Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday 24 June 2012

ፍትህን እና አልሸባብን ምን አገናኛቸው?

በተመስገን ደሳለኝ
እንደመንደርደሪያ
አዲስ ዘመን እና በተመሳሳይ መስመር የተሰለፉ ሚዲያዎች (አይጋ ፎረም፣ ዋልታ እና ዛሚ) በፍትህ ጋዜጣ ላይ ‹‹አርማጌዲዮን›› መጀመራቸው ይታወቃል። ሆኖም ለረጅም ጊዜ ምላሽ የመስጠት ፍላጐት ስላልነበረኝ ‹‹ውሾቹ ይጮኻሉ፤ ግመሉ…›› በሚል ብሂል ነበር ለማለፍ የመረጥኩት። አሁን ግን ይህ ውንጀላ አንድ ደረጃ ከፍ እያለ በመሄዱ እና አደገኛ አዝማሚያ እየያዘ በመምጣቱ፤ በአናቱም የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ በመሆኔ በአንዳንድ ባልደረቦቼ ላይ ከዚሁ ጫና የመነጨ የስነ ልቦና ተፅዕኖ እያደረሰ በመሆኑ ቢያንስ ህዝብ ይወቀው በሚል መንፈስ ነው ይህንን ፅሁፍ ለመፃፍ የተገደድኩት።
በቅድሚያ ግን አሁንም ከዚህ ቀደም ደጋግሜ እንደገለፅኩት እኔም ሆንኩ ባልደረቦቼ የምናገለግለው አንዱን ለማስደሰት ወይም ሌላውን ለማስከፋት የሚል አላማ ኖሮን አለመሆኑን አፅንኦት መስጠት እፈልጋለሁ። የእኛ አላማ አንድ እና አንድ ነው። ሀገርን ማገልገል እና ለምንወዳት ሀገራችን የዜግነት ግዴታችንን መወጣት። ስለዚህም ፍትህ ምንጊዜም የህዝብ አንደበት እና ጆሮ ሆና ትቀጥል ዘንድ አቅማችን የፈቀደውን ያህል እንሰራለን። ይህንን ግዴታችንን ስንወጣ ህገ-መንግስታዊ መብታችንን አክብረን እስከሆነ ድረስ ደግሞ ለየትኛውም ጫናም ሆነ የፈጠራ ክስ፣ አሊያም ማስፈራሪያ ወይም ማባበያ እጅ የምንሰጥበት ሁኔታ እንደማይኖር ደጋግመን በዚሁ ጋዜጣ፣ በዚሁ ገፅ ላይ ተናግረናል። ይህ አንድ እውነት ነው፡፡ ሌላው እውነት ደግሞ ይኽ ነው፡፡ ሰሞኑን የመጭውን ጊዜ የአደጋ ‹‹ቀለም›› የሚያመላክቱ ምልክቶች በፍትህና አዘጋጆቿ ዙሪያ እያንዣበቡ ነው። ስለነዚህ ምልክቶች ከመነጋገራችን በፊት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ፍትህን በሚመለከት ስለወጡ ፅሁፎች ጥቂት እናንብብ፡፡
የመንግስት አንደበት ምን አለ?
ከተመሰረተበት ዘመን (1933ዓ.ም.) ጀምሮ የመንግስት አይንና ጆሮ ሆኖ ዛሬ ላይ የደረሰው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚያንፀባርቃቸው አቋሞች እና ለንባብ የሚያበቃቸው መጣጥፎች ‹‹የመንግስትን አቋም›› ያመላክታሉ ወይስ አያመላክቱም? በሚል ክርክር ጉልበት ማባከኑ አስፈላጊ አይመስለኝም፤ ግልፅ ነውና። በዚህ ከተስማማን ደግሞ ከዚህ ቀደም በአዲስ ዘመን ላይ አዲስ ነገር እና አውራምባ ታይምስን በሚመለከት ይታተሙ የነበሩ ውንጀላዎች መንግስታዊ ባለቤት እንዳላቸው እንስማማለን ማለት ነው፤ ከ2002ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ፍትህን የሚመልከቱ የውንጀላ መጣጥፎች የጋዜጣው መለያ ሆነዋል። በተለይ በገፅ 3፤ አልፎ አልፎ ደግሞ በገፅ 11 ላይ ‹‹ፖለቲካ›› በሚል አምድ ስር ነው እነዚህ ውንጀላዎች የሚስተናገዱት። እዚህች ጋር አንድ አስቂኝ ነገር ልንገራችሁ። የአዲስ ዘመን ‹‹ገፅ ሶስት›› በትላልቅ ፊደል ‹‹አጀንዳ/ደብዳቤዎች›› የሚል የአምድ ስም ተሰጥቶት ሲያበቃ ‹‹ርዕሰ- አንቀጽና›› እንዲህ የሚል ማብራሪያ ተለጥፎበታል ‹‹ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጐች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው››፤ በዚህች ፉገራ ፈገግ ብለን በገፁ ላይ የሚስተናገዱ ፅሁፎችን ብናየው ሙሉ በሙሉ መጀመሪያ ላይ በኢንተርኔት በሚሰራጩ ድረ ገፆች (አይጋ ፎረም እና ዋልታ) ላይ ከታተሙ በኋላ ‹‹የህዝብ አስተያየት›› በሚል የዳቦ ስም ወደአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተላልፈው በድጋሚ እንደሚታተሙ እንረዳለን፡፡ መቼም እዚህች ጋርም ለተጨማሪ ጊዜ መሳቃችን አይቀርም ምክንያቱም በመንግስት የሚተዳደረው እና በቂ በጀት የተመደበለት ጋዜጣ ‹‹ፅሁፎችን የማትመው ከኢንተርኔት እየለቃቀምኩ ነው›› እያለን ነውና።
የሆነ ሆኖ አዲስ ዘመን እና ግብረአበሮቹ ለረጅም ጊዜ ፍትህን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ያለእረፍት እየሰሩ መሆኑን የጨረፍታ ግንዛቤ ለመስጠት ያህል የሩቆቹን ትተን የቅርቡን ማለትም በሚያዚያ እና ግንቦት ወር ብቻ የታተሙትን የውንጀላ ጽሑፎች የጥቂቶቹን ርዕሶች ብቻ ላመላክታችሁ፡-
‹‹ተነስ ያሉት እምቢ ቢል በ‹ጊዜ ለኩሉ…›› (የዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ የጋዜጣው ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ገፅ ም/ዋና አዘጋጅ የሆነው ሰይፉ ደርቤ ነው፣ ‹‹የገደል ጫፍ ላይ ሩጫ››፣ ‹‹በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል!› ሌላው የመድረክ የፕሮፓጋንዳ ‹ጭብጥ› ይሆን እንዴ?››፣ ‹‹ፍትህና አምደኞቿን በጨረፍታ›› (ስድስት ክፍል ያለው በስድስት እትም የተስተናገደ)፣ ‹‹የጨለማው ዘማሪዎች መናኸሪያና ደቀ-መዝሙሮቹ›› (በአራት ክፍል ለአራት ጊዜ የታተመ)፣ ‹‹የዋህ ነፍሰ ገዳይ››፣ ‹‹ለአመጽ እና ብጥብጥ የሚመች ፕሬስ ነፃ አይደለም››፣ ‹‹አንቀጽ 29፣ የፕሬስ ቀንና ማተሚያ ድርጅት››፣ ‹‹በደም የተፃፈው ህገ-መንግስት ያደፈው በማን ነው?››፣ ግራ የተጋባው የፖሊሲ ሰነድ ‹ትንተና›…›› በሚሉ ርዕሶች በሁለት ወር ውስጥ ብቻ በፍትህና ባልደረቦቿ ላይ ያነጣጠሩ አስራ ስምንት (18) ፅሁፎች ታትመዋል።
የፅሑፎቹን ይዘት ስንመለከት ደግሞ ሁሉም ፍትህ በአሸባሪ ድርጅቶች እና በኤርትራ መንግስት በገንዘብ ይደገፋል በሚል መደምደሚያ የሚያልቁ ናቸው። ለዚህ ደግሞ እንደምክንያት የሚያቀርቡት ጋዜጣዋ ያለ በቂ ማስታወቂያ እስከአሁን በህትመት መቆየቷን ነው። ለምሳሌ ‹‹የጨለማው ዘማሪዎች መናኸሪያና ደቀ-መዝሙሮቹ›› በሚል ርዕስ በወጣው ክፍል ሁለት ፅሁፍ ላይ ‹‹ፍትህ ጋዜጣ ባለ16 ገጽ እንደመሆኑ መጠን፣ 6 ገፅ ተኩል የሚጠጋውን ማስታወቂያና 9 ተኩል የሚጠጋውን ገፅ ደግሞ ፅሑፎችን መያዝ ይገባው ነበር። ሆኖም ጋዜጣው ግን 16ቱንም ገፆች ሊባል በሚችል የጭፍን ጥላቻ አሉባልታ መጋለቢያ ጽሑፍ አድርጎ ያለምንም ማስታወቂያ ወጪዎቹን በሙሉ እየሸፈነ ህልውናው ሳይናጋ ገበያው ላይ ከዘለቀ አራት ዓመቱን ሊያስቆጥር ነው።…. የገቢያቸው ምንጭ ከወዴት ነው? የሚለው ጥያቄ በማናቸውም መስፈርቶች ምላሽ የሚያሻው ጉዳይ ነው።›› ይልና ቀጥሎ እንዲህ ሲል ይጠነቁላል ወይም ይወነጅላል ‹‹የገቢ ምንጩም ከእነዚሁ ፀረ-ሰላም ኃይሎች እንደሚሆን ለመገመት አይከብድም። ጋዜጣውም ቢሆን በእነዚህ ኃይሎች የማይደጎም መሆኑን በአሳማኝ አመክንዮ ማረጋገጥ የሚችል አይመስለኝም። በእንካ ሰላምቲያ ዙሪያ ጥምጥም እየሄደ ዓይኔን ግንባር ያድርገው ለማለት ካልፈለገ በስተቀር።››
አሁንም ቆይታችንን ከአዲስ ዘመን ጋር እንዳደረግን እንቀጥልና ‹‹ፍትህና አምደኞቹን በጨረፍታ-ክፍል ሶስት›› በሚል ርዕስ ከታተመው ፅሁፍ ላይ ሌላ ጥንቆላ እንቀንጭብ ‹‹የፍትህና አምደኞቹን ጀርባ ለማየት ባደረኩት ጥረት የደረስኩበት ነጥብ የባዕድ እጅ ድጋፋቸው የጠላት ገንዘብ ኪሳቸውን መሙላቱን ነው›› ይላል። መቼም አዲስ ዘመን ‹‹ጋዜጣ›› እንጂ ‹‹የስለላ›› /የደህንነት/ መስሪያ ቤት እንዳልሆነ እናውቃለን። ነገር ግን ያለአንዳች ይሉኝታ ‹‹የፍትህና አምደኞቹን ጀርባ ለማየት ባደረኩት ጥረት…›› ይልና ሲሰልለን እንደቆየ ይነግረናል፡፡ አሁን ነው ‹‹እሪ በይ!›› ሀገሬ ማለት፡፡ እንግዲህ አዲስ ዘመን ስለራሱ፣ በራሱ ጋዜጣ ከሰጠን ምስክርነት ስንነሳ ከጋዜጣው ጀርባ እነማን ተሰልፈው የሀሰት ውንጀላ እየለጠፉ እንደሆነ ለመናገር ነቢይ መሆን አይጠይቅም።
‹‹የዋህ ነፍሰ ገዳይ›› የሚል ርዕስ ያለው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፅሁፍም እንደሌሎቹ ፅሁፎች በጥንቆላ የተገኙ ውንጀላዎችን ዘርዝሮ ሲያበቃ እንዲህ ይልና ይደመድማል፡- ‹‹የተመስገን ‹ተቀጣጣይ› አጀንዳዎቹ ደግሞ የተመስገን ብቻ ሳይሆኑ የግንቦት 7፣ የኦነግና የኦብነግ እንዲሁም የዜሮ ድምር ፖለቲካው ስብስቦች ሁሉ ናቸው። ለዚህ ነው የፍትህና የአምደኞቿ ጭንቀት የሽብር ተግባራቸውን የሚመሩበትን አካሄድ ውሉ እንዳያግድባቸው የፈጠረባቸው ስጋት ነው የምለው።››
እንግዲህ እነዚህን ሁሉ መንግስታዊ ሽብሮችን ነው መንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በምክትል ዋና አዘጋጁ ሰይፈ ደርቤ እና በተለያዩ ሰዎች ስም እያተመ በመወንጀል ላይ ያለው። በነገራችን ላይ ጋዜጣው ከፀሀፊዎቹ ጀርባ ማን እንዳለ አልፎ አልፎም ቢሆን ሳት እያለው ይናገራል። ለምሳሌ በስድስት የአዲስ ዘመን እትሞች ላይ በተስተናገደው ‹‹ፍትህና አምደኞቹን በጨረፍታ›› ፅሁፍ ክፍል አምስት ላይ ድንገት ተነስቶ ‹‹እነሆ የጨረፍታዬን አምስተኛ ክፍል በግሌ ለመፃፍ ስነሳ የመንግስት ማስፈራሪያ ስላለመሆኑ አንባቢያን እንደሚረዱልኝ በማመን ነው›› ሲል የውስጡን ይነግረናል። እዚህ ጋር የሚተኮርበት ነጥብ የዚህ ፅሁፍ ባለቤት ወይም ባለቤቶች እስከ ክፍል አራት ድረስ ሲፅፉ ‹‹መንግስት አልላከኝም›› የሚል ማሳሰቢያ አያይዘው አልፃፉም፡፡ አምስተኛው ላይ ነው ‹‹የአቡዬን መገበሪያ የበላ…›› እንደሚባለው መለፍለፍ የጀመሩት። እናም ከዚህ ‹‹ማሳሰቢያ›› ስነሳ ጋዜጣው ይህን ያለው በራሱ ፍላጎት ነው ለማለት ይቸግረኛል። ምን አልባት የጋዜጣው ባለቤት (መንግስት) ‹‹እንዴት አንድ ጋዜጣን እንዲህ ታስፈራራለህ?›› የሚል ጫና ስለተፈጠረበት ሊሆንም ይችላል እንዲህ በደፈናው ማስተባበል የፈለገው፡፡ ይህ ማስተባበያ ከዚህ ቀደም የታዋቂው አክቲቪስት እና አርቲስት ታማኝ በየነ ወንድም ተወልደ /ተቦርነ/ በየነ በፍትህ ላይ በፃፈው ፅሁፍ ያጣቀሳትን አይነት የጦጢት ታሪክን ያስታውሰኛል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፤ አንዲት ጦጣ ከዛፍ ስር ቆማ ሳለ ድንገት አንበሳ ወደ እሷ ሲመጣ ታያለች፤ እናም አደጋ ስለሸተታት በፈጣን ሁኔታ ተደግፋው በነበረው ዛፍ ላይ ዘላ ትወጣለች። አያ አንበሶም ‹‹ጦጢት ውረጂ! አልበላሽም›› ይላታል-የሆዱን በሆዱ ይዞ፡፡ ይህን ጊዜም ጦጣዋ ‹‹አልበላሽምን ምን አመጣው›› አለችው ይላል የተረቱ ትርክት። እኔ ደግሞ እንዲህ እጠይቃለሁ አዲስ ዘመን ሆይ! ‹‹በፍትህ ላይ የሚፃፈው ሁሉ የመንግስት ማስፈራሪያ አይደለም›› ማለትን ምን አመጣው?
ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በተደራጀ መልኩ መንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በፍትህ ላይ አፍራሽ እና ወንጃይ ዘመቻ እንደከፈተ ለማብራራት እየሞከርኩ እንደሆነ ይሰማኛል። በዚህ የውንጀላ ዘመቻ ውስጥም በዋናነት እየተራገበ ያለው ‹‹ፍትህ ያለማስታወቂያ እስከዛሬ ድረስ በገበያ ላይ የቆየችው በአለም አቀፍ አሸባሪ ድርጅቶች፣ በኤርትራ መንግስት፣ በግንቦት 7፣ በኦብነግ፣ በኦነግ፣ በአክራሪ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ… ድጋፍ ነው›› የሚል እንደሆነም ተነጋግረናል። (መቼም ከላይ የተጠቀሱትን ሀገር እና ድርጅቶች በጨረፍታም ቢሆን የሚያውቅ ግለሰብ እነዚህ ኃይሎች ‹‹ፍትህን መደገፍ›› በሚል አጀንዳ ቀርቶ፣ በሀገሪቱ የቀን አቆጣጠር ስርአት እንኳ በጋራ እንደማይስማሙ ይረዳል። ለዚህም ነው አዲስ ዘመን እንዲህ በአንድ ላይ ሊያሰልፋቸው የቻለበትን ምክንያት ከጋዜጣው አለቆች ባሻገር ሰይጣንም ቢሆን አያውቀውም እያልኳችሁ ነው ያለሁት)
የሆነ ሆኖ በተለይም ያለፈው ሳምንት ፍትህ ለንባብ ከበቃች በኋላ ነገሮች እየተበላሹ እየሄዱ እንደሆነ የሚያመላክቱ ‹‹እከሌ›› ወይም ‹‹እከሊት›› የሚል መጠሪያ እና ባለቤት የሌለው መልእክት እየደረሰን ነው። በእርግጥ ለእኔ የደረሰኝን መልእክት ከቀድሞዎቹ የአዲስ ዘመን ውንጀላዎች የተለየ የሚያደርገው የላኪው ማንነት እና የተፃፈበት ቋንቋ የተለየ መሆኑ ብቻ ነው። ምክንያቱም በዚህ መልእክት ላይ ‹‹ላኪ›› ተብሎ የተቀመጠው እንደተለመደው ‹‹አዲስ ዘመን›› ሳይሆን ‹‹አልሸባብ›› የተባለው የሶማሊያ አሸባሪ ድርጅት ነውና፡፡ የመልእክቱ ይዘት ግን አዲስ ዘመን በሚያዚያ እና በግንቦት ወር ፍትህን ሲወነጅልበት ከነበረው በምንም አይለይም፤ ተመሳስሎአቸው ቃል በቃል ነው። ይህንን መመሳሰል ለማስረዳት ሁሉንም እዚህ ቦታ ላይ መፃፉ አንድም የቦታ ጥበት ስላለ፣ ሁለትም አስፈላጊ ባለመሆኑ አንዱን ብቻ መርጬ በሁለት ምክንያት አቀርባለሁ፡፡ የመጀመሪያው ለአንባብያን ግንዛቤ እንዲረዳ የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው የሚመለከተው አካል እኛ ጋዜጠኞችን ከዚህ መሰሉ ማስፈራሪያ ይጠብቀንና ይከላከለን ዘንድ ግዴታው እንደሆነ ለማሳወቅ ነው፡፡ (ምንም እንኳን አስቀድሞም ቢሆን የሚያውቀው ቢሆንም እንዲህ በህዝብ ፊት ማሳወቁ ቢያንስ ለታሪክ መጥቀሙ ስለማይቀር ነው) መልእክቱ የመጣው ጋዜጣው ላይ በግልፅ በተፃፈ የጋዜጣው የ‹‹ኢ-ሜል›› (E-mail) አድራሻ ሲሆን ሙሉ ቃሉን እንደወረደ ስናነበው እንዲህ ይላል፡-
“To Ato Temesgen Desalegne
Chief Editor of Fitih magazine
Ethiopia
It has to be remembered that AlShebab has assigned me secretly to make propagation activities in Ethiopia, Somaliland, Kenya and Uganda. To accomplish the task we have agreed with you through your representative Ato Mamush Sentie in Eritrea to publish propaganda articles against the Ethiopian government, against the interest of the Ethiopian people and the American government. It has to be remembered that we have paid US dollar 24,000 for 30 consecutive editions. Now alshebab has made strategic change to accomplish its tasks. Therefore we need the 14 edition charges US dollar 11,200 dollar to alshebab. We believe that you will return back the money to our organization. If this is not fulfilled on time you will bear a cost on your representative Ato Mamush Sentie and your life according to the rule of the organization.
Alshebab wins
Ahmedin Nasir”
(ለአቶ ተመስገን ደሳለኝ
የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ
ኢትዮጵያ
እንደሚታወሰው አልሸባብ በኢትዮጵያ፣ በሱማሌላንድ፣ በኬንያ እና በኡጋንዳ የፕሮፓጋንዳ ስራ እንድሰራ በሚስጥር መድቦኛል። ይህንኑ ግዴታዬን ለመወጣት በአንተ ጋዜጣ ላይ የኢትዮጵያ መንግስትን፣ የኢትዮጵያ ህዝብን እና የአሜሪካንን መንግስት ጥቅም የሚጎዳ የቅስቀሳ ፅሁፎች ይታተሙ ዘንድ አቶ ማሙሽ ሴንጢ በተባለው ተወካይህ አማካኝነት ኤርትራ ውስጥ ተስማምተን ነበር። እንደምታውቀውም ለ30 ተከታታይ እትምች 24,000 የአሜሪካን ዶላር ከፍለንሃል። አሁን ግን አልሸባብ ዕቅዶቹን ለመፈፀም የስልት ለውጥ አድርጓል። ስለዚህም 11,200 የአሜሪካን ዶላር የሚሆነውን የ14 እትሞች ክፍያ ለአልሸባብ እንዲመለስ እንፈልጋለን። ይህንን ገንዘብ ለድርጅታችን ትመልሳለህ ብለንም እናምናለን። ነገረ ግን ምናልባት ይህ ሁኔታ በሰዓቱ ባይሳካ በድርጅቱ ህግ መሰረት በአቶ ማሙሽ ሴንጢና በአንተ ህይወት ዋጋ ትከፍላለህ።
አልሸባብ ያሸንፋል።
አህመድ ናስር)
እንግዲህ ይህ መልዕክት የተላከው ከአልሸባብ-ለእኔ መሆኑ ነው። በእርግጥ የዚህ መልዕክት ዋናው ቅጅ ሚያዚያ 2/2004 ዓ.ም በወጣው‹‹ፍትህና አምደኞቹን በጨረፍታ-ክፍል ሶስት›› በሚል ርዕስ የታተመው ጋዜጣ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን ይህ ደግሞ የእንግሊዝኛው ግልባጭ መሆኑ ነው፡፡ ለማስታወስ ያህልም በጠቀስኩት ቀን ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ልቀንጭብላችሁ፡- ‹‹ከምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ለተቀመጠችው ሀገራችን አልሸባብን ጨምሮ ሌሎችን ከውስጥም ከውጭም የፀረ-ሰላም ኃይሎች ያሰባሰበው የኢሳያስ አፈወርቄ መንግስት ናቅፋ እስከፍትህ ቢሮና አምደኞች ኪስ አይደርስም ማለት አይቻልም፤ ይህ ባይሆን እመኛለሁ፤ እኔ ግን በበኩሌ ጠረጠርኩ፤ በርካታ ማሳያዎች አሉኛ›› የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። አልሸባብ እንኳን ከፍትህ ጋር የስራ ስምምነት ሊያደርግ ቀርቶ ፍትህ የሚባል የአማርኛ ጋዜጣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስከመኖሩ ያውቃል? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ መልዕክቱን ስናነብው በእርግጥም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ደጋግሞ ፍትህን ሲወነጀል የነበረበት መልዕክት መሆኑ አያከራክርም። ልዩነቱ የአዲስ ዘመን በአማርኛ ቋንቋ፣ አልሸባብ ላከው የተባለው ደግሞ በእንግሊዝኛ መሆኑ ብቻ ነው። በነገራችን ላይ ይህንን የሀሰት መልእክት ፈጥሮ እኔን ለመወንጀል ያሰበው ሰው ለውንጀላው ከመጣደፉ የተነሳ፣ የላከው መልዕክት እና ከፍትህ ጋር ያቆራኘው አልሸባብ ጭራሹኑ እንደማይተዋወቁ በግልፅ የሚያሳይ ስህተት ሰርቷል። ይኸውም ላኪው የአራት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ወኪል ነኝ ብሎን ሲያበቃ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በላከው መልዕክት ላይ ግን የኢትየጵያ የስራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛ ደባልቆበታል፡፡ ‹‹አቶ…›› እያለ ፅፎ ማለቴ ነው፡፡
መቼም አልሸባብ የተቋቋመውም ሆነ እየታገለ ያለው እንደ አልቃይዳ ‹‹ድንበር የለሽ›› ወይም ሳውዲአረቢያን አልያም ግብፅን በሼሪያ ህግ ላስተዳድር ብሎ አይደለም፡፡ የአልሸባብ አፈጣጠር ግልፅና አጭር ነው፡፡ ይህ አሸባሪ ድርጅት የተመሰረተው ‹‹ሶማሊያ ሀገራችን›› ባሉ የሶማሊያ ተወላጆች ሲሆን አላማቸውም ‹‹ሶማሊያን በሼሪያ ህግ ማስተዳደር›› የሚል እንደሆነ ደጋግመው ገልፀዋል፡፡ እንግዲህ በዚህ ከተስማማን ‹‹በዕቅዴ ላይ ጣልቃ ገቡ›› በሚል ኩርፊያ በኢትዮጵያ፣ በኬኒያ፣ በኡጋንዳ እና ከራሷ ሶማሊያ በተገነጠለችው ሶማሌላንድ ላይ የሽብር ድርጊት ለማካሄድ አፉን በአማርኛ የፈታ ጎንደሬ ወይም ጎጃሜ የፕሮፓጋንዳ ሀላፊ የሚሾምበት ምንም አይነት ምክንያት የለውም፡፡ ስለዚህም የአልሸባብ ወኪል ነኝ የሚለው ሰው ‹‹አቶ…›› የሚለውን የአማርኛ የአክብሮት አጠራር ሳይሆን ‹‹ሚስተር…›› የሚለውን የእንግሊዝኛ አቻ ትርጉምን ነው ይጠቀም የነበረው ማለት ነው፡፡ ይህን አይነት ቅድመ-ጥንቃቄ ቢያደርግ ደግሞ ቢያንስ የእኔ አስፈራሪና ወንጃይ ‹‹ድርሰት›› የተዋጣለት ይሆን ነበር። አሊያም ‹‹አቶ…›› የሚለውን የአማርኛ ቃል የግድ መጠቀም አለበኝ ካለ እንደተለመደው ከአንዱ ኢትዮጵያዊ አሸባሪ ድርጅት ጋር አቆራኝቶ ቢወነጅለኝ የተሻለ ይሆንለት ነበር።
ሌላው የዚህ መልእክት ባለቤት የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ እንደሆነ የሚያሳየው ፍትህን በእንግሊዘኛ ሲፅፍ፣ እንግሊዝኛ ሆሄያት ተጠቅሞ አማርኛ በሚፃፍበት መልክ “Fitih” ብሎ መሆኑን ልብ ስንል ነው። መቼም ‹‹ፍትህ›› የሚለው ቃል የአማርኛ እንጂ የእንግሊዘኛ ቃል አይደለም። ስለዚም ፀሐፊው አልሸባብ ቢሆን ይህንን አፃፃፍ ከየትም ሊያገኘው ስለማይችል ‹‹ፍትህ›› ብሎ ለመፃፍ ሁለት አማራጭ ብቻ ነው የሚኖረው። የመጀመሪያው አማራጭ ከፍትህ ኢ-ሜል አካውንት ላይ ‹‹ፍትህ›› የሚለውን በሚያውቀው እንግሊዘኛ የተፃፈውን መውሰድ ነው። ይህን ቢያደርግ ኖሮ የፍትህ አካውንት ‹‹fetih_gazeta@yahoo.com” የሚል ስለሆነ የማስፈራሪያው ባለቤት ‹‹fitih›› ብሎ ሳይሆን የሚፅፈው ‹‹fetih›› ብሎ ይሆን ነበር፡፡ ሁለተኛው ምርጫው ደግሞ ከፍትህ ዌብሳይት ላይ መውሰድ ነው። ዌብሳይቱ ላይ ያለው “www.fetehe.com” ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያዊ ያልሆነው አልሸባብ ፍትህ የሚለውን የአማርኛ ቃል የዌብሳይቱ መጠሪያ የሆነውን ‹‹fetehe›› ብሎ ይጠቀም ነበር ማለት ነው፡፡ ታዲያ አማርኛ የማያውቀው አልሸባብ “Fitih” የምትለውን በእንግሊዝኛ ፊደል የተፃፈች የአማርኛ ቃል ከየት አመጣት? (እንዴት ነው ነገሩ? አልያም አንድዬውን እኛ እዚሁ አራት ኪሎ ተጎልተን ሳንሰማ አልሸባብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ድርጅት ተመስርቷል በሉንና በሳቅ እንፈንዳ? ሌላ ማድረግ ባንችል በሳቅ ራሳችንን ማፈንዳት ማን ይከለክለናል?)
የአልሸባቡ ሰው ፃፈው ከተባለው ተጨማሪ አንድ ስህተት እንምዘዝ፡፡ ደህና! እንደሚታወቀው የእኔ የሀላፊነት ደረጃ ‹‹ዋና አዘጋጅ›› የሚል ነው፡፡ ይህ ሀላፊነት በእንግሊዝኛ ሲሆን ደግሞ ‹‹Editor in chief›› የሚል ይሆናል፡፡ ሆኖም ‹‹ዋና አዘጋጅ›› የሚለውን ቃል ከአማርኛ ወደ እንግሊዘኛ ቃል በቃል ስንቀይረው ‹‹Chief Editor›› የሚል ይሆናል፡፡ ይህ ትርጓሜ ደግሞ አማርኛ ቋንቋን ለማይናገር ሰው ስህተት ሆኖ ሳለ፣ የአልሸባብ ወኪል የተባለው የፃፈው ግን ከአማርኛ በቀጥታ ተርጉሞ ‹‹Chief Editor›› ብሎ ነው፡፡ እዚሁ ጋር ያለው ሌላ ስህተት ፅሁፉን ለመወንጀል የቸኮለ ፀሀፊ እንደፃፈው ያሳየናል፡፡ ምክንያቱም ፍትህ ጋዜጣ ስትሆን፤ ጋዜጣ ደግሞ በእንግሊዘኛ ‹‹News paper›› እንጂ ‹‹Magazine›› አይደለም፡፡ ሜጋዚን ለሚለው ቃል አቻ የአማርኛ ትርጉም ‹‹መፅሄት›› ነው፡፡ አልሸባብ የተባለው ሰው ‹‹Magazine›› እያለ መፃፉን ልብ በሉ፡፡ እዚሁ መልዕክት ላይ አንድ ግጥምጥሞሽ ልጥቀስላችሁ፡፡ ከዚህ ቀደም የፍትህ ሚኒስቴር በበርካታ ክስ በከሰሰኝ ጊዜ ያቀረበው ማስረጃ በተከታታይ የታተሙ 14 የፍትህ እትሞችን ሲሆን፣ አልሸባብም ፍትህ ላይ ቀረኝ አለ የተባለው ሂሳብ የ14 ዕትም ነው፡፡ …ይህ መመሳሰልስ የአጋጣሚ ይሆን? ወይስ…
የሆነ ሆኖ ከዚህ የሀሰት መወንጀያ ለማሳያ ያህል እነዚህን የመዘዝኩት በሀገራችን ዜጎች ምን ያህል በሀሰተኛ ማስረጃ እና ምስክር ለእስር እየተዳረጉ እንደሆነ እንድትረዱት ነው። ከዚህ ውጭ ከአራት ሳምንት በፊት ያቀረብኩላችሁ የሲሳይ አጌና ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› መጽሐፍ ለፍርድ ቤት ይቀርቡ የነበሩ ማስረጃዎች በፎርጅድ እና በሀሰተኛ ምስክርነት የተሞሉ በመሆኑ ራሱ አቃቤ ህግ ለተደጋጋሚ ጊዜ በፍርድ ቤት ሲያፍር እንደነበረ ማስነበቡን አስታውሰን እንለፍ።
በተቀረ በመልዕክቱ ውስጥ አልሸባብ በፍትህ አስራ ስድስት ተከታታይ እትሞች ላይ የሽብር ፅሁፎቹ እንደታተሙለት ገልጿል፡፡ መቼም የትኛውም የፍትህ አንባቢ እንደሚያስታውሰው በፍትህ ላይ አንድም ቀን ቢሆን የኢትዮጵያን ህዝብና የአሜሪካንን መንግስት ጥቅም የሚፃረር ወይም አልሸባብን የሚደግፍ ፅሁፍ ታትሞ አያውቅም፡፡ ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያን መንግስት ደካማ ፖሊሲ፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የፕሬስ አፈና፣ የባለስልጣናቶችን ዘረፋና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምክንያታዊ ትችቶች አላቀረብንም ማለት አይደለም፡፡ ህዝብ ማወቅ አለበት ያልነውንም ህገወጥ ድርጊት አጋልጠናል፡፡ ይህ ደግሞ አንድም የሞያ ግዴታችን ሲሆን ሁለትም እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ ሀላፊነታችንን መወጣታችን ነው፡፡ ስለዚህም እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ፍትህን ከአልሸባብ ጋር አያይዞ መወንጀሉ ክፉ ጥርጣሬን ያጭራል፡፡ ከጥርጣሬዎቹ ውስጥ ምናልባት የተለመደው የክስ ቻርጅ በዚህ በኩል እንዲያልፍ ለማድረግ ይሆን? የሚለው አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ በመልዕክቱ ላይ የተገለፀውን ዛቻ ተከልሎ በፍትህ አዘጋጆች ላይ የ‹‹ቀይ ሽብር›› እርምጃ ለመውሰድ ያሰበ አካል ‹‹በልጅ አመካኝቶ…›› አካሄድን ለመከተል አስቦ ይሆን? የሚለው ደግሞ ሌላኛው ክፉ ጥርጣሬ ሊሆን ይችላል፡፡ …ጊዜ የሚፈታው ቋጠሮ ነው፡፡
ርዕሰ ጉዳዩን ስናጠቃልለውም እነዚህ በመንግስታዊው ጋዜጣ እና በአፍቃሬ ኢህአዴግ ድረ-ገፅ ከወጡት ቁጥራቸው የበዛ ፅሁፎች መሀከል በጥቂቱ ለማሳያነት ያህል የጠቀስኳቸው ውንጀላዎች በአምባገነዊ ስርዓት ውስጥ ያለውን የነፃ ጋዜጠኝነት ፈተና በበቂ የሚያሳይ ይመስለኛል። ስርዓቱ እዚህ ድረስ ወርዶ ለመወንጀል እየሞከረ ያለው ሀገራችንን ጥለን እንድንሄድ አልያም ራሳችንን በዝምታ እንድንሸብብ ከሆነ፤ የሚሰማ ካለ አቋማችንን በተደጋጋሚ ማሳወቃችንን ብቻ አስታውሶ ከማለፍ ውጭ አማራጭ የለውም፡፡ እንዲሁም የሃገሪቱ ህገ-መንግስት ላይ የሰፈሩ የዜግነት ነፃነት አክባሪ ዕሴቶችን አምነን ስለሀገራችን በዋተትን፣ ለተጎዱና ለተገፉት ወገኖቻችን ባበርን፣ የህዝባችን ያለስጋት በነፃነት የመኖር መሻት ይተገበር ዘንድ በብዕሮቻችን በቃተትን፤ በማንኛውም መልክ ሊመጣ የሚችል አደጋ ካለ ከመቀበል ውጪ ሌላ ምርጫ የለንም። ምክንያቱም ሀገራችን ኢትዮጵያ ብቻ ናትና።

No comments:

Post a Comment