Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday 26 August 2012

መነገር ያለበት ቁጥር ሦስት.......... በልጅግ ዓሊ

መነገር ያለበት ቁጥር ሦስት
በልጅግ ዓሊ
በድሮ ጊዜ ሰው ሲሞት ጥይት መተኮስ ልምድ ነበር። ታዲያ ጠራ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ አንድ ትልቅ ሰዉ ሞቶ ብዙ ጥይት ወደ ሰማይ ሲተኮስ የተመለከቱ አንድ ሽማግሌ ወደ ደብረብርሃን ሲጓዙ አንድ ሰው መንገድ ላይ ያገኝና ስለ ጠራ ይጠይቃቸዋል። ሽማግሌው ሃገሩ ሰላም ነው ግን እግዜርና ሰው ተጣልተው ብዙ እየተታኮሱ ነበር። እስከ አሁን እግዜር አንድ ጥሏል ። የሰዎቹን ግን የጣሉትን አላውቅም አሉት ይባላል። እንግዲህ በሰሞኑ ሁኔታ ወያኔ በሃይማኖት ላይ በከፈተው ጦርነት እግዜር ሁለት ጥሏል። ወያኔዎቹ ስንት እንደጣሉ ገና አልታወቀም።

ለወራት የተጠረጠረው ሁሉ እውን ሆነ። መለስ እንደ ሰው ልጅ ፍጡር ሁሉ ቀኑ ደርሶ ከዚህ ዓለም ተለየ። የሃገራችን ሰው ሙት ወቃሽ አታርገኝ ይላል ። አዎ የሞተ ሰው መውቀስ ጥቅም እንደሌለው ተረድቶ ነው። ግን መለስ ሃገሪቱን ለ 21 ዓመታት በመምራቱና እሱም ተክሎት የሄደው እሾህ ገና ስላልተነቀለ ሙት ወቃሽ ሳንሆን ሥርዓት ወቃሽ ነው የምንሆነው።

መለስ ገዳይ ነበርና እንኳን ሞተ የሚለው አባባል ላይ አልስማማም። በምድር ሆኖ ለሠራው ጥፋት በሕይወት እያለ ፍርዱን ቢቀበል እንደኔ ጥሩ ነበር። አሁን ግን ፍርዱን የሚሰጠው አምላክ ነውና በእሱ ሥራ መግባት ጥሩ አይሆንም። እንደ ሃገራችን ባህል ለቤተሰቦቹ መጽናናትን እመኛለሁ። መለስም ቢሆን ለልጅ አባት ፣ ለሚስት ደግሞ ባል፣ ለእናት ለአባት ልጅ ነበር። ብዙዎች ይህንን ተረድተው አፍ እላፊ የሆነውን ዘለፋን ተቆጥበው፣ ከንዴት ባሻገር የትልቅነት ባህሪን በሳዩ ጥሩ ነበር። ቢሆንም የግፉ ብዛት ምሬት ቢፈጥር ልንረዳቸውም ይገባል።

በዚህ ሰሞን የዚህን የጥፋት መልዕክተኛ የነበረ ከፋፋይ ሰው ስም እያነሱ ያደረሳቸውን በደሎች እየዘረዘሩ ሞት አነሰው ያሉ ቁጥራቸው ብዙ ነው። አዎ ይህ ሞት አነሰው የሚለው ፍርድ ቤተሰቦቻቸው ከተበተኑባቸው፣ ከቤታቸው በዘር ፖለቲካ ምክንያት ተፈናቅለው የላስቲክ ቤት ኑዋሪ ከሆኑ ፣ ልጆቻቸውን ፣ ባሎቻቸውን ፣ አባትና እናታቸውን ፣ ወይም የቅርብ የሚወዱትን ያጡ ሰዎች በእግዜር ፍርድ ገብተው ሞት አነሰው ቢሉ አነሰባቸው እንጂ በዛባቸው ማለት አንችልም።

በሌላ በኩል ደግሞ የጥቅሙ ተካፋይ የነበሩ፣ የነጻ ገበያ ፖለቲካ በሰጣቸውም የሙስና ነጻነት የከበሩ ፣ ወይም ኢንቨስተር ተብለው ያንን ደሃ ሕዝብ በመበዝበዝ በመለስ ጥላ ሥር ሃብት ያካበቱ ደግሞ ደረት ቢደቁ ፣ ጸጉር ቢነጩ ወይም ፊት ቢልጡ የሚያስደንቅ አይሆንም። ይህንን ሁለት ቀን ሲቪሊቲ የሚል የፓልቶክ ትልቅ ድንኳን ተክለው ምሬታቸውን፣ ብሶታቸውንና ወደፊት ምን ሊገጥማቸውም እንደሚችል ችግራቸውም ሲወያዩ ለተከታተለ መለስ ለእነዚህ ሰዎች ከእግዜር እኩል ፈጣሪቸው እንደነበር ይረዳዋል። በዚህ ድንፋታቸው አልሆን ብሎ እንጂ ፈጣሪ አምላክን እንደተለመደው በሽብርተኛ መድበው ቃሊቲ ይሰዱት ነበር።

የመለስ ሞት፣ የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ የሚፈጥረው አቧራ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይረጋል። መለስን ማን ነው የሚተካው? የሚለው ጥያቄ አደባባይ አይውጣ እንጂ አሁንም የውስጥ ንትርክ እንደሆነ ሾልከው የሚወጡ ዜናዎች ግልጽ አድርገውታል። እንደዚህ ተቃቅፈው ያለቀሱ ሁሉ እንደዚህ በፍቅር አይኖሩም። እያደር የውስጥ የሥልጣን ትግል ጥያቄ ጎልቶ ይወጣል። ሃይለማርያም ደሳለኝ የመለስን ቦታ ይተካል ብሎ የሚያምን ራሱን ለማቄል የተነሳ የዋህ ብቻ ነው። ሰውየው ከአሻንጉሊትነት አያልፍም። አቅሙም ፣ ችሎታውም እንደሌለውና የመለስ መጫወቻ እንደነበር ቀደም ብሎ የተነገረ ነው።

በወያኔም ሆነ በተቃዋሚዎች የሚተካው ጎልቶ ባልወጣበት በአሁኑ ወቅት ይህንን ጥያቄ አንስቶ መወያየት ተገቢ ነው። ምክንያቱም በጥንቃቄ ካልተያዘ መለስ ጥሎት ያለፈው የዘር ፖለቲካ ሃገሪቱን በክልል የከፋፈላት በመሆኑ አደገኝነቱ የጎላ ነው። ከዚያም አልፎ በአካባቢው ያሉ ቀደምት የሃገሪቱ ጠላቶች ይህችን ሃገር ለማፈራረስ እንቅልፍ አጥተው እየሠሩ መሆናቸውን ልንዘነጋው አይገባም። ለምሳሌ የመለስን ሞት ምክንያት አድርጎ በሶማሊያ የሚገኘው አሸባሪ ድርጅት አልሽባብ የሰጠው መግለጫ ዝም ብለን የምናልፈው አይሆንም።

http://www.bbc.co.uk/news/world-africa-19336176

አልሽባብ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር እንድትጠፋ እንደሚመኝና ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም መነሳቱ ደግሞ በጣም አሳሳቢ ነው። የአልሽባብ መግለጫ እንደሚያሳየው ጠላቱ መለስ ሳይሆን ኢትዮጵያ ነች። እንዲያውም በደንብ ቢፋቁ መለስና አልሽባብ ወዳጆች ሆነው እናገኛቸዋለን። መለስ ከአልሽባብ የተጣላው የውስጥ ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት የአሜሪካንን ድጋፍ ለማግኘት እንጂ የኢትዮጰያን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይህ ደግሞ ቀደምት የነበራቸው ወዳጅነት ሊጠቀስ ይችላል። አልሽባብ በኤርትራ የሚደግፍ ለመሆኑ ደግሞ አጠገባችሁ የሚገኘው አንድ ሶማሊያዊ መጠይቅ ነው። ሃቀኛ ከሆነ እውነቱን ይነግራችኋል። የሻዕብያ ደጋፊዎች ሌት ተቀን እንቅልፍ አጥተው ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሲሰሩ እንደ ነበር የሚታወቅ ነው።

ዛሬ ሃገራችን ለአንድነት ከሚታገሉ ኃይሎች በላይ ሃገራችንን ለማፍረስ የሚታገሉት እንቅልፍ አጥተው የሚሠሩ ብዙ ጠላቶች አሏት። እነ አልሽባብ፣ እነ ኢሳያስ አፍወርቂ ዓላማቸውን ለማሳካት የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም። ይህ አሁን የተፈጠረውን ሁኔታ በመጠቀም የቀድሞ ወዳጃቸው በሆነው ወያኔ ውስጥ ያሉ አባሎቻቸውን ወይም በተቃዋሚ ስም ባሰባሰቧቸው ከሃዲዎች በመጠቀም ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ። በዚሁ አጋጣሚ እንደ ተስፋዬ ግብረ እባብ ያሉ የኢሳያስ ካድሬዎችን ፕሮፖጋንዳ የሚያሰራጩ የኢትዮጵያን ድረ ገጾች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሃገራችንን አንድነት የሚፈታተን መሆን መዘንጋት አይኖርባቸውም። ዛሬ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚለው አይሠራም።

ተቃዋሚ ኃይሎች ለኤርትራ መሪዎችና ለአልሽባብ መሪዎች ግልጽ የሆነ አቋማቸውን ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። የኢትዮጵያ አንድነትን በሚመለከት ምንም ዓይነት ድርድር ወይም ዝምታ አይጠቅምም። ግልጽ በሆነ መንገድ ይህንን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረገውን ጥረት በቅድሚያ እንደሚዋጉት ማሳሰብ አስፈላጊም ነው። እነ ኢሳያስ አፍወርቂ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንጥራለን ካሉ የሚደርስባቸውን አጻፋ ግልጽ በሆነ መንገድ ሊነገራቸው ይገባል።

ከዚያ ባሻገር በተቃዋሚዎች በኩል በረጋ መንፈስ ይህንን ሁኔታ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ሊታሰብ ይገባል። ተቃዋሚዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለተፈጠረው ክፍተት ግልጽ በሆነ መንገድ መፍትሄያቸውን ማቅረብ አለባቸው። ይህንን ካላደረጉ ሕዝብ በእነርሱ ላይ እምነት ሊያጣ ይችላል። ተቃዋሚዎች ከወያኔ ስልጣኑን ተረክበው ሃገራችንን ወደ ዴሞክራሲ መሄጃውን መንገድ ማሳየታቸው የብቃታቸው መለኪያ ነውና የሕዝብ ድጋፍ ያስገኝላቸዋል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በሕብረት ሲንቀሳቀሱ ብቻ ነው። በራስ የፖለቲካ አመለካከት ተሸፍኖ ሌሎችን አሽንፎ የበላይ ሆኖ ለማለፍ የሚደረገው የፖለቲካ ጥሎ ማለፍ ተንኮል እንዳልሠራ እስከ አሁን ያልተገነዘበ መሪ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የነ አልሽባብ ዓላማ አስፈጻሚ ነው ሊሆን የሚችለው። ይህ ደግሞ ከታሪክ ተወቃሽነት አያድንም።

ይህች ሃገር ችግሯ ባለብዙ ፈርጅ ነው። መፍትሔው ግን በእጃችን ነው። የድርጅት መሪዎች ወቅቱ የሚጠይቀውን አንገብጋቢ ጥያቄ ተረድተው በውስጣቸው የዳበረውን የግል ታዋቂነት በሽታ፣ የሥልጣን ጉጉት አውልቀው ጥለው ታላቅነታቸውን ፣ የአመራር ችሎታቸውን፣ የመሪነት ብቃታቸውን ቅድሚያ ሃላፊነት በመውስድ ማሳየት ይኖርባቸዋል። ለድል የሚያቀርባቸው እሱ ነውና።

ስለ ሃገራችን አንድነት የሚያስቡ በሰላም ይክረሙ!
ነሐሴ . . . ለንደን

No comments:

Post a Comment