Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Saturday 22 September 2012

“አባይን የደፈረ መሪ” ቤተ መንግስቱን የደፈረ ሕዝብ …………..ከፍኖተ ዘመቻ ነጻነት “እናሸንፋለን” we will win (www)



አባይን የደፈረ መሪየሚለውን ሐረግ የመዘዝኩት ከኢህአዴግ የስብከት ፋይል ውስጥ ነው፡፡ መፈክሩ የእኔም ሆነ የብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ እምነት አይደለም ፡፡ የአቶ መለስ የትግል አጋርና የህወሓት የኋላ ደጀን ተደርገው የሚወደሱት አቦይ ስብሀት ነጋም አባባሉን በፅኑ ይቃወማሉ፡፡አባይን የደፈረው መለስም ኢህአዴግም ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ነውሲሉ ፍርጥም ብለው ተናግረዋል፡፡ በፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ላይ ባንድ ወቅትበአቶ መለስ የሚሸበሩ የአዲስ አበባ ጎዳናዎችበሚል ርዕስ ጥቂት ነገሮችን ጫጭሬ ነበር፡፡ አቶ መለስ ከቤተ መንግስትና በተለይም ለስራ ከሀገር ሲወጡና ሲገቡ ከቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ እስከ ምኒሊክ ቤተመንግስት ያለው ጎዳና ሽብር አያጣውም፡፡



በየጎዳናው የሚንቀሳቀሱ ዜጎችና ተሸከርካሪዎች እሳቸው እስኪያልፉ መግቢያ ይጠፋቸዋል፡፡ ወከባና እንግልቱ ሲታይአቶ መለስ መሪያችን ወይስ ደመኛችን?” ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ እኒህ አባይን መድፈራቸው እንደ ውዳሴ ማርያም የሚደገምላቸው አቶ መለስ በሚመሩት ህዝብ መሀከል ሥርዓት ባለው እጀባ ለመንቀሳቀስ መድፈር ለምን ተሳናቸው? ላለፉት 21 ዓመታት የማያምኑትን ህዝብ ሲመሩ እንደቆዩ ዓይነት ይሰማኝ ነበር፡፡ የልጅነት ዘመን ወዘናቸውን ለበረሀ ገብረው ነፃ ባወጡት ህዝብ መሀከል በነፃነት ለመመላለስ ከተቸገሩ ከመሞታቸው አስቀድመው ራሳቸውን ነፃ ማውጣት ነበረባቸው፡፡ 17 ዓመታትን በረሀ 21 ዓመታትን በምኒሊክ ቤተመንግስት ያሳለፉት አቶ መለስ ለሥልጣን ባርነት ተገዝተው የነባራዊውን ዓለም እውነተኛ ህይወት ሳያጣጥሙ እንደዋዛ አለፉ፡፡ ትናንት በህይወት ሳሉ እንኳን የቤተመንግስቱን ቅጥር ለመርገጥ እሳቸው በሚያልፉበት መንገድ ላይ ጀርባውን አዙሮ እንዲቆም የሚገደደው ህዝብ ደስታቸውን ሳይሆን ልቅሷቸው ላይ ለመገኘት ታደለ፡፡

ብሶቱን ሳይሆን ልቅሷቸውን ለመድረስ ሲነገረው ለወትሮው ባጠገቡ ለማለፍ የሚከብደው የምኒሊክ ቤተመንግስት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ እግር በዛበት፡፡ የኔ ቢጢ የዋሁም የመንግስተ ሰማያትን በር የመርገጥ ያህል ቆጠረው፡፡ ሟችን መውቀስ ባህሉ ያልሆነው ጨዋው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ስለ አቶ መለስ መልካም መልካሙን ለመናገር ጨዋ ባህሉ አስገደደው፡፡ ሽፍታው ሞርኮታ የኢትዮጵያ ህዝብ በሰው ልጅ ሞት አይደሰትም፡፡ በህይወቱ ሳለ የበደለውን ሰው ሞት እንኳን ሲሰማ ከልቡ ያዝናል፡፡ 1990 . መጀመሪያ አካባቢ ደቡብ ኦሮሚያን በተለይም ከያቬሎ እስከ ሞያሌ (ኬኒያ ጠረፍ) ድረስ የህዝብን ሰላም ያናጋ ሞርኮታ የሚባል ሽፍታ ለተወሰኑ ዓመታት አስቸግሮ ነበር፡፡ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎችን እያስቆመ ያገኘውን ይዘርፋል፡፡ ጥቂት ሊገዳደረው የሞከረውን ሰው በጭካኔ ይገድላል፡፡ የሚያማልሉትን ሴቶች በጭካኔ አፍኖ እየወሰደ የወሲብ ባሪያ አድርጎና ለቀናት ያህል እያቆየ ሲያሻው ይገድላቸዋል፤ ከራራም ይለቃቸዋል፡፡ በዚያ መስመር የሚደረገው እንቅስቃሴ ከሽፍታው ሞርኮታ የተነሳ የፍርሃት ድባብ ያንዣበበት ነበር፡፡


 ሕዝቡም በተለያዩ አጋጣሚዎች ምሬቱን ሲገልፅ ቢቆይም  በአንድ ወቅት በታጠቁ ኃይሎች ታድኖ መገደሉ በዜና ሲነገር ብዙዎች ከልባቸው አዘኑ፡፡ አንዳንዶችማጀግና ነበር፡፡ ምን ያደርጋል? ሞተሲሉ ተደመጡ፡፡ ይህን ያነሳሁት ይሄ ህዝብ ምን ያህል የዋህ ህዝብ እንደሆነ ለማሳየት አስቤ ነው፡፡ የሙሴን በትር ከመለስ ታንክ ታላላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎችና አጥኚዎች ሙሴን የዘመነ ብሉይ ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ እንደ አዲስ ኪዳኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞታችንን በመስቀል ሞት የሻረና የዘላለም ህይወትን በትንሳኤው ያበሰረ ባይሆንም እግዚአብሄር እስራኤላውያንን ከግብፅ አገር የፈርኦን ቤት ባርነት መርቶ እንዲያወጣ የቀባውና እግዚአብሄርም በአለት ስንጥቅ ውስጥ ሸሽጎት ክብሩን ያሳየው አገልጋይ ነበር፡፡ የሙሴን ታሪክ ያነሳሁት የወንጌል ሰባኪ መሆን ዳድቶኝ አይደለም፡፡ ሰሞኑን በአቶ መለስ ሞት ምክንያትየአገራችን አርቲስቶች በግልና በጋራ በርካታ ነጠላ ዜማዎችን በሀዘን ማጀቢያነት መልቀቃቸው ይታወቃል፡፡ በኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ካደመጥኳቸው በአንዱ ሙዚቃ ውስጥ የተቋጠረው ስንኝ በብርቱ አስገረመኝ፡፡ አቶ መለስን ከሙሴ ጥሪ ጋር በማነፃፀር እሳቸው ለሙሴ የተሰጠውን በትር ይዘው ኢትዮጵያን እንደመሩ የድህነት ባህርን ከፍለው እንዳሻገሩን ተደርጎ መዘመሩ በእጅጉ ያስተዛዝባል፡፡ የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ በየዘመኑ ከሚለዋወጥ የፖለቲካ ንፋስ ጋር መንፈሷ ሕዝባዊነቷን እየጎዳው ነው፡፡

ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ልመለስና ሙሴ የእስራኤልን ህዝብ 400 ዓመታት ከዘለቀው ከግብፁ ፈርኦን ቤት ባርነት እንዲያወጣ እግዚአብሄር ሲያስነሳው የሰጠው ብትር እንጂ ክላሽ ወይም ታንክ አይደለም፡፡ ግብፃውያንንገድለህ፣ ጨፍጭፈህ፣ ህዝቤን ነፃ አውጣአላለውም፡፡በበትርህ ቀይ ባሕርን ሁለት ቦታ ከፍለህ ህዝቤን ከግብፃውያን ጦር አስመልጥነበር ያለው፡፡ ሙሴ እስራኤላውያን ተስፋይቷን ምድር እስከሚወርሱ 40 ዓመታት ህዝቡን በምድረበዳ ሲመራ ከአምላኩ ዘንድ መናን ለምኖ ምህረትን ተማፅኖ እንጂ ወንድም ወንድሙን እንዲገድል እያደረገ አይደለም፡፡ አምላኩ በእስራኤላውያን የኃጢአት ሥራ ክፉኛ አዝኖ የቅጣት ክንዱን ሊዘረጋ ከዙፋኑ ሲነሳ ሙሴከህዝብህ በፊት እኔን አጥፋኝሲል ይማፀን ነበር፡፡ አቶ መለስጎበዝና ብልህ መሪ ነበሩ ወይ?” ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በርካታ የሚያስመሰግኑና በታሪክ የሚዘከሩ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ለውጥ ለማምጣትም ጥረዋል፡፡

ነገር ግን ከሙሴ ጋር ልናነፃፅራቸው አይገባም፡፡ ሙሴ በሰማያዊ ምሪት ህዝብን ሲመራ አቶ መለስ በራሳቸው ፍልስፍናበአብዮታዊ ዲሞክራሲኢትዮጵያን ያስተዳደሩ፤ ሙሴ ጠዋት ማታ የፈጠረውን ትዕዛዝ የፈፅመ አቶ መለስ የራሳቸውን አመለካከት ያራመዱ፤ ሙሴ የእግዚአብሄር ሀይል ባረፈባት በትር ተአምራትን ሲያደርግና የቀይ ባህርን ለሁለት ሲከፍል አቶ መለስ ትውልድን እርስ በርስ ባፋጀ መድፍና ታንክ ታግዘው ለስልጣን የበቁኧረ እየተሰተዋለ፡፡ እንዲያው ነገር አሳመርን ብለን የማይሆነውን ከሚሆነው ባንደባልቅ ጥሩ ነው፡፡ሸማ በየፈርጁ ይለበሳልእንዲሉ ነገሮችን በማመጣጠን ማነፃፀር ብንችል ለሁሉም ይበጃል፡፡ አቶ መለስን አንደኛው ወገን እጅግ አግዝፎ ስላሞካሻቸው ከሞት አይነሱም፣ ወይም ገነትን አይወርሱም፡፡ ሌላኛው ወገንም በጭፍን ጥላቻ ተነሳስቶ ህፀፃቸውን ስለከመረው ገሀነም አይገቡም፡፡ እውነትን መሰወር ግን ታሪክንም ያዛባል፣ ፈጣሪንም ያሳዝናል፡፡

በዚህም ሆነ በቀደሙት መጣጥፎቼ ያነሳኋቸው ሀሳቦች የሞተን ሰው ለመውቀስ ያነጣጠሩ አይደሉም፡፡ አቶ መለስ ከሰሯቸው መልካምና አኩሪ ሥራዎች ጎን አስከፊና አሳዛኝ ተግባራትንም ፈፅመው እንዳለፉ ማመን አለብን፡፡ ሙሴ በምድረበዳ የመራቸው እስራኤላውያን በሰላም ከምንኖርበት የግብፅ ምድር አውጥተህበምድረ በዳ ለምን ታሰቃየናለህ?” እያሉ ባመፁበት ቁጥር ፈጣሪውን ልቦናና ትዕግስት እንዲሁም ፍላጎታቸውን እንዲያሟላላቸው ይማፀን ነበር እንጂአመፅ ናፋቂዎች፣ ሽብ ፈጣሪዎች፣ የጎዳና ላይ ነውጠኞች. . .” እያለ በጥይት አልመታቸውም፡፡ ጩኽታችን በእሳቸው እግር የሚተኩት ጠቅላይ / የአቶ መለስን ደካማ ጎኖች አርመው ጠንካራ ጎኖችን ምርኩዝ አድርገውና ስህተቶቻቸውን አስወግደው አገር እንዲመሩ ካለን ፅኑ ፍላጎት የመነጨ ነው፡፡ ይሄን ደግሞ የማድረግ የዜግነት ግዴታችን ነው፡፡ ግለሰብን የተደገፈ ፓርቲ ፈጣሪውን የተደገፈ ህዝብ ኢህአዴግ ከአቶ መለስ ውጪ ህይወት እንደማይኖረው ህወሓት/ ኢህአዴግም ሆነ  ህዝቡ ከተረዳው ውሎ አድሯል፡፡

ላለፉት 21 ዓመታት እሳቸው ባመነጯቸው አዳዲስ አስተሳሰቦችና በቀየሷቸው የብልጠት መንገዶች ነበር ፓርቲው የተጓዘው፡፡ ለዚህም ሁለት ዋና ዋና ማሳመኛዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንደኛው በየ5 ዓመቱ ምርጫ በመጣ ቁጥር እሳቸውን የሚተካ በሳልና  አስተዋይ ሰው ባለመኖሩ ረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ እንዲቆዩ በፓርቲያቸው መገደዳቸውን እሳቸውም ሆኑ የትግል አጋሮቻቸው በተደጋጋሚ ሲገልፁትነበር፡፡ እጅግ ግዙፍና ካለፈው ዘመናቸው የተሻለ ሥራ መሥራት በሚችሉበት እድሜ ላይ ሳሉ ባጭሩ ለመቀጨታቸው ዋንኛው ምክንያት ይሄ ነበር፡፡ ሁለተኛው ማሳመኛ ከነሀሴ 15/2004 . ጀምሮ ባሳለፍናቸው የሀዘን ቀናት የአገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ከትጥቅ ትግሉ ወቅት ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ የተመዘገቡት ድሎች በአጠቃላይ የሳቸው ትሩፋቶች እንደሆኑ ሲናገሩ ከርመዋል፡፡ ከጎጥና ከቀበሌ አንስቶ እስከ ፌደራል መንግስት የተሰሩ ሥራዎች ሁሉ ለሳቸው ተጠቅልሎ መሰጠቱ የፓርቲው ምሰሶና ዋልታና ማገር እንደነበሩ በጉልህ የሚመሰክር ነው፡፡ ሌሎቹ ሹማምንት የማንን ጎፈሬ ሲያበጥሩ እንደከረሙ ወደፊት የሚነሳ ጥያቄ ይሆናል፡፡

ከእነዚህ ሁኔታዎች የተነሳ የአቶ መለስ ድንገተኛ ሞት የኢህአዴግን ጎራ አውራ የሌለው ንብ ሊያደርገውእንደሚችል ለመገመት አያዳግትም፡፡ ሁኔታው ያሳሰባቸው አያሌ የዓለማችን የፖለቲካ ሳይንስ ጎምቱ ምሁራንና ተመራማሪዎች በማህበራዊ ድረ ገፆችም ሆነ በአለም አቀፍ ሚዲያዎች የድህረ መለስ የስልጣን ሽግግር ለኢትዮጵያ እጅግ ፈታኝ እንደሚሆን አሳማኝ ማስረጃዎችን እየጠቀሱያትታሉ፡፡ ህወሓት በግንባሩ ስብስብ ውስጥ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ገዝፎ የቆየውን የአዛዥነት ሚና እንዳያጣ የሚደረገው ፍትጊያ 1993 . በባሰ መልኩ እንደሚያሰጋው በእርግጠኝነት ይከራከራሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ዋንኛ መንስኤ ፓርቲው በአንድ ሰው ማንነትና የፖለቲካ ፍልስፍና ላይ መደገፉ ነው፡፡ ነውጥ በመጣ ቁጥር የሚለወጠው መንግስትና መሪ እንጂ አገርና ህዝብ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በፈጣሪ ሰማያዊ መዝገብ ውስጥ አስቀድማ የምትታወቅ ምድር ናት፡፡ ይህች ዛሬ የምንኖርባት በነገስታት የፈረቃ አገዛዝ ዘመን የተጎሳቆለች ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ 40 ጊዜ በላይ ስሟ ተጠቅሶ እናነባለን፡፡ በመከራዋ ዘመንም እጆቿን ወደ እግዚአብሄር እንደ ምትዘረጋ በግልፅ ተፅፏል፡፡ በስመሥዩመ እግዚአብሄር በአገሪቱ የነገሱት አፄ ኃይለ ሥላሴ ከስልጣናቸው ሲወገዱ ህዝቡ በየዋህነት መሬት የምትንቀጠቀጥ መስሎት ቢጠብቅም አንዳችም የተፈጠረ አዲስ ክስተት አልነበረም፡ መሬትን ለማንቀጥቀጥ ሥልጣኑያለው በፈጣሪ እጅ እንጂ ስልጣን ላይ በሚወጡ ነገስታት አይደለም፡፡

ቀናት ይፈራረቃሉ ወራቶች ያልፋሉ፣ ዓመታት ይነጉዳሉ፣ያረጀው ትውልድ በአዲስ ይተካል፣ ቀላያት በክረምት ጢም ይላሉ፣ በበጋም ይጎድላሉ፣ የተፈጥሮ ዑደት ጊዜና ሚዛኑን ጠብቆ ይዟዟራል፣ ነገስታት ያልፋሉ፣ በአዲስም ይተካሉ፤ የኢትዮጵያ አምላክ ግን ለዘላለም በዙፋኑ ላይ ነው፡፡


አሜን!

No comments:

Post a Comment