Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Monday, 27 August 2012

የአባባ መለስና የአባባ ታምራት ልጆች ተንጫጩ! ....... ፍቅር ይበልጣል

ይሄ የአቶ መለስ ሞት ግዴላችሁም ገና ብዙ ጉድ ሳያሳየንና ሳያሰማን አይቀርም፡፡ ነገሩ ደግሞ ከ2005ዓ.ም መስከረም ጋር በመግጠሙ የተለመደውን ‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም› ብንል ወቅታዊነት አለው፡፡ ለካንም ለዚህ ኖሯል የቀብሩን ጊዜ ለሁለት ሣምንታት አራዝመው ዓለምን በሚያስደምምና ከዓለምም በተለዬ ሁኔታ አዲስና የሰሜን ኮሪያን የሚመስል የሀዘን ሥነ ሥርዓት ያወጁት፡፡ አራት ኪሎ ድንጋይ መጣያ ቦታ የለም – ሰው በሰው ተጨናንቋል፡፡ ይህ ሁሉ በአራትና አምስት ዙር ተሰልፎ ለሰዓታት ዝናብና ብርድ የሚፈራረቅበት ሕዝብ ቤተ መንግሥት እየገባ መለስን ለመሰናበት ባለው ብርቱ ፍላጎት ነው፡፡ አንዳንዱ ለጊዜ ማሳለፊያ ነው፤ አንዳንዱ ቤተ መንግሥት የሚባል ለማየት በ76 ዓመት አንዴ ትታያለች እንደምትባለዋ ሃሊዮ ኮሜት እንደብቸኛ አጋጣሚ በመቁጠር ለደራው ነው፣ አንዳንዱ ለወሬ ነው፣ አንዳንዱ ለጊዜ ማሳለፊያ ነው፤ አንዳንዱ ከምር በማዘን ነው፣ አንዳንዱ በጣም ያዘነ ወዳጅ ዘመዱን ለማጀብ ነው፣ አንዳንዱ በመሥሪያ ቤት ተገድዶ ነው፣ አንዳንዱ ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተለ ለመታዘብ ነው፣… ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ በግርግር ግን መሌ ገሞራው ከቁሟ ይልቅ ስትሞት ይበልጥ ተመቻት፡፡ ከዚህ አጋጣሚ ሌላ፣ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ መፃጉዕ የታሪክ አራሙቻና ወበሎ ሰውዬ በመልካም የሚነሳ አይመስለኝም፡፡ ‹ይህች አጋጣሚ በአንድ አገናኝታን› አለ ጥላሁን፡፡ ‹ለራሱ ያልኖረ፣ ከልጅነት እስከዕውቀት መላ ጊዜውን ለሀገር ልማት ያዋለ፣ የማያዳላና ለሁሉም እኩል አመለካከት የነበረው፣ ለአፍሪካ ቀርቶ ለዓለም የሚበቃና ዓለም ልታጣው የማይገባት ምርጥ መሪ፣…› ተባለለት፤ ተዘፈነለት፤ ቅኔ ተዘረፈለት፤ መወድስ ተወረበለት፤ … አይ ያለው ማማሩ! በነዚህ ተመሳሳይ አፎች ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ምን እንደሚባል ለማየት ዕድሜ ይስጠን፡፡


መንጌ ከሀገር እንደወጣ እንዲህ ተባለ፡- ‹ለሀገሪቱ ሰላም የፕሬዝደንት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ከሥልጣን መነሣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፕሬዝደንት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ዛሬ ጧት ከሀገር ወጥተዋል፡፡› ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ደግሞ በዚያው ጣቢያ ዝርጠጣው ተጀመረና እንዲህ መባል ተጀመረ፡- “የሰው ምክር የማይሰማውና ሀገሪቱን ለውድቀት የዳረገው የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃ/ማርያም ‹አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀር እንዋጋለን› እያለ ሕዝብን ሲያታልልና ሲያጭበረብር ቆይቶ ለሥራ ጉብኝት በማሳበብ የተሣፈረበትን የጦር ሄሊኮፕተር አስገድዶ ከጠለፈ በኋላ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ችግር በማጋለጥ ዛሬ ጧት ሀገር ጥሎ ወደኬንያና ቀጥሎም ወደዚምባብዌ ኮብልሏል፡፡” አይ ይቺ ዓለም! ዓለም እንዲህ ናት – ሕይወትም፡፡ እናም የአሁኑ ድራማ የተገላቢጦሹን የሚሆንበት ዘመን በእጅጉ እየተፋጠነ ነውና ምሥኪኖች ደስ ይበለን፡፡ ውሸት ለጊዜው እንጂ ለዘላለሙ አትነግሥም፡፡ አሁን እየሆነ ባለው ነገር ሁሉ ከምናውቀው እውነት ጋር ዐይንና ናጫ እየሆነ ክፉኛ እየተጣረሰብን ቢዘገንነንም ይህ ዓይነቱ ነገር ያለ ነውና እንጽናናና እንደምንም ወቅቲቱን እናሳልፋት፡፡

በመሠረቱ የመንግሥቴን ሬዲዮም ሆነ ቲቪ አልከፍትም፡፡ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ቀደም ባለ አንድ ወቅት እንዳሉት – አንሻፍፌም ቢሆን እጠቅሳለሁ- ‹ኢቲቪን ማየት ካቆምኩ ወዲህ ጤንነቴ ተመለሰ› – የጥቅሱ መጨረሻ – እኔም ይህን የውሸት ቆሻሻ ገንዳ አልከታተልም፡፡ ሰሞኑን ግን አልፎ አልፎ እከፍታለሁ፤ የከፈቱ ሳገኝም ጆሮየን ጣል አደርጋለሁ – ምን አዲስ ቱሪናፋ ይኖር ይሆን ከሚል ተላላነት፡፡ ግን አልጠቀመኝም፡፡ በጣም እየጎዳኝ ነው፡፡ ኧረ እንዲያውም ሊያሳብደኝ ደርሷል!

ከደቂቃዎች በፊት በአንደኛው ኤፍ ኤም የነንዋይን አዲስ መለሳዊ ዘፈን ስሰማ ከምር ደነገጥሁ፤ አፌን በመዳፌ ይዤ ለተወሰኑ ደቂቃዎች አረመምኩ፡፡ ለቆራጡ መሪ ለመንግሥቱ ኃ/ማርያም በተስረቅራቂ ወፍራም የወንዳወንድ ቅላጼዋ ያቀነቀነችው አሥር አለቃ ውብሻሽም ትዝ አለችኝ፡፡ እሷ በቁም ለነበረ መሪ ነው የዘፈነችው፡፡ እነዚህኞቹ ማፈሪያዎች ግን በታሪክ የቁም ፖለቲካዊ ሞት ከዓመታት በፊት ገና ከማለዳው በወጣትነት ዘመኑ ለሞተና በመጨረሻም በልዩ ኃይል ጣልቃ ገብነት – በጣም በርግጠኝነት በኃያሉ የኢትዮጵያ አምላክ ተራዳኢነት – አካላዊ ሞቱን ሳይወድ በግዱ ለተጎነጨ አረመኔ መሪ ሲዘፍኑ በመስማቴ በነሱም የማዲንጎን ዘፈን አዝማች ርዕስ ልዋስናም ስያሜ ባጣሁለት እነሱነትም፣ በኢትዮጵያዊነቴም  መሬት ተሰንጥቃ ብትውጠኝ እስከምደሰት ድረስ እጅጉን አፈርኩ፡፡ ‹ምነው ሞቴን ከመለስ በፊት ባደረግኸው!› ብዬም ከምር ተቆጨሁ – ልብ አድርጉ ቁጭት ነው፡፡ ከነማን ጋር ተቆጥረን 80 ይሁን 90 ሚሊዮን ሕዝብ እንደሆንም ግራ ገባኝ፤ ያቺ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር 500 ነው ያለችዋ የልዑላን ቤተሰብ የነበረች ልዕልት ማንትሲት አሁን በሕይወት ብትኖር ስንት ታደርገን ይሆን ብዬ የኋሊት አንድ አራት አሠርት ዓመታትን በብርሃን ፍጥነት ተጓዝኩ፡፡

ከነዚህ ዘፋኞች ጥቂቶቹን በትናንትና ማታው የኢቢኤስ የካሣሾው ዝግጅት ላይ ከሰውነት ክፍላቸው ዐይናቸው ሁሉ ሳይቀር በጥቁር መነጽር የሀዘን ዐይነርግብ አዝኖና ተክዞ አንዳንዶቹ በዕንባ እየታጠቡና እየተንሰቀሰቁ፣ አንዳንዶቹ እንደምንም ተጽናንተው ሀዘኑ በረድ ብሎላቸው ስለጠቅላይ ሚኒስትራቸው ገድል የማያውቁትን ሲዘላብዱ – በጨዋ አማርኛ ሲናገሩ ሰምቻቼዋለሁ – ማናት ያቺ – ትግስት ወዮሳ የምትባለዋማ ተንፈቅፍቃ ልትሞት ነበር፡፡ እንዴት እንዳየችውና ምን ስትልም እንዳየችው አልገባኝም ‹መለስ እኮ በሥራ ብዛት ቀበቶ እንኳን የማያደርግ ነበር፤ ለአለባበሱ ግድ የሌለው ለእኛ ሕይወት ብቻ ሌት ተቀን የሚጨነቅ፣ የራሱን ሕይወት ሳይኖር ያለፈ የጀግኖች ጀግና ነው…› ስትል ስሰማት በተለይ የግንዛቤ መቋጠሪያ ሥልቷ አስደነቀኝና እኔም ከእንግዲህ የቀዳማዊ እመቤቶችን መቀነት አዋዋል ለመታዘብ ቃል ገባሁ፡፡ ኢቢኤስ እሚሉት ጣቢያ ግን ከእውነት የማን ነው? የአዜብ መስፍን ይሆን እንዴ?

ንዋይ ልክ እንደ ‹ጥቅምት አበባ›ውና እንደ ‹ማዕበል ነው ፍቅሯ› የራፕ ሥልት የቁም ንባብ ዘፈኑ በስሜት እየደነፋ ለአባባ መለስ ሲዘፍን አንጀቴን በላው – ሶሎሞን ተካልኝም ለአፍታ በጭንቅላቴ ብቅ ብሎ ጠፋ፤ የሱስ ዘፈን እንዴት ያለ ይሆን፤ መቼም ልምምዱን ጨርሶ ሊመደርከው ሳይቃረብ አይቀርም፡፡ የአባባ ታምራት ቅምጥ እንደነበረች በከተማው የምትታማዋ ፍቅራዲስ ነቅዓጥበብ ደግሞ በዚሁ የኅብረት ዘፈን ውስጥ ላባባ ታምራት ‹የሐሙሱ ፈረስ …የልብ ሲያደርስ(?)› እያለች ባቀነቀነችበት የድምጽ ሞገድ ለመለስ ስታስገመግም ስሰማት አሁንም ለዚች ደንቆሮ አሻንጉሊት አንጀቴ ተላወሰላት – የኔ ነገር – የአሻንጉሊት ደንቆሮ እንጂ አድማጭ ዱሮውንስ የት አለና ነው እንዲህ ማለቴ? ሌሎች ደናቁርትና ሆዳም ሶሎሞን ተካልኞችና ንዋይ ደበበዎችም አሉበት በዚህ ዘፈን፤ የሽማግሌ ነገር ሆኖብኝ ልለያቸው ግን አልቻልሁም፡፡ ይሄኔ እኔንም ጨነቀኝ – እኔስ ምን ላድርግ አልኩና አሰብኩ፡፡ ዘፋኝ አይደለሁ አልዘፍንለት፤ አልቃሽ አይደለሁ አላስለቅስለት፡፡ ሯጭ አይደለሁ በስሙ ሙሉ ወይ ግማሽ ማራቶን አልሮጥለት፡፡ እንዲሁ ዝም ብዬ ግን ምድር ትቅለልህ አልኩ፡፡ አይበቃኝም? ይሄውም ሲበዛበት ነው፡፡

የመለስ ዘመን በርግጥም ለዘፋኝና ለሯጭ ነበር የሆነው፡፡ ዘፋኝ ስል ደግሞ ለነንዋይ ዓይነቱና ለነ‹መራኝ እጄን ይዞ› ዓይነቷ እዚህ ግባ የሚባል ማኅበረሰባዊ ረብ ለሌላቸው የቁራ ጩኸቶች እንጂ እንደነጥቂቶች የምንሳሳላቸው ሕዝባዊ አርቲስቶች ያለውን አይደለም፡፡ እነዚህን መሰሎቹ የሕዝብ አለኝታዎች በዚህ ዓይነቱ ቅሌት አይገቡም – ከዚህ ዓይነት ሀዘንም ይጠብቀን፡፡ ወያኔ እያስገደደ የማያስደርገው ነገር ስለሌለ ምን ይታወቃል ከዚሁ ጉደኛ መስከረም በፊት ይህን መሰል ጉድ እንዳያሰማን እነሱም መጠንቀቅ እኛም አጥብቀን መጸለይ ነው፡፡ ማን ያውቃል – በረከት ስምዖን ግጥምና ዜማ ደርሶ – ደራሲስ አይደል? – አሁን ጫፍ ጫፉን እንደምንሰማው ቴዲ አፍሮን ዝፈንልን አለበለዚያ ‹ባለፈው የጊዮርጊስ ዕለት በመኪና ገጭተህ ገድለኸው ባመለጥከው ወንጀል ቃሊቲ እንወረውርሃለን› ቢለውስ? ኢትዮጵያ ውስጥ የማይታይ መንግሥታዊ ወንጀልና የማፊያ ሥራ የለም፡፡ ዕንቁ ልጃችንን ከዚህ ይሠውርልን፡፡ ብዙ የገሙ ዕንቁላሎች ስላሉን ከዚህ በኋላ ለመክሰር ብዙ አቅም የለንም፡፡ ደግሞም ባለጥቂት ዐይና ማኅበረሰብ በአፈር አይጫወትም፡፡

እንዲያው ግን ለመዝፈንና ለመሮጥ አንጎል አያስፈልግም ማለት ይሆን? እንዴ፣ ‹ከሩጫ ትራክ በቀጥታ ወደ ቤተ መንግሥት አቀናለሁ› የሚል ሯጭም አለ ሲሉ ሰምቼ ‹ምንኛ ቢንቀን ይሆን? ለካንስ ‹አንበሣ ሲያረጅ የሯጭ መጫወቻ ይሆናል› የተባለው ብሂል እውነት ነው አልኩኝ በሆዴ፡፡ የመለስን እልቅሶ በሚመለከት ግና ሰውን ሁሉ ምን እየነካው ይሆን እንዲህ በቁሙ እየተበከለና እየተበለሻሸ ያለው? ኤዲያ! አሽቃባጭ ሁላ! ‹ሲነጋ ለማፈር› ይሉ ነበር ሴት አያቴ፡፡ አሁንም እንደዚያው ነው፡፡ ዛሬ አንጎሉን ባለመጠቀም በዚህ አውሬ ሰውዬ ሞት ያለቀሰና ያስለቀሰ፣ ጥቁር የለበሰና ያስለበሰ፣ ድንኳን የተከለና ያስተከለ፣ ዳስ የጣለና ያስጣለ፣ ሙሾ ያወረደና ያስወረደ፣ የመንግሥትን ሥራ ለሣምንታት የበደለና እንዲበደል ያስደረገ ወይም ያደረገ፣ … በነጻነት ቀን ይገባበትን ቀዳዳ ያጣል – ላጠፋው ጥፋትም የቀባጭ ምሱን ተመጣጣኝ ቅጣት ያገኛል፤ በሀፍረትና በቁጭትም ይሸማቀቃል፤ ከምላሴ ጠጉር ይነቀል – ይህ አውን እንደሚሆን መጠራጠር አይገባም፡፡ እየተሠራ ያለው ሥራ  በሰው ብቻ አይደለምና!
ለማንኛውም ቲያትሩ ላልተወሰነ ጊዜ ይቀጥላል፡፡ እኛም በነጻ ይህን የክፍለ ዘመኑን – የሚሌንየሙን ልበለው- ዕፁብ ድንቅ የበሬ ወለደ ድራማ በነጻ – በውሸት ጊዜያዊ ንግሥና ምክንያት አንዳንዶቻችን በንዴት የጨጓራና የደም ግፊት በሽታዎችን እየሸመትን – መኮምኮማችንን እንቀጥላለን፡፡

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከሞላ ጎደል በተለይ የመንግሥት ሥራ ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ለታ አንድ ቀበሌ ድራፍት ልንጠጣ ብንሄድ ‹አቶ መለስ ሳይቀበሩ ምንም ዓይነት አገልግሎት አንሰጥም› አሉንና አፍረን ተመለስን፤ ያ እንደቤተ መንግሥት ጠጅ ቤት ውካታው ጆሮን የሚበሳበት ቤት የተወረረ ከተማ መስሎ ጭር ብሏል – መገናኛ አካባቢ የመኪና ዓመታዊ ምርመራ የሚደረግበት ቢሮ አጠገብ ነውና ከፈለጋችሁ ሂዱና አረጋግጡ፡፡ እንዲህ ዓይነት አስገራሚ ነገር በሀገራችን እየተፈጠረ ነው፡፡ ‹መለስ እስኪቀበር ሁሉም ነገር ለመለስ› የተባለ መፈክር ሀገር ምድሩን እየገዛ ነው፡፡ ይሄ መለስ የሚሉት ሰውዬ እንዴት ያለ ‹መተታም› ኖሯል ልጄ? ደግነቱ እነዚህ ወያኔዎች መለስ እስኪቀበር አትብሉ፣አትጠጡ፣ አትራመዱ፣አትራቡ(መራባት)፣ ጋቢና አንሶላ አትጋፈፉ …  ቢሉን ኖሮ እነአቦይ ስብሃትን ጨምሮ ሁላችን ምን ይውጠን ነበር? ሕዝበ አዳም በውስጥ መመሪያ ጥቁር እንዲለብስና በግዱ እንዲያለቅስ፣ ዕንባ ባይወጣው ሚጥሚጣ፣ ሰናፍጭና ቪክስ የመሳሰሉ አስለቃሽ ንጥረ ነገሮችን በኪስና በቦርሣው እየያዘ በዐይኑ አካባቢ ብን ወይም ጠብ እያደረገ ሲቆጠቁጠው እንዲያለቅስና በቲቪ መስኮት እንዲታይ ተነግሯል – ‹አውነት ቢጋነን ንባብን ያበረታታል እንጂ ጉዳት የለውም› ይሉኝ ነበር ወንድ አያቴ፡፡ ከዚህ ሁሉ ችግር ግን አስለቃሽ ጋዝ አስመጥተው ከተማዋን እንደሕዳር 12 ከዳር እዳር ቢያጥኑት ይሻላል፡፡ ያኔ ሳንወድ በግዳችን የምንወደውም የማንወደውም እናለቅስለታለን፡፡ የአሁኑስ ብዙዎቻችን እያስመሰልን እንጂ ልቅሶው ጉራማይሌ ቢጤ ነው፡፡ እናንተዬ ሙዚቃ ናፈቀኝ እኮ! ዋሽንትና ማሲንቆ ሰለቸኝ፡፡ አንድም ቡና ቤት ዘፈን አይከፍትም፡፡ ቢከፍት አሳር ይደርስበታል፡፡ እስኪ ስለውጭ ሀገር ገጠመኛችሁ ከታች በአስተያየት መስጫው ላይ ንገሩኝ፡- በውጪ ሀገር መሪ ሲሞት ለዚህን ያህል ጊዜ ሕዝቡ ዘፈን እንዳይከፍት፣ ጮክ ብሎ እንዳይስቅ… የሚደረግበት ሀገር አለ? ከሰሜን ኮርያ ሌላ የምታውቁት ካለ ‹ፕሊዝ›(እባካችሁ ለማለት ነው!) ንገሩኝ፡፡ እንግሊዝኛየን እንዳልረሳው ነውና አትዘከሩብኝ፡፡

አቤት አቤት የመለስ ጀብድ ግን! እኔ ያላወቅሁለት ስንትና ስንት ጀብድ ሠርቶ የለም እንዴ? ይህን ሀሉ ሲያከናውን እኔ የት ሄጄ ይሆን? ይሄ ሰላቢ ሰውዬ ሚዲያውን በራሱ ቁጥጥር አድርጎ፣ ወጣቱን በዬፎረሙና በዬአነስተኛና ጥቃቅን የአምራቾች የሥራ ማኅበር አደራጅቶ፣ በዐርከበ ሱቅ ወጣቶችን መስጎ፣ ምሩቃንና ሥራ አጥ ወጣቶችን በኮብል ስቶን አዋቅሮ፣ አእሩግንና ወጣቶችን በየቀበሌው አሰባስቦ በዚህም ሂደት ለልማት ከበጎ አድራጊዎች በብድርና በዕርዳታ የተገኘን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለፖለቲካ ሥራውና ለግላዊ የሙስና ካዝናው አውሎ በመጨረሻ ልቅሶውን አሳመረበት አይደል? የሀገርን ዕዳ ለፖለቲካ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ያደረገ አስተዋይ መሪ የት ይገኛል? ብልኅ አመራርስ ከዚህ በላይ የት አለ? በልማት ላይ ቢውል ድህነትን በተወሰነ ደረጃ መቅረፍ ይችል የነበረ ብዙ ቢሊየን ዶላር በዚህ መልክ ለቀብር ማስፈጸሚያነት መዋሉ ለሀገር ወዳድ ዜጎች በእጅጉ የሚያናድድ ነው፡፡ ግን ምን አማራጭ አለን? ለጊዜው አማራጫችን ማልቀስ ነው … ቢያንስ ቀባሪያችን እስኪቀበር፡፡ ከዚያስ ወዲያ … ከዚያ ወዲያ አለ ነገር፣ አለ ነገር – አቀበቱን ወጥተን እሜዳው ስንገባ… እያሉ መዘመር ነው፡፡ ‹እኛ ምን ቸገረን ግጥማችን ቢያምር ባያምር፤ ለግጥምማ ማማር አዝማሪ አለ አይደለምወይ› ብለዋል ፊታውራሪ መሸሻ በከሸፈው የሰብለና በዛብህ ሠርግ ዋዜማ ላይ፡፡ አይይ… ኢትዮጵያዊ ሆኖ የመፈጠር ዕዳ! ደህና ቀን ናፈቀኝ… ሊነጋ ይሆን ጨለማው በረታሳ!

No comments:

Post a Comment