Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday 16 January 2013

የናሽናል ጂኦግራፊ ጋዜጠኛ የሰባት ዓመታት የእግር ጉዞ ከአፋር ክልል ጀመረ

ናሽናል ጂኦግራፊ የተሰኘው ታዋቂ የሚዲያ ተቋም ዕውቅ ተመራማሪና ጋዜጠኛ የሆነው ሚስተር ፖል ሳሎፔክ ‹‹አውት ኦፍ ኤደን ወክ›› የተባለ ሰባት ዓመታት የሚፈጅ በርካታ የአፍሪካ፣
የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የእስያ፣ የሰሜን አሜሪካና የደቡብ አሜሪካ አገሮችን የሚያካልል የእግር ጉዞ ባለፈው ዓርብ በአፋር ክልል ሄርቶ ቡሪ ከተባለ የሆሞ ሳፒያን መገኛ ቦታ ጀመረ፡፡

ከዚህ ቀደም በሠራቸው ምርጥ የምርመራ ዘገባዎች ሁለት ጊዜ የፑሊትዘር ሽልማት ተሸላሚ የሆነው ፖል ሳሎፔክ ጉዞውን በጀመረበት ሄርቶ ቡሪ ለሪፖርተር በሰጠው መግለጫ የአፋር ክልል ጥንታዊ የሰው ልጅ መገኛ መሆኑን ጠቅሶ፣ ከ150,000 ዓመት በፊት ዘመናዊ የሰው ዘር (Modern Homo Sapien) ከአፋር ክልል በመነሳት ወደተለያዩ አኅጉራት የተሰደደ በመሆኑ፣ እርሱም ይህን የስደት ጉዞ መስመር ተከትሎ ጉዞውን ለማድረግ መወሰኑን ተናግሯል፡፡ የአፋር ክልል በርካታ የጥንታዊ ሰው ቅሪተ አካላትና መገልገያ መሣሪያዎች በየጊዜው የሚገኝበት ቦታ እንደሆነ የገለጸው ፖል፣ ‹‹አውት ኦፍ ኤደን ወክ›› የተሰኘው የሰባት ዓመታት የእግር ጉዞ 24,000 ማይልስ እንደሚሸፍን ተናግሯል፡፡

ዘመናዊ የሰው ልጅ ስደት ከጀመረበት ሄርቶ ቡሪ ጉዞውን በመጀመሩ የተሰማውን ደስታ የገለጸው ፖል፣ የመጀመሪያ ጉዞውን የሚያደርገው ከአፋር ክልል ወደ ጂቡቲ እንደሆነና ጂቡቲ ለመድረስ 27 ቀት እንደሚፈጅበት ተናግሯል፡፡ በጂቡቲ ለአንድ ወር ዕረፍትና ዝግጅት ካደረገ በኋላ ቀይ ባህርን በጀልባ በማቋረጥ ሳዑዲ ዓረቢያ ይገባል፡፡ ከዚያም የእግር ጉዞውን በመቀጠል የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችን በማቋረጥ ከአንድ ዓመት በኋላ እስራኤል ይደርሳል፡፡ በመቀጠልም የጉዞ አቅጣጫውን ወደ እስያ በማድረግ ፓኪስታን፣ ቻይናና ህንድን አካሎ ወደ ሩሲያ በመዝለቅ ሳይቤሪያን አቋርጦ በአሜሪካ አላስካ በኩል በማቅናት የደቡብ አሜሪካ አገሮችን፣ አቆራርጦ ከሰባት ዓመታት በኋላ የጉዞ ማብቂያ ወደሆነው ደቡብ አሜሪካ ጫፍ ይደርሳል፡፡

ናሽናል ጂኦግራፊ የፖል ሳሎፔክን የጉዞ ገጠመኝ የሚተርክበት ‹‹Out of Eden Walk›› የሚል ድረ ገጽ የከፈተ ሲሆን፣ ዘገባው በናሽናል ጂኦግራፊ ቴሌቪዥን ቻናል በየጊዜው ይተላለፋል፤ በናሽናል ጂኦግራፊ መጽሔትም ይታተማል፡፡ ፖል የሰባት ዓመታቱን የእግር ጉዞ ካጠናቀቀ በኋላ ይህን ረጅም ጉዞ የሚተርክ መጽሐፍ እንደሚያሳትም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ፖል ታሪካዊውን ጉዞ ከመጀመሩ በፊት በአፋር ክልል የአርኪዎሎጂ ምርምር የሚያደርግ አሜሪካዊያንና ኢትዮጵያዊያን ተመራማሪዎች የሚገኙበት የመካከለኛው አዋሽ የአርኪዎሎጂ ምርምር ፕሮጀክትን ለስድስት ቀናት ጐብኝቷል፡፡ በአሜሪካዊው ፕሮፌሰር ቲም ዋይት የሚመራው ቡድን በመካከለኛው አዋሽ በሄርቶ ቡሪና በሌሎችም ሥፍራዎች ላለፉት 31 ዓመት በርካታ የአርኪዎሎጂ ምርምሮች በማካሄድ በርካታ ጥንታዊ የሰው ልጅ ቅሪተ አካላትና የድንጋይ መሣሪያዎች እንዳገኘ የቡድኑ አባላት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የቅሪተ አካላቱ ዕድሜ ከ150,000 እስከ 2.4 ሚሊዮን ዓመት እንደሚገመት የቡድኑ መሪ የሆኑት የ61 ዓመቱ አዛውንተ ፕሮፌሰር ቲም ዋይት ገልጸዋል፡፡ የቡድኑ ከፍተኛ አርኪዎሎጂስት ዶ/ር ብርሃኔ አስፋው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቡድኑ በተለያዩ ጊዜያት ያገኛቸው ቅሪተ አካላት ኢትዮጵያ የጥንታዊ የሰው ዘር መገኛ ብቻ ሳትሆን የዘመናዊ ሰው መገኛ ጭምር መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡ ቡድኑ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን በታዋቂ የሳይንስ ጆርናሎች እንዳሳተመ የተናገሩት ዶ/ር ብርሃኔ፣ በቅርብ ጊዜ ባካሄዳቸው ምርምሮች በርካታ አስደናቂ ቅሪተ አካላትና የድንጋይ መገልገያ መሣሪያዎች ማግኘቱን ገልጸው፣ ግኝቶቹን በቅርቡ ለመላው ዓለም ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የግኝቶቹን ሪፖርት ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ለቅርስ ጥበቃ ኤጀንሲ ሪፖርት ከማድረጉ በፊት ለሚዲያ መግለጽ እንደማይፈልጉ በማስረዳት ስለግኝቶቹ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ፖል ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት በመካከለኛው አዋሽ ሁለት የምርምር ካምፖች የስድስት ቀናት ቆይታ በማድረግ ሳይንቲስቶቹ የቅሪተ አካል ፍለጋ ሥራቸውን እንዴት እንደሚያካሂዱ ተመልክቷል፡፡ የሪፖርተር ጋዜጣም በመካከለኛው አዋሽ በመገኘት የሳይንቲስቶቹ ቡድን የሚያደርገውን የመስክ ምርምር ተመልክቷል፡፡

በሄርቶ ቡሪ አካባቢዎች በቡድኑ አባላት የተገኙ ከመሬት ያልተነሱ የተለያዩ የሰው፣ የዝንጀሮና ጉማሬ ቅሪተ አካሎችና ጥንታዊና ዘመናዊ የሰው ዘሮች ለአደንና ሥጋና አጥንት ለመቁረጫ ይጠቀሙባቸው የነበሩ በርካታ የድንጋይ መሣሪያዎች ለመመልከት ችለናል፡፡

በሁለት ግመሎች ጓዙን ሸክፎ የሰባት ዓመታት የእግር ጉዞ የጀመረው ፖል በመካከለኛው አዋሽ ፕሮጀክት በሚሠራው የአርኪዎሎጂ ምርምር ሥራዎች በእጅጉ መደነቁን ገልጾ፣ እንደዚህ ዓይነት የዳበረ የአርኪዎሎጂ ዕውቀት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ሳይንቲስቶች በማግኘቱ እንደተደሰተ ተናግሯል፡፡ ፖል ጉዞውን አስመልክቶ በሚያስተላልፋቸው ዘገባዎች ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ለዓለም እንደሚያስተዋውቅ አስታውቋል፡፡ የ‹‹አውት ኦፍ ኤደን ወክ›› ፕሮግራምን በድረ ገጽ የናሽናል ጂኦግራፊ ቴሌቪዥን ጣቢያንና መጽሔት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚከታተሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ፖል በኢትዮጵያ የሚደረገው ጉዞ የተሳካ እንዲሆን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የቅርስ ጥበቃ ኤጀንሲ፣ የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የአፋር ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና የመካከለኛው አዋሽ የአርኪዎሎጂስቶች ቡድን ላደረጉለት ትብብር ምሥጋናውን አቅርቧል፡፡ ፖል የሚያደርገውን የእግር ጉዞ በቪዲዮና በፎቶ ካሜራ የሚቀርፀው ታዋቂ የሆነው የናሽናል ጂኦግራፊ የካሜራ ባለሙያ ጆን ስታንማየር ጉዞውን ከፖል ጋር አብሮ የጀመረ ሲሆን፣ እስከ ጂቡቲ ለሚደረገው ጉዞ መንገድ የሚመራ ኢሌማ መሐመድ የተባለ የአፋር መንገድ መሪ አብሮ ተንቀሳቅሷል፡፡ ተጓዦቹ የሚጠቀሙባቸውን ካርታዎች፣ ጂፒኤስ፣ የሳተላይት ስልኮችና ሌሎች መሣርያዎች አሟልተው ይዘዋል፡፡ ሳይበላሹ የሚቆዩ ምግቦች፣ የመጀመሪያ ሕክመና መስጫ መሣርያዎችና መድኃኒቶች እንዲሁም ውኃ በብዛት በግመሎቹ ላይ ተጭነዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ታደለች ዳሌቾ የ‹‹አውት ኦፍ ኤደን ወክ›› ፕሮጀክት የኢትዮጵያ የጥንታዊ ሰው ዘር መገኛ መሆኗን በመላው ዓለም የሚያስተዋውቅ ፕሮጀክት በመሆኑ፣ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ ጋዜጠኞቹ በጉዞአቸው ወቅት በአፋር ክልል የሚገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሙሉ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡         

No comments:

Post a Comment