ሚያዚያ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ በፍትህ ፣ በመልካም አስተዳዳር እጦት ና በችጋር ህይወታቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ ነው
የኢሳት የክልል ወኪሎች አጠናክረው የላኩት መረጃ እንደሚያሳየው በተለይ በደቡብ ክልል ከማዳበሪያ እዳ ጋር በተያያዘ፣ በመልካም አስተዳዳር እጦትና የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም የተሳናቸው ዜጎች ራሳቸውን ማጥፋት እንዳማራጭ አድርገው እየተጠቀሙ ነው። በያዝነው ወር ብቻ በዳውሮ ዞን ውስጥ ሁለት አርሶአደሮች የማዳበሪያ እዳ መክፈል ተስኖአቸው ራሳቸውን ያጠፉ ሲሆን በጋሞ ጎፋ ዞንም ወደ 4 የሚጠጉ አርሶ አደሮች በማዳበሪያ እና በምርጥ ዘር እዳ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸማቸው ታውቋል። ራሳቸውን ካጠፉ ሰዎች መካከል አንድ ሴት ራሳቸውን ወደ ገደል ወርውረው ያጠፉበት መንገድ አሰቃቂ መሆኑን የደቡቡ ዘጋቢያችን ገልጧል። በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞን በጩኮ ወረዳ ማንጉዶ ቀበሌ በግብርና ስራ ይተዳዳሩ የነበሩት አቶ ካሚሶ ካያሞ የቀበሌው ሊቀመንበር የይዞታ መሬታቸውን ስለቀማቸው ራሳቸውን ማጥፋታቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም ሙከራ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥርም መበራከቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በትናንትናው እለት መምህር የኔሰው ገብሬ ይኖርበት በነበረው ተርጫ ከተማ ውስጥ አንድ የመንግስት ሰራተኛ ትናንት ዘፋ ላይ ወጥቶ ፍትህ ካልተሰጠኝ ራሴን አጠፋለሁ በማለት ለ13 ሰአት ያክል በዘፍ ላይ ቆይቷል። ቀደም ሲል የዞኑ ፍርድ ቤት የሰው ሀብት ልማት ኦፊሴር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አየለ አባተ የአንድነት ፓርቲ አባል ናቸው በሚል ተጠርጥረው ከስራ እንዲባረሩ ከተደረጉ በሁዋላ ችግራቸውን ለክልል ባለስልጣናት አመልክተው ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ቢደረጉም፣ የዞኑ ባለስልጣናት በበቀል መልክ ለ1 አመት አስረዋቸው በነጻ ፍትተዋቸው ነበር። አቶ አየለም በእስር ቤት እያሉ ለሰብአዊ መብቶች ችግራቸውን ማቅረባቸው በመሰማቱ ለተጨማሪ 6 ወር ታስረው እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የአካባቢው ሰው የአቶ አየለን ድርጊት በአግራሞት ሲከታተል እንደነበር፣ በመጨረሻም በባለስልጣናት ውትወታ ራሱን ከማጥፋት መታቀቡን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጠዋል።
ራሳቸውን የሚያጠፉ ወይም ለማጥፋት የሚሞክሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በመንግስት ታጣቂዎች ያለ ህግ የሚገደሉትም እንዲሁ እየጨመረ ነው። በደቡብ ኦሞ ዞን አርሶ አደር ባዩ ወልድቡ በቀበሌው ሊቀመንበር መገደላቸውን ሰሞኑን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆነው ዘመኑ አዱኛ የተባለ ወጣት የፋሲካን በአል ከቤተሰቦቹ ጋር ለማክበር ወደ ደባርቅ ከተማ በሄደበት ተገድሎአል። ወጣት ዘመኑ ከመገደሉ በፊት ደባርቅ ወረዳ ወጋንባ ኪዳንምረት ቀበሌ ከሚገኙት እናቱ ጋር እያወራ ነበር። የአካባቢው ፖሊሶችና ሚሊሺያዎች ከምሽቱ 2 ሰአት ላይ እንደሚፈልጉት ገልጠውለት፣ ወጣቱም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማምራቱን፣ ከዚያ በሁዋላ ከፍተኛ ደብደባ እንደተፈጸመበት ድብደባውን መቋቋም ሲሳነው ለማምለጥ ሲሞክር በሁለት ጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፎአል። የወጣቱ ሞት እንደተሰማ የቀበሌው ህዝብ ቁጣውን በመግለጡ ፖሊሶቹ አንዱን ሚኒሺ ገዳዩ እርሱ ነው በማለት ለይምሰል ይዘው እንዳሰሩት ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ወጣት ዘመኑ የአሸባሪ ድርጅቶች አባል በመሆን ህዝቡ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ሲቀሰቅስ ነበር የሚል ክስ ቀርቦበት እንደነበር ታውቋል።
በጋምቤላ ባለፈው ማክሰኞ አንድ ወጣት በወታደሮች መገደሉን መዘገባችን ይታወሳል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የመለስ መንግስት ከጊዜ ወደ ጊዜ አገሪቱን ለማስተዳዳር እየተቸገረ ነው። የመንግስት ደጋፊ ተደርገው የሚቆጠሩት ሪፖርትርን የመሳሰሉ ጋዜጦች ሳይቀሩ የፖለቲካ ለውጥ ያስፈልጋል በማለት መጻፍ ጀምረዋል።
No comments:
Post a Comment