Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday 7 October 2012

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩት አቶ ከፍያለው አዘዘ ኮበለሉ

በውድነህ ዘነበ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የነበሩት አቶ ከፍያለው አዘዘ አሜሪካ ሄደው ሳይመለሱ መቅረታቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡
አቶ ከፍያለው ከወራት በፊት ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ ኔትወርክ በመዘርጋት ሥራዎች በአግባቡ እንዲካሄድ አድርገዋል በሚል ከምክትል ከንቲባነት ተነስተው የከንቲባ ኩማ ደመቅሳ የውጭ ግንኙነት አማካሪ ሆነው ተሾመው ነበር፡፡ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ አቶ ከፍያለው ከነበራቸው ኃላፊነት ዝቅ በመደረጋቸው ይበሳጩ ነበር፡፡

አቶ ከፍያለው ምክትል ከንቲባ እያሉ የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙኅን ኤጀንሲ ሊገነባ ላቀደው አዲስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዕቃዎችን ለመምረጥ ከባልደረቦቻቸው ጋር አሜሪካ ተጉዘው ነበር፡፡ በወቅቱ አቶ ከፍያለውና የሚመሩት ልዑክ ከ15 ቀናት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ አገሩ ሲመለስ፣ የመገናኛ ብዙኅን ኤጀንሲ አንድ ቴክኒሻን ሳትመለስ ቀርታለች፡፡ አቶ ከፍያለው ከአሜሪካ ከተመለሱ ከጥቂት ወራት ቆይታ በኋላ ከምክትል ከንቲባነታቸው ተነስተዋል፡፡

ከዚህ ጊዜ በኋላ አቶ ከፍያለው ከደረጃቸው ዝቅ መደረጋቸው ሲያብሰለስላቸው በነበረበት ወቅት ድንገት የመገናኛ ብዙኅን ኤጀንሲ ለሚገነባው የቴሌቪዥን ጣቢያ ተጨማሪ ዕቃ ለመግዛት ለዱባይ ጉዞ አዘጋጀ፡፡ አቶ ከፍያለው ወደ ዱባይ የሚጓዘው ቡድን አካል ሆነው ዱባይ የተጓዙ ሲሆን፣ ቡድኑ ሥራውን አጠናቆ አዲስ አበባ ሲመለስ አቶ ከፍያለው በዱባይ አድርገው አሜሪካ ገብተዋል፡፡

አቶ ከፍያለው አሜሪካ መቅረታቸውን የተረዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቶ ከፍያለው ሲገለገሉበት የቆዩትን ተሽከርካሪ ተረክቧል፡፡ ምንጮች እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው የአቶ ከፍያለው ሾፌር የሆኑትን አቶ ደምስ አሰፋን በጉዳዩ ዙርያ ማነጋገራቸው ተሰምቷል፡፡ ‹‹ከፍያለው ሲሄድ ለምን አልተናገርክም?›› ሲሉ አቶ አባተ ለአቶ ደምስ ጥያቄ ማቅረባቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡


በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ ደምሴ ስለአለቆች መሄድና መምጣት መከታተል የእሳቸው ሥራ እንዳልሆነ መግለጻቸው ታውቋል፡፡ አቶ ደምሴ ባለፉት 20 ዓመታት በሾፌርነት ሲሠሩ እንደዚህ ዓይነት ነገር አጋጥሟቸው አያውቅም ሲሉ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች ጨምረው እንደገለጹት፣ የአቶ ደምስ ምላሽ ያበሳጫቸው አቶ አባተ፣ የሾፌሩ ጉዳይ በዲስፒሊን ኮሚቴ እንዲታይ ሊያደርጉ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ አቶ ደምሴ መኪናውን ካስረከቡበት ጊዜ ጀምሮ ግን ያለ ሥራ መቀመጣቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ ከፍያለው ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሬዲዮ በጋዜጠኝነት፣ በፕሬስ ድርጅት ደግሞ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሠርተዋል፡፡ የአቶ ኩማ ደመቅሳ አስተዳደር ሥልጣኑን ከባለአደራው አስተዳደር ሲረከብ አቶ ከፍያለው ከፕሬስ ድርጅት በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር በመሄድ ምክትል ከንቲባ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment