Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday 12 December 2012

ተቋርጦ የነበረው የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ክስ እንደገና ተጀመረ

-    ዋስትና ተፈቅዶለት በ50 ሺሕ ብር ዋስ ተለቀቀ
በታምሩ ጽጌ

ሦስት ክሶች ተመሥርተውበትና ዋስትና ተከልክሎ ለአራት ቀናት በማረሚያ ቤት ከቆየ በኋላ፣ ክሱ ተቋርጦ በነፃ የተሰናበተው የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ የተቋረጠው ክስ በድጋሚ ትናንትና ፍርድ ቤት ቀርቦበት በ50 ሺሕ ብር ዋስ ተለቀቀ፡፡ ከነሐሴ 23 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በፍትሕ ጋዜጣ ላይ በራሱና በጽሑፍ አቅራቢዎች አምስት ጊዜያት ታትመው በወጡ መጣጥፎች ምክንያት ክስ ተመሥርቶበት፣ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ ዋስትና በመከልከሉ ማረሚያ ቤት እንዲቆይ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ክስ መሥርቶበት የነበረው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ ‹‹የማጣራው ምርመራ ስላለኝ እስከዚያው ድረስ ክሴን አቋርጫለሁ፤›› በማለት ነሐሴ 21 ቀን 2004 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ አማካይነት፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ነሐሴ 22 ቀን 2004 ዓ.ም. ከእስር ተፈትቶ ነበር፡፡ ዓቃቤ ሕግ ላለፉት ሦስት ወራት አቋርጦት በድጋሚ በተንቀሳቀሰው ክስ ውስጥ ጋዜጠኛ ተመስገን በተለያዩ ጊዜያት ዕትሞች ‹‹ሞት የማይፈሩ ወጣቶች፣ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን እስከ መጨፈር፣ የሁለተኛ ዜግነት ሕይወት እስከመቼና ሲኖዶስና መጅሊስ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ማጥመቂያ›› የሚሉ መጣጥፎች ማወጣቱ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም በወጡት መጣጥፎች ወጣቶችን ለአመፅ አነሳስቷል፣ ቀስቅሷል፣ ስም አጥፍቷል በሚል ነበር የመጀመሪያው ክስ የቀረበው፡፡ አሁንም የቀረበው ክስ ይኼው ነው፡፡

በትናንትናው ዕለት ዓቃቤ ሕግ ለምን ክሱን ማንቀሳቀስ እንደፈለገ እንዲያስረዳ ችሎቱ ጠይቆት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ክስን የማቋረጥና የመጀመር ሥልጣን እንዳልው ከመግለጽ ባለፈ በዝርዝር አላስረዳም፡፡ ፍርድ ቤቱ በሁለተኛነት ክስ የተመሠረተበትና የፍትሕ አሳታሚ የሆነው ማስተዋል የሕትመትና የማስታወቂያ ድርጅትም እንዲቀርብ አዞ፣ ክሱ መቀጠል አለመቀጠሉን በሚመለከት ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ፍትሕ ጋዜጣ ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. ለሕትመት ወደ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የገባ ቢሆንም፣ ‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር እንዳታትም ብሎኛል›› በሚል ምክንያት ማተሚያ ቤቱ አላትምም ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ጋዜጣው በወቅቱ ለምን እንዳልታተመ እስካሁን በግልጽ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት በአቶ መለስ ዜናዊ ሕመምና በአጠቃላይ በወቅቱ ስለነበሩበት ሁኔታዎች የሚያትት መጣጥፍ ይዞ ስለነበር፣ ሕዝብን አላስፈላጊ ውዥንብር ውስጥ ይከታል በሚል ተሰግቶ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ ጋዜጣው ከዚያን ጊዜ አንስቶ ተዘግቶ የቆየ ቢሆንም፣ ጋዜጠኛ ተመስገን በማኔጂንግ ኤዲተርነት ‹‹አዲስ ታይምስ›› በሚባል መጽሔት ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡

No comments:

Post a Comment