Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Thursday, 20 September 2012

የሃይለማርያም አንገት (ከተስፋዬ ገብረአብ)


ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ፕሬዚዳንት ሆነው በተመረጡ ጊዜ በመከላከያና በሲቪል የህወሃት አባላት ዘንድ አቧራው ጨሶ እንደነበር አስታውሳለሁ። አባላቱ የፖለቲካውን ጨዋታ አልተረዱትም ነበር። በወቅቱ የነጋሶ ሹመት የይስሙላ መሆኑን ማስረዳት፣ ለህወሃት መሪዎች ፈተና ሆኖባቸው ነበር። ህወሃት አሁንም ተመሳሳይ ችግር ገጥሞታል። ምናልባትም በቀጣዩ የሃይል አሰላለፍ የህወሃት የበላይነት እንደተጠበቀ መሆኑን ማሳመን ካልቻሉ መፈንቅለ መንግስት ሊያጋጥም ይችላል።
የህወሃት ሲቪልና የመከላከያ አባላት በአብዛኛው፣ “የኢትዮጵያ ስልጣን ሙሉ በሙሉ ለኛ ይገባል” ብለው ያምናሉ። ለሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የሚሰጡ ሹመቶችን በቀና አይመለከቱም። “አቅም የላቸውም፣ ሰነፎች ናቸው፣ ሌቦች ናቸው” ይሏቸዋል።
እዚህ ላይ እውነት አላቸው።
ህወሃት በአብዛኛው ወደ ስልጣን የሚያመጣቸው፣ ደካሞችን እየመረጠ ነው። አባተ ኪሾን ራስህ ሾመህ፣ አባተ ኪሾን መክሰስ ግን ስላቅ ነው። እያወቅህ ለምን ከአቅሙ በላይ ስልጣን ትሰጠዋለህ?
ከሰሞኑ በተፈጠረው ሁኔታም በህወሃት ካምፖች አካባቢ አለመረጋጋት መስፈኑ እውነት ነው። በአመራሩ ደረጃ፣ “መከላከያ፣ ደህንነት፣ ውጭጉዳይ እና ኢኮኖሚውን ከያዝን ያለችግር መቀጠል እንችላለን” የሚል እምነታቸውን ማሰማን ስለመቻላቸው ግን ከወዲሁ ርግጠኛ መሆን አይቻልም። በሂደት የሃይል ሚዛኑ ሊቀለበስ ይችላል። ከህወሃት ባሻገር ያሉት አባል ድርጅቶች፣ በራሳቸው ጭንቅላት መመራቱን ሊለማመዱ ይችላሉ። መለስ አለመኖሩ ድፍረታቸውን ሊጨምርላቸው ይችላል። የህዝብ እና የአለማቀፉ ህብረተሰብ ግፊት በራሳቸው ማሰብ እንዲጀምሩ ሊያግዛቸው ይችል ይሆናል።
ሃይለማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የበቃው በመለስ ስለተመረጠ ብቻ ነው። ሃይሌ የውሃ ባለሙያ ነው። በአንድ ውሱን ሙያ መሰልጠኑ ለሃገር መሪነት ብቁ አያደርገውም። ፖለቲካም ሙያ ነው። ሙያ ብቻ ሳይሆን ተሰጥኦም ነው። ሃይሌ የህክምና ባለሙያ እንዳልሆነው ሁሉ፣ ለፖለቲካው ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ፕሮፌሰር አስራት ያልተሳካላቸው በወያኔ አፈና ብቻ አይደለም፤ የፖለቲካ ጨዋታውን አሻጥር አላወቁበትም። እየተንደረደሩ ከግንቡ ይጋጩ ነበር። ከባድ ነፋስ ሲመጣ ማጎንበስ ይገባ ይሆናል። መለስ በጣም ጮሌ ነበር። ማጎንበስ ይችልበት ነበር። ምርጫ 97 ጠርጎት ሊሄድ ጫፉ ላይ ሲደርስ፣ አንገቱን ዝቅ አድርጎ አሳለፈው። በርግጥም ተቃዋሚዎችን ለድርድር በመጥራት፣ ከባዱን ማእበል ማሳለፍ ችሎአል። ማእበሉ ካለፈ በሁዋላ፣ ቅንጅቶቹን ሰብስቦ አሰረ።

የሃይለማርያም የግል ባህሪ የኢትዮጵያን ውስብስብ ፖለቲካ ለማስተናገድ አቅሙ ያጥረው ይሆናል። ኢትዮጵያ መሰረቱ በተደላደለ ህግ የምትመራ ሃገር ብትሆን ኖሮ፣ እንኳን ሃይለማርያም፣ ሃይሌ ገብረስላሴም ሊመራት በቻለ ነበር። በዚህ ወቅት ህግ እያነበብክ ብቻ ኢትዮጵያን መምራት አይቻልም።
ሃይለማርያም የመለስን ቢሮ ተረክቦ ስራውን ሲጀምር፣ ከመለስ ጠረጴዛ ላይ ተቆልለው የሚጠብቁት በርካታ ስራዎች አሉ። ተቃዋሚዎች እርቅ እየጠየቁ ነው። የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ አለ። ቀጣዩ ምርጫ እየመጣ ነው። የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ጥያቄ ገና አልተፈታም። የኑሮ ውድነቱ እያሻቀበ ነው። ሙስናው ጣራ ነክቶአል። አበዳሪዎችና ለጋሾች እጅ የመጠምዘዝ ልማዳቸውን አጠናክረው እየመጡ ነው። መለስ አቅዶት የሄደው የግንባታ ስራ ጥናት የጎደለው ቅዠት ይመስላል። የምእራባውያን መሪዎች እና የስለላ ድርጅቶች ስልክ እየደወሉና ቢሮው እየመጡ ጥያቄዎች ያቀርቡለታል። ሃይሌ እንዴት ያስተናግዳቸው ይሆን?
“አንድ ጊዜ ይጠብቁኝ፣ ነገ ይደውሉ እባክዎ?፣ ተመካክሬ ልንገርዎ!” እያለ እስከመቼ ይሸኛቸዋል?
ኤታማዦር ሹሙ እና የደህንነት ዳይሬክተሩ አንዳንድ አስደንጋጭ ድርጊት ሊፈፅሙ ይችላሉ። ስለተፈፀመው ድርጊት ማብራሪያ የሚጠየቀው ግን ሃይለማርያም ይሆናል።
“ትናንት አስር ሰላማዊ ኦጋዴንያን ተገደሉ። ማብራሪያ?” የሚል ጥያቄ?
ሃይለማርያም፣ “ጌታቸው አሰፋን ያነጋግሩ” ማለት አይችልም።
ነገ አንዱ አበዳሪ መጥቶ፣
“የፕሬስ ህጉን ካላሻሻላችሁ፣ ይህን ብድር አንለቀውም” ሊለው ይችላል።
“እስኪ ከበረከት ጋር ተነጋገሩበት” ይሆናል የሃይሌ ምላሽ።
የመለስ ሞት ከተጠበቀው ጊዜ በጣም ቀድሞ በመምጣቱ፣ ተደነጋግረዋል። መለስ ቢሞት ሊያደርጉ ስለሚችሉት ነገር ቀደም ብለው አላሰቡበትም፣ አልተዘጋጁበትም። መለስ ሲሞት ከያቅጣጫው ግፊቱ በረታባቸው። ስለዚህ በዚህ መልኩ ሸፋፍነው አገር እንዳይተራመስባቸው ሞካክረዋል። በሚፈልጉት መልኩ ስልጣናቸውን እስኪያደላድሉ፣ አገሪቱን በኮሚቴ ሊመሩ ወስነዋል። የኮሚቴ ስራ የተሳካ የሚሆነው የኮሚቴው ሰብሳቢ ጠንካራ፣ ተፅእኖ የመፍጠርና የማዳመጥ አቅም ካለው ብቻ ነው። 44 መርፌዎች፣ አንድ ማረሻ አይወጣቸውም።
አገር እንዲህ ሊመራ አይችልምና በዚህ መንገድ ብዙም ሊቀጥሉ አይችሉም። እና ታዲያ የሃይለማርያም እጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ክፉ አልመኝለትም። በተፈጥሮው ጥሩ ሰው ስለሆነ እንዲጎዳ አልሻም። ሆኖም ሃይለማርያም ጭንቀታም እንደመሆኑ፣ ደግና ቀና የሚያስብ እንደመሆኑ፣ በታወቁት ጭንቀት ወለድ በሽታዎች ሊጠቃ ይችላል። እና ሁለት እድሎች ይገጥሙታል። የህወሃት ሰዎች ዳግም አንሰራርተው ራሳቸውን በአዲስ መልክ ማደራጀት ከቻሉ፣ “የአቅም እጥረት” በሚል ሃይሌን ያሰናብቱታል። ካልሆነ እሱ ራሱ የመልቀቂያ ደብዳቤ ለማስገባት ይገደዳል። መጪውን ስምንት አመታት በኮሎኔል መንግስቱ ቢሮ ውስጥ ይቆያል ብዬ ግን አልጠብቅም።
ይህ ኢትዮጵያ ነው። የምኒልክ ዙፋን ቀለሙ ቀይ ነው። አማን ሚካኤል አንዶም፣ ተፈሪ በንቲ፣ ተፈሪ መኮንን፣ እያሱ ሚካኤል፣ አጥናፉ አባተ፣ በዚህ ቀይ አውሬ ተበልተዋል። ሃይለማርያም ብዙም ሳያስብበት እንደ በግ እየተጎተተ አንገቱን ጊሎቲኑ ስር አስገብቶአል። “ጌታን የተቀበለ ሰው ስለሆነ፣ የእየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በላዩ ላይ አድሮ ሃይል ይሆነዋል” ብለው የነገሩኝ ሰዎች አሉ። እውነት ያድርገው! ምናልባት የዚህች አገር የዝንተአለም ችግር በሃይለማርያም በኩል ይወገድ ይሆናል። እግዚአብሄር ሰጠ፣ እግዚአብሄር ነሳ። እግዚአብሄር የተመሰገነ ይሁን። አሜን!

No comments:

Post a Comment