- Sunday, 08 April 2012 00:00
- By Asrat Seyoum
ሪፖርተር ጋዜጣ
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን የአንድ ዓመት ጉዞ የገመገመው የዓለም ባንክ፣ እጅግ የተለጠጡ ግቦችን
አንግቦ በመነሳቱ ምክንያት ከባድ የፋይናንስ ችግር እንደገጠመው ማረጋጠጡን ይፋ ባደረገው ረቂቅ አስታወቀ፡፡
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተጠሪ ጉዋንግ ዜ ቼን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ በሁለተኛ ዓመት አፈጻጸሙ ላይ
የሚገኘውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸምን ባንኩ ገምግሞ ለባለድርሻ አካላት አስተያየታቸውን
እንዲሰጡበት ያሰራጨው ረቂቅ ሰነድ እንደሚያረጋግጠው፣ የአውሮፓ የኢኮኖሚ ቀውስን ተከትሎ ከአውሮፓ አገሮች ይገኝ
የነበረው ብድርና ዕርዳታ ቀንሷል፡፡ ይህም በመሆኑ ረቂቅ ሰነዱ ትኩረቱን በፋይናንስ ጉዳዮች ላይ እንዳደረገ
ተገልጿል፡፡
የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በአምስት ዓመታት ውስጥ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን አንድ
ትሪሊዮን ብር ሲሆን፣ ከመንግሥት በጀትና ከተለያዩ ምንጮች የሚፈለገው ይህ አንድ ትሪሊዮን ብር የዕቅዱን ግቦች
ለማጠናቀቂያ በመንግሥት ይፈለጋል፡፡
መንግሥት የገጠመውን የፋይናንስ ችግር ማኬንዚና ኩባንያው ከተባለ
ተቋም ጋር በመሆን ለመፍታት እንደሚጥር የጠቆሙት ሚስተር ቼን፣ ችግሩን ለመፍታት አንዱ እየታየ ያለው መፍትሔ
የአገር ውስጥ ቁጠባን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት እንደሆነ አስረድተው፣ በመረጃዎች ላይ ተመሥርተውም የአገሪቱ የቁጠባ
መጠን ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አኳያ ከአምስት በመቶ እንደማይዘል አመልክተዋል፡፡ በመሆኑም
መንግሥት የውጭና የአገር ውስጥ ቁጠባን ማስፋፋት ከቻለ ለዕቅዱ የሚያስፈልገውን የፋይናንስ መጠን በመጠኑም ቢሆን
በማሟላት የተፈጠረውን ክፍተት ለማጥበብ እንደሚችል ቼን መክረዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥት ሌላው
አማራጭ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በስፋት ማስገባት ነው፡፡ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ባለፉት
ጥቂት ዓመታት ለኢትየጵያ የተሳካላት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የውጭ ካፒታል ፍሰት በተለይ በግብርናና በማዕድን
ዘርፎች ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ እንደሚገኝም አስታውሰዋል፡፡
መንግሥት የፋይናንስ ምንጮችን
ከማፈላለግ ባሻገር በተጨማሪ፣ ወጪ ለመቀነስ የሚያስችሉትን ዕርምጃዎች በመውሰድ በዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ሊያሳካ
የሚችልበትን አማራጭ እያየ ነው ያሉት የዓለም ባንክ ተጠሪው፣ ወጪ ለመቀነስና ወጪ ለመቆጠብ ያስችላሉ ከሚባሉ
ዕርምጃዎች አንዱ ደግሞ፣ አነስተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸውን ግቦች በመምረጥ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር
እንደሚጠበቅበት አስገንዘበዋል፡፡ እያንዳንዱ ግብ የሚጠይቀውን ወጪ በመከፋፈል የበለጠ ተቀናሽ ማድረግ የሚቻልባቸውና
መቆጠብ የሚያስችሉ አማራጮች እየታዩ ናቸው ብለዋል፡፡
መንግሥት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽኑን ዕቅዱን ለማሳካት ከሚወስዳቸው ዕርምጃዎች መካከል በተለይ የበለጠ ወጪ ቆጣቢ መሆን ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባዋል ሲሉ ሚስተር ቼን አስረድተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment