(ኢ.ኤም.ኤፍ) በየትኛውም አገር አንድ መንግስት ሲቀየር አዲስ የሚመረጠው አካል፤ ወደ አስተዳደር ቢሮው
መግባት ይኖርበታል። በራሺያ የክሬምሊን ቤተ መንግስት ወይም በአሜሪካ ኋይት ሃውስ የመንግስት መቀመጫ ስፍራዎች
ናቸው። ለኢትዮጵያ ደግሞ የመንግስት ስራ ማከናወኛ የአራት ኪሎው ምኒልክ ቤተ መንግስት መሆኑ ይታወቃል። ታዲያ
በሌሎች አገራት የመንግስት ለውጥ ሲደረግ፤ ፕሬዘዳንቱም ሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ በጨዋ ደንብ ጨርቅ እና ማቃቸውን
ይዘው ይወጣሉ። በኢትዮጵያ ግን ይህ አልሆነም። የቀድሞው እመቤት ቤተ መንግስቱን የሙጥኝ እንዳሉት ነው።
አቶ ኃይለማርያም ምኒልክን ቤተ መንግስት ከሩቅ ከማየት ውጪ ከነቤተሰባቸው ወደ ቅጥር ግቢው አልተዛወሩም።
ሌላው ቀርቶ በትላንትናው እለት የሁለቱን ሱዳኖች ልዑካን ተቀብለው ያነጋገሩት፤ ፕሬዘዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ
በሚገኙበት ኢዮቤልዩ ቤተ መንግስት ውስጥ ነበር። ከዚህ በፊት በመለስ ዜናዊ ይደረጉ የነበሩ የእንግዳ አቀባበል
ስርአቶች ይፈጸሙ የነበረው በአራት ኪሎው ምኒልክ ቤተ መንግስት ሲሆን፤ አሁን ግን ሴትዮዋ አልወጣም በማለቷ
ምክንያት… አቶ ኃይለማርያም ፕሬዘዳንቱ የሚገኙበትን ቤተመንግስት በጋራ ለመጠቀም ተገደዋል።
በአሁኑ ወቅት ስልጣን ያለምንም ኮሽታ “ከኢህአዴግ ወደ ኢህአዴግ ተሸጋግሯል” ቢባልም፤ አዜብ መስፍንን ጨምሮ
በርካታ የህወሃት ባለስልጣናት ደስተኛ አይመስሉም። ሌላው ቀርቶ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር (በፈጣሪ ፋንታ) ለመለስ
ዜናዊ ዘላለማዊነትን በተመኙበት ፓርላማ፤ ወ/ሮ አዜብን ጨምሮ ሌሎች የህወሃት አባላት፤ የራሳቸውን ስብሰባ አዲስ
አበባ ላይ ሲያደርጉ ቢቆዩም በፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አልተገኙም ነበር። ይህ ብዙዎችን ቢያሳዝንም፤ ውስጥ
ውስጡን ግን የርስ በርሱን ሽኩቻ አጉልቶ የሚያሳይ ነው።
ሌላው ቀርቶ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚንስትር ተብለው ከመሰየማቸው በፊት፤ ባስቸኳይ ለህወሃት አባላት
የጄነራልነት ማዕረግ ማንበሽበሹ በራሱ፤ የርስ በርሱ የስልጣን ሽኩቻ ውጤት ነበር። ህወሃት በትግርኛ ባወጣው
መግለጫ ላይ አስፈላጊ ከሆነ፤ እንደገና የትጥቅ ትግል ሊያደርግ እንደሚችል ማስፈራሪያ ቢጤ በመግለጫው ላይ
አስፍሯል። ይህ ማስፈራሪያ ለማን እና ለምን እንዳስፈለገ እስካሁን ድረስ ግልጽ አይደለም። አቶ ኃይለማርያም
ደሳለኝም የአራት ኪሎውን ቤተ መንግስት ከሩቅ ከማየት በቀር፤ በለቅሶ ሰሞን ጎዳና ተዳዳሪ ጭምር ሲንሸራሸርበት
ወደነበረው የምኒልክ ቤተመንግስት እንዳይገቡ ተደርገዋል።
አቶ ኃይለማርያም በአሁኑ ወቅት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ሳይሆን፤ እንደበታች
የኢህአዴግ ሰራተኛ ነው። በፓርላው ቃለ መሃላ በፈጸሙበት ወቅት፤ “ከኋላ ደግፉኝ፤ ከፊትም ሆናችሁ ምሩኝ!”
እንዳሉት፤ ሌሎች የሚመሯቸው እንጂ ሌሎችን የሚመሩ አይነት ጠቅላይ ሚንስትር አልሆኑም። ወ/ሮ አዜብም ቢሆኑ፤
“የመለስን አልጋ ማንም አይተኛበትም!” ብለው ከመፎከር አልጋውን ይዘው ቢወጡ፤ የርስ በርስ የስልጣን ሽግግሩን
ይበልጥ ሰላማዊ ያደርገው ነበር። ይህ ግን አልሆነም። ሌላው ቀርቶ በአቶ መለስ ዜናዊ ጠቅላይነት ዘመን፤ የመንግስት
ከፍተኛ ሹሞች (ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ) ከስራ በሚሰናበቱበት ወቅት የሚያርፉበት ትላልቅ ቪላዎች እያንዳንዳቸው
በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ ተሰርተዋል። በቂ ጥበቃም ይደረጋል። ወ/ሮ አዜብ ግን ወደነዚህ ቪላዎች ለመሄድ ዝግጁ
አልሆኑም። ይልቁንም ከቤተ መንግስቱ የመውጣት ምንም አይነት አዝማሚያ አላሳዩም።
አሁን ያለው ችግር… አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ማዘዝ አለመቻላቸው እና የቀድሞዋ እመቤትም በዙሪያቸው የሚገኙ
የህወሃት ጄነራሎችን በመተማመን ለመታዘዝ ዝግጁ አለመሆናቸው ነው። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እልህ እየተናነቃቸው፤
“የመለስን ሌጋሲ አስቀጥላለሁ” ቢሉም፤ አሁን ደግሞ እንባ እየተናነቃቸው ከቤተ መንግስቱ ውጪ ቆመው ነው ያሉት።
ከሳቸው ጎን የቆሙት አቶ በረከትም ቢሆኑ፤ ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር ሊታረቅ በማይችል የግል ጸብ ውስጥ ከገቡ
አመታት በመቆጠራቸው፤ ጠንከር አድርገው ሴትዮዋን “ለቀው ይውጡ!” ማለት አይችሉም። በዚህ ጉዳይ እርምጃ መውሰድ
የሚችሉት፤ የቤተ መንግስቱን ጥበቃ ጭምር በሃላፊነት የሚመሩት የደህንነት ሚንስትሩ አቶ ጌታቸው አሰፋ ነበሩ። ምንም
እንኳን አቶ ጌታቸው አሰፋም የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ቢሆኑም፤ የቤተ መንግስቱ ጥበቃ ከእጃቸው ወጥቶ
በመከላከያ ሚንስትር ስር የሚመሩ ልዩ ታጣቂዎች ተሰማርተዋል። እነዚህን ቀላል የሚመስሉ ልዩነቶችን ገጣጥመን
ስናነባቸው ግን የሚሰጠው ስዕል እምብዛም ደስ የሚያሰኝ አይደለም።
እንዲህ ያለው ነገር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያጋጠመው የዛሬ መቶ አመት፣ በ1902 ዓ.ም. እቴጌ ጣይቱ፤ ከልጅ
እያሱ አሳዳጊ ከነደጃዝማች ተሰማ ጋር በተጣሉበት ወቅት ነው። ከምኒልክ ሞት በኋላ እቴጌይቱ ከሌሎቹ መኳንንት እና
እንደራሴ ጋር ስላልተስማሙ፤ “በሉ ወዳገሬ ወደ የጁ ላኩኝ” ቢሉ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እንደራሴ ከሌሎቹ
ሚንስትሮች ጋር መክረው፤ “አገሬ መልሱኝ ያሉት፤ ወንድማቸው ራስ ጉግሳ ወሌን ይዘው ወሎን ሊያስሸፍቱ ነው” በሚል፤
እሳቸው ከቆረቆሯት አዲስ አበባ ከተማ እንዳይወጡ ከለከሏቸውና አዲስ አበባ ውስጥ የአሁኑ ተክለሃይማኖት አካባቢ
ብዙ ሰራተኞችና አጃቢዎች ተመድቦላችው፤ በክብር ቤተ መንግስቱን ለቀው በሰላም መኖር ጀመሩ። አሁን ግን ወ/ሮ አዜብ
መስፍን አገር እንደሌለው ሰው፤ ቢያንስ እንደ እቴጌ ጣይቱ “ወዳገሬ መልሱኝ” ሳይሉ፤ ወደተዘጋጀላቸውም መኖሪያ
ቤት ሳይዛወሩ፤ ቤት አይቶ እንደማያውቅ ሰው “ከምኒልክ ቤተ መንግስት አልወጣም” ብለው በማንገራገር ላይ ናችው።
ለነገሩ ወ/ሮ አዜብ “ወዳገሬ መልሱኝ፡” ቢሉ፤ የሚወስዷቸው ወደአያቶቻቸው ራስ ጎላ አገር ወልቃይት ነው።
ወልቃይቴዎች ደግሞ በሴትዮዋ አዝነውባቸው ከተቀያየሙ ሰንብተዋል። ወደ ትግራይ እንዳይሄዱ ደግሞ፤ የትግራይ ህዝብ
ደግሞ ውስጥ ውስጡን የመለስ ዜናዊን የሞት ምክንያት ከወ/ሮ አዜብ ጋር እያያዘ ውስጥ ውስጡን ስለሚያወራ፤ ሴትዮዋ
የአድዋንም ሆነ የመቐለን ህዝብ የማየት፤ እነሱን የሴትዮዋን አይን ማየት የሚፈልጉ አይመስልም። የሆኖ ሆኖ ግን
የአቶ መለስ ዜናዊ የሞት መንስዔ እንደማይታወቀው ሁሉ፤ ሴትዮዋም ለምን ከምኒልክ ቤተ መንግስት መውጣት እንዳልፈለጉ
ግልጽ አይደለም።
No comments:
Post a Comment