- Wednesday, 04 July 2012 09:27
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ትናንትና በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጸው፣ በከተማው ያሉትን የጐዳና ላይ ተዳዳሪዎች ወደ መልካም ሕይወት ለመመለስ፣ አስተዳደሩ በማድረግ ላይ ባለው እንቅስቃሴ መምህር፣ ነርሶችና በተለያዩ ሙያዎች የተመረቁ ዜጐች የጐዳና ላይ ተዳዳሪ ሆነው መገኘታቸውን አረጋግጧል፡፡
እነዚህ የተማሩ ዜጐች ለጐዳና ሕይወት የዳረጋቸውን ምክንያት በማጣራትና አስፈላጊውን የማስተካከያ ውሳኔ በማስተላለፍ ቀድሞ ወደ ነበሩበት ሥራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን፣ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ካህሣይ ገብረ መድኀን ገልጸዋል፡፡
አስተዳደሩ በጐዳና ላይ የሚኖሩትን ዜጐች ለማቋቋምና ሥራ በመፍጠር ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ፣ በአራት ዙር ከሰባት ሺሕ በላይ የጐዳና ተዳዳሪዎችን በተለያዩ የሥራ መስኮች ማለትም በኮብል ስቶን ሥራ፣ በጥቃቅንና አነስተኛና በመሳሰሉት ለማሰማራት ባደረገው ጥረት አስደሳችና አሳዛኝ ገጠመኝ እንዳለው ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለጊዜው ቁጥራቸውን በውል አላውቀውም ቢልም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ጎዳና ላይ ይኖራሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ ገበታቸው የተፈናቀሉ፣ በተለያዩ ሱሶች የተለከፉና በሕመም ምክንያት ሥራቸውን ማከናወን ያልቻሉ የመጀመርያና የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች መኖሪያቸውን ጎዳና ላይ አድርገዋል፡፡ ቢሮው በሥሩ በተዋቀረው የማኅበራዊ ችግሮች፣ መንስኤዎች መከላከልና ተሃድሶ ዋና የሥራ ሒደት በከተማው ውስጥ ያሉ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በተመለከተ ያደረገው ጥናት ቢጠናቀቅም፣ ምን ያህል ምሩቃን ጎዳና ላይ እንዳሉ ውጤቱን ይፋ አለማድረጉ ታውቋል፡፡
ሕፃናትን በመምከር ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ በማድረግ፣ ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች ዕርዳታ በመስጠት አስተዳደሩ ዜጐች ወደ ተሻለ ሕይወት እንዲያመሩ ቢያደርግም፣ በጐዳና ላይ ቆይታቸው በተለያዩ ሱሶች የተጠመዱና ያለ ሥራ እየለመኑ መኖር የወደዱ፣ ተመልሰው ወደ ጐዳና ሕይወት መግባታቸውን አቶ ካህሣይ ገልጸዋል፡፡ በቀን አራት መቶ ብርና ከዚያም በላይ እያገኙና እየቆጠቡ ብዙ ወጣቶች ሕይወታቸውን ሲለውጡ፣ የራሳቸውን ሥራ በመሥራት መለወጥ የማይፈልጉ ደግሞ ጐዳና ላይ እንዳሉም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
አስተዳደሩ የካ ትንሳኤ መንደርና ቦሌ ህዳሴ መንደር በማለት ባቋቋማቸው የማሠልጠኛ ቦታዎች ለሁለት ወራት እየሠለጠኑ ወደተለያዩ ሥራዎች (ኮብል ስቶን፣ ኮንዶሚኒየም ግንባታና ሌሎችም) እየተሰማሩ እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ካህሳይ፣ ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ዜጐች አዲስ አበባ የሚያርፉ በመሆኑ የጐዳና ተዳዳሪዎችን ብዛት ለመቀነስ አለመቻሉን አውስተዋል፡፡
ከየክልሉ በመልካም አስተዳደር እጦት በተለይ በቀበሌ ሹማምንት መሬታቸውን እየተነጠቁና የተለያዩ በደሎች እየደረሱባቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የጐዳና ላይ ተዳዳሪ የሆኑትን ሳይቀር፣ አስተዳደሩ ወደ መጡበት ለማጓጓዝ ወይም ለመርዳት የበጀት እጥረት እንዳለበት የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ ክልሎች የየራሳቸውን ሰዎች የሚያቋቁሙበት ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ቡድን ተቋቁሞ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በየቀበሌ ማኅበሩ የሚደርስባቸው ወከባና ጫና ቀርቶላቸው ሕይወታቸውን በመልካም ሁኔታ እንዲመሩ ለማድረግ እንዲሠሩና ወደየቀያቸው ለሚመለሱትም የሦስት ወራት ቀለብ ለመርዳት ስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል፡፡
ዜጐችን ለማጓጓዝ እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ ሆነው በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩትን ለመርዳት፣ ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ በተደረገ ቴሌቶን ብራይት ሆፕ የሚባል በጐ አድራጐት ድርጅት ለእያንዳንዳቸው የጐዳና ተዳዳሪዎች 120 ዶላር የሚገመት ጫማና ለቀለብ የሚሆናቸው ሩዝ ለመርዳት በድምሩ ስምንት ሚሊዮን ብር ሲለግስ፣ በአጠቃላይ ከቴሌቶኑ ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ አስተዳደሩ ግን 15 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ተጠቁሟል፡፡
በሥራ አጦችና በጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ ለመምከር የአስተዳደሩ ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ በየክልሉ የሚገኙ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዎች ባህር ዳር ላይ ስብሰባ መቀመጣቸውን አቶ ካህሳይ አስረድተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment