Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday, 8 April 2012

ብልሹ የኤሌክትሪክና የፖለቲካ ትራንስፎርመሮች ተስፋና ራዕይ እያጨለሙ ናቸው

Sunday, 08 April 2012 00:00

ሪፖርተር ጋዜጣ ርእሰ አንቀጽ


የኤሌክትሪክ ኃይልን በማመንጨትና በማሰራጨት ኢትዮጵያ ከፍተኛ ራዕይ ሰንቃለች፡፡ ለአገር ውስጥ በቂና አስተማማኝ ኃይል በማስገኘት ለአጎራባች አገሮችም የኤሌክትሪክ ኃይልን ኤክስፖርት በማድረግ፡፡
ራዕዩን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የማይካድ የሚያኮራ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ጣና በለስ፣ ተከዜ፣ ግልገል ጊቤ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስትና የዓባይ ግድብ ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ከፍተኛ ዕቅድ፣ ከፍተኛ በጀት፣ ከፍተኛ ውሳኔና ርብርብ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ እንኳን ተገነቡ እንጂ ለምን ተገነቡ የሚል ሀቀኛ ዜጋ አይኖርም፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ጉዳይ ግን በማመንጨት ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡ የማሰራጨትና የማከፋፈል ኃላፊነት አለበት፡፡ የመነጨው ኃይል ካልተሰራጨና ካልተከፋፈለ እንዳልተሠራ ይቆጠራል፡፡

ኤሌክትሪክ ለማሰራጨትና ለማከፋፈል ደግሞ ትራንስፎርመሮች ያስፈልጋሉ፡፡ አስተማማኝና በርካታ ትራንስፎርመሮች፡፡ ትራንስፎርመር ከሌለ ኤሌክትሪክ አይሰራጭም፡፡ ዘመናዊ ትራንስፎርመር ከሌለም እየተቃጠለ ያቃጥላል፣ እየጨሰ ያጨሳል እንጂ ኤሌክትሪክ ለሕዝቡ አይደርስም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኃይል ለማሰራጨት የትራንስፎርመር ችግር በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ያለውን ሁኔታ ለማሳያ ያህል ብንወስድ በየጊዜው ኤሌክትሪክ እየጠፋ ነው፡፡ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በቀን ሁለቴና ሦስቴ እየጠፋ ነው፡፡ ሥራም እየተስተጓጎለ ነው፡፡ በቂ ኃይል ስላልመነጨ አይደለም፡፡ በቂ ኃይል አለ፡፡ የሚያሰራጩና የሚያከፋፍሉ አስተማማኝና በርካታ ትራንስፎርመሮች ስለሌሉ ግን የሕዝብን ተስፋ እያጨለሙ ነው፡፡

የኃይል ማመንጫዎች ተገንብተዋል ይባላል፡፡ ምነው የኤሌክትሪክ መጥፋት በዛ ታዲያ? ወደ ውጭ ኤሌክትሪክ ኤክስፖርት እየተደረገም ነው ሊደረግም ነው ይባላል፡፡ አገር ውስጥ ችግር እያለ ለምን ወደ ውጭ መላክና መሸጥ አስፈለገ ታዲያ? አሁንም ግድቦች በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተው እያለ የውኃ እጥረትና የዝናብ መጥፋት ምክንያት ሊሆን ይችላል ወይ? የሚሉና የመሳሰሉት ጥያቄዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ መነጋገሪያ ናቸው፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች መኖርያ ቤቶች ተሠርተው፣ ፋብሪካዎች ተገንብተው በትራንስፎርመር አለመኖር ምክንያት ሥራም ኑሮም አልተጀመረም፡፡ በአንዳንድ አካባቢ እዚህ ግባ የማይባል ትራንስፎርመር አለ፡፡ ነገር ግን ከኤሌክትሪክ አቅም ጋር የማይመጣጠን፣ አቅም የሌለውና ተልካሻ ትራንስፎርመር ይሆንና ሲፈነዳና ሲጨስ ይስተዋላል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ትራንስፎርመሮች ለምን ይገዛሉ? አለማወቅ? ሙስና? አሻጥር? በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ቦታዎች ሁሉም ምክንያት ሆነው ይታያሉ፡፡

ዋናው ቁምነገር ግን የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማሳደግ ያለው ራዕይ ይመሰገናል፡፡ ለዕድገት ተስፋ ይሆናል፡፡ ለሕዝቡ ኃይል ያደርሳሉ የተባሉት ትራንስፎርመሮች አለመኖርና ብልሹ አሠራር ግን ራዕይንና ተስፋን እያጨለሙ ይገኛሉ፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ መስማት የሚፈልገው ከግድቦች ኤሌክትሪክ እየመነጨ ነው የሚባለውን ሳይሆን፣ መኖርያ ቤት ደርሶ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል የኤሌክትሪክ ኃይል ነው፡፡ “የትም ፍጪው ብርሃኑን አምጪው” ነው፡፡

በአገራችን እየታየ ያለው ችግር ግን የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር ችግር ብቻ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ትራንስፎርመር ችግርም እየታየ ነው፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲም እንደ መንግሥትም ለልማት፣ ለፍትሕ፣ ለዲሞክራሲ የቆመና የፀደቀ ሕገ መንግሥት አለኝ ይላል፡፡ አዎን አለ፡፡ አይካድም አለ፡፡ ፍትሕ እንዲነግስ፣ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ድህነት እንዲጠፋ፣ የሚያደርግ ራዕይና ተልዕኮ አለኝ ይላል፡፡ አዎን አለ፡፡ ተጽፎም አይተነዋል፤ ተነግሮም ሰምተነዋል፡፡

ይህ ደግሞ በየጊዜው በየቦታው ለሕዝብ በተግባር መተላለፍና መሰራጨት አለበት፡፡ የፖለቲካ ትራንስፎርመር ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ትራንስፎርመሮቹ ተቋማትና ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ካላመነጩ፣ ካላሰራጩና በተግባር ካላሳዩ ራዕዩ ይበላሻል ይጨልማል፡፡

ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮች በአንዳንድ ቦታ የፖለቲካ ትራንስፎርመሮች ጨርሰው የሉም፡፡ እነሱ በሌሉበት አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ስለ መንግሥት ሐሳብና ፍላጎት የሚያውቀው ነገር የለም፡፡

በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ የፖለቲካ ትራንስፎርመሮች አሉ፤ ነገር ግን የፖለቲካውን ጭነት ሊሸከሙ የማይችሉ በቀላሉ የሚቃጠሉና የሚጨሱ ናቸው፡፡ ተቃጥለው ያቃጥላሉ፤ ጨሰውም ያጨሳሉ፡፡

በአንዳንድ ቦታ ደግሞ ያለመኖራቸው ችግር አይደለም፡፡ የፖለቲካ ትራንስፎርመር ተብለው የተቀመጡ አሉ፡፡ የአቅም ማነስ ችግር የለባቸውም፤ ጭነት በዝቶ ተቃጠሉ ጨሱ የሚባሉ አይደለም፡፡ ችግሩ ትራንስፎርመሮች ነን ብለው ለማስመሰል ይሞክራሉ እንጂ ሥሪታቸውም የትራንስፎርመር አይደለም፡፡ እውነተኛ ትራንስፎርመር መጥቶ ሥራውን እንዳይሠራና ሕዝብን እንዳያገለግል ለማሰናከል ትራንስፎርመር ነን የሚሉ ፀረ ትራንስፎርመሮች ናቸው፡፡

ዋናው ቁምነገር የፖለቲካ ትራንስፎርመር ባለመኖሩ ይሁን፣ በአቅም ማነስ ይሁን፣ አስመሳይ የውሸት ትራንስፎርመሮች በመሆናቸውም ይሁን ፍትሕን፣ ዲሞክራሲንና ልማትን እውን አደርጋለሁ የሚለው ራዕይ በእነዚህ የፖለቲካ ትራንስፎርመሮች ብልሹነት፣ አለመኖርና አስመሳይነት ምክንያት ይጨልማል፡፡

መንግሥት በትኩረትና በአጽንኦት ሊንቀሳቀስበት የሚገባው ጉዳይ ይህ የትራንስፎርመር ጉዳይ ነው፡፡ ኃይል ቢመነጭም ወደየቤቱና ወደየፋብሪካው የሚያሰራጭና የሚያከፋፍል ትራንስፎርመር ከሌለ የሚነግሰው ብርሃን ሳይሆን ጨለማ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለምን ብቁ ትራንስፎርመሮች የሉም? ካሉስ ለምን ደካማና ብልሹ ሆኑ? ለምን ደካማዎችና ብልሹዎች በቢሊዮን ብር ወጪ ተገዙ? ደካማነታቸው ከተረጋገጠ ለምን አልተተኩም? ብልሹዎች ሲቃጠሉ ሀቀኞችና ጠንካራ ትራንስፎርመሮች ለምን ሆን ተብሎ መጋዘን ውስጥ ሲታፈኑና ሲታሸጉ ዝም ይባላል? ብሎ ይፈትሽ፡፡ የፈለገውን ያህል ኃይል ቢመነጭ ቤት ውስጥ ካልገባ ቤቱ ብቻ ሳይሆን ራዕዩም ይጨልማል፡፡

በፖለቲካውም እንደዚሁ ሀቀኛ የፖለቲካ ትራንስፎርመሮች ለምን የሉም? ለምን ደካማና ብልሹ ሆኑ? ሀቀኞች ተገፍተውና ተጥለው ብልሹ የፖለቲካ ትራንስፎርመሮች ተመድበዋል ወይ? ለመሆኑ እውነት ትራንስፎርመሮች ናቸው ወይስ ትራንስፎርመር መሳይ የተቀበሩና የተገጠሙ ፈንጂዎች? ይህን ሁሉ መንግሥት ይፈትሽ፤ አስቸኳይ መፍትሔም ይስጥ፡፡

ብልሹ የኤሌክትሪክና የፖለቲካ ትራንስፎርመሮች ራዕይን እያጨለሙ ናቸው፡፡  

No comments:

Post a Comment