· አራት መነኰሳት በፖሊስ ተይዘው ተወስደዋል፤ ሌሎቹ መነኰሳት እየተደበደቡ ተበታትነዋል።
·
የገዳሙ የሱባኤ ወቅት በፖሊስ የኀይል
ርምጃ እየታወከ ነው።
·
በዛሬማ ወንዝ ላይ የሚገነባውን
የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ግድብ የሚሠራው ሱር ኮንስትራክሽን ለቆ መውጣቱ እየተነገረ ነው፤ በምትኩ የቻይና ተቋራጭ የገባ ቢኾንም በእርሱም
ላይ ተቃውሞው መቀጠሉ ተሰምቷል።
ትናንት፣ ሰኔ 23 ቀን 2004
ዓ.ም፣ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ገዳሙን በተቆጣጠረው የፖሊስ ኀይል አራት የገዳሙ መነኰሳት ተይዘው ወደ ወረዳው ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱ
ሲኾን ሌሎቹ መነኰሳት ደግሞ ለሱባኤ (ሕርመት) ከተሰበሰቡበት በቆመጥ እየተደበደቡ መበታተናቸው ተጠቁሟል፡፡
ከአራቱ መነኰሳት መካከል ሦስቱ፣
አባ ኀይለ ኢየሱስ፣ አባ ግርማይ፣ አባ ገብረ እግዚአብሔር
እንደሚባሉ ተረጋግጧል፤ የአራተኛውን መነኰስ ስም ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ማኅበረ መነኰሳቱን የማሳደዱ ተግባር ከገዳሙ ውጭም የቀጠለ
ሲኾን ፖሊስ አባ ገብረ ሕይወት የተባሉ ሌላ የገዳሙ መነኮስን ለመያዝ በደባርቅ ከተማ አሠሣ እያደረገ መኾኑ ተገልጧል፡፡ የአሠሣው
እና ስምሪቱ መጠናከር ምክንያት፣ ከግንቦት 22 ቀን አንሥቶ የዋልድባ ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም ሴት መነኰሳዪያት፣ የወልቃይት
ስኳር ልማት ፕሮጀክት በገዳሙ ላይ የሚያደርሰውን አካባቢያዊና ማኅበራዊ ጉዳት በመቃወም “ኑና ገዳሙን ተረከቡ፤ እኛ መሰደዳችን
ነው” በሚል ለሕዝቡ ጥሪ ካስተላለፉ በኋላ በተለይም በዛሬማ ቀበሌና በእንዳባጉና ወረዳ ዲማ ቀበሌ እየተጠናከረ የመጣው የተቃውሞ
እንቅስቃሴ መኾኑ ተመልክቷል፡፡
በዋልድባ አብረንታንት ገዳም፣ በዋልድባ
ሰቋር ኪዳነ ምሕረት ገዳም እና በዋልድባ ዳልሽሐ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም በየዓመቱ ከሰኔ 21 - ኅዳር 8 ቀን የሱባኤ ወቅት ነው፡፡ ገዳሙ ዓመት እስከ ዓመት ሱባኤ የሚያዝበት፣ አባቶች ያለማቋረጥ
ከእግዚአብሔር የሚገናኙበት የሰማይ በር ቢኾንም፣ ይህ ወቅት
ግን ከሌላው ጊዜ ተለይቶ ማንም አቋርጦ ለመውጣት የማይፈቀድበት ነው፡፡ በአንድነትና በፍቅር ተሰብስበው የሚኖሩት ማኅበረ መነኰሳት ጭው ካለው በርሓ ገብተው በቋጥኝና በዋሻ እንደሚኖሩት
ግሑሳን ባሕታውያን ከሰው ተለይተው በአንድ ቦታ ተወስነው በጾም፣
በጸሎትና በስግደት መንፈሳዊ ተጋድሏቸውን የሚያጠናክሩበት ወቅት ነው፡፡
ዋልድባን በአራቱም ማእዝናት የከበቡት
የእንሰያ (ምሥራቅ)፣ ዛሬማ (ምዕራብ)፣ ተከዜ (ሰሜን)፣ ዛሬማና
ወይባ (ደቡብ) የተሰኙት ታላላቅ ወንዞችም በሰኔ የሞሉ እስከ
ኅዳር አይጎድሉም፡፡ ከሱባኤው ፍጻሜ በኋላ፣ ኅዳር ስምንት ቀን የአርባእቱ
እንስሳ ክብረ በዓል ቀን፣ ወንዞቹን ተሻግረው በምሥራቅ - ፀለምትና በምዕራብ - ወልቃይት በሚገኙ የገዳሙ እርሻ ቦታዎች
ከተዘጋጀው ድግስ የሚቀምሱ አሉ፡፡ ለዚህም በተለይም ማይ ለበጣ ታላቁ
የማኅበሩ መገናኛ ቦታ ነው፡፡
የዘንድሮው የገዳሙ የሱባኤ ወቅት
ግን ይህን ለዘመናት የቆየ የአበው ሥርዐትና ትውፊት የሚደግምበትን የጥሞና ጊዜ የታደለ አይመስልም፡፡ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት
በገዳሙ ህልውናና ክብር ላይ በጋረጠው ስጋት ሳቢያ የሰቋር ኪዳነ ምሕረት ማኅበረ መነኰሳት በተለይም ከግንቦት 22 ቀን ጀምሮ “ኑ ፣ ታቦቱን፣ ቅርሱን ተረከቡ፤ እኛ እንፈልሳለን (ወደ በርሓ እንሰወራለን)”
በሚል ለምእመኑ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ከስድስት ያላነሱ የዓዲ አርቃይ ወረዳ ቀበሌዎች (ሳንቅ፣ ዛሬማ፣ ያሊ፣ የጥራይና፣ ጅሮሰ፣ ነብራና ፍድቃ) አርሶ አደሮች
ከግንቦት 23 እና 24 ቀን አንሥቶ ዛሬማና ሰቋር ላይ በመሰብሰብ ተቃውሟቸውን አጠናክረው መቀጠላቸው ተነግሯል፡፡
የአማራ ብ/ክ/መ ፖሊስ ኮማንደርና
የሰሜን ጎንደር ዞን ብአዴን ጽ/ቤት ሓላፊ ግንቦት 27 እና 28 ቀን ዛሬማ ቀበሌ ላይ የወረዳ አመራሮችንና ምእመኑን በአንድነት
ጠርተው ስለ ፕሮጀክቱ ለማሳመን ስብሰባዎችን አካሂደዋል፡፡ ይኹንና በዚያው ዛሬማ ቀበሌ የመድኃኔዓለም ታቦት ማረፊያ ዋርካ ሥር በመገናኘት ስብሰባው አሳታፊ አለመኾኑንና በስብሰባው ላይ ተገኝተው አቋማቸውን
እንዳይገልጹ መከልከላቸው አግባብ አለመኾኑን በመቃወም እስከ 50 ያህል ወጣቶችን ለእስር ከመዳረግና በጭከና ከመደብደብ በቀር ውጤት
እንዳላስገኘላቸው ነው የተዘገበው፡፡ ግንቦት 29 ቀን ከታሰሩት ኀምሳዎቹ ወጣቶች መካከል “ወጣቱን ለስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ቀስቅሰዋል፤ ከተቃዋሚዎች ጋራ በመገናኘት እንቅስቃሴውን አስተባብረዋል፤”
በሚል ስምንት ወጣቶች ተለይተው ከዛሬማ ቀበሌ 40 ኪ.ሜ ወደሚርቀው የወረዳው ከተማ (ዓዲ አርቃይ ፖሊስ ጣቢያ) ሲወሰዱ ሌሎቹ
በዋስና በገንዘብ ቅጣት ደረጃ በደረጃ መለቀቃቸው ተገልጧል፡፡
ይህ ሁሉ ሲኾን የዋልድባ ገዳም
የሚገኝባቸው ሦስቱ አህጉረ ስብከት ይኹን ወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ድምፃቸውን ባለማሰማታቸው ምእመኑ ከዘንድሮው ዓመት ጀምሮ
“የነፍስ ዐሥራት በኵራት” ሲል የሚጠራውን መባዕና የሰበካ
ጉባኤ አስተዋፅኦ እንደማይከፍል ለወረዳ ቤተ ክህነት በጻፈው ደብዳቤ ማስታወቁ ተመልክቷል፡፡ የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱ ጉዳዩን
ለአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች ያስታወቁ ቢኾንም ምን ምላሽ እንደተሰጠ ለማወቅ አልተቻለም፡፡
የተቃውሞው ከዕለት ወደ ዕለት መጠናከር
ያሳሰበው የክልሉ (የአማራ ብ/ክ/መ) አስተዳደር፣ ፕሬዝዳንቱን አቶ አያሌው ጎበዜን፣ የክልልና ዞን ጸጥታ ሓላፊዎች እንዲሁም የብአዴን
ጽ/ቤት ሓላፊዎች በተገኙበት ሰኔ ሰባት ቀን 2004 ዓ.ም ዓዲ አርቃይ ላይ ስብሰባ ጠርቶ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ከዋልድባ አብረንታንት
ቤተ ጣዕማና ቤተ ሚናስ፣ የሰቋር ኪዳነ ምሕረትና ዳልሽሓ ኪዳነ ምሕረት ገዳማት ከእያንዳንዳቸው ዐሥር፣ ዐሥር መነኰሳት፤ 28 የቀበሌ
አመራሮችና “የልማት አርበኛ” የተሰኙ አርሶ አደሮች እንዲሳተፉ ጥሪ ተደርጎላቸው ነበር፡፡
የክልል፣ የዞንና ወረዳዎች (ደባርቅ፣ ፀለምት - ማይ ፀብሪ፣ ዓዲ አርቃይና ጎንደር) አመራሮች
የታደሙበት ይኸው ስብሰባ ልጆቻቸው በታሰሩባቸው ወላጆች ጥያቄ ከዓዲ አርቃይ ወደ ዛሬማ እንዲዞር የተደረገ ቢኾንም በስብሰባው ከተሳተፉት
ብዙኀኑ “ከጎንደር እስከ ማይ ፀብሪ ያሉ የኢሕአዴግ ደጋፊዎችና የተለየ
ሐሳብ የማያነሡ ናቸው” ብለዋል ታዛቢዎች፡፡ ከዋልድባ አብረንታንት ዘቤተ ጣዕማ ስድስት መነኰሳት ቢገኙም ከዋልድባ አብረንታንት
ዘቤተ ሚናስ ማኅበር የታየ አልነበረም፡፡ ከሰቋር እና ዳልሽሓ የተገኙትም የተወሰኑት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ
በጸሎት ሲያሳርጉ ከመሰብሰቢያው ወጥተው ሄደዋል፤ የቀሩትም ባሉበት በመቀመጥ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፤ መስቀላቸውንም ለመሳለም ፈቃደኛ
አልኾኑም፡፡
በዚሁ ስብሰባ እንደ ማይ ፀብሪው
አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ መረሳ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት፡- “ሃይማኖትን
ሽፋን እያደረጋችኹ የፖለቲካ ዘመቻ ታደርጋላችኹ፤ የፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰለባ ኾናችኋል፤ የእነርሱን ድምፅ
ነው የምታስተጋቡ” በማለት ግልጽ ዘለፋ ማሰማታቸው ተገልጧል፡፡ “ብትስማሙና ልማት ቢለማ ምናለበት?” የሚሉ ልመናዎችም ተደምጠዋል፡፡
መነኰሳቱ በበኩላቸው “በልቅሶ ነው ያለነው፤ ዐፅም ወጥቶ ውኃ አይቆምም፤
ቤተ ክርስቲያን እየፈረሰ በሚለማ ልማት አንስማማም፤ ዋልድባ ቅንጣት ያህል አትነካም›፤ ይህ የሃይማኖት ጉዳይ እንጂ ፖለቲካ አይደለም”
በሚል ቁርጡን ማስታወቃቸው ተነግሯል፡፡
በዚሁ ስብሰባ ዋዜማ፣ ሰኔ ስድስት
ቀን 2004 ዓ.ም፣ በዓዲ አርቃይ ከተማ አስጋሪት ማርያም
በተሰኘችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተገናኙ የከተማው ወጣቶች ስብሰባው ወደሚካሄድበት ዛሬማ ቀበሌ በመሄድ ድምፃቸውን ለማሰማት እየተመካከሩ
በነበረበት ወቅት የወረዳው ፖሊስ ደርሶ በሽመል በመደብደብ እንዲበተኑ ማድረጉን የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ
ፊት ለፊት በምትገኘው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰብሰበው የነበሩት ቁጥራቸው ከ30 የማያንሱ ወጣቶች ከተበታተኑ በኋላ
ፖሊስ በየቤቱ በመዞር ወላጆች ልጆቻቸውን ይህን ዐይነቱ የተቃውሞ ምክክር ከማድረግ እንዲቆጠቡ የማይመክር ከኾነ ጥብቅ ርምጃ እንደሚወስድባቸው
ሲያሳስብ መዋሉ ታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ንድፉ በትግራይ
ውኃ ሥራዎች ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ተሠርቶ በትግራይ ውኃ ሥራዎች
ኮንስትራክሽን ግንባታው የተጀመረውን የዛሬማ ወንዝ ግድብ
ሥራ ተረክቦ ሲመራ የቆየው ሱር ኮንስትራክሽን ሥራውን አቋርጦ
መውጣቱ ተሰምቷል፤ ምክንያቱ ቁፋሮው የሚካሄድበት ቦታ ከመሬት በሚፈልቅ ውኃ እየተሞላ ማስቸገሩና የምእመኑ ተቃውሞ ያሳደረው ግፊት
ነው ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ስሙ ያልተገለጸ አንድ የቻይና ተቋራጭ የግድቡን ሥራ ለመቀጠል የተተካ ቢኾንም በተመሳሳይ አስቸጋሪ
ኹኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡ የሱር ኮንስትራክሽን መውጣት ከተጠቀሰው ምክንያት ጋራ መያያዙን የሚጠራጠሩ ሌሎች ምንጮች በበኩላቸው፣
በግድቡ ዲዛይን (የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ውኃ አጠቃቀም) ላይ መሠረታዊ ለውጥ በማድረግ ሥራውን ለመቀጠል ሳይታሰብ እንዳልቀረ ያላቸውን
ሐሳብ ገልጸዋል፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን።
No comments:
Post a Comment