Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday 11 July 2012

አቶ ጁነዲን ሳዶ ስለ ኮብል ስቶን ያደረጉት ንግግር ተቃውሞ ገጠመው

Wednesday, 11 July 2012 09:45 
የቀድሞው ድምቀቱና ውበቱ በተለየው የዘንድሮ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ በንግግራቸው ስለ ኮብል ስቶን በማንሳታቸው ከፍተኛ የተቃውሞ ጩኸት ገጠማቸው፡፡ አቶ ጁነዲን ባለፈው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግራቸውን ሲጀምሩ በአድናቆት ጭብጨባና በፉጨት ቢታጀቡም፣ ድንገት የንግግራቸውን አቅጣጫ ወደ ኮብል ስቶን በማዞራቸው ነበር ሳይታሰብ ከፍተኛ የተቃውሞ ጩኸት፣ ጉርምርምታና ፉጨት ከተመራቂዎቹ የተሰማው፡፡ ይኼው የተማሪዎች ተቃውሞ አይሎ ቢቀጥልም ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ከመቀጠል አልተገቱም፡፡

ሚኒስትሩ ‹‹ኮብል ስቶን›› የሚለውን ቃል ገና መናገር ሲጀምሩ ተመራቂዎቹ ከአፋቸው ተቀብለው በተቃውሞ እንዲጮኹ ምክንያት የሆናቸው፣ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀረበው የአንድ ባለዲግሪ ወጣት በኮብል ስቶን መሰማራቱን ስላስታወሳቸው እንደሆነ ነው ተመራቂዎቹ የተናገሩት፡፡

ተማሪዎች ስለሚገጥሙዋቸው ችግሮችና በትምህርት ቤት ቆይታ ስለሚታየው ከባድ ሕይወት እያዋዙ በመናገራቸው የሙገሳ ፉጨት ሲቀርብላቸው የነበሩት ሚኒስትር ጁነዲን፣ ንግግራቸውን በተቃውሞ ጩኸት ለማስቆም ተመራቂዎች ያደረጉት ጥረት አልተሳካም፡፡ ተመራቂዎቹ በተቃውሞ እየጮኹ ሊያዳምጡዋቸው በማይችሉበት ሁኔታ እሳቸው ንግግራቸውን ጨርሰው ከመድረክ ወርደዋል፡፡

‹‹ያለቦታውና ያለጊዜው ያደረጉት ንግግር ነው፤›› በማለት በርካታ ተማሪዎች የሚኒስትሩን ንግግር የተቹ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ባለፈው ቅዳሜ ረፋዱ ላይ በማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተናገሩት መሆኑም የተመራቂዎቹን ቅሬታ በእጅጉ እንዳባባሰው ገልጸዋል፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ በኮብል ስቶን ትምህርት ላልሠለጠኑ ተመራቂዎች የኮብል ስቶን ጉዳይን ማንሳት አይገባም ነበር ያሉት ተመራቂዎቹ፣ እሳቸውም ቢሆኑ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴርን የሚመሩ ባለሥልጣን ሆነው፣ ዘርፉም ሆነ የግንባታ ጉዳይ ለማይመለከታቸው ተመራቂዎች ስለ ኮብል ስቶን ማንሳታቸው፣ ለተቃውሞው መነሻ ሰበብ መሆኑን ተመራቂዎቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ሳይጠናቀቅ በርካቶች የስድስት ኪሎ ካምፓስን የልደት አዳራሽ ጥለው ወጥተዋል፡፡ በወቅቱ ተመራቂዎቹ ያሰሙት የነበረውን ጩኸትና ፉጨት ያዳመጡ አንዳንድ መንገደኞች ያልተለመደ ስለሆነባቸው፣ ‹‹የዘንድሮ ተማሪዎች በፉጨት ሆነ እንዴ የሚመረቁት?›› በማለት እንዲቀልዱ አድርጓቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment