Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday 12 May 2013

የአቶ አስገደ ልጆች (አሕለፎምና የማነ አስገደ) ምን ወንጀል ሠሩ? – መስፍን ወልደ ማርያም


Prof. Mesfin Woldemariamአቶ አስገደ ከቀደሙት የወያኔ ታጋዮች አንዱ ነው፤ ወያኔ ለሥልጣን እስከበቃበትና ከዚያም አልፎ አባል ሆኖ ቆይቶአል፤ በኋላ ግን የተመለከተውን አሠራርና አካሄድ እየተመለከተ ወያኔ ዱሮ የነበረውን ዓላማ በሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ከሚደረገው ጋር ሲያነጻጽር መነሻውን እየሳተ መሆኑን በመገንዘቡ የወያኔን አሠራር በቁጭት መተቸትና መንቀፍ ጀመረ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፎችንም ደረሰ፤ አጫጭር ጽሑፎችም በጋዜጦችና በመጽሔቶች ላይ ጻፈ፤ ከጓደኞቹ ከቀድሞ የወያኔ አባሎች ጋር በመሆን አሬና የሚባል ተቀናቃኝ ፖሊቲካ ፓርቲ አባል ሆነ፤ ይህ ሁሉ እንደሰውም፣ እንደዜጋም የአቶ አስገደ መብቱ ነው፤ ወያኔን በመተችትና በመንቀፍ አቶ አስገደ የመጀመሪያው አይደለም፤ የመጨረሻውም እንደማይሆን እየታየ ነው፤ ከዚህ በፊት አቶ ገብረ መድኅን አርአያ ወያኔን ሲያጋልጥ ቆይቷል፤ አሁንም እየቀጠለ ነው፤ አሁን ደግሞ ከአቶ አስገደ ጋር ኤንጂኒር አብደልወሃብ ቡሽራ አለ፤ … እውነት የብረት ግንብም ቢሆን ሰርስሮ የመውጣት ኃይል አለው፤ እየወጣም ነው፡፡
Prof. Mesfin Woldemariam

በሚያዝያ (2005) ውስጥ የአቶ አስገደ ሁለት ወንዶች ልጆቹ ከተለያዩ ከተሞች ተይዘው ታሰሩ፤ አቶ አስገደ እንዳለው አንዱ ልጁ፣ አሕለፎም አስገደ ሚያዝያ 16/2005 ‹‹በአንድ ሻይ ቤት ቡና ሲጠጣ›› ተያዘ፤ ሌላው ልጁ ደግሞ፣ የማነ አስገደ የሚባለው የሶፍትዌር ኤንጂኒር ታሞ ስለነበረ ጠበል ለመጠመቅ ወደአያቱ መኖሪያ ሄዶ ሳለ በሚያዝያ መጨረሻ ሳምንት አካባቢ ተይዞ ታሰረ፤ የሁለቱ የአቶ አስገደ ልጆች በሚያዝያ 16ና ምናልባትም 25 መሀከል በሁለት በተለያዩ ከተሞች ተይዘው መታሰር አድፍጦ የሚጠብቃቸው ኃይል የነበረ ያስመስለዋል፤ ልጆቹ ከወያኔ ድርጅት ጋር ያላቸው/የነበራቸው ግንኙነት አይታወቅም፤ አባታቸው አቶ አስገደ ግን ወያኔ የነበረ የወያኔ ነቃፊ መሆኑ ይታወቃል፤ የሁለቱ ወጣቶች መታሰር ምክንያት ከመንግሥት ጋር ሳይሆን ከወያኔ ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚያመለክተው አሕለፎም የሚባለው በመጀመሪያ የታሰረው በመደበኛ ፖሊስ ጣቢያ ወይም ቀበሌ ሳይሆን 06 በሚባል የወያኔ እስር ቤት መሆኑ፣ የፖሊስ ጣቢያውን ኃላፊ አቶ አስገደ ሲጠይቀው የሰጠው መልስ ‹‹አስገደ እራስህ ተበክለህ እየጮህክ እዚህ ያለውን ሰው እየበከልክብን ነው›› ማለቱ የልጆቹ መታሰር የተያያዘው ከአባታቸው ጋር እንደሆነ የሚያመለክት ያስመስለዋል፡፡
የአክሱም ጽዮን የሃይማኖት አባቶች እንዳስተማሩን ‹‹አዳም በበደለ መድኃኔ ዓለም ካሠ፤›› የተባለበት ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ የሰው ሥጋ ለብሶ፣ ተደብድቦ፣ ተሰቅሎ፣ ተቀብሮ፣ ተነሥቶ ወደሰማይ ያረገውና በገሃነመ እሳት ያሉትን ነፍሳት ነጻ ያወጣቸው የሰውን ልጅ ከኃጢአት ውርስ ነጻ ለማውጣት ነው፤ በአዳም ኃጢአት የሰው ልጆች አይቀጡም፤ እያንዳንዱ ሰው ለሚሠራው ራሱ ኃላፊ ይሆናል፤ ስለዚህም አዳም ዕጸ በለስን በልቶ በበደለ መድኃኔ ዓለም (ኢየሱስ ክርስቶስ) በሞቱ የሰውን ልጅ ነጻ አወጣው፤ ካሠው፤ ይህ የሐዲስ ኪዳን መልእክት ነው፤ በአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ዘመናዊ ሕግ እስቲወጣ ድረስ የሕግ መሠረት የነበረው ፍትሐ ነገሥት ልጆች በአባታቸው ወንጀል አባትም በልጁ ወንጀል እንዳይከሰሱ ይደነግጋል፤ የኦሪት ሕግ በሐዲስ ኪዳን ተሸሮአል፤ ወያኔ ይህንን ሁሉ የሕግ አስተሳሰብ እድገት አያውቅም፤ ሊያውቅም አይፈልግም፡፡
ስለዚህ በዘመነ ኦሪት በነበረ አስተሳሰብ እንገዛለን፤ የአቶ አስገደ ልጆችም በዘመነ ኦሪት አስተሳሰብ እንደተያዙ ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ያስረዳሉ፤ ከዚህም በፊት እናት በልጅዋ ምክንያት እንደተገደለች፣ ሚስቶች በባሎቻቸው ምክንያት እንደተደበደቡ እናውቃለንና ነገሩ አዲስ አይደለም፤ እንኳን ከወያኔ ውጭ ባሉ ሰዎችና በወያኔዎችም ላይ ይኸው የኦሪት ሕግ በወንድማማቾች ወያኔዎች ላይ ሲፈጸም አይተናል፤ ነገር ግን ከጫካ በኋላ በሃያ ዓመታት የሥልጣን ዘመንም ይቺን ቀላል የፍትሕ ትምህርት አለመማራቸው የሚያስገርም ብቻ ሳይሆን የሚያሳፍርም፣ የሚያስፈራም ነው፤ ሥልጣን የኃላፊነት ሸክም በመሆኑ ያስተምራል፤ በሥልጣን መማር የማይቻል ሲሆን ሥልጣን የውድቀት ምክንያት ይሆናል፡፡
በቅንነትና በእውነት ላይ ያልተመሠረተ ኃይል የጭቆና መሣሪያ እንደሚሆን የታወቀ ነው፤ በልጅነትና ባለመብሰልም ይሁን በእውቀት ማነስ ትንንሾች ልጆችና ወጣቶች በስሜት ብቻ በአንዳንድ መፈክሮች ተማርከው አጥምደው ለሚጠብቋቸው ቡድኖች ሲሳይ ይሆናሉ፤ ይህ ተደጋግሞ የታየና እየታየ ያለም እውነት ነው፤ ‹‹አታስቡ – እኛ እናስብላችኋለን፤›› በሚሉ ቡድኖች ውስጥ ገብተው የሰውነት ባሕርያቸውን ሁሉ ያጣሉ፤ ከብዙ ዘመናት በኋላ እየነቁ ማሰብ ሲሞክሩና የራሳቸውን አስተያየት መስጠት ሲጀምሩ አንድ ወንጀል ይለጠፍባቸዋል፤ የታወቁትን ብቻ ለማስታወስ ያህል ታምራት ላይኔንና ስዬ አብርሃን መጥቀስ ይቻላል፤ በሁለቱም ላይ የተለጠፉባቸው ወንጀሎች የግል ሳይሆኑ ቤተሰቦቻቸውን የሚጨምሩ ነበሩ፤ አንድ የቡድኑ አባል እኔም ማሰብ እችላለሁ ሲል መሠረታዊውን ሕግ ይጥሳል፤ ሁሌም ቅጣቱ በማራቆትና ደሀ በማድረግ ከጥቅልነት ወደሰውነት የተመለሰውን አስጨንቆ እንዳያስብ ለማድረግ ነው፤ የከፈተውን የአእምሮውን በር እንደገና ዘግቶ አንዲያፍነው ለማድረግ ነው፡፡
ብሩኅ አእምሮ ያላቸውን ልጆች እየለቀሙ አምጥቶ አንድ ከፍተኛ ስም ያለው የትምህርት ተቋም ውስጥ አስገብቶ ዘመኑ ያፈራውን የእውቀት ጥበብ አንዲማሩ አድርጎ ታዛዥ ሎሌ ለማድረግ መሞከር የትምህርትን ባሕርይ አለማወቅ ነው፤ የትምህርትን ባሕርይ በጫካ ውስጥ መማር አይቻልም፤ የትምህርትን ባሕርይ በሥልጣን ወንበር ላይ ተቀምጦና በዕብሪት ተወጥሮ መማር አይቻልም፤ በኢትዮጵያ ባህላዊ ትምህርት ብዙ ልፋት አለበት፤ ከሞቀ ቤት ርቆ፣ በቀፈፋ ተመግቦ፣ ከሌሎች ትምህርት ፈላጊዎች ጋር እየተንከራተተ ብዙ ዓመታት አሳልፎ ነው የትምህርት ባሕርይ የሚገለጠው፡፡ በዘመናዊው ትምህርትም መንከራተቱና ልፋቱ ይቀንስ እንጂ ከባድና አድካሚ ነው፤ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የትምህርት ሚኒስትር ከነበሩት ከአቶ አካለ ወርቅ ጋር ስለወጣቶች ችኩልነት ስንነጋገር አንድ ነገር ነገርኋቸው፤ ‹‹ተማሩ ብላችሁ ትምህርት ቤቶች ከፈታችሁልን፤ ለአንዳንዶቻችን የአዳሪነት ምቾትም ሰጠታችሁን፣ ከዚያም በኋላ በየፈረንጅ አገሩ እየላካችሁ አስተማራችሁን፤ ተማርን፤ መማር ማለት መለወጥ ነውና እኛ ተለወጥን፤ እናንተ ግን አልተለወጣችሁም፤ መሠረታዊ ችግራችን ይህ ነው፤›› የተናገርሁት ነገር በጣም ተሰምቶአቸው ለጥቂት ሰኮንዶች ትክዝ አሉ፤ ‹‹እውነትህን ነው፤ ታዲያ ይህንን ቸግር ማን ይፍታው?››
ወያኔ/ኢሕአዴግ እየጠበበ ሲሄድ ከውስጥ እየነቃ ነው፤ አንዳንድ አባሎቹ ነጻነታቸውን እያወጁ ነው፤ የሰው ልጅ ነጻነትን ከቀመሰ በኋላ የማሰብ ችሎታው እያደገና እየሰፋ ይሄዳል፤ በዚያው መጠን የሰውነቱን ልክ ይረዳል፤ የወያኔ መሪዎች ይህንን እውነት ቢረዱና አገሪቱንና ሕዝቡን ከመከራ ቢያድኑ ለራሳቸውም ይጠቅማቸው ነበር፡፡

No comments:

Post a Comment