Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday 3 October 2012

ጉዞ ወደ ለንደን ሚጢጢ ማስታወሻ! ከአቤ ቶኪቻው

በአሁኑ ሰዓት ራሷን “ታላቋ” እያለች መጥራት የሚቀናት “ግሬት ብሪታኒያ” ውስጥ እገኛለሁ። ከሀገሬ ከተሰደድኩ በኋላ እንግሊዝ ሁለተኛዋ መቀመጫዬ ሆነች ማለት ነው። ከዚህ በፊት ለነበሩት አስር ወራት ኬኒያ ናይሮቢ ከጆጎ ቤት ፊት ለፊት ባለው ግቢ ውስጥ እኖር ነበር።
ኬኒያ በርካታ ኮሚክ ነገሮች አሉ። ከፖሊስ እና ሀበሻው አባሮሽ ጀምሮ አስከ ሙስናቸው ድረስ አስማታዊ ክስተቶች ሁሉ እንደመደበኛ ነገር የሚቆጠሩበት ሀገር ኬኒያ ነው። ኬኒያውያን፤ መንግስታቸውን እግዚአብሄር፣ አሜሪካ እና እንግሊዝ ደግፈው ባይዙላቸው ኖሮ በሙስና ጎርፍ ተጥለቅልቀው አጠገባቸው ያለው ህንድ ውቂያኖስ ውስጥ ይሰጥሙ ነበር። ቆይ እዝች ጋ ፍሬን ያዝ እናድርግ ስለ ኬኒያ ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን።
አሁን ስለ ታላቋ እንግሊዝ እናውራ፤ እግረ መንገዳችንንም ከታለቋ ኢትዮጵያ ጋር አንዳንድ ጉዳዮች ላይ እናነፃፅራት ምናባቱ፤ የፈጀውን ይፍጅ…! ፤አንቺም ጠጪ ለኔም ቅጂ ነው ነገሩ…!
እንግሊዝ እንደገባሁ አንድ ኮንዶሚኒየም ህንፃ ላይ አንድ መኝታ ቤት አንድ ሳሎን አንድ ኩሽና… አሃ… ማድቤት ጢስ አልባ ሲሆን ለካ “ኪችን” ነው የሚባለው ስለዚህ እናስተካክል… አንድ ኪችን… አንድ ባኞ ቤት እና አንዲት የእቃ ቤት ያለው ክፍል ተሰጠኝ።
ከኬንያ ስመጣ የራሴን አንድ የሰው ረከቦት እና ከሰል ምድጃ ይዤ ነው የመጣሁት። መቼም ሀበሻ ተሰዶ አይሰደድም። ወደ እንግሊዝ እንደምሄድ የሰሙ አንድ እናት ለንደን ለምትገኝ ልጃቸው ረከቦት እና ከሰል ማንደጃ ሲልኩኝ። ከዚህ በፊት አንድ ሰው፤ “ሀበሻ ሀገሩን ይዞ ነው የሚሰደደው” ብለው የተናገሩት ነው ትዝ ያለኝ። እውነትም በስደት ሀገር የጎበኘኋቸው አበሾች፤ አብዛኛዎቹ ቤታቸው ውስጥ ስገባ ኢትዮጵያ ያለሁ እስኪመስለኝ ድረስ፤ ከጤፍ እንጀራ ጀምሮ ሽሮ ወጥ በቃሪያ ሁሉ አግኝቻለሁ። አረ ያዩትን ሁሉ ማውራት ምንድነው ብዬ እንጂ ለንደን በእንግድነት የተቀበሉኝ ወዳጆቼ ቁርጤን አውቄ የተውኩትን ቁርጥ እና ከየት ይምጣል ብዬ የተውኩትን የዶሮ አይን የመሰለ ጠላም አጠጥተውኛል። ሀገርን ይዞ መሰደድ ታድያ ይሄ አይደል!?

እናልዎ… ከአንዲት ሻንጣ በቀር ምንም አልነበረኝምና እሷኑ ይዤ ሳልመዘገብ የተሰጠኝ ኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ ገባሁ። ደግነቱ የተባረከ የእንግሊዝ መንግስት ሙሉ ዕቃ አሟልቶ ነው ቤቱን የሰጠኝ። የሀገሬ መንግስት “ኪቻ” ብሎ ያስወጣኝን ሰውዬ የሰው ሀገር መንግስት እንዲህ አንቀባሮ የያዘኝ በምን እዳው ነው? ብዬ ብጠይቅ ከአዋቂ ወዳጆቼ መካከል አንዱ “ማንኛውም ሰው መጠለያ የማግኘት መብት አለው” አለኝ። ክበበው ገዳ ቢሰማ…. “ወ….ይ መብት…!” ይለን ነበር…
ቤቱ እንደተሰጠኝ የጠቅላዩ ለቅሶ ላይ በኢቲቪ “መለሰ ኮንዶሚኒየም ቤት ሰጥቶ አንቀባሮኛል…” ብለው ደረት ሲመቱ የነበሩት እናት ናቸው ትውስ ያሉኝ። እሳቸው ተመዝግበው እና ስንት አመት ጠብቀው በዕጣ ላገኙት ቤት ውለታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሞቱ እንዲያ ደረት ከመቱ፤ እኔ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሞቱ ከአስረኛ ፎቅ ላይ መፈጥፈጥ አለብኝ ማለት ነው።
ለማንኛውም አሁን ከምኖርባት ማንችስተር ከተማ ወደ ለንደን እየሄድኩ ነው። ኢሳት ላለው ዝግጅት እግዜር ያክብራቸውና አክብረው የጋበዙኝ ወዳጆቼ “ኤክስፕረስ በተባለ አውቶብስ ሀገሩን እያየህ ና” ብለው ትኬት ቆርጠውልኛል።
አውቶብሱ እኔ ከምኖርባት ሰፈር ሲነሳ እኔን ጨምሮ ሰው 4 ሰዎችን ብቻ ነበር ያሳፈረው። ደነቀኝ እኛ ሀገር እንኳንስ ወደ ክፍለሀገር የሚሄድ አውቶብስ ይቅርና ከሽሮሜዳ አራት ኪሎ የሚሄድ ታክሲ ነዳጅ ባይሞላ ግድ የለውም። ሰው ካልሞላ ግን አይንቀሳቀስም። እናም አውቶብሱ አራት ሰው ይዞ ጉዞ መጀመሩ ተዓምር ሆነብኝ።
መንገዴ ላይ የጎተራውን ማሳለጫ የሚመስሉ በርካታ ድልድዮች አለፍን። የድልድዮቹ ስር ለመኝታ ምቹ መጠለያ አለው። ይሄኔ የሀገሬ ጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ትዝ አሉኝ። ፒያሳ ጋ “ባርች እስቲ የሚስቀውን ስጠኝና አስቀኝ…” ብለው አንድ ብር እየለመኑ እኔኑ የሚያስቁኝ ጨዋታ አዋቂዎች፤ በነገራችን ላይ የጎዳና ተዳዳሪ “ጀለሶቼ” ከማስባቸውም በላይ ጨዋታ አዋቂ እንደሆኑ ግንዛቤ ያገኘሁት ያኔ በቤተ መንግስት ግቢ ለቅሶ ሲደርሱ “እሳቸውን ተማምነን ነበር ጎዳና የወጣነው ከእንግዲህማ ወደቤት እንመለሳለን እንጂ… ምን ዋጋ አለን!?” ያሉ ግዜ ነው። ስብሀት ገብረ እግዚአብሔር አንጀት ጠብ የሚል ቀልድ ሲሰማ “ነብሴ ናትኮ…!” ይል ነበር። ነብሶቼ ባላችሁበት ይመቻችሁ እላችኋለሁ።
እዚህ አገር የማሳለጫው ስር ለማደር ምቹ ቢሆንም አንድም የጎዳና ተዳዳሪ አላየሁበትም። በሀሳቤ እዚህ ያሉ ወጣቶች በጠቅላይ ሚኒስትራቸው አይተማመኑም ማለት ነው። ስል አሰብኩ።
የተሳፈርኩበት፤ ኤክስፕረስ ባስ በሀገራችን ካለው “ሰላም ባስ” ጋር የሚመሳሰል ነገር አለው። ልዩነቱ ሰላም ባስ ሹፌሩ እና ሁለት ረዳቶቹን ጨምሮ ሶስት ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በኤክስፕረስ ግን ስራውን የሚሰራው ሹፌሩ ብቻውን ነው። አንድም ረዳት አላየሁም። እንኳን ሌላ ቀርቶ “አቡነ አረጋዊ ይርዱኝ” የሚል ፅሁፍም አልተመለከትኩም። እርግጥ ነው አንዳንድ ውስብስብ የከተማ አካባቢዎች ላይ “ወደ ቀኝ፣ ወደ ግራ፣ የመጀመሪያውን መንገድ ያዝ ኋላ ጉድ እንዳትሆን…” እያለች በድምፅ ብቻ የምትመክረው ሴትዮ ሰምቻለሁ። እንደኔ የዋህ ለሆነ ሰው ውቃቢ አምላኩ አፍ አውጥታ የምትመራው ሊመስለው ይችላል። ለነቄዎቹ ግን “ጂፒኤስ” የተሰኘች ቴክኖሎጂ እንደሆነች ይገባቸዋል።
ሰላም ባስ ወደ ጎንደርም ይሂድ ወደ ደንቢዶሎም ይሂድ ወደ ትግራይም ይሂድ የስራ ቋንቋው ትግርኛ ሲሆን በኤክስፕረስ ባስ ውስጥ ግን የስራ ቋንቋ ፍሬን፣ ፊሲዮን፣ እና መሪ መዘወር ነው።
በመንገዴ ላይ በርካታ የእንግሊዝን ገጠር መንደሮች ተመለከትኩ። ከፊት ሊፊታቸው ሰፋፊ ማሳ እና የግጦሽ መሬት ይታየኛል። መስኩ አረንጓዴ ምንጣፍ ይመስላል። በምንጣፉ ላይ የምመለከታቸው በሬዎች ተጠምዶ ለማረስ ተነሳሽነቱም፣ ልምዱም እንደሌላቸው ያስታውቃሉ። ስራቸው ያለ ሀሳብ ሳር መጋጥ ብቻ መሆኑን አይቼ ለሀገሬ በሬዎች አዘንኩላቸው። እኛ ሀገር ያለው በሬ በመስክ ላይ ሲግጥ እንኳ፤ “ከአሁን አሁን መጥተው ጠመዱኝ” በሚል መሳቀቅ ነው።
በእውነቱ ለስንቱ እንስሳት መብት ተከራካሪ ሲመጣ ለበሬ በተለይም ለኢትዮጵያ በሬ የሚቆረቆር መጥፋቱ አሳዛኝ ነው። ለነገሩ እኛ ሀገር እንኳን በሪያችን እኛ ራሳችን መጠመድ ብርቃችን አይደለም።
አብዛኞቹ የኢህአዴግ ታጋዮች በግብርና ከተሰማሩ ቤተሰቦች የተገኙ እንደሆኑ ደጋግመው ነግረውናል። እናም በሬ በመጥመድ ቤተሰቦቻቸውን ያግዙ እንደነበረም ሰምተናል። እኛም ቤተሰቡን የሚረዳ የተባረከ ነው ብለን… ስናመሰግናቸው ኖረናል።
ችግሩ ግን፤ እኒህ የቀድሞ በሬ ጠማጆች ትግል ሜዳ ገብተው፣ ደርግን ከደመሰሱ በኋላ፤ በእርፍ ምትክ ስልጣን ጨብጠው ቀንበሩን እኛው ላይ ጭነው እኛን መጥመድ ጀምረዋል። ደሞ መጥመድ ብቻ በሆነ፤ አለንጋም አለ… አለንጋ ብቻም ደግሞ በሆነ፤ አታጩኸ መባልም አለ።
ታድያ አንዳንድ ወገኖች አረ ጎበዝ ሰልጠን እንበል እና ከመጥመድ እና መጠመድ ነፃ የሆነ ኑሮ እንኑር እንጂ እያሉ እየመከሩ ይገኛሉ። አንዳንዶችን የመሰለ መካሪ ከወዴት ይገኛል!? አይሉልኝም!
ለማንኛውም ወደ ለንደን እየሄድኩ ነው። በመንገዴ ላይ የማያቸውን የገጠር መንደሮች አይቼ አልጠገብኳቸውም። ወደ ገበሬው ጎጆ የሚሄዱ ቀጫጭን አስፋልት መንገዶች ተመልክቼ ተከዝኩ… ወደ ኢትዮጵያ ገበሬ ቤት የሚሄዱ ቀጫጭን አስፋልት መንገዶች የሉም። በምትኩ ግን ቀጫጭን የመንግስት ከድሬዎች በእያንዳንዱ ገበሬ ደጃፍ ይሄዳሉ። ሄደውም ቀጫጭን ትዕዛዞችን በየጊዜው ያስተላልፋሉ።
የእንግሊዝ ገበሬ ቤቶች በከተማ ካየኋቸው ቤቶች በላይ ያማሩ፤ በሸክላ የተሰሩ ቪላ ቤቶች ናቸው። እነዚህ ገበሬዎች ስንት ጊዜ የጀግና አርሶ አደር ሽልማት እንደተሰጣቸው መረጃ አላገኘሁም።
እኛ ሀገር ቢሆን ኖሮ ሸክላ ቪላ መስራት ቀርቶ በአዲስ የቻይና ቢላ ሽንኩርት መክተፍ ራሱ እንደ ትልቅ ውጤት ተቆጥሮ ለሽልማት እንደሚያበቃ አይተናል። እዚህ ላይ አንድ መረሳት የሌለበት ነገር አለ። ለአርሶ አደር፣ ለላብ አድር፣ እና ለጦም አደር ግለሰቦች ሁሉ በየጊዜው መሸለም ታላቅ ጠቀሜታ አለው። ይሄንን ለማረጋገጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ለቅሶ አንድ አፍታ ከዩቲዩብ ላይ ፈለግ አድርጎ ማየት በቂ ነው።
አሁን ለንደን ከተማ ገባሁ። የታላቋ ብሪታኒያ ውብ እና ትልቅ ከተማ። የታላቋ ኢትዮጵያ ልጆች እነ ቲኬ ገላና በማራቶን ድል ታላቅነታችንን ያስመሰከሩባት እነ መሰረት ደፋር ማነው የሚደፍረን ያሉባት እነ ጥሩነሽ ዲባባ ጥሩነታቸውን ያስመሰከሩባት ለንደን።
ትንሽ ቀደም ብል ባንዲራ ለብሼ አትሌቶቻችንን ስደግፍ ታዩኝ ነበር። ለነገሩ ምን ቢፈጥኑ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ መድረስ እንደምን ይቻላል? ልክ ይሄንን ሳስብ ኢትዮጵያዬ እንደምን ብትፈጥን ይሆን እንግሊዝ ላይ የምትደርሰው? የሚል ጥያቄ አቃጨለብኝ… ወድያውም ፍቅር ፐር ሰከንድ፣ መዋደድ ፐር ሚኒት፣ ስምምነት ፐር ታይም፣ ህብረት ፐር ዴይ… ስል ፈረንጅ መንፈስ እንዳደረበት ሰው አነበነብኩ!

No comments:

Post a Comment