ሐምሌ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-99 ነጥብ ስድስት በመቶ በአንድ ድርጅት አባላት የተሞላው ፓርላማ ለአስቸኳይ ልዩ ጉባኤ የተጠራው አዲሱንና አወዛጋቢውን የቴሌ ህግ ለማጽደቅ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኗል።
ዘጋቢያችን እንዳለው በጥሪው ላይ አስቸኳይና ልዩ የተባለው ፓርላማው ካለፈው ሰኔ ሰላሳ ቀን ጀምሮ እንደተዘጋ በመቆጠሩ ነው። የፓርላማ አባላቱ ፓርላማው እንደተዘጋ የማያውቁ ሲሆን፣ የዛሬው ልዩ ስብሰባ የተጠራው የፓርላማ አባላቱ እረፍት ላይ በሚሆኑበት ጊዜ አፈ ጉባኤው አስኳይ ስብሰባ መጥራት እንደሚችሉ ህጉ ይፈቅድላቸዋል በሚል ምክንያት ነው።
እስከ ዛሬ ድረስ በነበረው የፓርላማ አሰራር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሚቀጥለው አመት በጀት ላይ ጥያቄ ቀርቦላቸው መልስ ከሰጡ በሁዋላ ፓርላማው ለእረፍት ይዘጋል። ይህ አሰራር ላለፉት 18 አመታት የነበረ ሲሆን በዚህ አመት ግን የበጀት ዝርዝሩ ሳይጸድቅ ፣ አቶ መለስም በበጀቱ ላይ አስተያየት ሳይሰጡ እንዲሁም አፈ ጉባኤው ፓርላማው መዘጋቱን ሳያሳውቁ ፓርላማው ተዘግቷል ተብሎአል።
ሰንደቅ ጋዜጣ ፓርላማው ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓም ለምን እንዳልተዘጋ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑትን ወ/ሮ አሰፉ ገ/አምላክን የጠየቀ ሲሆን ፣ ሃላፊዋም ፓርላማው ሰኔ 30 መዘጋቱን በማረጋጋጥ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 58 ንኡስ አንቀጽ 4 ላይ ምክር ቤቱ በእረፍት ላይ በሚሆንበት ወቅት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ስብሰባ ሊጠራ እንደሚችል ስለሚገልፅ በዚሁ መሠረት ቀጣይ ስብሰባዎች እንደሚካሄዱ ገልፀዋል። ቀኑ ለጊዜው ባይታወቅም የ2005ቱ በጀትም ከሰሞኑ ይፀድቃል ብለዋል።
ጋዜጣው ለዶ/ር መረራ ጉዲና እና ለብቸኛው የፓርላማ ተመራጭ አቶ ግርማ ሰይፉ ጥያቄ አቅርቦላቸው ሁለቱም ላቀረበላቸው ጥያቄ በሕገ-መንግስቱ መሠረት ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም መዘጋት ሲገባው መቀጠሉ አነጋጋሪ እና ከተለመደው የፓርላማው አሰራር ውጪ ነው ብለዋል። አቶ ግርማ ያልፀደቁ አዋጆች ስላሉ ፓርላማው እንደሚቀጥል እንደተነገራቸው ገልፀዋል።
ለፓርላማው መዘጋትና ለ2005ቱ በጀት በጊዜ አለመፅደቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት በምክንያትነት ስለመነሳቱ በተመለከተ ዶ/ር መረራ ጉዲና ፤ “የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤንነት በከተማው የመንገድ ወሬ ሆኗል፤ ባለፈው ጊዜ በቴሌቪዥን ባየሁዋቸው ጊዜ ፊታቸው የተለወጠ ይመስላል” ሲሉ ለጋዜጣው ገልጠዋል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ የስልጣን ክፍፍል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከገባ ቆይቷል” የሚሉት ዶ/ር መረራ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አለመመቻቸት የመንግስት ስራ መስተጓጎሉ በኢህአዴግ ውስጥ የቡድን አመራር አለመኖሩን ያሳያል ሲሉም አክለዋል።
በዛሬው ስብሰባ እንደ ስካይፒ፣ጎግልቶክ ያሉ የኢንተርኔት አገልግሎቶች ለንግድ እንዳይውሉ የሚደነግገው የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅ ጸድቋል፡፡
አዋጁን ዝርዝር ተመልክቶ ፣የሚመለከታቸውን ወገኖች አወያይቶ የውሳኔ ኀሳብ ይዘው እንዲቀርቡ ረቂቁ የተመራላቸው ሁለት ኮሚቴዎች ባቀረቡት የውሳኔ ኀሳብ አከራካሪ ለነበረው ጉዳይ መጠነኛ ምላሸ አሰገኝተዋል፡፡
ኢንተርኔትን በመጠቀም የድምጽና የፋክስ መልዕክትን ማስተላለፍ ማለትም ስካይፒና ጎግል ቶክን የመሳሰሉትን እና በድምጽ የኢንተርኔት መግባቢያዎች ይከለክል የነበረው በሥራ ላይ የነበረው አዋጅ ቁጥር 281/1994 እንደነበር፤ ይህ አዲሱ አዋጅ ግን ይህንን በመሻር የኦፕሬተር አገልግሎት በሕገወጥ መንገድ ከሚሰጡ በስተቀር ማንኛውም ዜጋ መጠቀም እንዲችሉ ፈቅዶአል ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረት የተከለከለው የቴሌኮም አገልግሎትን በመጠቀም ሌሎችን በማስደወል መንገድ መሆኑን፣ዜጎች ግን በቤታቸው፣በሥራ ቦታቸው አገልግሎቶቹን በግል እንዳይጠቀሙ እንደማይከለክል ግልጽ አድርገዋል፡፡
የመድረከ ተወካይ አቶ ግርም ሰይፉ አዋጁ የቴሌን ሞኖፖሊ በማጠናከር ዜጎች ምንም አማራጭ እንዳይኖራቸው ለማድረግ የታለመ መሆኑን በመጥቀስ የአዋጁን መጽደቅ ተቃውመዋል፡፡
No comments:
Post a Comment