Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday, 24 October 2012

ሐሙስን ከሚኒስትሩ ጋር!

ዕለቱ ሐሙስ ነው፡፡ ቀኑ ደግሞ ‘08’፡፡ ወርሃ ጥቅምት፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢህአዴግ ግንባር ቀደሞች ተሰብስበናል፡፡ በታሪካዊው የ”FBE” አዳራሽ፡፡ ታሪካዊ ማለቴ ቆራጡ መንጌ የፖለቲከ ርዮት ያጠጣበት የነበረ አዳራሽ በመሆኑ ነው፡፡ ካለመናችሁ ወንበሮቹን እዩአቸው፡፡ መደገፊያዎቹ ላይ “ፖ/ት ይላሉ፡፡ ፖለቲካ ት/ቤት እንደማለት፡፡
በቀኝ እጃቸው ሴ
ቷ ማጭድ ወንዱ መዶሻ ይዘው ግራ እጃቸውን “የሁሉም ሐገር ሠራተኞች ተባበሩ!” የሚል መፈከር ያነገቡ የሚመስል ቅርፅም መግቢያው ላይ አለ፡፡ እናስ ታሪካዊ አይደለም ትላላችሁ?! እኛም ግንባር ቀደሞቹ በዚህ ታሪካዊ አዳራሽ ታሪካዊ ስብሰባ እያደረግን ነው፡፡ ሰብሳቢዎቻችን ደግሞ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም እና የ ዩኒቨርስቲያችን ፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ ናቸው፡፡
ከጠዋቱ 3፡00 ከአራቱ የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች የተውጣጣን ግንባር ቀደሞች አዳራሹን ሞላነው፡፡ የመሰረታዊ አደረጃጀት አመራሮች በር ላይ ሆነው ግንባር ቀደም ያልሆነውን ግንባሩን አዙሮ እንዲሄድ ለማድረግ በጥንቃቄ እየለቀሙ ያስገባሉ፡፡ አዳራሹ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞላ፡፡ ስብሰባው ለታላቁ መሪያችን ጸሎት በማድረግ ተጀመረ፡፡ ክቡር ሚንስትሩ አጀንዳውን አስተዋወቁ፡፡ ስለ ‘አክራሪነት’ ነው፡፡ አቶ አምባዬ የተባሉ ሰው (ይቅርታ ማዕረጋቸው ስላልተነገረን) ያዘጋጁትን ጽሑፍ “በፕሮጀክተር” ዘረገፉት፡፡ የቀረ የለም፡፡ ሁለም በአክራሪነት ተፈርጇል፡፡ አንዳንድ ዋሃቢያዎች… አንዳንድ ሰለፊዎች… አንዳንድ ካዋርጃዎች… አንዳንድ ማኅበረ ቅዱሳኖች… አንዳንድ…፡፡ አክራሪዎች ናቸው ተባለ፡፡ ከንጉሡ ጀምሮ እስከ አምባ ገነኑ ደርግ ድረስ የሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት እንዳልነበር አስተጋቡ ፤ የዛሬውንም መንግሥት ቸርነት ሰበኩ፡፡ አቶ አምባዬ ረጅሙን ትንተናቸውን ሲጨርሱ ክቡር ሚንስተሩ ተተኩ፡፡ ትንሽ ላጠናክረው ብለው አንዳንድ ነገሮችን አንስተው በአንዳንዶች ላይ ዙሩን አከረሩት፡፡ እኝህ ክቡር ሚኒስትር ንግግራቸው ጠንካራ ነው ፤ ልክ እንደ ጓዳችን፡፡ ትንሽ የሚለዩት በአማርኛቸው ነው፡፡ ያዝ! ያደርጋቸዋል፡፡ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 90/2/ን ተነተኑት፡፡ “ትምህርት ከፖለቲካ ፤ ከሃይማኖት እና ባህላዊ ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት” ይላል አሉ፡፡ በእርግጥ እሳቸው ከ‘ሃይማኖት’ የሚለው ላይ ነው ጠበቅ ያሉት፡፡ ይሄኔ ከጎኔ የተቀመጠው ግንባር ቀደም ጓደኛዬ “what about this” አለኝ፡፡ በዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ ፖለቲካ እየሰበኩ እንዴት ነው አንቀጹ የሚነሳው ማለቱ ነው፡፡ የአይኖቼን ቅንድቦች ብቻ ከፍና ዝቅ በማድረግ “እኔም አልገባኝ!” አልኩት፡፡ ክቡር ምኒስትሩ ማጠናከሪያቸውን እስኪበቃው ድረስ እንደ ብረት ካጠነከሩት በኋላ መድረኩ ለውይይት ክፍት ሆነ፡፡
የመጀመሪያው ተናጋሪ ‘ማይኩን’ ተቀበለ፡፡ ወደፊት አካባቢ ስለነበር አካላዊ ገፅታው አይታየኝም፡፡ ድምፁ ግን ወፍራም ነው፡፡ “በእውነቱ ዛሬ የተወያየንበት ነገር በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ እህ! (ድምፁ ይበልጥ እየወፈረ መጣ) ሥራ አጥነት አገብጋቢ ሆኖብን ፣ ተምረን መውደቂያ እያጣን እናንተ አክራሪነት ትላላችሁ!” ከባድ ጭብጨባ፡፡ ክቡር ሚንስትሩ ገላመጡን፡፡ “ስሙ! ይሄ ጭብጨባ እኮ የደርግ መገለጫ እንጂ የግንባር ቀደሞች አይደለም፡፡ ደርግ ነው በባዶ አዳራሽ የሚያስጨበጭብ፡፡” ሌላም ተግሳፅ አወረዱብንና ለሌላኛው እድል ሰጡ፡፡ ሁለተኛው ተናጋሪ ስሙንና ድርጅቱን ተናግሮ ቀጠለ “እኔም የምለው ነገር ስለ ሥራ ነው፡፡ ሥራ ስጡነ ስንል ‘ኮብልስቶን’ ስሩ ትሉናላችሁ፡፡ የተማረውም ያልተማረውም ‘ኮብልስቶን’ ከሰራ ልዩነቱ ምንድነው?” ደማቅ ጭብጨባ ፤ በጭብጨባው ታግዞ ንግግሩን አረዘመ፡፡ “እናንተ መብታችሁ ተከብሮ ትላላችሁ የትኛው መብታችን ነው የተከበረው? በቀደም ለታ እሁድ ቀን ኳስ ልናይ ከተሰለፍንበት ፌደራል ቀጠቀጠን፡፡ ስንቱን ሽባ አደረገው፡፡ ደሞ… ምን መብት አለነ፡፡” ሌላ ጭብጨባ… “ደሞ ሚዲያዎቻችን ውሸት ብቻ ነው ሥራቸው፡፡ ትናንት በቴሌቭዥን 40 ኩንታል ጤፍ በጭልጋ ተመረተ ሲል ነበር፡፡ እኔ ራሴ የጭልጋ ልጅ ነኝ፡፡ እንኳን 40 ኩንታል አንድ ገበሬ ሊያመርት 4 ኩንታልም የለ፡፡ ይህ ለምን ነው እሚዋሽ? እንዴ! ነውር አይደለም?” አዳራሹ በሁካታ ተሞላ፡፡ የ‘ህዋስ’ አመራሮች ዐይናቸውን ማፍጠጥ ጀመሩ፡፡ የአንዳንዶቹ ጉንጭ የበሰለ ቲማቲም ይመስል ጀምሯል፡፡ ክቡር ሚንስትሩ ድምፅ ማጉያውን አበሩ፡፡ “ጎበዝ! ይሄ እኮ የግንባር ቀደሞች ስብሰባ መስሎኝ ነበር (ትንሽ ፋታ ወስደው)… እና እንግባባ፡፡ አታጨብጭቡ ማለት አታጨብጭቡ ነው፡፡ በቃ!... እንስማማ እንጂ…”
ሦስተኛው ተናጋሪ ‘ማይኩን’ ያዘ፡፡ ጀንተል ያለ ነገር ነው፡፡ ነጭ ቦዲው ሰውነቱን አላንቀሳቅስ ብሎታል፡፡ “እኔ በዚህ ውይይት በጣም አዝኛለሁ፡፡ ስለ ‘ኮብልስቶን’ የተባለው እንዳለ ሆኖ የዱሮውን ታሪክ እየበረዝን ፣ እየከለስን የዛሬውን ለማግዘፍ ለምን እንደምንሯሯጥ አይገባኝም፡፡ ይሄ ነገር ድርጅታችን እንዳይንደው መጠንቀቅ ያሻል፡፡ ሌላው ፅንፈኛው ማን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ያን ለመንካት ሌሎችንም በጎን ማሰለፉ ‘አህያውን ፈርቶ ዳውላውን’ ያስመስላል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በጣም የገረመኝ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ሚኒስትሩ ሲናገሩ ‘የከሰሩ ፖለቲከኞች’ ብለዋቸዋል:: በምርጫ ተወዳድሮ መሸነፍ መክሰር ነው እንዴ? እንግዲህ ኢህአዴግ ላለመክሰር እድሜልክ ይገዛል ማለት ነው? ይህ በጣም ያሳፍራል፡፡ ቃል ብንመርጥ አሪፍ ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡” ከእስካሁን የበለጠ ጭብጨባ አዳራሹን ናጠው፡፡ ክቡር ሚንስትሩ መላ መፈለግ ጀመሩ፡፡ እስካሁን የተናገሩት ወደ ስምንት የሚጠጉት (እኔ ሦስቱን ብፅፈውም) ከ‘ብአዴን’ ነው፡፡ ሁሉም ተቃውሞ በዛበት፡፡ “ከዚህ በኋላ ብአዴኖች በቃችሁ፡፡ ሌሎች ድርጅቶች ተናገሩ” አሉን፡፡
ሌላኛው ተናጋሪ ማይኩን ተቀበለው፡፡ ስሙን ተናገረ፡፡ ዲፓርትመንቱን አስተዋወቀ፡፡ ወደ ንግግሩ ሊገባ ሲል ክቡር ሚኒስትሩ “ከየትኛው ብሔራዊ ድርጅት ነህ?” አሉት፡፡ እሱም “ኢህአዴግ” አላቸው፡፡ በሳቅ አጀብነው፡፡ ደግመው ጠየቁት ፤ ያንኑ ደግሞ መለሰ ፤ ያንኑ ሳቃችንን ደግመን ሳቅን፡፡ “እሺ ቀጥል አሉት፡፡”… ቀጠለ፡፡ “መወያየት ያለብን ስለዩኒቨርስቲያችን ችግር እንጂ ስለ ፅንፈኛና አክራሪነት አልነበረም፡፡ ደግሞ ለምን እኛ ኢህአዴጎች ብቻ እንወያያለን ሌሎች ተማዎሪዎችስ?...
መነፅሩን ያደረገ ፤ የተረጋጋ ወጣት እድሉን አገኘ፡፡ ከ“ኦፒዲዮ” ነኝ አለ፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ተስፋ የጣሉበት ይመስላሉ፡፡ ግንባር ቀደም ቢሆን ብለው፡፡ እሱም እንዲህ ተናገረ፡፡ “እኔ እንደማምነው ርዕሱ በራሱ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ብዙ ጊዜ ችግሮቹን ከመፍታት በላይ ችግሮቹን ማስተጋባት ፤ ቀዳዳዎችን ከመድፈን ይልቅ ማድመቅና ማደንቆር ይቀናዋል፡፡ ያምናውን አጀንዳ ነው ዘንድሮም የደገማችሁት፡፡ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡”
ለዚህ ጽሑፍ የመጨረሻው ተናጋሪ እጁን አወጣ፡፡ ፀጉሩን እንደ ገመድ ገምዶታል፡፡ አገጩ እንደ ቄስ ፂም ቁልቁል የወረደ ፤ አፍንጫው ሰልካካ የ‘ጆርናሊዝም’ ተማሪ ነው፡፡ “እኔ የመጣሁት ከ“ኦፒዲዮ” ነው፡፡ ባይገርማችሁ ምንድነህ? ስባል “ኦፒዲዮ” እላለሁ እንጂ መታወቂያ እንኳን የለኝም፡፡ ለምን እንደማይሰጡኝም አይባኝም፡፡ ሁለተኛ ምንም እንኳን ብኖርበትም የተማሪዎች መማክርት አመራረጥ ትክክል አይደለም፡፡ ፖለቲካና ብሔር ያጠላበት ነው፡፡ እንኳን የተማሪውን መብት ተከራክረው ሊያስከብሩ በራሳቸው መቆም የማይችሉ ናቸው፡፡ እና ኢህአዴግ ለምን በሁሉም ጣልቃ ይገባል? ስለ‘ኮብልስቶን’ የተባለው እኛ ስንመረቅ እሱም ያልቅና ተደራጁና ‘ኮብልስቶኑን’ ውሃ አጠጡ እንዳንባል፡፡” ሳቅና ሁካታ… ንግግሩን ቀጥሎ “ሦስተኛ እኔ የ‘ጆርናሊዝም’ ተማሪ እንደመሆኔ ቅድም ተገልፅዋል፡፡ ኢቲቪ ያሉ ጋዘጠኞች ‘ጆርናሊዝም’ ሳይሆን ‘ጆካይዝም’ ነው ያጠኑት፡፡” ሌላ ሳቅ… “የሚዲያ ኤቲክስ የላቸውም ፤ ሁልጊዜ ውሸት ነው፡፡ ኢቲቪ (1) ሲታረስ ነው የሚያሳየን ፣ ኢቲቪ (2) ሲዘራ ፣ ኢቲቪ (3) ሲከመር ፣ ኢቲቪ (4) ሲሸጥ…፡፡” የሳቁ ንጉስ በላቸው የገባበት ይመስል አዳራሹ በሳቅ ተናጋ፡፡ ከክቡር ሚኒስትሩና ከሴል አመራሮች በቀር ያልሳቀ የለም፡፡ ምናልባት ድርጅታዊ እርምጃ እንዳይወሰድባቸው በመፍራት ሳቃቸውን ያፈኑት ይመስላል፡፡
እንደ ምርቃት አንደበተ ርዕቱ ተናጋሪ በተናገረው ልሰናበታችሁ፡፡ “እኔ ለመድረኩ የምጠይቀው ከድሮ እስከ ዘንድሮ ፣ ከአምና እስከ አሁን ሪፖርት ሲቀርብ ‘አንዳንድ… አንዳንድ’ የሚባል ነገር አለ፡፡ እነዛ አንዳንድ እነማናቸው? እነዛንስ ለይቶ መቅጣት አይቻልም? እስከ መቼ አንዳንድ እየተባለ በጅምላ እየተወቀጠ ይኖራል፡፡ ሌላው… ‘ዋሃቢያ’ የሚባል ነገር አለ ወይ? ቢሮ አለው? አድራሻ አለው? ድርጅት ነው? ምንድነው? ግራ ገባኝ እኮ፡፡ እኔ ራሴ ምንድን ነኝ፡፡”
የምሳ ሰዓት ደርሷል፡፡ መውጫችን ነው፡፡ ክቡር ሚንስትሩ በጥያቄዎቻችን እንዳልተደሰቱ ያስታውቃሉ፡፡ ከምሳ መልስ መልሳቸውን እንደ‘ላውንቸር’ ሊያምዘገዝጉት እንደሆ ገምተናል፡፡ ከእሳቸው በላይ የህዋስ አመራሮች አምርረዋል፡፡ የስብሰባው መስመር ተስቶ እንደጠበቁት ሳይሆን እንዳልጠበቁት እየሄደ ግንባር ቀደምት የተባሉት ጭራ ቀደም ሆነው አረፉት፡፡ ይሄ ነገር ምን ይመስላችኋል? ተስፋ መቁረጥ ይሆን???
ቸር እንሰንብት

No comments:

Post a Comment