በምርጫ
ዘጠና ሰባት ሰሞን በጠቅላይ ሚኒስትሩ እዝ ስር የሆነው መሳሪያ የታጠቀው ሃይል አንዱ ከአንዱ በመተባበር ከምርጫ
ጋር ተያይዞ በመጣ ቀውስ ምስኪኑን ህዝብ በተለይ በሰኔ 97 እና በጥቅምት 98 ዓ.ም እያለሙ አጥንቱንም ቅስሙንም
ህይወቱንም ይሰብሩት ነበር።
ታድያ በተለይ የጥቅምቱን ግድያ የተመለከቱ አንድ አዛውንት “እነዚህ ሰዎች በጥቅምት አንድ አጥንት ሲባል የሰው
አጥንት መስበር መሰላቸው እንዴ!?” ብለው በህመማችን እንድንስቅ አድርገውን እንደነበር ከዚህ በፊትም አውግተናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ ትላንት በእርሳቸው እዝ ሲገደሉ የነበሩ ሰዎች ዘንድ ሄደዋል። እነዛ
ምስኪን ሟቾች መለስን ሲያገኟቸው እንዴት ያደርጓቸው ይሆን? ብዬ ልጠይቅ ነበር ለካስ የገደለ እና የተገደለ ቦታው
ለይቅል ነው!
በነገራችን ላይ ባለፈው ግዜ ኢሳት ቴሌቪዥን “ሰብዓዊ መብት” በተባለው ፕሮግራሙ አንድ ዶክመንተሪ አሳይቶን
ነበር። “ባለ ራዕዩ” መሪ ያስገደሏቸውን ሰዎች የሚዘክር ዶክመንተሪ። ይህንን ፕሮግራም የተከታተለ አንድ በአዲሳባ
የሚገኝ ወዳጄ፤ “ባለፈው “ህዝቡ ሲያለቅስላቸው” አሳዝነውኝ እኔም አልቅሼ ነበር። ለካስ ይሄንን ሁሉ
አድርገውናል!? በእውነቱ ለቅሶዬ ተጭበርብሯል ቤተመንግስት ሄጄ እንባ መልስ ጠይቃለሁ!” ብሎኛል። የምርም አቶ
መለስ እኔ ራሴ ካሰብኩት በላይ ነፍስ በእጃቸው ጠፍቷል። የሆኑ ሰው የማይበረክትላቸው ሰው ነበሩና!
ከመለስ በኋላ አዲስ ባለ ራዕይ ንጉስ ይመጣልናል ብለን ብንጠብቅ “ከኔ በፊት የነበረውን ጫማውን እንኳ ልሰም
አቅም የለኝም! እኔ የርሱን ራዕይ አስፈፅማለሁ እንጂ ከኔ ራዕይ አትጠብቁ!” ብለው የተናገሩት ሰውዬ መጡ!
አሁን የመለስ ራዕይ በአግባቡ እየተፈፀመ እንደሆነ ተጨባጭ ነገሮች እየታዩ ነው
በአማራ ክልል ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ ልክ እንዳለፈው ግዜው ጥቅምት አሁንም “እነዚህ ሰዎች በጥቅምት
አንድ አጥንት ሲባል የሰው አጥንት መስበር መሰላቸው እንዴ!?” በሚያሰኝ መልኩ ብዙዎችን ቁስለኛ አድርጎ አራት
ሰዎች ደግሞ መሞት ዕጣ ፈንታቸው ሆኗል። ይሄ በጣም አሳዛኝ ነው… መጨረሻው ምን እንደሆነም አይታወቅም። መንግስት
እንደ ጥሩ ወጠብሻ ጎረምሳ ከህዝቡ ጋር እልህ ተጋብቶ ልክ አቶ መለስ ሲያደርጉ እንደነበረው ሁሉ “ምን
ታመጣላችሁ!?” እያለ የሚያደርገውን እያደረገ ነው።
እኔ የምለው በአሁኑ ጊዜ አቶ መለስ ያሉት እውነቱ ቦታ ነው። እግዜሩ የምናደርገውን ይታዘባል። ለእያንዳንዱ
መለስ ሰራሽ ሴራም እዛ አስር ጊዜ እያስጠራ አበሳቸውን ከሚያበላቸው ለእርሳቸው ሲባል እንኳ የእስካሁኑ ይብቃ…
ራዕያቸውን ለማስፈፀም ተብሎ ነብሳቸው በጋነብ እሳት ካረረችው በላይ አናሳርራት! ብዬ እንደፈረደብኝ እመክራለሁ!
No comments:
Post a Comment