Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Tuesday, 5 June 2012

ኦብነግ ጅጅጋ አጠገብ “ከ50 በላይ የወያኔ ወታደሮችን ገደልኩ” አለ

VOA | June 4th, 2012 at 4:37 pm, posted by Dawit Wasihun
(VOA) — ግንባሩ ጥቃቱን የፈፀመው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ደበች ሕሪሶ በተባለ አካባቢ ባለፈው ዕሁድ ግንቦት 19 አድርሰውታል ላለው ጥቃት በወሰደው የበቀል እርምጃ ነው፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር በጠቅላላው ስድስት መኮንኖችን ጨምሮ 168 ወታደሮችን መግደሉን መግለጫው አክሎ ጠቁሟል፡፡
ባለፈው ዕሁድ የመከላከያ ሠራዊቱ አድርሶታል ሲል ኦብነግ በሚያሰማው ክስ 18 ሠላማዊ ሰዎችን መግደሉንና ከ15 በላይ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የግንባሩ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባልና የኢትዮጵያ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሃሰን አብዱላሂ ገልፀዋል፡፡
ተዋጊዎቻቸው እንደወሰዱት በተናገሩት የበቀልና እስረኞችንም የማስፈታት እርምጃ ሁለት መኪኖችን ማቃጠላቸውን፣ የተለያዩ መሣሪያዎችና የመገናኛ ሬዲዮኖችን መማረካቸውን፣ ብርቆት ከተማንም ለ15 ሰዓታት ተቆጣጥረው መቆየታቸውንና ለወታደራዊ ስትራተጂ ሲባል ለቅቀው መውጣታቸውን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በተጠቀሰው ውጊያ ውስጥ መሣተፋቸውን የተናገሩትና “ለሕዝቡ አገልግሎት የተሠራ የውኃ መሣቢያ ሊያወድሙ የመጡ ወንበዴዎችን ከአካባቢው አባርረናል” ያሉት ሻለቃ ሙክታር ሼኽ ሞሐመድ የሚባሉ የክልሉ ልዩ ፖሊስ አዛዥ በግጭቱ ወቅት 35 የኦብነግ ተዋጊዎችን መግደላቸውንና አሥር መማረካቸውን ለሶማሊኛ ቋንቋ አገልግሎት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡
ቀደም ሲልም የክልሉ ልዩ ፖሊስ አሥር ሲቪሎችን ራቅዳ በተባለች ቀበሌና በአካባቢዋ ገድሏል፤ ዘፈፋ አካሂዷል፤ የከፉ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎችንም ፈፅሟል ሲሉ ሂዩማን ራይትስ ዋች የሚባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው ስለሰጡት መግለጫ የተጠየቁት ሻለቃ ሙኽታር ሼክ ሞሐመድ መግለጫው “አንዳችም መሠረት የሌለውና የተለመደ የሂዩማን ራይትስ ዋች ፕሮፓጋንዳ ነው” ብለውታል፡፡

No comments:

Post a Comment