑን የገለጸው፤ እኔም ለሚሰድቡኝ እና ጉዳዩ ላንገበገባቸው ጥቂት አቀንቃኞች አምባገነኑን ቢሳሉም ላያገኙት እስከወዲያኛው ሄዷል እንደውም ስርአቱም እንደሚከተል ሊረዱት ይገባል፣ እንዲሁም በመከራ ለጠበሱትና ለጋቱት ኢትዮጵያዊ ወገኔ የሳቸውን መሄድ በማስመልከት የልቡን ስሜት ቢጠየቅ የማልኮሜክስን ጥቅስ በመጥቀስ ደስታውን እንደሚገልጽ እርግጠኛ ነኝ።

እኔ አሁንም ያልገባኝ ነገር አለ፤ እነኝህ ጭፍን ደጋፊዎች መለስ መሞት ከውድ ኢትዮጵያ አገሬ ጋር ያገናኙታል፣ ምን አገናኘው? እንደውም ምድሪቷ ራሷ እፎይ አለች እንጂ፣ መለስ ሞተ ታዲያ ምን ይጠበስ ብል፣ አንተ አገርህን የማትወድ ተብሎ ከዋና አሸባሪዎች መደዳ እሰለፋለሁ፣ መለስን መውደድ አገርን መውደድ ነው እንዴ ጃል፣ መለስ ማለት እኮ አንድ ሰው ነው፣ መለስ ተወለደ ሞተ፤ ኢትዮጵያ እሱ ከመወለዱ በፊትም ነበረች አሁንም አለች ወደፊትም ትኖራለች እሱ ሳያስፈልጋት። 

ለጭፍን ጥቂት የመለስ እውራን የማስተላልፈው መልእክት አገራችሁን ከመለስ በላይ ውደዱ ወደፊት ለሚፈጠረው የፍትህ፣ የእኩልነትና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የበኩላችሁን ተወጡ፣ አገራችሁ ኢትዮጵያ ከመቼውም ገዜ በላይ ትፈልጋችኋለች፣ ለመመለስ ግዜው አልረፈደም።      
በመልእክት ማቆሪያ ሳጥኔ ውስጥ ከሚቀመጡልኝ መጠነ ሰፊ ስድቦች ጠባብ፤ የጨለመበት፤ የተደናበረ እና የሚያረገው ግራ የገባው የሚሉ ይገኙበታል፣ በውነት ለመናገር አሁን እነኝህ ሁሉ አባባሎች ማንን ነው የሚወክሉት? የአመለካከት ልዩነትን የማያከብር፣ ከተቃወሙ እንደ ጠላት የሚፈረጅበት፣ በመንቀጥቀጥ ብቻ እሺ ብሎ እንዲገብር የሚያስገድድ፣ ከልኩ በላይ ያበጠ ስርእት ያለበት አስተዳደር፤ እንግዲህ ጠባብ ማን ነው? በመለስ መሞት የሚያረጉት የጠፋባቸው አይናቸው ታውሮ በጨለማ እየተደናበሩ ያሉ ደጋፊዎች የመለስ ሬሳውም እንዲገዛቸው የሚማጸኑት ናቸው የጨለመባቸው ወይስ እኔ? ተደናብረው ሁሉንም እንደ አበደ ውሻ እየተናከሱ ያሉና ቅብዥርዥራቸው የወጣ እነማን ናቸው? 

ዛሬ ጎረቤታችን ጋና መሪዋን ታውቃለች፣ እኛ ግን፣ ማን እንደሚመራን እንኳን፣ አገዛዙ ምን እየሰራ እንዳለ፣ ያምነናል ለሚሉት ህዝብ ቀርቶ ለራሳቸው ቅርብ አባላት እንኳን የሚናገር የጠፋበት፣ ግራ ገብቷቸው ግራ የሚያጋቡ መረጃዎች በየቀኑ እያመረቱ ራሳቸው የተደናበሩት ሳያንሳቸው ህዝቡን እያደናበሩ የሚገኙበት፣ የሚያረጉትን ራሳቸው አምታተውት በእውርናና በደመነፍስ እየታመሱ ያሉ እነማን ናቸው? 

ታላቁ መጽሃፍ አምላክም የፈርኦንን ልብ አደነደነ የትእቢትም ቃል ይናገር ነበር ይላል የኛ የአሁን ዘመን አስገባሪዎቻችን ልባቸው ከማበጡና ከመደንደኑ ብዛት የትናንት ማንነታቸውን እረስተው ዛሬ ዜግነት እሚሰጡንና አገር ቤት ለመግባትና ከአገር ቤት ለመውጣት የሚፈቅዱልን እነሱ ሆነዋል፣ ወንጀላችን ምንድነው ብለን ብንጠይቅ መልሱ እነሱ ከሚያስቡት የተለየ ስላሰብን ብቻ ነው፣ ማሰብም ወንጀል የሆነበት ስርአት። 

ነገሩ እንግዲህ እንዲህ ነው ለኔ ድል! ድል! ይሸተኛል ማረፊያችንም ቅርብ እንደሆነ ይታየኛል፤ ይህንን የተገነዘቡ ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ የመለስና የስርአቱ ፍርፋሪ ለቃሚዎች ከገቡበት የሞት መቃብር አንሰራርተው ነፍስ ለመዝራት የመጨረሻ የሞት ሽረት የጣር መንፈራገጣቸውን እያረጉ ይገኛሉ በመሆኑም ይህንን በመገንዘብ የነጻነት ሃይላት የሚደረጉ አንዳንድ በጣም ከቁጥር የማይገቡ ትንኮላዎችን ከመጤፍ በመቁጠር ሃይላችንን እና ጉልበታችንን በማቀናጀት እልህ አስጨራሽ የሆነውን ትግላችንን እንቀጥል ስል፣ ከዋናው አላማችን ፈቀቅ ሊያረጉን የሚፈልጉ ሃይላትን በመናቅ ነገር ግን አላማቻውን በመታገል ነጻነት፤ ፍትህና ዲሞክራሲ ለጠማው ህዝባችን መልስ እንስጥ።

ጸሃፊውን ለማግኘት ይህንን ኢሜይል ይጠቀሙ
Zoloaba112@yahoo.com

No comments:

Post a Comment