Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Tuesday, 26 June 2012

የሕወሃት መንግስት በእርዳታ ያገኘውን ምግብ ኤክስፖርት ማድረግ ሊጀምር ነው

ሰኔ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የሕወሃት አስተዳደር ከበጎ አድራጊ ድርጅቶችና መንግስታት በረሃብ ለተጎዳው ወገናችን የሚላከውን የእርዳታ እሕል፤ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት በተሰኘው ተቋም በኩል በአለም ዓቀፍ ገበያ አውጥቶ ለመሸጥ እንዳቀደ ሬውተር የተሰኘው የዜና ወኪል ዘገበ።
በቅርቡ ሃላፊነቴን ለሌላ ሰው አስረክባለሁ ያሉት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድሕን፤ በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ላነጋገራቸው ለሬውተር የዜና ወኪል እንደገለፁት፤ መንግስት በእርዳታ ያገኘውን እህል፣ በተለይም በቆሎና ስንዴ በድርጅቱ አማካኝነት ለሽያጭ በማቅረብ ከዚሁ በሚገኘው ገንዘብ የውሃ ጉድጓዶችን ለመቆፈሪያና፣ ለኤሌክትሪክ ሃይል ማስፋፊያ ሊያውለው እንዳቀደ ጠቁመዋል። ሆኖም  ዶ/ር እሌኒ ይህ እቅድ እንዴት እንደሚተገበር በዝርዝር ማስረዳት እንዳልቻሉ ሬውተርስ በዚሁ የዜና ዘገባው ሳይጠቅስ አላለፈም።
ምንም እንኳን መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ 1995 ከአስር ዓመት በኋላ ስለምትኖረው ኢትዮጵያ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ የሚችልበትን አቅም እንገነባለን ሲሉ በተስፋ አስክረውን የነበር ቢሆንም፣ ያልውን ነባራዊ እውነታ ዛሬ ከ16 ዓመታት በኋላ ስናስተውል፤ አብዛኛው የኢትዪጵያ ሕዝብ የሚቀምሰው እንኳን በማጣት እየገፋው ያለው አስከፊ ሕይወት  የህዝብ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል
ሂዮመን ራይትስ ወች የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት፤ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው፣ 20 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከውጭ አገር የሚመጣ እርዳታ ጠብቆ የሚኖር ሲሆን፣ ከ7 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በመጠባበቂያ ምግብእርዳታ፣  ከ7-10 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ በአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ሕይወቱን እንደሚታደግ አስታውቆ ነበር።
በያዝነው ዓመትም 12 ሚልዪን የሚጠጋ ኢትዮጵያዊ  ከወዲሁ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ካላገኘ በአገራችን አስከፊ እልቂት ሊከሰት እንደሚችል፣ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ለዓለም ማሕበረሰብ ለማስገንዘብ እየጮሁ ባለበት ወቅት፣ የወያኔ መንግስት፤ በጎ አድራጊዎች የሚመፀውቱትን የምግብ እርዳታ ሳይቀር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የያዘው ዕቅድ ብዙዎችን ያስገረመ ብቻ ሳይሆን ያስደነገጠ ሆኖ ተገኝቷል።
የቀድሞው የህወሃት የፋይናንስ ክፍል ሃላፊ አቶ ገ/መድህን አርአያን ጨምሮ ሌሎች ውስጥ አዋቂዎች ካሁን ቀደም እንዳጋለጡት፤ የሕወሃት ሹሞች ለስልጣን ከመብቃታቸው በፊት ጀምሮ በረሃብ እየረገፈ ለነበረው የትግራይ ሕዝብ ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች የተመፀወተውን የምግብ እርዳታ፣ በድብቅ ዞር አድርገው በመቸብቸብ  ይከሰሳሉ። አሁንም በዚሁ መልኩ ለችግረኛ ወገናችን የመጣውን እርዳታ በይፋ ለመሸጥ ማቀዳቸውን ተከትሎ፤ ለጋሽ ድርጅቶችና መንግስታት ያደርጉ የነበረውን የምግብ እርዳታ ሊቀንሱ አንዳንዶቹም ጨርሶ ሊተውት ይችላሉ የሚለውን ስጋት ብዙዎች ይጋሩታል።
በቀድሞው  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰ የቦርድ ሊቀመንበርነት የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት፣ ቤተመንግስቱ ድረስ የሚዘረጋ ረጅም እጅ ያለው በሙስና የተጨማለቀ ተቋም እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገርለታል።
ከወራት በፊት የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ሊሰጠው አቅዶት ከነበረው 5 ሚልዮን የሚጠጋ ገንዘብ ውስጥ፤ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ 4 ሚሊዮን 8 መቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላሩን የድርጅቱን አቅም ለመገንባት በሚል ሰበብ ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን ለሚመሩት ተቋም እንዲሰጥ ጠይቆ ነበር። ሆኖም ዶ/ር እሌኒ “ሚልንየም አይቲ” ከተሰኘው የስሪላንካ ድርጅት ጋር በመመሳጠር አሸንፌአለሁ ሲሉ ያቀረቡት የጨረታ ኮንትራት፤ የሃሰት ድራማ መሆኑን የአለም ባንክ አስቀድሞ ስለደረሰበት፣ እርዳታውን ሙሉ ለሙሉ መሰረዙን  ኢሳት በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል።
በያዝነው የፈረንጆቹ አመት መጀመሪያ ላይም “የአገራችን ቡና ላኪዎች ወደ ውጭ አገር የምንልከው ቡና አጥተናል፤ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ግብይት የተፈጸመበት ቡናም ከመሃል አገር ወደ ኬንያ፣ ሱዳን፣ እንዲሁም ኤርትራ በሕገወጥ መንገድ እየተጫነ ነው።” በማለት አቤቱታቸውን አሰምተው ነበር። በዚህ ድርጅት በኩል ለውጪ ገቢያ ሊቀርብ የተዘጋጀ ከአስር ሺህ ቶን በላይ የተጣራ ቡናም በድንገት ከመጋዘን ጠፋ መባሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ሲሆን ይህን ተከትሎም አቶ መለስ ዜናዊ “የአሁኑን እንተወው ከኣሁን በኋላ ግን በእንደዚህ ኣይነት ተግባር ላይ የሚሳተፍ  እጁ ይቆረጣል” በማለት ጥፋተኞቹ እንዳይጠየቁ ጉዳዩን አለባብሰውት ማለፋቸው የሚዘነጋ አይደለም በማለት ቅዱስ ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment