Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday, 30 September 2012

የታላቁ ሩጫ ሀብትና ንብረት ሊወረስ ነው

‹‹ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየተደራደርን ነው››  አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ
በዮሐንስ አንበርብር
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ (Great Ethiopia Run) ላለፉት 12 ዓመታት በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልልሎች የጎዳና ላይ ሩጫ ለተለያዩ ዓላማዎች በማካሄድ ያገኘው ሀብት ሕገወጥና ከተመሠረተበት ዓላማ ውጪ ነው ተብሎ ሊወረስ ነው፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴና ጓደኞቹ የተመሠረተ ሲሆን፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በመሆንም ከ12 ዓመታት በፊተ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር ተመዝግቦ ዕውቅና አግኝቷል፡፡

ከተመሠረተ ጀምሮ በየዓመቱ በአዲስ አበባ ላይ የ10 ሺሕ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ  በማከናውን የበለጠ ትኩረትን ያገኘው ታላቁ ሩጫ፣ በአዲሱ የበጎ አድራጎት አዋጅ መሠረትም ተመዝግቦ ዕውቅና አግኝቷል፡፡

ይሁን እንጂ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ ባካሄደው የኦዲት  ሥራ ታላቁ ሩጫ የበጎ አድራጎት ሥራ ለመሰማራት ፈቃድ ቢሰጠውም ተግባሩ ግን ከተመዘገበበት ዓላማ ውጪ መሆኑን፣ በአትራፊ ድርጅትነት ሲንቀሳቀስ መገኘቱንና ከዚህም መንግሥት ተገቢውን ጥቅም አለማግኘቱን ለመረዳት እንደተቻለ፣ የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ሒደት ባለቤት  አቶ አሰፋ ተስፋዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአብዛኛው አትራፊ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየው ታላቁ ሩጫ፣ አልፎ አልፎም የበጐ አድራጐት ተግባራትን ያከናውን እንደነበረ አቶ አሰፋ ይናገራሉ፡፡  ከዚህም ውስጥ ሜሪ ጆይና አበበች ጐበና የተባሉ የበጐ አድራጐት ድርጅቶች ከታላቁ ሩጫ የገንዘብ ልገሳ አግኝተው እንደሚያውቁ አስረድተዋል፡፡

ኤጀንሲው የታላቁ ሩጫን ሕገወጥ እንቅስቃሴ በተረዳበት ወቅት የድርጅቱን ኃላፊዎች በመጥራት ማነጋገሩን ታላቁ ሩጫ በበጐ አድራጎት ድርጅትና የተመዘገበው በፍፁም የዋህነት እንደሆነና ምንም ዓይነት የማጭበርበር ተግባር ለመፈጸም እንዳልነበረ ለመረዳት እንደተቻለ፣ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ሒደት ባለቤቱ ተናግረዋል፡፡

አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴም ይህንኑ ሁኔታ ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡ “ታላቁ ሩጫን ለመመሥረት በመጀመሪያ የሄድነው ይመለከታቸዋል ብለን ካሰብናቸው ፈቃድ ሰጪ የመንግሥት ድርጅቶች ዘንድ ነበር፡፡ እንደ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የመሳሰሉት ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ ድርጅቶች ተገቢውን ትብብር ማግኘት አልቻልንም፤” በማለት ኃይሌ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል፡፡

“በመጨረሻ የነበረን አማራጭም በአትራፊ ድርጅትነት ለመሥራት ካልተፈቀደልን ለትርፍ ያልተቋቋመ የበጐ አድራጐት ድርጅት ሆነን መሥራት የመጨረሻ አማራጫችን በመሆኑ ነው ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር አምርተን ፈቃዱን ያገኘነው፤” ሲል አትሌት ኃይሌ ገልጿል፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴር  በበጎ አድራጎት ድርጅትነት ከመዘገበውና ፈቃድ ከሰጠው በኋላ ዓመታዊ የጐዳና ላይ ሩጫ ማዘጋጀት የጀመረው ታላቁ ሩጫ፣ ከተለያዩ ግዙፍ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ የስፖንሰር ድጋፍ ያገኝ የነበረ መሆኑ በግልጽ የሚታወቅ ሲሆን፣ ፍትሕ ሚኒስቴር ግን አንድም ቀን የታላቁ ሩጫን ተግባር ከሕግ አግባብ በመፈተሽ ችግሮችን ለመለየት አልሞከረም፡፡

በአዲሱ አዋጅ መሠረትም በበጐ አድራጐትና ማኅበራት ኤጀንሲ በድጋሚ ሲመዘገብም ምንም ዓይነት እክል አልገጠመውም፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የሥራ ሒደት ባለቤቱን ‹‹ለምን?›› ያልናቸው ሲሆን፣ የሰጡት ምላሽም አጭርና “በወቅቱ ሁላችንም ለሥራው አዲስ ነበርን፤” የሚል ነው፡፡

በአዲሱ የበጐ አድራጐትና ማኅበራት አዋጅ መሠረት አዋጁን በመጣስ እንቅስቃሴ ውስጥ የተገኙ ድርጅቶች እንዲዘጉ ሲወሰንባቸው፣ ሀብትና ንብረታቸውም ተወርሶ በበጐ አድራጐት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ተመሳሳይ ተቋማት እንዲከፋፈል ይደረጋል፡፡ አሊያም መንግሥት ኅብረተሰቡን ለሚጠቅም የልማት ሥራ ያውለዋል፡፡

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታም በዚህ ሕግ የሚወሰን ቢሆንም፣ በአገር ገጽታ ግንባታ ላይ ባደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ግን የተለየ አስተያየት ተደርጐለታል፡፡

ከዚህም መካከል ድርጅቱን በአፋጣኝ ከመዝጋት በመቆጠብ ወደ አትራፊ ድርጅትነት ወይም በተለየ አወቃቀር እንዲደራጅና ከሌላ የመንግሥት አካል ፈቃድ እንዲወስድ ቀነ ገደብ ተሰጥቶታል፡፡

በመሆኑም እ.ኤ.አ. እስከ ዲሴምበር 2012 መጨረሻ ድረስ አሁን ያለው ሕጋዊ ሰውነት የሚጠበቅለት ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ግን ከኤጀንሲው መዝገብ እንደሚሰረዝና ሀብትና ንብረቱም ተወርሶ በሕጉ መሠረት እንደሚስተናገድ አቶ አሰፋ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

በባንክ ያለው ገንዘብ ተጣርቶ አሥር ሚሊዮን ብር እንዳለው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ሌሎች ተንቀሳቃሽና ቋሚ ንብረቶችም ተመዝግበዋል ያሉት ኃላፊው፣ እስከተሰጠው ቀነ ገደብ ድረስ የሚያገኘውን ሌሎች ገቢዎች ጨምሮ ለኤጀንሲው እንዲያስረክብ  መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ ካልሆነ ግን ኤጀንሲው ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ አቶ አሰፋ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከስፖርት ኮሚሽንና ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር ውድድሩን ማስቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከመግባባት ተደርሷል ያለው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ የታላቁ ሩጫን ሀብትና ንብረትን በተመለከተ ግን ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

“አንድ ቀን ስፖንሰሮችን ብናጣ ሩጫው መቋረጥ የለበትም በሚል እሳቤ ያስቀመጥነው ሀብትና ንብረት አለ፤ ይህ ሀብት ተወርሶ ታላቁ ሩጫን ማስቀጠል አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ የለፋንበትን ታላቁ ሩጫን በገንዘብ እንደመግዛት ይሆንብኛል፤” ሲል ይህ እንዳይከሰትና ታላቁ ሩጫ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ኃይሌ ምኞቱን ገልጿል፡፡

No comments:

Post a Comment